Sunday, 06 November 2016 00:00

‘የሠራ የእጁን፣ የተቀመጠ የእንትኑን ያገኛል…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…የሠራ የእጁን፣ የተቀመጠ የእንትኑን አያጣም የሚሏት አባባል አለች፡፡ እንደ ጨዋታ ማሳመሪያ አሪፍ ነች፡፡ ችግሩ ግን…ጨዋታ ማሳመር ሌላ፣ ‘መሬት ያለው እውነት’ ሌላ! ልክ ነዋ…‘የሠራ’ አጨብጭቦ ሲቀር፣ ‘የተቀመጠ’…አለ አይደል… ‘ቅቤና ማሩ’ አልጋው ድረስ ሲመጣለት እያየን ነዋ። (ለሚመለከተው ሁሉ…ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ለ‘ሹገር ማሚዎች’ አገልግሎት የሚያበረክቱትን አይመለከትም። ልጄ…ማን ጠላት ያበዛል!)
ሁለት ሰዎች ስለሆነ ሰው እያወሩ ነበር፡፡ እናማ ስለምኑም ስለምናምኑም እየተጨዋወቱ እያለ፣ ሰውየው ሥራ ላይ እንዴት እንደሆነ ማውራት ይጀምራሉ፡፡
“ሥራ ላይ ግን እንዴት ነው?”
“የሥራውን እንኳን ተወው…”
“ተወው ማለት… እንዴት?”
“እሱ ማለት ማን እንደሆነ ልንገርህ! ፔስኮ በለው…
አሪፍ አይደል!
ስሙኝማ… የእነሞሪንሀ ፊልም ላይ ፔስኮ የሚሉትን ሰውዬ አይታችሁልኛል? እኔ የምለው…እሱን ድራማ የጻፈችው ሴትዮ፣ ከእኛ ጋር ለጥቂት ጊዜ ኖራለች እንዴ! ልክ ነዋ…ብዙዎቻችንን የሚመስል ገጸ ባህሪይ ቀርጻለቻ!
‘የሠራ የእጁን፣ የተቀመጠ የእንትኑን ያገኛል…’ የምትለው አባባል የማትሠራበት ጊዜ መአት ነው!
የምር ግን…ዘንድሮ እኮ እንደ ፔስኮ ‘የደላን’ መአት አለን፡፡ አለ አይደል… ጋደም ብለን በሌላው ሰው እጅ የምንጎርስ፡፡ ወፍራምም ይሁን ‘ወደፊት ወፍራም ሊሆን የሚችል’ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ‘ተፈትፍቶ ያለቀለትን’… በሌላው እጅ የምንጎርስ ቁጥራችን የዋዛ አይደለም፡፡ ምንም ሳይኖረን፣ ያጣን የነጣን እንኳን ሆነን…ሌላው ፈጭቶ፣ አቡክቶ፣ ጋግሮ ያዘጋጀውን ዓለም ዘጠኝ ብለን የምንቀለብ ቁጥራችን ቀላል አይደለም፡፡
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ፣ ሳይሠሩ ተኝቶ ሌላው ላቡን ጠብ ያደረገበትን ‘በሁለት ጉንጭ መፍጨት’…አለ አይደል… ለእርግማን የሚያደርስ ሳይሆን ለጽድቅ የሚያበቃ እየመሰለ ነው፡፡ ‘ጮሌነት’…“እንደው ምን ሲሉ ይህን አይነቱን ወለዱት!” የሚያሰኝ ሳይሆን ሽልማት ‘ሊዘጋጅለት የሚገባው’ ባህሪይ ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡
‘የሠራ የእጁን፣ የተቀመጠ የእንትኑን ያገኛል…’ የምትለው አባባል የማትሠራበት ጊዜ መአት ነው!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው አማቱን አይወዳቸውም። (የሆነ ሰው… ‘አማቶቻቸውን የሚወዱ ምርጥ ባሎች’ ምናምን የሚል ሽልማት ቢያዘጋጅ አሪፍ ነው፡፡ ምናልባትም ከሦስት ወር በኋላ “መስፈርቱን የሚያሟሉ በቂ ባሎች ባለመገኘታቸው ወድድሩ ተሰርዟል...” ምናምን ሊባል ይችላላ! ቂ…ቂ…ቂ…) እናላችሁ…ውሻውን ወደ እንስሳት ሀኪም ቤት ይወስደውና ዶክተሩን… “እባክህ የውሻዬን ጭራ ቁረጥልኝ…” ይለዋል፡፡ ዶክተሩም የውሻውን ጭራ ሲያየው ፍጹም ጤነኛ ነው፡፡
“ጭራው ምንም ችግር የለበትም፡፡ ለምንድነው እንዲቆረጥ የፈለግኽው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ የውሻው ባለቤት ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“አማቴ ቤታችን ለክረምቱ ልትመጣ ነው፡፡ ውሻው ጭራውን ሲቆላ ቤት ውስጥ ያለነው ሁሉ በመምጣቷ ደስተኛ የሆንን እንዳይመስላት ነው…” ብሎ አረፈላችሁ።
እንዲህ አይነትም ‘ብልጥነት’ አለ፡፡
እናላችሁ…
“ልጄ፣ እሱ እኮ ቆቅ ነው…”
“እሷዬዋ እኮ ነገሩ የገባት ናት…”
“ጂኒየስ በለው፣ አንዲት ጠጠር ሳያነሳ ፍራንኩን ይዝቀዋል…”
ምናምን መባሉ አንገት የሚያስደፋ ሳይሆን ደረት የሚያስነፋ ነገር ሆኗል፡፡ በቃ የሆነ…‘ከአፍሪካ ምናምነኛ፣ ከኢትዮዽያ ምናምነኛ’ አስብሎ ሽልማት የሚያሰጥ አይነት ነገር፡፡
እናላችሁ…ዘንድሮ ‘ቆቅ’ በመሆንና ባለመሆን መካከል ያለው ልዩነት… አለ አይደል… ‘የጨሰ’ የሚባለው አይነት እንደመሆንና እንደ የእኔ ቢጤዎች ደግሞ ‘ዘላለሙን እርጥብ’ እንደመሆን አይነት ነገር ነው፡፡
ስሙኝማ… የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው። የሆነ ሰውን ‘ፈጣንነት’ ለመግለጽ “አጅሬው እኮ ጭልፊት ነው…” የሚሏት አባባል አለች። ጭልፊት እኮ የሚወስደው “ስጠኝ…” ብሎ ሳይሆን ሳይታሰብ በድንገት ሞጭለፍ አድርጎ ነው! እናማ… “አጅሬው እኮ ጭልፊት ነው…” የሚባልላችሁ ሰዎች ነገርዬው ውስጠ ወይራ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ደግ ነው!
እናማ…ቀደም ባለው ጊዜ ‘ማታለል’ ለሚለው ቃል እንሰጠው የነበረው ትርጉም በግሎባላይዜሽን ምክንያት ይሁን በሌላ እግዜር ይወቀው…አሁን የተለወጠ ይመስላል፡፡ ‘አጭበርባሪ፣’ ‘አምታች’  ምናምን ከሚሏቸው ትርጉሞች ይልቅ … ‘ከሌሎች ቀድሞ መገኘት’ ‘ከዘመኑ ጋር መሄድ’ ሆኗል፡፡
‘የሠራ የእጁን፣ የተቀመጠ የእንትኑን ያገኛል…’ የምትለው አባባል የማትሠራበት ጊዜ መአት ነው!
“ስማ አጅሬው እኮ የዛ የአማኑኤል እህል በረንዳ ነጋዴን ሚስት ጠብ አደረጋት…” የተባለለት ሰው፣ የሚወርድበት እርግማን ሳይሆን የሚወርድለት ‘አብሶሉት ቮድካ’ ነው፡፡ (ድሮስ ቢሆን ቮድካ…ያውም ‘አብሶሉት’… እየጠጣ!…ቂ…ቂ…ቂ…)
እናላችሁ…ነገርዬው ሁሉ “ሌላ ሌላውማ ለማን ይነገራል አይነት ሆነብን፡፡ ብልጥነት አንድ ሺህ አንድ መልክ እየለዋወጠ ግራ አጋባና!
