Sunday, 06 November 2016 00:00

‹‹ባልመረጥም እመረጣለሁ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ከትናንት ጀምሮ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡ በጉባኤው ከዓመታዊ አጀንዳዎቹ በተጨማሪ
ለሚቀጥሉት 4 ዓመታት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን የሚያስተዳድሩ አመራሮች ምርጫ የሚያከናውን በመሆኑ አበይት ትኩረት ስቧል፡፡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የቀድሞና
የአሁን አትሌቶችም ለፕሬዝዳንትነት እና ለስራ አስፈፃሚ አባልነት ምርጫ መቅረባቸው አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ይህ የስፖርት አድማስ ልዩ ቃለምልልስ የኢትዮጵያ
አትሌቲክስ ፌደሬሽንን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት አዲስ አበባን በመወከል እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ከቀረበው ክቡር ዶክተር ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ጋር ነው፡፡

          እንደመግቢያ
ክቡር ዶክተር ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በ42ኛ ዓመቱ  ከሩጫ ስፖርት በክብር የተሰናበተው ከዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው  15ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ ነበር።  በሩጫ ዘመኑ 27 ዓመታትን የተወዳደረ ሲሆን በኦሎምፒክ፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በሌሎች ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች 9 የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፏል፡፡  ወደ ማራቶን ከገባ በኋላ በዓለም ዙርያ 15 ትልልቅ ማራቶኖችን በመሮጥ 9 ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን ለሁለት ጊዜያት የዓለም ማራቶን ሪከርዶችን አከታትሎ ለማስመዝገብም በቅቷል፡፡ ለ27 አመታት በቆየበት የሩጫ ስፖርት ከመካከለኛ ርቀት 800 ሜትር አንስቶ፤ በረጅም ርቀት የ10ሺ እና 5ሺ ሜትር የትራክ እና የቤት ውስጥ ውድድሮች፤ ከ1 ማይል እስከ 10 ማይል በሚወስዱ ሩጫዎች፡ ከ10 እስከ 25 ኪሎሜትር በሚለኩ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና በማራቶን እና በግማሽ ማራቶን ውድድሮች በአጠቃላይ እስከ 26 በሚደርሱ የሩጫ ውድድር ዓይነቶች በመወዳደር እና አስደናቂ ውጤት በማግኘት በታሪክ መዝገብ ስሙን ያሰፈረ ሲሆን እስከ 61 የኢትዮጵያ ሪከርዶችን ማስመዝገብ የቻለበት ነበር፡፡ በተለይ   ከ27 በላይ የዓለም ሪከርዶችን ሲያስመዘግብ ከ5ሺ ሜትር 25.25 ሰከንዶች፤ ከ10ሺ 13.80 ሰከንዶችና ከማራቶን 46 ሰከንዶችን ማሻሻሉም ይጠቀሳል፡፡
በመላው ዓለም ከአትሌቲክስ ውድድር በተያያዘ፤ በስራ እና ጉብኝት  ከ100 አገራት በላይ ተጉዟል፡፡  በ2015 እኤአ ላይ ታዋቂው የቢዝነስ ጥናት አድራጊ የሚዲያ ተቋም ፎርብስ  ከአፍሪካ ተጽእኖ ፈጣሪ 40 እውቅ ሰዎች አንዱ  ነበር፡፡ በታላቁ አትሌት ዙርያ  ኢትዮጵያ ውስጥ የተፃፈ ዳጎስ ያለ የግለታሪክ መፅሃፍ ባይኖርም ጉልህ ተጠቃሽ የሚሆነው የጥበብ ውጤት በህይወት ታሪኩ ዙርያ የተሰራው እና ፅናት ወይም ‹‹ኢንዱራንስ፤ ዘ ስቶሪ ኦፍ ዘ ግሬተስት ዲስታንስ ራነር ኢን ሂስትሪ›› የተባለው ፊልም ነው፡፡ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ግን ቢያንስ አምስት እውቅ መፅሃፍት የሩጫ ዘመን ስኬቱንና ህይወት ታሪኩን በመንተራስ ለንባብ በቅተዋል፡፡ “ዘ ግሬተስት፡ ዘ ሃይሌ ገብረስላሴ ስቶሪ” የሚባለው መፅሃፍ በጂም ዴኒሰን የተፃፈ ነው፡፡ ሁለተኛው መፅሃፍ ደግሞ “ኃይሌ ገብረስላሴ ዘ ግሬተስት ራነር ኦፍ ኦል ታይም” በሚል ርእስ በክላውስ ዊዴት የተፃፈው ነው፡፡ ሶስተኛው በጀርመንኛ ቋንቋ የተፃፈውና ስለልምምድ ፕሮግራሙ እና የውድድር ብቃቱ “ላውሪን ዊዝ ሃይሌ ገብረስላሴ፤ ዳትሬኒንግ ፕሮግራም” በሚል ርእስ አበበ በተባለ ግለሰብ፤ በቀድሞ አሰልጣኙ ወልደመስቀል ኮስትሬ እና በራሱ  ትብብር የተዘጋጀው  ነው፡፡ አራተኛው መፅሃፍ  በታዋቂው ጃፓናዊ የአትሌቲክስ ፎቶግራፈር ጂሮ ሞቺዙኪ ‹ኃይሌ ገብረስላሴ ኤምፐረር ኦፍ ሎንግ ዲስታንስ› በሚል ርእስ በተለያዩ ፎቶዎች ታጅቦ የቀረበ ነው፡፡ አምስተኛው መፅሃፍ ደግሞ “ኃይሌ ገብረስላሴ፤ አፍሪካ ሌጀንድ ሲርዬስ” በሚል በኤልዛቤት ቴብላ የተዘጋጀው ነው፡፡
በኦሎምፒኳ ከተማ ሉዛን ውስጥ  86 ዓመታት እድሜ ያለው በ‹ዘ አሶሴሽን ኢንተርናሲዮናሌ ዴላ ፕሬስ ስፖርትስ›  የሚዘጋጅ ልዩ ክብር ሽልማትም ተሰጥቶታል፡፡ ሽልማቱ AIPS Power of Sport Award  ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በየዓመቱ በስፖርቱ ዓለምን፤ አገርንና ማህበረሰብን  የለውጡ አስተዋፅኦ ላበረከቱ  የሚሰጥ ልዩ ክብር ሲሆን በአትሌቲክስ ስፖርት ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ውጤት በመቆየቱ፤ በስፖርቱ ያገኘው ተወዳጅነት በአገሩ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በመሆኑ፤ በጂ4ኤስ ታዳጊዎች ፕሮግራም 14 ወጣት አትሌቶችን በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎ እንዲያገኙ በፈጠረው መነቃቃት እና በሰጠው ድጋፍ፤ በፀረ ኤድስ ዘመቻ ለአመታት ባበረከተው አስተዋጽኦ፤ በአፍሪካ ትልቁ የሆነውና  የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በመመስረቱና በዚሁ ስር የሚካሄዱ ውድድሮችን በተለያዩ የተባበሩት መንግስታት እና የበጎ አድራጎት ተቋማት ብሄራዊ መልዕክቶች እንዲታጀብ በማድረግ በፈፀመው ተግባር እውቅና ተሰጥቶት ነበር፡፡   በስፔን ትልቅ ክብር የሚሰጠውን ‹ፕሪንስ ኦስተሪዬስ አዋርድስ ፎር ስፖርትስ› በስፖርት የሰው ልጅን የላቀ ብቃት እና ችሎታ ያሳደገ አትሌት በመባል ከስፔን ንጉሳውያን ቤተሰብ እጅም ተቀብሏል፡፡   በዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር (AIMS) በ2006፤2007 እና 2008 እኤአ የዓለም ምርጥ አትሌት ተብሎ ከመሸለሙም በላይ ከወር በፊት ከዚሁ ዓለም አቀፍ ተቋም የህይወት ዘመን ሽልማቱን ወስዷል፡፡ አሁን 43ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተባበሩት መንግስታት የበጎ ፈቃድ አምባሳደርነት እያገለገለ ሲሆን በዛፍ ተከላ በመንገዶች ግንባታ አስተዋፅኦ እያደረገም ነው፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመግባት ፍላጎት እንዳለውና ፕሬዝዳንት ለመሆን  እንደሚፈልግ በበርካታ ዘገባዎች ሲጠቀስለት የቆየው ክቡር ዶክተር ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ወደ ፖለቲካ መግባትን የፈለገው የብዙ ወገኑን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሆነ ለአሶስዬትድ ፕሬስ ባንድ ወቅት ገልፆም ነበር፡፡  ህዝብን የበለጠ የሚረዳበት እድል ስለሚሻ መሆኑን በመጥቀስ፡፡  
ከአትሌቲክስ ስፖርት በጡረታ ከተገለለ በኋላ በኢንቨስትመንቱ ላይ አተኩሮ ቆይቷል። በታላቁሩጫ የ10ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እናሌሎች ውድድሮች የበላይ ጠባቂነት፤ በሪል ስቴት ፕሮጀክቶች፣ በ4 ሆቴሎች፣ በቡና ግብርና፣ በማር፤ በማዕድን ቁፈራና በሃዩንዳይ ወኪልነት ዘርፈ ብዙኢንቨስትመንቶች ተሰማርቶ ከ2000 በላይ ሰራተኞችን እያስተዳደረም ነው፡፡
