Sunday, 06 November 2016 00:00

አዲሱ ሚኒስትር ለኢትዮጵያ ሚዲያ ምን አስበው ይሆን?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

• አንድ አገር ናት ያለችን፤ የግልና የመንግስት ጋዜጠኞች በሚል መፈራረጅ አያዋጣም
• ሚዲያዎች፤ ያለ ምንም ፍርሃት እኩልነት ተሰምቷቸው መስራት አለባቸው
• ኢትዮጵያን የሚለውጣት የሌላ ሀገር ሚዲያ ሳይሆን የራሷ ሚዲያ ነው
ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ (የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚ/ር)

አዲሱን የሥራ ሃላፊነነት (ሹመት) እንዴት አገኙት?
ሹመቱን ጠብቄ የነበረ ባይሆንም ኃላፊነቱ ሲሰጠኝ በደስታ ነው የተቀበልኩት፡፡ ምክንያቱም ለሀገርና ለህዝብ አንድ ጥሩ ነገር የምሰራበት እድል ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ሁሉ እረዳለሁ፤ነገር ግን በተፈጥሮዬ መሰናክሎችን ተጋፍጬ የተሻለ ነገር ለማምጣት ነው የምጥረው። ፈተናዎችን አልፈራም፡፡ በግሌ ለስልጣን ፍላጎት ባይኖረኝም፣ ሹመቱ ህዝብን ለማገልገል የበለጠ እድል የሚሰጠኝ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡
አዲሱ ካቢኔ ምን ያህል ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ብለው ያምናሉ? ከካቢኔውስ ምን ይጠበቃል?
ይሄ ካቢኔ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ “ቴክኖክራት” የምንላቸው ሰዎች የተካተቱበት ነው። ለኔ እንደሚገባኝ ህዝብ የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ካቢኔው ቁርጠኛ ይሆናል፡፡ እንዲሁ በመናገርና የፖለቲካ ዲስኩር በማሰማት ብቻ ሳይሆን በመስራትና በማሰራት፣ራስን እንደ ህዝብ አገልጋይ አድርጎ በማየት፣ለራሱም ታሪክ ሲል ሰርቶ የሚያልፍ ይመስለኛል፡፡ አሁን በአብዛኛው የተሾምነው ሰዎች፣ በትጥቅ ትግል ተሳትፈን የምንኮራበት ነገር የለንም፡፡ በትጥቅ ትግሉ የተሳተፉ ሰዎች ዛሬም ይሁን ትላንት ያደረጉት አስተዋጽኦ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት ነው፡፡ ሀገሪቱ እነሱን ለማስተማር የለፋችባቸው ምሁራን፣ አገራቸውን የማገልገል እድል ሲያገኙ ደስተኞቸ ይሆናሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ የሚኮሩበት የትጥቅ ሜዳ ታሪክ ባይኖራቸውም፣ አሁን የተመረጡት አብዛኞቹ የካቢኔ አባላት በፊት የተለፋበትንና የህይወት ዋጋ የተከፈለበትን የተሻለ ሀገር የማየት ህልም፣ለፍተው እውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አብዛኞቹ የፓርቲ ሰዎች አይደሉም፡፡ ከዚህ አንፃር የህዝብ አገልጋይ ናቸው ብዬ ነው የማምነው። መስራቱና ለውጥ ማምጣቱ ግዴታ ነው እንጂ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም መንግስት መስራት ይችላሉ ብሎ፣ እውቀትና አመለካከታቸው ተመዝኖ የመጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ የምርጫ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡ ለራሴም እንደዛ ብዬ ነው የተቀበልኩት፡፡ ሰው በህይወት ዘመኑ ደግሞ ለሀገሩ አንድ ነገር አድርጎ ማለፍ አለበት፡፡ ይህን ማድረጉ ክብርም ይመስለኛል፡፡ ሌሎች የስራ ባልደረቦቼም በዚህ መንፈስ በቅንነት ያገለግላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
