Sunday, 06 November 2016 00:00

አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ 91 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ አገኘ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቀዳሚውና ከተመሰረተ 2 ዓመት የሆነው አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ አ.ማ ጁን 30, 2016 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ 81 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ኩባንያው የዛሬ ሳምንት በሂልተን ሆቴል ባደረገው 22ኛ ዓመታዊ መደበኛ የባለ አክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ የቦርድ  ሊቀመንበሩ አቶ ቀነዓ ዳባ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ ምንም እንኳን ዓመቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ቢያልፍም ኩባንያቸው ባደረገው ጠንካራ እንቅስቃሴ አመርቂና የተሳካ ውጤት ማስመዝገቡን ገልፀዋል፡፡ አጠቃላይ የአረቦን ገቢያቸው ከኢንሹንስ ኢንዱስትሪውና ከአቻ ኩባንያዎች ዓመታዊ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ብልጫ በማሳየት በ18.5 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡
በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት በአገሪቷ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከመልካም ዕድሎች ይልቅ ተግዳሮቶች የበዙበት እንደነበር የጠቀሱት አቶ ቀነዓ ትርፋማና ውጤታማ ሆኖ ለመቀጠል እነዚህን አስቸጋሪና ጠጣር የገበያ ውድድሮች በበላይነት ለመወጣት ከሁሉም ተሽሎና በልጦ መገኘት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የዋጋ ሰበራ፣ የዘርፉ ምሰሶ የሆኑትን ዋና ዋና መርሆዎች ለድርድር ማቅረብ፣ የካሳ ክፍያ እጅግ በናረበት፣ በኢንሹንስ ኩባንያዎች መካከል ልምድ ያለው ባለሙያ ነጠቃ በጦፈበት፣ ሁኔታ በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮች በአሸናፊነት ለመወጣት ከፍተኛ ጥንካሬ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በአገሪቷ አጠቃላይ ኢንሹራንስ 16.3 በመቶ፣ በሕይወት ኢንሹራንስ 5.7 በመቶ ዕድገት የታየ ሲሆን ዕድገቱ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በአጠቃላይ ኢንሹራንስ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን በሕይወት ኢንሹራንስ ግን የማያረካ ዕድገት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው በዓመቱ ባደረገው እንቅስቃሴ አኩሪና አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን የጠቀሱት አቶ ቀነዓ፣ ከታክስ በፊት 104.6 ሚሊዮን ብር ማግኘታቸውን፣ ታክስ፣ መጠባበቂያና ሌሎች ወጪዎች ከተቀነሱ በኋላ 91.15 ሚ. የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ይህም ትርፍ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ የ41 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በወጪ ረገድ በአጠቃላይ ዘርፉ 218.7 ሚ. ብር ለካሳ የተከፈለው ክፍያ ትልቁ ሲሆን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ የ29.1 ሚ. ብር ወይም የ15.4 በመቶ ብልጫ እንዳለው ታውቋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል 190.3 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን የአንድ ዕጣ የትርፍ ክፍያ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር 48 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ በዓመቱ በአዲስ አበባ ከተማ ሁለት ቅርንጫፎች ከፍቶ፣ ከአገናኝ ቢሮዎችና ከሕይወት አቢይ ቅርንጫፍ ጋር የቅርንጫፎቹ ቁጥር 41 መድረሱና በአገሪቷ የሚገኙ ቅርንጫፎች በሙሉ በኔትዎርክ የተገናኙ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ኩባንያው 444 ሰራተኞች ሲኖሩት ከዚህ ውስጥ ግማሽ ወይም 50 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡   

Read 1556 times