ሰሞኑን ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንትነት መታጨቱን ያወሱ ዓለም አቀፍ ዘገባዎች በማኔጅመንት የሚሰራለትን የሆላንዱ ግሎባል ስፖርት ኮሚኒኬሽን በመጥቀስ ባሰራጩት ዘገባ ‹‹አትሌቲክስ ህይወቴን ሙሉ ለሙሉ ቀይሮታል። በስፖርቱ ባሳለፍኳቸው ዓመታት ከፍተኛ ልምድ እና እውቀት አካብቺያለሁ፡፡ አሁን ወቅቱ ለአገሬ እና በአጠቃላይ ለስፖርቱ አስተዋፅኦ የማደርግበት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት ስፖርቱን ወደ የላቀ ደረጃ ለማሳደግ በጣም እፈልጋለሁ›› ብሎ መናገሩን አውስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን 20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ  በሚካሄደው የፕሬዝዳንት ምርጫ ትወዳደራለህ፡፡ በፌዴሬሽኑ አስተዳደር ለውጥ ያስፈልጋል በሚል ከተነሳችሁባቸው ጉዳዮች ብንጀምርስ…
በርግጥ በፌዴሬሽኑ አስተዳደር ላይ ለውጥ ያስፈልጋል ብለን የተነሳነው ከ9 ወራት በፊት ነበር። ይሁንና ለስፖርቱ እድገት በመቆርቆር በየጊዜው ሃሳባችን ስንገልፅ መኖራችን ይታወቃል፡፡ ለሁሉም ዋና መነሻው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በክብር፤ በዝና እና በውጤት ክፉኛ እየወረደ መምጣቱ ነው፡፡ ይባስ ብሎ መጨረሻ ላይ በዶፒንግ ችግር ከሚጠቀሱት አምስት አገራት ተርታ መፈረጃችንና በስፖርቱ የማይሆን ስም የተሰጠን ግዜ ላይ መድረሳችን ከፍተኛ እልህ ፈጥሮብናል፡፡
እናም ወሳኙ ጉዳይ በፌዴሬሽን አስተዳደር ገብተን በባለቤትነት በመስራት ስፖርቱን እንዴት እንታደገው የሚል ሆነ፡፡ ስፖርቱን ሊታደጉ የሚችሉት እነማን ናቸው? ማንን ከማን እናገናኝ በማለት ለውጥ ለመፍጠር ስንነሳ የመጀመርያው ስራችን ሙያተኛውን ከሙያው ማገናኘት እንደሚኖርብን በማመን ነበር፡፡ ምናልባት ይህ አይነቱ የለውጥ አቅጣጫ ለዓመታት ሲተገበር በነበረው የስፖርቱ አስተዳደር ግፊት በመፍጠር ሁኔታዎችን ጥርቅም ማድረጉ አልቀርም፡፡ የሚገርምህ ግን ሙያተኛን ከሙያው ማገናኘት የሚለው አጀንዳ ዛሬ በመንግስት ደረጃም መልካም አስተዳደር ለማስፈን ከዚያ ውጭ  አማራጭ የለም ብሎ የተነሳበት ነው፡፡
መቼም ስፖርት አፍቃሪው የኢትዮጵያ ህዝብ እና የስፖርት ሚዲያው እኩል የሚታዘቡት ነገር አለ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት በየጊዜው እየወረደ የመምጣቱ ጉዳ ነው፡፡ ከ16 ዓመታት በፊት 4 የወርቅ ሜዳልያዎች ያገኘንበት የኦሎምፒክ ተሳትፎ ዘንድሮ ወርዶ በአንድ የወርቅ ሜዳልያ ብቻ ተወስኗል ፡፡ ታድያ ከዚህ በላይ ለአትሌቲክሱ ምን እንስራ ብለን የምንነሳበት ሌላ ምክንያት ይኖራል? ትናንት ከኋላ ያደረግናቸው ኬንያዎች ዛሬ እኛን ጥለው 6 ወርቅ በኦሎምፒክ 7 ወርቅ በዓለም ሻምፒዮና ይሰበስቡ ጀመር፡፡ ይህን የወረደ ነገር እባካችሁን እናስተካክለው ብለን ነው በሙሉ ትኩረት መታገል የጀመርነው፡፡ በመጀመርያ የተነሳነውሙያ በሙያተኛ ይግባና ይቀመጥ ብለን ነበር፡፡ የሚሰማ ጠፋ፡፡ ከዚያም ሪዮ ኦሎምፒክ ላይ ሁላችንም የታዘብነው ደካማ ውጤት ተመዘገበ፡፡ ይህን ስናወግዝ የምናሾፍ ነበር የመሰለው፡፡  ማን ይስራላችሁ ተባልን፡፡ ገብተን እንሰራለን ማለት ጀመርን፡፡ ግን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን እኛ ገብተን የምንሰራበት ክፍተት ጭራሽ አልነበረም፡፡ ወደ ፌደሬሽኑ አስተዳደር ለመግባት  በክልሎችና በከተማ መስተዳድሮች መወከል አለባችሁ፤ ለስራ አስፈፃሚ አባልነትም ሆነ ለፕሬዝዳንትነት ምርጫ  በእጩነት ሊያቀርቧችሁ ያስፈልጋል ተባለ።  ከጅምሩ እኛ ሙያተኞች እንደመሆናችን ቦታ ተሰጥቶን እንስራ ብለን ተነሳን እንጅ አንዳችንም የስልጣን ጥማት የለብንም፡፡
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አንተን ለፕሬዝዳንትነት ምርጫ በእጩነት እንዴት አቀረበ?