ከዚህ ቀደም በጋዜጠኝነትና በሚዲያ ዙሪያ በሚያቀርቡት ጥናቶችና በሚሰጡት ስልጠናዎች ነበር የሚታወቁት፡፡ አዲሱን የሥራ ሃላፊነትዎን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ ሚዲያ ንፍቀ ክበብ ምን አይነት ለውጦች ይኖራሉ?
ሁሌም ጥናታዊ ፅሁፍ እንዳቀርብ ስጋበዝ፣ የኔ ማዕከል ህዝብ ነው፤ሚዲያ ህዝብን ማገልገል አለበት፤ ባለቤቱ ማንም ይሁን፣የመንግስት ሚዲያ ለህዝብ ነው ማገልገል ያለበት፡፡ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም መስራት አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። ጋዜጠኛ በሚፅፈውና አየር ላይ በሚያውለው ሁሉ ለህዝብ ምን ጥቅም አለው? የትኛውን ጥያቄ ይመልሳል? ህዝብን የሚጎዳ አሰራርን ምን ያህል ፈትሾ ለህዝብ ያቀርባል? ይሄንን ምንም ሳላወላውል በጥናቶቼ ሳቀርብ ነበር፡፡ ስለ ልማት ስናነሳ፣ ሙስና አለ፤ ስለዚህ ሚዲያ በዚህ ላይ ሊሰራ ይገባል የሚል እምትና አቋም አለኝ፡፡ አሁንም ቢሆን ኃላፊነቱ ሲሰጠኝ ይህ አቋሜ አይቀየርም፡፡ እኔ በብዙ ቢሮክራሲ ውስጥ አልፌ አይደለም ይህ ኃላፊነት የተሰጠኝ፡፡ ያለኝ ቁርጠኝነት ታይቶ በመሆኑ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ በምትፈልገው ልክ እንዲሆኑ መስራት አለብኝ ብዬ ነው የማምነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚለውጣትና ዲሞክራሲዋ የበለጠ እንዲያድግ የሚያደርጋት የሌላ ሀገር ሚዲያ አይደለም፤የሀገሪቱ ሚዲያ ነው፡፡
ሁሉም ዜጎች ህገ መንግስቱ የሰጣቸውን እኩልነት እንዲጎናፀፉ፣ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲያገኙ የሚያደርግ የኢትዮጵያ ሚዲያ እንዲፈጠር ነው የምፈልገው፡፡ ጋዜጠኞች “የግል ነን፤ የመንግስት ነን” በሚል እርስ በእርሳቸው መናቆር ሳይሆን አንድ አገር አለችን ብለው፣ ይህቺን ሀገር የተሻለች ለማድረግ በትጋት መስራት ነው ያለባቸው፡፡ በቂና ጥራት ያለው መረጃ ህዝቡ ጋ መድረስ አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ያሉትን ችግሮች በጥናቶች ፈትሸን፣ እኔም ከዚህ በፊት ባደረኳቸው ጥናቶች የማውቃቸውን ችግሮች ፊት ለፊት በማውጣት ተወያይተንበት ሚዲያውን ለማጠናከር፣ የጋዜጠኞችን አቅም ለመገንባት እንሠራለን፡፡
የጋዜጠኞች ማህበራትም አሉ፡፡ አንዱ የግል፤ሌላው የመንግስት እየተባባሉ መፈራረጅ ብዙም የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ያለችን አንድ ሃገር ነች፡፡ መረጃን በተመለከተ ደግሞ በተለይ በህዝብ ግንኙነት ቢሮ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች፣እንዲሁ ላይ ላዩን እያስመሰሉ፣ ችግራችንን እንድንቀበል የማያደርጉን ከሆነ፤ ድክመታችንን እንደ ድክመት የማያቀርቡ ከሆነ መለወጥ አንችልም፡፡ ስለዚህ የህዝብ ግንኙነት ስራ የሚሰሩ መረጃ አምራቾች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት አለበት፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው መቀጠል የለበትም፡፡ አለቃውን ብቻ ለማስደሰት የሚሠራ የህዝብ ግንኙነት  ባለሙያ፣ እንዲሁ መቀጠል አይችልም፡፡
የግልም ይሁኑ የመንግስት ሚዲያዎች በህግ ጥላ ስር ነው ያሉት፤ያለ ምንም ፍርሃት እኩልነት ተሰምቷቸው መስራት አለባቸው፡፡ ማንም ሰው ሃገሩን የሚጎዳ ነገር እስካልሰራ ድረስ ነፃነት ተሠምቶት የሚያስፈራው ነገር እንደሌለ አውቆ መስራት አለበት፡፡ ነፃነቱ የበለጠ የዲሞክራሲ ባህላችን እንዲያድግና የራሱን ድርሻ እንዲውጣ ያደርገዋል፡፡

Read 1957 times