Sunday, 06 November 2016 00:00

“ቃና” ሁለት አዲስ ዝግጅቶችን ማስተላለፍ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የፌስ ቡክ ተከታዮቹ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሆነዋል

ቃና ቴሌቪዠን የተመልካቾቹን የመዝናኛ አማራጭ ለማጎልበት ሁለት አዳዲስ ዝግጅቶችን (አንድ ወጥ እና አንድ በአማርኛ የተመለሰ) ማቅረብ መጀመሩን ገለጸ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ጣቢያው በየሳምንቱ የ30 ሰዓት አዳዲስና ያልታዩ ዝግጅቶችን ለተመልካቹ እንደሚያቀርብ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ሰሞኑን 5ኛ ክፍሉ የተሰራጨው የ #ምንድን ዝግጅት፣ የተለያዩ ወቅታዊ ማሕበረሰብ ተኮር ርዕሶችን እያነሳ ከተለያዩ ምልከታዎች አንጻር የሚያወያይ ሲሆን በዚህም የተመልካቾችን ተሳትፎና ጤናማ ውይይቶች ያበረታታል ተብሏል። አዲስ የተጀመረው “ልጅቷ” የተባለው የኮሎምቢያ ድራማ፤ በእውነተኛ ክስተቶች ላይ የተመረኮዘ ሲሆን የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ያሳያል፡፡ ታሪኩ አንዲት ሴት በሽምቅ ተዋጊዎች ተመልምላ የጦርነትን አስከፊ ገፅታ በአፍላ እድሜዋ እንድትኖረው ስትገደድና ከብዙ ዓመት በኋላ አምልጣ አዲስ ኑሮ ለመጀመር ስትሞክር፣ ከሕብረተሰብ ጋር ለመቀላቀል፣ ነፃነትዋን ለመልመድና ቤተሰብዋን ለመጋፈጥ የሚደርስባትን ውጣ ውረድ ያስቃኛል፡፡ ድራማው ከፍተኛ አድናቆትን ያገኘ ሲሆን በቅርቡ ኔትፍሊክስ በተባለው ታዋቂ የፊልም አቅራቢና አከፋፋይ ተገዝቶ፣ በብዙ አገሮች እየታየ ይገኛል ብሏል - ቃና በመግለጫው፡፡
በተመልካቾች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈውን ጥቁር ፍቅር የተሰኘ ድራማ የሚተካ ቅጣት የተባለ ወደ አማርኛ የተመለሰ የቱርክ ድራማ በቅርቡ ማቅረብ እንደሚጀምር ጠቁሞ ቅጣት በይዘቱ ልክ እንደ ጥቁር ፍቅር በተለያዩ አገሮች ዝና እና ሽልማት ተቀዳጅቷል ተብሏል፡፡
ጣቢያው የተመልካቾቹን ዕይታ ለማበልፀግና ፍላጎታቸውን ለመገንዘብ፣ በየጊዜው የተለያዩ ጥናቶችና ዳሰሳዎች እንደሚያካሂድ ጠቁሞ ግኝቶችንም በሚያቀርባቸው ዝግጅቶች ላይ እንዲንፀባረቁ ይደረጋል ብሏል፡፡
በስርጭት ላይ በቆየበት የስድስት ወር ጊዜያት ውስጥ ጥሩ አቀባበል ማግኘቱን የጠቀሰው ቃና.፤ የፌስ ቡክ ተከታዮቹ ከ1 ሚሊዮን በላይ መድረሳቸውን አስታውቋል፡፡ በቅርቡ በቤል ካሽ የተካሄደ በ 5000 ሰዎች ላይ የተደረገ አገር አቀፍ የስልክ መጠይቅ፤ ከሶስት ተጠያቂዎች ውስጥ አንዱ የቃና ቴሌቪዥን ዝግጅቶችን ከሰኞ እስከ አርብ በየቀኑ እንደሚያዩ አመልክቷል፡፡
“ቃና ቴሌቪዥን በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው አቀባበል አበረታችና ከጠበቅነው በላይ ነው። ወደፊትም  የመዝናኛ አማራጭ የሆኑ አዝናኝና አሳታፊ ዝግጅቶችን ለማቅረብ የተመልካቾቻችንን ፍላጎት ማጥናት እንቀጥላለን” ብለዋል፤ የቃና ቴሌቪዥን የኮሙኒኬሽን እና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር፡፡  
ቃና ቴሌቪዥንና የዝግጅት አጋሩ ቢ ሚዲያ በቅርቡ ይፋ የሚሆኑ ተጨማሪ ወጥ ስራዎችን እያዘጋጁ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Read 3157 times