Sunday, 06 November 2016 00:00

የደራሲው እውነት ወዴት አለች!? ይድረስ ለጋሼ አያልነህ ሙላት፤

Written by 
Rate this item
(2 votes)

መነሻ
ባለፈው ሳምንት በወጣው “ቁምነገር” መጽሄት ላይ የጸሀፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ቃለመጠይቅ ታትሞ ነበር፡፡ በሁለት ክፍል ያሳተማቸው ግጥሞች ላይ የተሰነዘሩ ትችቶች አሉ ወይ? ብሎ ጋዜጠኛው ላቀረበለት ጥያቄ እንዲህ ሲል መለሰ፡
‹‹ፊት ለፊት መጥቶ የነገረኝ ሰው የለም፡፡ አንድ ግን ዶ/ር በድሉ የሚባል ሰው በጋዜጣ ላይ ትችት ጽፎ ነበር፡፡ በኋላ ራሱ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ እንዴት ነው የተቸኸው ሲባል፣ በየ 100 ገጹ አንዱን ግጥም አንብቤ ነው የምተቸው አለ፡፡ ይሄ ምን አይነት ንቀት ነው፡፡ በፍጹም እንዲህ አይደረግም፡፡ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ደራሲው የጻፈበትን ርእዮተ አለምስ አይተኸዋል ወይ ሲባል፣ ‹ይሄ ምን ርእዮተ አለም አለው› አለ፡፡ ሰዎች ናቸው ይህን የሚነግሩኝ፡፡ የኔ ግጥም እኮ የተጻፈው በሶሻሊስት ርእዮተ አለም ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ‹ይሄን ርእዮተ አለም ሳታውቅ እንዴት ጻፍክ?› አሉት፡፡ ከዚያ፣ ‹ይቅርታ፣ እኔ ይህንን አላወቅኩም ነበር አለ፡፡ በድሉ ጥሩ ገጣሚ ነው፡፡ ስራዎቹንም አንብቤለታለሁ፡፡ ቢሆንም ግን የኔን ግጥም ለመተቸት ብቃቱ ያለው አይመስለኝም። . . . እንዲያውም በእሱ ላይ የሆነ ልጅ መልስ ጽፎ ነበር፡፡ ግን “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ወስዶ ሲሰጣቸው አይታተምም ብለው ከለከሉት፡፡ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ቢታተም ኖሮ መከራከሪያ ነጥብ ይሆን ነበር፡፡ ለውይይት በር ይከፍታል፡፡ ግን እምቢ አሉት፡፡›› (ቁምነገር፣ ቅጽ 15፣ ቁጥር 270፡፡)
በዚህ አንቀጽ ከሰፈረው የጋሽ አያልነህ ንግግር ያለው እውነት አንድ ብቻ ነው፤ የእኔ ስም፡፡ ግራ ተጋባሁ፡፡ የእጅ ስልኬን አነሳሁና ጋሽ አያልነህ ዘንድ ደወልኩ፤ ስልኩ ተይዟል፡፡ ቆይቼ ደወልኩ፤ ይጠራል፡፡ አላነሳውም፡፡ ከአንድ ሰአት በሁዋላ ደወልኩ፡፡ ስልኩ ተዘግቷል፡፡ ሲከፈት እንዲነገረኝ አንድን ጨቁኜ ዘጋሁት፡፡ ይህ የሆነው ቅዳሜ ነው፡፡ እሁድ አልፎ ሰኞ መጣ፤ ስልኩ አልተከፈተም፡፡ ሰኞ እለት የ”ቁም ነገር” መጽሄት አዘጋጅ ዘንድ ደወልኩ፡፡ የሰፈረው መረጃ ሀሰት መሆኑን ስነግረው፣ ‹‹እንዴት ሊሆን ይቻላል? ጋሼ አያልነህ አይዋሽም፤ ትልቅ ሰው ነው፡፡›› አለኝ፡፡ አያይዞም፣ እንደሚያናግረውና ማስተባበያ ካለው እንደሚያትመው ገልጸልኝ፡፡ እራሴን ተጠራጠርኩት፡፡ የጋሽ አያልነህ ግጥሞች የታተሙ ሰሞን ሚዩዚክ ሜይዴይ በሚያዘጋጀው ሂሳዊ ውይይት ላይ፣ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሀሳብ፣ እራሱ ጋሽ አያልነህ ባለበት እንዳቀረብኩ ትዝ ይለኛል፡፡ በጋዜጣ ግን በፍጹም አልጻፍኩም፡፡ ምን አልባት ለውይይት ያቀረብኩትን አትመውት ይሆን? በወቅቱ የሚዩዚክ ሜይዴይ አስተባባሪ የነበረው በፍቃዱ አባይ ስለነበር በእጅ ስልኩ ላይ ደወልኩ። ሁኔታውን በዝርዝር ገለጥኩለት፡፡ ለዚያ ውይይት ያቀረብኩት መነሻ ሀሳብ በየትኛውም ጋዜጣ እንዳልታተመ ገለጠልኝ፡፡ አያይዤም፣ ‹‹ለመሆኑ በውይይቱ ላይ ይቅርታ ጠይቄው ነበር እንዴ?›› ስል ጠየኩት፡፡ ‹‹በጭራሽ! እንዲያውም መጨረሻ  ላይ እኮ እራሱ ጋሽ አያልነህ፣ ‹ስሜታዊ ሆኜ በድሉን ያስቀየምኩት ይመስለኛል፤ ይቅርታ ልጠይቅ ብሎ› ይቅርታ የጠየቀው እሱ ነው፤ ካስፈለገ እኮ ሙሉ ውይይቱ በምስል መቅጃ ተቀድቷል፡፡›› አለኝ። “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ አዘጋጅ ዘንድ ደወልኩ፤ ‹‹በእኔ ስም ጋሽ አያልነህ ግጥሞች ላይ የታተመ ሂስ አለ እንዴ?›› ጠየቅኩ፡፡ ‹‹ኧረ በጭራሽ›› መለሰልኝ፡፡ ‹‹እሺ የሆነ ልጅ መልስ አምጥቶ ለምን አናትምም አላችሁ?›› ደግሜ ጠየቅኩ፡፡ ‹‹እንዴ! መጀመሪያ አንተ ካልጻፍክ መልስ እንዴት ይመጣል?›› በጥያቄ መለሰልኝ፡፡ ‹‹እሺ መልስም አይሁን፣ ስለ ጋሽ አያልነህ ግጥሞች፣ የተጻፈ፤ የእኔን ስም የሚጠቅስ ጽሁፍ መጥቶላችሁ ነበር?›› ደግሜ ጠየቅኩ፡፡ ‹‹ኧረ በፍጹም!››፡፡
ማክሰኞ ጠዋት የስልኬ የመልእክት ማሳበቂያ ድምጽ ጮኸ፡፡ ከፍቼ ሳነበው፣ ‹ጋሽ አያልነህ ስልኩን ከፍቷል፤ አሁን ብትደውል ታገኘዋለህ ይላል›፡፡ ደወልኩለት፡፡ ተነሳ፡፡
‹‹ሀሎ ጋሽ አያልነህ››
‹‹ማን ልበል?››
‹‹በድሉ ነኝ፡፡››
‹‹አያልነህ መኪና እየነዳ ነው፤ ‹ከደቂቃዎች በኋላ እደውልልሀለሁ› እያለህ ነው፡፡››
‹‹ጥሩ፡፡ በቁምነገር መጽሄት ላይ እኔን ጠቅሶ የተናገረውን እንዳነበብኩትና ስለዚያ ጉዳይ ላነጋግረው እንደምፈልግ ንገርልኝ፡፡››
‹‹እነግረዋለሁ፡፡ ይደውልልሀል፡፡››
አንድ ሰአት. . . ሁለት ሰአት አለፈ፤ አልተደወለም። እኔ ደወልኩ፡፡ መጥራት እንደጀመረ ጥሪው ተጨናገፈ፡፡ ደግሜ ደወልኩ፤ አሁንም ተጨናገፈ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ምርጫ ሁለት ነው፡፡ አንድ፣ ንቆ መተው፡፡ ሁለት፣ እሾህን በሾህ እንዲሉ፣ የሚዲያውን ሁከት በሚዲያ ማጥራት፡፡ እኔ ሁለተኛውን መረጥኩ፡፡ ንቆ መተው፣ ይሉኝታ . . . የሚባሉት እሴቶች፣ በመቻቻልና በመከባበር አብሮ ለመኖር ትልቅ ዋጋ ቢኖራቸውም፣ ያለ ቦታቸው ሲገቡና ደፋር ሆን ብሎ ሲጠቀምባቸው የሀሰትን፣ የበደልንና የእስስታዊነትን ጡንጫ ያደነድናሉ፡፡ በተለይ እንደ ጋሽ አያልነህ አይነት በእድሜ አንጋፋና ታዋቂ ሰው በርካታ ወጣቶች ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ ቀላል ስላልሆነ፣ እንዲህ አይነቱን ‹ጅብ ወለደ› ንቆ መተው፣ በተለይ እንደኔ ግማሽ እድሜውን መምህር ሆኖ ለኖረ፣ ሀላፊነትን ያለመወጣትም ጭምር ነው፡፡  