 እኔው ራሴ በቀጥታ ወደ  እነሱ ሄጄ    ምረጡኝ  ብዬ ጥያቄ ያቀረብኩላቸው፡፡ ከእኔ የሚሻልና  የሚወዳደር ሰው ካላዘጋጃችሁ በቀር ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት አዲስ አበባን ወክዬ ልወዳደር በማለት ነበር፡፡ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በምላሻቸው እንኳን አንተ እዚህ ድረስ መጥተህልን… እኛ  መጥተን መጠየቅ ነበረብን አሉ፡፡ የምንፈልገውን ለውጥ ለመፍጠር የግድ ገብተን መስራት አለብን በሚል ነው፡፡
እንግዲህ የቀድሞና የአሁን አትሌቶች እንዲሁም ነባር አሰልጣኞች የተሰባሰቡበት ኮሚቴ በብሔራዊ ፌደሬሽኑ የአመራርነት ድርሻ እንዲኖራቸው ያነሱት ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል ማለት ይቻላል? ሰሞኑን አንዳድ ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ያቀርቧቸውን የስራ አስፈፃሚ አባልነት እና የፕሬዝዳንትነት እጩዎች ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች እየሰማን ነበር፡፡ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አንተን ለፕሬዝዳንትነት ምርጫው እጩ አድርጎሃል፡፡  የኦሮሚያ ክልል አትሌት ገዛሐኝ አበራን፤ የትግራይ ክልል ደግሞ ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያምን ለስራ አስፈፃሚ አባልነት እጩዎች በማድረግ አቅርበዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አስተዳደር ታሪክ አዲስ ምእራፍ መከፈቱን የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡ በሌሎች ክልሎች እና የከተማ መስተዳድር የቀረቡት እጩዎች ሙሉለሙሉ ባይታወቁም …
በርግጥ ከጠቅላላ ጉባኤው  በፊት ሁሉንም እጩዎች በዝርዝርና በግልፅ ማወቅ አለመቻሉ በቂ ግንዛቤ እና ዝግጁነት ለማድረግ ባያስችልም፤ የእኛ ፍላጎት በይፋ ያልታወቁት ሌሎቹ እጩዎች ልክ እንደ አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፤ ኦሮምያ እና ትግራይ ክልሎች ሙያተኞችን እንደሚያማክሉ ተስፋ አድርገናል፡፡
አሁን እኛ የምንጠይቀው ምን መሰለህ፡፡ እስካዛሬ ድረስ ፌደሬሽኑ ለረጅም ዓመታት በምናውቀው እና አትሌቱን ባላሳተፈ አስተዳደር መቀጠል የለበትም ነው፡፡  የሚሄደውም እየሄደ የሚሰራውም እየሰራ ቆይቷል፡፡  የኢትዮጵያ ህዝብ  የሚፈልገው ነገር ግን አልተሟላትም፡፡  የወርቅ ሜዳልያዎች እንዲበዙና ውጤት እንዲሻሻል ነው የሚፈልገው፡፡ ግን ውጤት ደግሞ በየዓመቱ የሚያሽቆለቁል ከሆነ አስተዳደር በየጊዜው ቢቀያየር ማን ይቀበለዋል፡፡ ፌደሬሽኑ 100 ሚሊዮን አገኘ፤ 200 ሚሊዮን አስገባ ቢባል ውጤት ከሌለ ምን ትርጉም አይኖረውም፡፡ የሚቻል ከሆነ መቶ ሚሊዮን ኢንቨስት ተደርጎ የወርቅ ሜዳልያ ቢመጣ ፤ ውጤትን ቢያድግና ቢሻሻል ነበር፡፡
በአጠቃላይ እኛ ወደ አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ገብተን እንስራ ብለን የተነሳነው በእልህ ነው፡፡ በሪዮ ኦሎምፒክ ወቅት ሪዮ ዲጄኔሮ እንደነበርኩ ታውቃለህ፡፡ በፊት በተለያዩ የዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ውጤታማ ሆነህ ትስቅባቸው የነበሩ ሲስቁብህ፡፡ አሁን ለምሳሌ ኬንያ  6 የወርቅ ሜዳያዎች ስትሰበስብ እና በየቀኑ  ባንዲራዋ በኦሎምፒክ ስታድዬም ሲውለበለብ የኢትዮጵያ ህዝብ በቁጭት ውስጡ አሯል፡፡ እኔን ደግሞ በስፍራው ስታድዬም ውስጥ ሆኜ  በአብዛኛው የሆነውን በገሃድ እየተመለከትኩ እንዴት እንደታመምኩ ማመን ነው የሚያቅትህ፡፡ በርግጥ ይህ ሁሉ እንዳይፈጠር አስቀድመን ብዙ ጥረት አድርገን ነበር፡፡ ይህ ደካማ ውጤት እንደሚከሰት ስጋት ቢኖረንም ብዙዎቻችን ሁለት እና ሶስት የወርቅ ሜዳልያዎች ጠብቀን ነበር ግን ከዚያም የባሰ ውጤት ሲወርድ ከልብ አዘንን….
እስቲ የአትሌቶች ማህበርን እዚህ ጋር አያይዘን አናንሳው፡፡  በአትሌት ስለሺ ስህን ፕሬዝዳንትነት የሚመራው ማህበሩ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን  ማንም የሚገነዘበው ነው፡፡ የቀድሞም እና የአሁን አትሌቶችና አሰልጣኞች የተሰባሰቡበት ኮሚቴ በብሔራዊ ፌደሬሽኑ የአመራርነት ድርሻ እንዲኖራቸው  የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡  የአትሌቲክሱን ባለድርሻ አካላት በተለይ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ጋር ግንኙነቶችን በመፍጠር  ማህበሩ ሲንቀሳቀስ ፈታኝ ሂደቶችን እንዳሳለፈ  ነው የምረዳው፡፡ በማኅበሩና በሌሎችም አትሌቶች እየቀረቡ በሚገኙት በፌደሬሽኑ አመራር የመካተት  ፍላጎት ዙርያ 50 በመቶ ያህል በጎ ምላሾች ተገኝተዋል…   በአጠቃላይ በዚህ ዙርያ የምትሰጠው አስተያየት ምንድነው…..