የምር ግን…ይሄኔ እኮ ከእንጀራ ጋር ጄሶ የሚቀላቅለው ሰውዬ በ‘አድናቂዎቹ’ …“የጊዜው ነገር የገባው ነው…” ምናምን ይባልለት ይሆናል እኮ!
‘የሠራ የእጁን፣ የተቀመጠ የእንትኑን ያገኛል…’ የምትለው አባባል የማትሠራበት ጊዜ መአት ነው!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…አሮጊቷ ባህር ዳርቻ ሆነው የልጃቸው ልጅ ሲጫወት ያያሉ፡፡ ድንገትም…ኃይለኛ ማዕበል ይመጣና ልጁን ይውጠዋል፡፡ ከዛም አሮጊቷ… “እባክህ አምላኬ፣ ብቸኛው የልጅ ልጄን አድንልኝ! እባክህ መልሰህ አምጣልኝ!”… ሲሉ ይጸልያሉ፡፡ ከዛም ሌላ ማዕበል ይመጣና ልጁን አስፈንጥሮ ከእነ ነፍሱ ባህር ዳርቻው ላይ ይጥለዋል። ሴትዮዋ ልጁንን አየት አድርገው ቀና አሉና ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“ባርኔጣውንስ የት ረሳኸው!”
እንዲህ አይነትም ‘ብልጥነት’ አለላችሁ፡፡
እናማ ‘ማታለል፣’ ‘ማጭበርበር’ ምናምን አይነት ቃላት “የገባው ነው…” “ከተማዋን በጥፍሯ ነው የሚያቆማት …” ምናምን በሚሉ ቃላት ሲተኩ አሪፍ አይደለም፡፡
እናላችሁ…‘በሌላው እጅ መጉረስ’ እንደ ስንፍና ሳይሆን፣ ሥራ እንዳለመውደድ ምናምን አይነት ነገር ሳይሆን…አለ አይደል… ‘ብልጥነት’ ሲሆን አሪፍ አይደለም፡፡፣
እንግዲህ መሥራትን የመሰለ ነገር የለም። እናላችሁ…ሠርተንም፣ ለፍተንም አዲስ የአንድ ሺህ ብር ሙሉ ልብስ ለብሰን ብንወጣ… “ይሄ መናጢ ድሀ ከየት አምጥቶ ነው!” ምናምን ብለው ስሜን ያጠፉታል ብለን እንሰጋለን፡፡ እነ ፔስኮ ግን…‘በባዶ ኪስ’ የሰባት ሺህ ብር ገጭ አድርገው ሲሄዱ…”ዋዛ አድርገኸዋል፣ እንዴት አይነት ነገር የገባው መሰለህ…” ይባላሉ፡፡ ተከታዩ ምላሽ ምን  መሰላችሁ… “እንደምንም ብለህ ከእሱ ጋር ብታስተዋውቀኝ የማደርግልህን አታውቅም…” የሚል ይሆናል፡፡ ልክ ነዋ… ብዙዎቻችን በውስጣችን የፔስኮ እንጥፍጣፊ ስላለችብን፣ የእነሱን ታክቲክና ስትራቴጂ ማወቅ እንፈልጋለና!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው አርፍዶ ሥራ ይመጣል።
“ለምንድነው ያረፈድከው?”
“አንድ ሰው መንገድ ላይ መቶ ብር ጠፍቶበት ነበር…”
“አሀ…ስታፋልገው ነዋ የቆየኸው…”
“አይደለም…እሱ እስኪሄድልኝ ድረስ መቶ ብሩ ላይ ቆሜበት ነበር፡፡”
እናላችሁ እንዲህ አይነትም ‘ብልጥነት’ አለላችሁ።
‘የሠራ የእጁን፣ የተቀመጠ የእንትኑን ያገኛል…’ የምትለው አባባል ትከለስልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4195 times