በጋሽ አያልነህ ንግግር ላይ መልስ ለመስጠት ከወሰንኩ በኋላ፣ ጽሁፌ ምን አይነት መሆን፣ ምን ምን ጉዳዮች መያዝ አለበት? ብዬ እራሴን ጠየቅኩ። በ‹‹እንዲህ ብለሀል!  . . . እንዲህ አላልኩም!››  ብቻ የታጀለ ፍሬ ከርስኪ እንዲሆን አልፈለግኩም፡፡ ጋሽ አያልነህ ‹‹ . . እንዲህ አለ አሉ›› ብሎ የጠቃቀሳቸውን ሀሳቦች፣ ከ‹‹አለ አሉ›› የሀሜት ግርግም አውጥቼ፣ ከእውቀትና እውነት መስክ ላግጣቸው ወደድኩ፡፡
ለምን ይዋሻል!?
ጋሽ አያልነህ፣ በጸሀፊነት የማውቀህ የመጀመሪያ ዲግሪ የቋንቋና ስነጽሁፍ ተማሪ ከነበርኩበት፣ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ነው፡፡ በእሳት ሲነድ፣ ትግላችን፣ ሻጥር በየፈርጁ፣ የመንታ እናት. . . ወዘተ. በመሳሰሉት አብዮታዊ ተውኔቶቹ አውቅሀለሁ፡፡  
ጋሽ አያልነህ ትዋሻለህ፡፡ ‹‹. . ዶ/ር በድሉ የሚባል ሰው በጋዜጣ ላይ ትችት ጽፎ ነበር፡፡›› አልክ፤ እኔ በየትኛውም ጋዜጣ ትችት አልጻፍኩም፤ ጋዜጣውን አምጣና ሞግተኝ፡፡ በአንድ ውይይት ላይ ለውይይት የሚሆን የመነሻ ሀሳብ በቃል አቅርቤያለሁ፡፡  ‹‹በኋላ ራሱ ይቅርታ ጠይቋል፡፡›› አልክ፤ እኔ አንተን ይቅርታ አልጠየቅኩም፡፡ ይቅርታ ያልጠየቅሁ ይቅርታን ስለምጸየፍ ወይም የተሸናፊነትና የአሽናፊነት መግለጫ አድርጌው አይደለም፡፡ ባጠፋ እንኳን አንተን ታላቄን፣ ታናሼንም ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ አንተ ግን ይቅርታ መጠየቅን የተሸናፊነት መገለጫ አድርገህ ትመለከተዋለህ፡፡ ይህን ያስባለኝ፣ አዳራሽ ሙሉ ሰው በተሰበሰበበት፣ ውሉ ዝግጅቱ በምስል መቅጃ በተቀዳበት ዝግጅት መጨረሻ ይቅርታ የጠየከኝ አንተ ሆነህ ሳለ ገለበጥከው፡፡ ምነው እኔ አጥፍቼ በሆነና ይቅርታ በጠየቅኩህ (በነገራችን ላይ ዘንግተኸው ከሆነ ሚዩዚክ ሜይዴይ የተቀረጸው ፊልም አለ)፡፡ ጋሼ በጣም ያዘንኩት በአንተ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሰው ልጅ ላይ ያለኝን እምነት የፈተነብኝ፣ ‹‹ፊት ለፊት መጥቶ የነገረኝ ሰው የለም፡፡. . . . . ሰዎች ናቸው ይህን የሚነግሩኝ፡፡›› ያልከውን ሳነብ ነው፡፡ ምነው ጋሼ! አዳራሽ ሙሉ ሰው ፊት፣ መድረክ ላይ ተቀምጠን፣ ወጣት በፍቃዱ አባይ ውይይታችንን እየመራው፣ የግጥሞችህን ጉድፎች ያልኩትን ፊት ለፊት አልነገርኩህም?  