በእኛ በኩል አብረን እንደተነሳን ነው የምናስበው፡፡ እንደጠቀስከው በስለሺ የሚመራው ማህበር የእኛን ሃሳብ በመደገፍ ብዙ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ የአትሌቶች ማህበሩ ሃሳባችንን በመደገፍ ለሚመለከታቸው ሁሉ ደብዳቤዎችን ፅፏል። በፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ እና ሌሎች የሃላፊነት ድርሻዎች ሙያተኞቹ ማለትም አትሌቶቹ፤ አሰልጣኞቹ መካተት አለባቸው የሚል ድጋፉን ያንፀባረቀባቸው ናቸው፡፡  በእኛ በኩል ከማህበሩ ጥረቶች ባሻገር እንቀሳቀስ ብለን ግፊት አድርገናል። ዞሮ ዞሮ ዋናው አቋማችን የአትሌቲክሱ ባለቤት አሰልጣኙ ወይም አትሌቱ ይሁን ነው፡፡ የቀድሞ አትሌት አሁን አሰልጣኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ትኩረታችን ፕሬዝዳንት መሆን እና በስራ አስፈፃሚ አባልነት መካተት ብቻ አይደለም፡፡ አሁን ጊዜው ደርሷል፡፡ ዋና አጀንዳ የስፖርቱ ባለቤት አትሌቱ እና አሰልጣኙ ይሁኑ ነው ፡፡ ዛሬ በፌደሬሽኑ አስተዳደር የባለቤትነት ደብተራችንን መያዝ እንደሚገባ ያመንበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡
በዓለም ላይ ያሉ ፌዴሬሽኖችን መርምረህ ብትመለከት ከስፖርተኛውና ከሙያተኛው ውጭ አስተዳደሩ እየተመራ ያለ ፌደሬሽን እዚህ እኛ አገር ላይ ብቻ ነው፡፡ እኔ ባሳለፍኩበት የሩጫ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ በፌደሬሽን አስተዳደር አንድም የቀድሞ ወይም ታዋቂ አትሌት ገብቶ አያውቅም፡፡ በነገራችን ላይ በኬንያ ፌደሬሽን ውስጥ የሚሰሩት አመራሮች እኮ ታላላቅና ውጤታማ ስፖርተኞች ባይሆኑም የቀድሞ አትሌቶች የነበሩ ናቸው፡፡ ምናልባት በሙስና ችግር ውስጥ የተዘፈቁት ያለአግባብ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ውስጥ በመቆየታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የኬንያ ፌደሬሽን ፀሃፊ ዳግላስ ዋኩሪ የተባለ የማራቶን ሯጭ  ነው፡፡ ያው እንደምታውቀው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዓለም አቀፉን የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር እየመሩ የሚገኙትም ስፖርተኞች ናቸው፡፡ እንግሊዛዊው የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ እና ኦሎምፒያን ሴባስትያን ኮው በፕሬዝዳንትነት፤ የራሽያ ምርኩዝ ዘላይ ሰርጄይ ቡብካ በምክትል ፕሬዝዳንትነት እየሰሩ ናቸው፡፡ በቅርቡ በዚሁ ዓለም አቀፍ ተቋም ምክር ቤት እነ ፓውላ ራድክሊፍ፤ ሌላ ስሙን የዘነጋሁት የጀርመን ታዋቂ ስፖርተኛም ገብተዋል። ዓለም አቀፍ ፌደሬሽኑ ፅህፈት ቤት ውስጥ ስትገባ የምታውቃቸው  ስፖርተኞች ብዙ ሆነዋል፡፡ አሜሪካ ያለውን ፌደሬሽን የሚመራ የቀድሞ የዝላይ ስፖርተኛ ነው፤ የሚገርምህ በእነሱ አስተዳደር በየጊዜው በፌደሬሽኑ አመራር ላይ የሚፈራረቁት በስፖርቱ ውስጥ ያለፉት ናቸው፡፡ በትሪንዳድ እና ቶቤጎ ፌደሬሽን በአመራሩ ላይ ያሉት የቀድሞ ኦሎምፒያኖች ናቸው፡፡ እንግሊዝ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፅህፈት ቤት ውስጥ ብትገባ በየሃላፊነቱ ተቀምጠው የምታገኛቸው ቀድሞ በተለያዩ የስፖርት መድረኮች እኛ ራሳችን የምናውቃቸው ስፖርተኞች ናቸው፡፡ በጣም የሚገርምህ ብዙ ኢትዮጵያውያኖች የሚያውቋት እና በአንድ ወቅት በታላቁ ሩጫ እንግዳ ሆና አዲስ አበባ የመጣችው ጋብሬላ ዛቦ አሁን የሮማንያ ስፖርት ሚኒስትር ሆናለች፡፡ ከእነዚህ የጠቃቀስኩልህ ምሳሌዎች የምትረዳው በተለያዩ የዓለም አገራት ስፖርተኞች  የስፖርት አስተዳደሩ ባለቤት እየሆኑ መምጣታቸውን ነው። በመላው ዓለም የሚታይ አቅጣጫም ሆኗል፡፡ ታድያ በኢትዮጵያ ይህ አይነቱን አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻለው ለምንድነው፡፡ በአገራችን አትሌቱ በየአቧራ ወድቆ፤ በየጊዜው እርዳታ እና ገቢ ማሰባሰቢያ እየጠየቀ እስከመቼ እንዲቀጥል ነው የሚፈለገው፡፡
ሙያተኛው የስፖርቱ ባለቤት እየሆነ መምጣቱ በመላው ዓለም የሚታይ የአስተዳደር አቅጣጫ መሆኑን በዝርዝር አስረድተሃል፡፡ በኢትዮጵያስ ይህ አዲስ ምእራፍ ሊከፈት ነው ማለት ነው? አንተ በፕሬዝዳንትነት ሌሎች ታዋቂ አትሌቶች በስራ አስፈፃሚ አባልነት ሊመረጡ እንደሚችሉ ትጠብቃለህ?
