Sunday, 06 November 2016 00:00

የገቢዎችና ጉምሩክ ሚኒስትሩ ምን አቅደዋል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ፈተናውን በአግባቡ መስራት ያልቻለ ሊወድቅ ይችላል

አቶ ከበደ ጫኔ (አዲሱ የገቢዎችና ጉምሩክ ሃላፊ ሚኒስቴር)
   አዲሱ ሹመት ለእርስዎ ትርጉሙ ምንድን ነው?
ሹመቱ ለኔ አዲስ አይደለም፡፡ ከአሁን በፊትም የንግድ ሚኒስትር፤ የጠ/ሚኒስትሩ የህዝብ ግንኙነትና አማካሪ ሚኒስትርም ነበርኩ፡፡ አሁን ደግሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሃላፊ ሚኒስትር ሆኜ ተሹሜያለሁ። ዞሮ ዞሮ አሁን የተሠጠን ሃላፊነት ፈተና ነው። ፈተናውን በአግባቡ መስራት የቻለ፣ በህዝብ ዘንድ ይመሠገናል፡፡ ፈተናውን በአግባቡ መስራት ያልቻለ ደግሞ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ለኛ ለተሾምነው ሰዎች ከፊታችን የተደቀነው እንግዲህ ይህ እድል ነው፡፡ መንግስት ሃላፊነት ሰጥቶናል፤ እምነት ጥሎብናል፤ ይሄን የመወጣት ያለመወጣት የኛ ድርሻ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ መሠረት የተመደብንበትን መስሪያ ቤት ለማስተካከል፣ የሃገራችን የግብር ስርአቱ መልክ እንዲይዝ በማድረግ፣ የንግዱ ማህበረሰብ የሚያነሣቸውን ቅሬታዎች በአግባቡ ተረዳድቶ የመፍታት ሃላፊነት ይጠበቅብናል፡፡ ከመስሪያ ቤቱ የስራ ባልደረቦች ጋር ሆነን፣ በአዲስ መንፈስ በተቀመጠው የህዳሴ አቅጣጫ መሠረት ለመስራት እንጥራለን ብዬ ነው የማምነው፡፡
ለህዝቡ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ከአዲሱ ካቢኔ ምን ይጠበቃል?
ከአዲሱ ካቢኔ የሚጠበቁ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ህዝቡ በጣም የሚጠብቃቸው በርካታ መፍትሄ የሚሹ ችግሮች አሉ፡፡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አለ፤ የወጣቶችና የሴቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ አለ፡፡ የከተማ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል የኑሮ ውድነት ጥያቄ አለ፡፡ በአጠቃላይ በየመስሪያ ቤቱ ሄደው ተገልጋዮች ፈጣንና ፍትሃዊ የሆነ አገልግሎት ከማግኘት አንፃር ምሬቶች አሉ፡፡ እነዚህን ምሬቶች በየተመደብንበት መስሪያ ቤት፣ በተናጥልም ይሁን በጋራ እንደ ካቢኔ የመፍታት ሃላፊነት አለበት፡፡ በአዲስ መንፈስ ተነሳስቶ የተዋቀረ ካቢኔና ለለውጥ የሚተጋ አመራር ስለሆነ፣ በእርግጠኝነት ይለውጠዋል ብዬ አምናሁ፡፡
እርስዎ የተመደቡበት መስሪያ ቤት ብዙ ባለጉዳዮች የሚስተናገዱበት ከመሆኑ አንፃር፣ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ብዙ ቅሬታዎች ይቀርባሉ፡፡ ችግሩን ለመፍታት ምን አይነት ለውጦች ይኖራሉ?
በተወሠነ ደረጃ ንግድ ሚኒስቴር በነበርኩበት ወቅት፣ በተጓዳኝ በጋራ የምንሠራባቸው ስራዎች ነበሩ፡፡ ስለ መስሪያ ቤቱ የተወሠነ መረጃና እውቀት ነበረኝ፡፡ በጣም ውስብሰብና ሃላፊነት የሚጠይቅ ቦታ እንደሆነ አውቃለሁ። ከዚያ አንፃር የተጀመሩ ሪፎርሞችን ከግብ እንዲደርሱ፤ አጠቃላይ ሲስተሙ እንዲስተካከል የማድረግ ኃላፊነት እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ በቅርብ ጊዜ የወጣ አዋጅ አለ፡፡ ይህ አዋጅ ገና ወደ ንግዱ ማህበረሰብና ህብረተሰቡ የተሸጋገረ አይደለም። በቅርብ ጊዜ ነው የፀደቀው። የተሻሻለውን ህግ ሰራተኛውና የንግዱ ማህበረሰብ እንዲያውቀውና በዚያ መሰረት ህግና ስርአት በተከበረበት አኳኋን ሰው ለሀገሩ ተገቢውን የግብር ክፍያ እንዲከፍል ማድረግ እንዲሁም በሂደቱ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በጋራ እየተነጋገሩ የመፍታት ኃላፊነት አለብኝ ብዬ አምናለሁ። የበለጠ ደግሞ በመስሪያ ቤቱ የተመደበው የሰው ኃይል ውስጣዊ ጤንነቱ እንዲጠበቅና ለንግዱ ህብረተሰብ ተገቢና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ኃላፊነት አለብኝ፡፡ የተጀመሩ የገቢ ሪፎርሞችን መሬት እንዲነኩ የማድረግ ኃላፊነት ይዘን እንሰራለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ዞሮ ዞሮ ብቻችንን የምንሰራው ስራ የለም፡፡ በቦታው ካሉ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሰራተኞች ጋር ሆነን የምንሰራው ነው፡፡ ከዚያ ወጣ ሲል ደግሞ ከግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ጋር ነው የምንሰራው፡፡ ስለዚህ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገራችንን ለማሳደግ የሚያስችለን እውቀት እየገነባን፣ ፍትሃዊ የሆነ የግብር ክፍያ እንዲኖር በትጋትና በጋራ ልንሰራ ይገባል፡፡

Read 1865 times