ጋሼ አንድ ጸሀፊ ለቤተሰቡ፣ ለወገኑ፣ ሲልቅም ለሰው ልጆች ክብር ሊኖረው ይገባል፡፡ ለዚህ ሁሉ መሰረቱ ግን ራስን ማክበር ነው፡፡ የጸሀፊው የራስ ክብር ደግሞ መሰረቱ እውነትን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ (ህይወቱን የሚያስከፍለው ቢሆን እንኳን) ለመመስከር ያለው ቆራጥነት ነው፡፡ ራስህን ለእውነትና ፍትህ ስታስገዛ፣ ለማህበረሰብህ እውነትና ፍትህን ትመግበዋለህ፡፡ ከዚህ አንጻር ለራስህ ክብር የለህም ብልህ ቅር ይልህ ይሆን? ለራስህ ክብር ቢኖርህ እንደምን እንዲህ ያለ የሀሰት ቅሌት ውስጥ አያልነህን ትጨምረዋለህ? ‹‹እንዴት ነው የተቸኸው ሲባል፣ በየ 100 ገጹ አንዱን ግጥም አንብቤ ነው የምተቸው አለ፡፡ ይሄ ምን አይነት ንቀት ነው፡፡ በፍጹም እንዲህ አይደረግም፡፡ ትልቅ ስህተት ነው። ደራሲው የጻፈበትን ርእዮተ አለምስ አይተኸዋል ወይ ሲባል፣ ‹ይሄ ምን ርእዮተ አለም አለው› አለ፡፡ የኔ ግጥም እኮ የተጻፈው በሶሻሊስት ርእዮተ አለም ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ‹ይሄን ርእዮተ አለም ሳታውቅ እንዴት ጻፍክ?› አሉት፡፡ ከዚያ፣ ‹ይቅርታ፣ እኔ ይህንን አላወቅኩም ነበር አለ።››  በየ100 ገጹ አንድ ግጥም ብወስድማ፣ 1156 ገጽ ካለው አንዱ መጽሀፍህ ውስጥ 11 ግጥሞች ብቻ ነበር የሚሆነው፡፡ እኔ ግን ሌላው ቀርቶ ጋሼ፣ በዘጠኝ ቀን የእስር ቤት ቆይታህ (ከግንቦት 28 ቀን 1996 እስከ ሰኔ 7 ቀን 1969) የጻፍካቸውን ወደ 22 የሚጠጉ ግጥሞች ገምግሜ፣ ‹‹አንድ ጓድ ለሌላው ጓድ የጻፋቸው ደብዳቤዎች ይመስላሉ፤አንተ ራስህ በመግቢያህ ውስጥ ስለ ግጥም ያስቀመጥካቸውን ባህርያት አያሟሉም.›› ብዬህ ነበር፡፡
ሌላው የተሟገትንበት ነጥብ፣‹ ‹በድሉ ሶሻሊዝምን አያውቅም፤ የተማረው አሜሪካ ስለሆነ ሶሻሊዝምን ይጠላል፡፡›› ስትል፣ የተማርኩት አሜሪካ ሳይሆን ኖርዌይ መሆኑን አስተካክዬህ፣ ስለ ሶሻሊስት ሪያሊዝም ስነጥበባዊ ፍልስፍና ተነጋግረን ነበር፡፡ አሁንም ደግሜ ልንገርህ ጋሼ፣ በየዘመኑ የተጻፉ ስነጽሁፎችን ለመገምገም በየዘመኑ መኖር አያሻም፤ እንዲያ ቢሆን