በርግጠኝነት የምነግርህ እንደምመረጥ ነው፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው ፍትሃዊና ትክክለኛ የሆነ የምርጫ ሂደት ይኑር ብቻ፡፡ በፌዴሬሽኑ አመራርነት ማን ይቀመጥ ብለው ጉባኤተኛዎቹ የቀረቡ እጩዎችን ሚዛናቸው ላይ ያስቀምጡ፡፡ እኔ ካልተመረጥኩ ከዚያ በኋላ ዳኝነቱ የህዝብ ነው የሚሆነው፡፡ ራሱ የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑት አትሌቶችም በውሳኔው ሊፈርዱ ይችላሉ፡፡ ይገርምሃል እኔ ወደዚህ ሁኔታ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ትችቶች እየተሰጡ ቆይተዋል፡፡ ኃይሌ ወደ ፌዴሬሽኑ ሲመጣ ድብቅ ተልዕኮዎች  አሉት በሚል የሚሰሙ አሉባልታዎች ብዙ ናቸው፡፡ ምን አይነት ተልዕኮዎች እንዳያዝኩ በግልፅ የሚጠቅሱት አንዳችም ነገር ግን የለም። የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ እንደመወጣጫ አድርጎ ወደ ዓለም አቀፉ ፌደሬሽን የሚሄድበትን መንገድ ለመጥረግ አስቧል ሲባልም ሰምቻለሁ፡፡ ገብሬ ሆነ ገዛሐኝ በእንዲህ አይነት ተመሳሳይ ትችቶች ተብጠልጥለዋል፡፡   ግን እስቲ ሃቁን እንነጋገር ወደ ፌዴሬሽን አመራርነት መምጣት የሚፈልጉት ለገንዘብ  ነው ሲባል እውነት በገንዘብ የምንታማ ነን ወይ? የውጭ አገር ጉዞዎችን ስለሚፈልጉ ነው ከተባለስ ያልሄድንበት የዓለም ክፍል አለ እንዴ…..
ለእኔ አትሌቲክስ ህይወቴ፤ ሁለመናዬ ነው። በስፖርቱ ያለኝ ፍቅር በምንም የምደራደርበት አይደለም፡፡ አንዳንዶች የአትሌቲክስ ስፖርት እንዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየተዳከመ ሲመጣ እነኃይሌ  የት ነበሩ እያሉ ይናገራሉ፡፡ ሯጭ እንደነበርኩ ለምን ይዘነጉታል፡፡ በምወዳደርበት መድረክ ውጤታማ ለመሆን ስፍጨረጨር እኮ ነው የኖርኩት፡፡ ድሮም ቢሆን ሯጭ ሆኜ እየተወዳደርኩ በአትሌቲክሱ ላይ የማስበውን ከመናገር መቼ ተቆጥቤ አውቃለሁ፡፡ አሁን ግን መሮጡን አቁሜ ተመልካች እና ባለቤት ሆኛለሁ፡፡ አሁን በአገር ውስጥ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅእኖ መፍጠር የምንችልበት እውቅና እና በቂ ግዜ አለን ብዬ ነው የማስበው፡፡ወደ ስፖርቱ አስተዳደር ስንገባ ብዙ አቅም መፍጠር የምንችለው ለራሳችን ሳይሆን ለምንሰራለት አገር ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ድጋፎች፤ በተለያዩ ውሳኔ ሰጭ አካላት ብዙ ድምፆች፤ በተለያዩ የልነማ እና የእድገት ትብብሮች ብዙ ስምምነቶች ለማረግ የምንችለበት ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡ ይህን ዝና ተሰሚነት በመጠቀም ስንሰራ እየሮጥን አይደለም በዋናነት የአገራን የአትሌቲክስ አስተዳደር እያጠናከርን የምንሄድበት ነው፡፡
እንግዲህ ከጠቅላላ ጉባኤው ሳምንት ቀደም ብሎ   የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ፤ የትግራይና የደቡብ ክልላዊ መንግሥታት ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የፕሬዝዳትነት ምርጫ ያቀረቧቸው ዕጩዎች ማንነት የታወቀው ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር አንተን፤  የኦሮሚያ ክልል   የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ ዳኛቸው ሺፈራውን፤ የትግራይ ክልል የብሔራዊ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙትን አቶ ወልደገብርኤል መዝገቡን እንዲሁም የደቡብ ክልል አቶ ተፈራ ሞላን  በእጩነት እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል። ሌሎችም እጩዎች ምርጫው እሁድ ሲካሄድ የሚታወቁ ይሆናል። አዲስ አበባን በመወከል በእጩ ፕሬዝዳንትነት ምርጫ ላይ ተወዳድረህ ብታሸንፍ በምን አይነት እቅዶች ለመስራት ነው?
በአጠቃላይ ፌደሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ስትነሳ ያነገብካቸውን  ዓላማዎች ወይንም ተልዕኮዎች በዝርዝር ብታብራራቸው….