ለሀምሌትና ኦቴሎ የሼክስፒር ዘመነኛ ሀያሲ ከየት አባታችን እናመጣ ነበር! ስለ የዘመኑ ስነጥበባዊ ፍልስፍና እና ስለየ ስራዎቹ ባህርያት ማወቅ፣ በንባብ የመተንተንን አቅም ማዳበር ለአንድ ሀያሲ በቂው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጋሼ፣ ሶሻሊዝምን እንዳንተ በቅርብ ባይሆንም፣ በመኖርም አውቀዋለሁ፡፡ ገና በ11 አመቴ፣ በጠዋት የኪራይ ወተት ሳመጣ፣ ከደጃችን ላይ ክብ ሰርቶ የከበበውን ሰው፣ ግራ ቀኝ ሰርስሬ ስገባ፣ ቀይ ሽብር የጣለውን የጎረቤታችንን የእንሰሳት ሀኪሙን የዶ/ር መክብብ ተሰማን ሬሳ ስመለከት፣ከእጄ ካመለጠው የወተት ሽጉጥ (የቢራ ጠርሙስ ሽጉጥ ይባል ነበር) የፈሰሰው ወተት አፈሩ ላይ ከረጋው ደም ጋር ሲደባለቅ የፈጠረው ህብረ ቀለም ዛሬም ደምቆ ይታየኛል፡፡ ‹‹ሁሉም ለአብዮታዊት እናት ሀገር ዘብ ይቁም!›› ብላችሁ ባወጃችሁት የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት፣ ገና 18 አመት ልደፍን መንፈቅ ሲቀረኝ ከትምህርት ቤት ታፍሼ፣ የሁለት አመት ከመንፈቅ ግዳጄን ተወጥቻለሁ፡፡ እና ጋሼ እንዳንተ ባልንቦጫረቅበትም፣ እንደ አንድ የዘመነ ደርግ ወጣት ሶሻሊዝምን በመኖርም በመጠኑ አውቀዋለሁ፡፡
‹‹እንዲያውም በእሱ ላይ የሆነ ልጅ መልስ ጽፎ ነበር፡፡ ግን “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ወስዶ ሲሰጣቸው አይታተምም ብለው ከለከሉት፡፡ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ቢታተም ኖሮ መከራከሪያ ነጥብ ይሆን ነበር፡፡ ለውይይት በር ይከፍታል። ግን እምቢ አሉት፡፡›› ላልከውም ተደራቢ ውሸትና (ካፈርኩ አይመልሰኝ) መሆኑን የጋዜጣው አዘጋጆች አረጋግጠውልኛል፤ እና ጋሼ ግን ለምን? እንዳንተ ያለ አንጋፋ፣ የኢትዮጵያን ደራስያን ማህበርን በምክትል ሊቀመንበርነት የሚመራ፣ ብዙ ወጣቶች በአርአያነት ቀና ብለው የሚመለከቱት ሰው ለምን ይዋሻል? አንድ የሰውን ልጅ እታደጋለሁ የሚል ደራሲ፤ እንደምን ከዚህ አይነቱ ውሸት ጋር አደባባይ መቆም ይቻለዋል?
የደራሲው እውነት ወዴት አለች!?
የደራሲ እውነት የግሉ እውነት ብቻ አይደለም፤ እንዲያውም ማህበራዊና ሰብአዊ እውነቱ ነው ጸሀፊን በማህበሰቡ ውስጥ የመሪነት ሚና የሚያጎናጽፈው፡፡ በዚህ ረገድ አኔና አንተ በዘመናችን እንደ አቤ ጉበኛና በአሉ ግርማ ያሉ ስለ ሰው ልጅ እውነት መስዋእት የሆኑ ደራስያን እናውቃለንና ታድለናል። ለሰው ልጅ እውነት ለመቆም የሚውተረተር ነፍስ ካለንም ድጋፍ ልናደርገው እንችላለን፡፡ ጋሼ መቼም አደባባይ ቆመን እንድንነጋገር መርጠሀልና እስቲ ስለዚህ አይነቱ የደራሲ እውነት እንነጋገር፡፡ ከአንተ ዘንድ ይህች የደራሲው ማህበራዊና ሰብአው እውነት አለችን? እኔ አታውቃትም ብዬ እማኝ ጠቅሼ እሞግትሀለሁ። እማኝ የምጠቅሰው አንተኑ ነው፤ ተግባርና አንደበትክን፡፡
ባለፈው ሳምንት በዚያው በ”ቁምነገር” መጽሄት ላይ እንዲህ ብለሀል፤ ‹‹ዛሬ የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ህዝብ እየመራ አይደለም፡፡ በመሰረቱ ኪነጥበብ ህዝብን መምራት አለበት፡፡›› ልክ ብለሀል ጋሼ፤ እኔም በዚህ ነጥብ እስማማለሁ፡፡ ስለዚህ ሁላችንም እንደ አቅማችን የምንኖርበት ማህበረሰብ መንገዱን ያስተውልበት ዘንድ ጭላንጭል ለመፈንጠቅ እንሞክራለን፡፡ የሚገርመው ግን ይህ አባባልህ ከሰበካነት አልፎ የደራሲ ነፍስህ ግብር አለመሆኑ ነው፡፡ ‹‹እኔ በደርግ ውስጥ የነበርኩ ሰው ነኝ። በእዚያ ውስጥ እያለሁ ምን እጽፍ ነበር? በአንድ በኩል ለእንጀራ የሚሆን ስራ ትሰራለህ፡፡›› ትላለህ፣ እዚያው ቃለመጠይቅ ውስጥ፡፡ ‹‹ለእንጀራ›› ማለት ምን ማለት ነው ጋሼ? በደርግ ዘመን ወጣቶች ላመኑበት፣ ለሀገርና ማህበረሰብ ይበጃል ላሉት እውነት መስዋእት ሲሆኑ፣ ደራስያን ባመኑበት እውነት ፍቅር ተነድፈው ሲጠፉ፣ አንተ ለእለት እንጀራ ትጽፍ ነበር! እስቲ ልጠይቅህ፤ ትግላችንን፣ የመንታ እናትን፣ ሻጥር በየፈርጁን፣ እሳት ሲነድን . . . .  ጽፈህ የበላኸው እንጀራ ምን ምን ይላል? ይህን የምጠይቅህ ለምን አብዮቱን በብእርህ አፋፋምክ፣ ደገፍክ ብዬ አይደለም፡፡ ብዙዎች በደርግ ዘመን ስለ አብዮቱ ጽፈዋል፡፡ ‹ሶሻሊዝም የሀገራችንን ህዝቦች ለዲሞክራሲና ለብልጽግና ያበቃል፤ በህዝቦች መካከል እኩልነትን ያሰፍናል› ብለው ከልብ አምነው እንጂ፣ለእለት ጉርስ ብለው ግን አይደለም። ባለቅኔውንና ጸሀፌ ተውኔቱን ደበበ ሰይፉን ታውቀዋለህ፡፡ ለሶሻሊዝም የነበረው እምነት መቼም ከሀይማኖት የላቀ ነበር፡፡ ‹መስከረም›፣ ‹በስሙ ሰየማት›፣ ‹ትዝታ ከበሮ›ን የመሳሰሉት ግጥሞቹ፣ደበበ ሶሻሊዝምን ምን ያህል ከልቡ ያምንበት እንደነበር ከማሳየታቸውም በላይ፣ እውነቱና ምናቡ  ተቃቅፈው ያዘመሩትን ቅኔ ምጥቀት ይመሰክራሉ። ደበበ ከደርግ መውደቅና ከሶሻሊዝም ቀብር በኋላ፣ የኖረውን ኑሮና መጨረሻውን የምታውቅ ይመስለኛል፡፡ በአሉንም ከእኔ በተሻለ ታውቀዋለህ። ጋሼ እንዲህ ያለችው እውነት አንተ ዘንድ የለችም፡፡ ትላንት እውነቴና እምነቴ ነው ብለህ፣ ‹እሳት ሲነድን› ያንቀለቀልክለትን አብዮት፣ ዛሬ እንጀራ ገዶኝ ነው ማለት፣ በዚህኛው ዘመንም ማኛ ለማነጎት ምጣድ ከማስማት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡


Read 2363 times