ምንም አይነት ድብቅ ተልዕኮዎች የሉኝም፡፡  የተነሳሁት ስፖርቱን በባለቤትነት በመምራት ለውጥ ማምጣት አለብኝ በሚል እልህ ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም አትሌቶች፤ አሰልጣኞች በአጠቃላይ ሙያተኞች በፌዴሬሽኑ አስተዳደር ገብተን በባለቤትነት መስራት አለብን፡፡ ባሰለፍኳቸው የሩጫ ዘመናት ስንት ውድድሮችን ስናሸንፍ አልቲትዩዱ፤ አኗኗራቸው፤ አመጋገባቸው እየተባለ ብዙ ምክንያት ቢገለፅም ዋናው አቅማችን ግን እልህኛነት ነው፡፡ አሁንም በእልህ ማሸነፍ ይቻላል። ስለዚህም ተልዕኮዬ ወርቅ ነው፡፡ የእኔ ዓለማ ትናት ያሸነፍኩትን ዛሬም መልሼ ማሸነፍ ነው፡፡
እኔ ብመረጥ በመጀመርያ ደረጃ የማደርገው በፌደሬሽኑ አስተዳደር ሙያን ከሙያተኛው፤ አትሌቱን ከአሰልጣኙ፤ አሰልጣኙን ከአትሌቱ በማቀራረብ እና በማገናኘት በአንድ ዓላማ የሚሰሩበት ሃሳብ እንዲኖራቸው ማግባባት ይሆናል። በዕህፈት ቤቱ፤  በፌደሬሽኑ የተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ያሉ ባለድርሻ አካላትን የኢትዮጵያን አትሌቲክስ አስቀድመው እንዲሰሩ ማስተባበር ማለት ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ በፌዴሬሽኑ አስተዳደር በመላው አገሪቱ በስፖርቱ ያለውን ተሳትፎ ለማስፋፋት የሚኖረን ሙሉ አቅም በጥልቀት በመፈተሽ መንቀሳቀስ ይሆናል፡፡ እንደሚታወቀው ፌደሬሽኑ እስካሁን አተኩሮ ሲሰራ የቆየው በሩጫ በተለይም በረጅም ርቀት ላይ ብቻ ሲሆን ይህንንም ሲያካሂድ የቆየው በተወሰኑ ክልሎች ባሉ ሁኔታዎች ብቻ በመንቀሳቀስ ነው፡፡ በ5ሺ፤ በ10ሺ በማራቶን ሩጫ ላይ መወሰን የለብንም ነው፡፡ የምንሰራባቸው አቅጣጫዎች ላይ በተጨማሪ መሰራት ያለባቸውን ሌሎች የስፖርት መስኮች መፈተሽና አዳዲስ አቅጣጫዎችን መፍጠር ትኩረት እናደርግበታለን። በየክልሎቹ  በውርወራ፤ በዝላይ እና በአጫጭር ርቀት ሩጫ የት አካባቢ መስራት እንደሚገባን ለመረዳት በሚስችሉ አቅጣጫዎች የተለያዩ የመስክ ጉብኝቶችን በአመራር ደረጃ ለማከናወን እናስባለን። በየክልሉ በተለያዩ የስፖርት መስኮች ያሉትን አቅሞች ማጠናከር የሌሉትን ደግሞ በአስተማማኝ መሰረት ላይ ገንብቶ ለመስራት ነው፡፡ በዚህም ዋና ዓላማችን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የምናስመዘግባቸውን ሜዳልያዎች ብዛት ለመጨመር የምንሳተፍባቸውን ስፖርቶች ማብዛት የሚለውን አቅጣጫ ለመተግበር ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከገብረእግዚአብሄር እና ከገዛሐኝ ጋር ብዙ ምክክር እያደረግን ቆይተናል፡፡ ይህንን በተግባር መፈፀም ነው የምንፈልገው፡፡ እራሳችን በየክልሉ ተዘዋውረንና ከክልል ፌደሬሽኖች ጋር አብረን በመስራት ውጤታማ ልንሆን የምንችልበትን አሰራር መዘርጋት ነው፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የፌደሬሽኑን የፋይናስ አቅም በሚያሳድጉ አቅጣጫዎች መስራት ነው፡፡ የፈዴሬሽኑን የገቢ አቅም ጨመር የተለያዩ የፋይናስ ድጋፎችን በስፋት የምናገኝባቸውን አሰራሮች ቀርፀን የምንቀሳቀስበት ነው፡፡ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ስፖርት በስፖንሰሮች ድጋፍ እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡ ስፖርት ለብቻው ፋብሪካ አይከፍትም፡፡ በእኛ አገር ፋብሪካዎቻችን ስፖርተኞቹና ውጤቶቻቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ስፖርቱን በመደገፍ ሊሰሩ የሚችሉ ኩባንያዎችን በመቅረብ የምንሰራባቸው አቅጣጫዎች ይኖራሉ፡፡ አሁን ለምሳሌ በአገር ውስጥ የሚካሄዱ ውድድሮችን የሚደግፉ ስፖንሰሮች በቂ አይደሉም፡፡ በየዓመቱ የሚካሄዱት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮናና ሌሎች ውድድሮችን በስፖንሰርሺፕ ደግፈው የሚሰሩት የሳምንሰንግ አጋር ኩባንያ ጋራድ እና ሞሃ የለስላሳ መጠጦች ብቻ ናቸው፡፡ በበቂ ሁኔታ የሰራንበት ባለመሆኑ ይህን ማጠናከር እንፈልጋለን። በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎችን በስፋት ማሳደግ እንፈልጋለን፡፡ ይገርምሃል በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር እነሰባስቲያን ኮው በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ስንመርጣቸው ለኢትዮጵያ ምን እንስራ ብለው ጠይቀው፤ ምን ትሰሩልናላችሁ ብለን ጠይቀናቸው ነው፡፡ አንድ ምሳሌ እዚህ ጋር ልጥቀስልህ ላሚን ዲያክ የአይኤኤኤፍ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት በአገራቸው ሴኔጋል ሰባት ስታድዬሞች ተገንብተዋል፡፡ በሴኔጋል የአትሌቲክስ ስፖርት ብዙም ያልተስፋፋ ቢሆንም 3 ስታድዬሞች ሙሉ ለሙሉ የሞንዶ ትራክ የተነጠፈላቸው ናቸው፡፡ እነ ሞንዶ በኢትዮጵያ ትራኮችን በማንጠፍ እንዲሰሩ በትኩረት ተንቀሳቅሰን ለማሳካት አቅደናል፡፡ በሌላ በኩል ለረጅም ጊዜ ከፌዴሬሽኑ ጋር በመሮጫ እና የትጥቅ አቅርቦት የሚሰራው የጀርመኑ የትጥቅ አምራች ኩባንያ አዲዳስ ምንም እንኳን የስፖንስርሺፕ ውልና ስምምነቱን በቀጣይ 4 ዓመታት ለማከናወን ኮንትራቱን አስቀድሞ የተፈራረመ ቢሆን ተጨማሪ እድሎችን ለመፍጠር እያሰብንበት ነው፡፡ በውሉ አስቀድሞ በተከፈለው ገንዘብ ላይ የተለየ ጭማሪ ማድረግ አይቻልም ይሆናል፡፡ ግን ካሉት የስምምነት ግዴታዎች መካከል  የኢትዮጵያ ቡድን በዓለም ሻምፒዮና፣ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና፣ በዓለም አገር አቋራጭ እና በመሳሰሉት ውድድሮች ላይ በሚኖረው ተሳትፎ እና ውጤታማነት የሚገኙ የገንዘብ ቦነሶች እያጠናከርን ለመሄድ ነው፡፡  እኛ ታዋቂ አትሌቶች ከጀርመኑ ኩባንያ ጋር ያሉን ቅርበቶች በማጠናከር በቀሪው የኮንትራት ዘመን ለኢትዮጵያ አትሌቶች በገንዘብ ሳይሆን በአይነት የተለያዩ የትጥቆች እና የስፖርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ለማግኘት መስራት እንደሚኖርብን ስለተገነዘብን በዚህ አቅጣጫ በመስራት በየገጠሩ፤ በየክልሉ ያሉ አትሌቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡
በአራተኛ ደረጃ ለየት ያለው የትኩረት አቅጣጫችን በዶፒንግ ጥፋቶች ክብሩ እና ዝና የጎደፈውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ ጥረቶችን የምናደርግበት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያገኘነውን ተዓማኒነት እና ተሰሚነት ተጠቅመን በምንፈጥራቸው ግንኙነቶች የጠፋውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስም በመልካም እንዲነሳ ለማድረግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች በዶፒንግ ቀውስ በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዱ መምጣታቸውን መቀየር አለበት፡፡ አገሪቱ በዶፒንግ ጥቁር ነጥብ ውስጥ ከገቡት አምስት አገራት አንዷ በመሆኗ ብዙ ነገሮችተበላሽተዋል፡፡ ዋናው ደግሞ በየውድድር ዘመኑ ከ400ሺ ዶላር በላይ ለዶፒንግ ምርመራ እና ክትትል ወጭ በማድረግ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋችን ነው፡፡ በፊት የኢትዮጵያ አትሌት ለዶፒንግ ምርመራ የሚከፈለው ሂሳብ አልነበረም። ካለፈው ዓመት ወዲህ ግን አንድ አትሌት በአንድ የውድድር ዘመን 4 የዶፒንግ ምርመራዎች የሚያደርግ ሲሆን በእያንዳንዱ ምርመራ ላይ ከ400 ዶላር ወጪ እየሆነ ይገኛል፡፡ የገባንበት ገብተን ይህን ወጭ ማስቀረት አለብን ብለን ነው የምንቀሳቀሰው። ይህ ብቻ አይደለም በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች አትሌቶቻችን አላግባብ ስማቸው ከዶፒንግ ጋር ተያይዞ እየተነሳ ነው፡፡ ይህን በመቀየር በሄድንበት ሁሉ ኢትዮጵያኖች ንፁህ ናቸው ተብለን እንደድሮው እንድንከበር ነው የምንፈልገው፡፡
በአምስተኛ ደረጃ ደግሞ እውቅ አትሌቶች የአየር ንብረቱ ተስማሚ ባልሆነበት በአዲስ አበባ ተከማችተው ልምምድ መስራታቸውንና መኖራቸውን ተገቢ እንዳልሆነ በቶሎ ግንዛቤ እንዲፈጠር አድርገን ከከተማ ውጭ ስፖርቱን የሚያካሂዱበትን መመርያ አዘጋጅተን ተግባራዊ ለማድረግ ነው የምናስበው፡፡ በኬንያ ያልው ተመክሮ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ናይሮቢ የነበሩት የኬንያ አትሌቶች ሁለት ብቻ ነበሩ፡፡ ፖል ቴርጋት እና ካተሪን ንድሬባ፡፡ በአሁኑ ወቅት ናሮቢ ተቀምጦ የሚሰራ አትሌት የለም፡፡ ሁሉም አትሌቶች ከከተማ ወጣ ብለው በኤልዶሬት እና በኢቴን ነው የሚሰሩት፡፡ ብዙዎቹ የኬንያ አትሌቶች በየከተሞቹ መኖርያ ቢኖራቸውም አትሌቲክሱን በቋሚነት የሚሰሩት ከከተማ ወጣ ብለው በሚገኙ  እና ንፁህ አየር በሚገኝባቸው መንደሮች በየካምፖቹ በመክተም ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች በአዲስ አበባ ተከማችተው አትሌቲክሱን የሚለማመዱበት ሁኔታ እንዲቀየር በጥናት ላይ የተደገፉ ስራዎችን ለመተግበር አስበናል፡፡
በስድስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የምታስደናግድባቸውን እድሎች መፍጠር እንችላለን፡፡ አሁን በ2017 ይገርምሃል የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን የምታስተናግደው የምስራቅ አፍሪካዋ ኡጋንዳ ናት፡፡ እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ ይህን አይነት ውድድር ማስተናገድ አትችልም ነበር ወይ? ከጥቂት ዓመታት በፊት የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ከዚያም የአፍሪካ ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ብቻ ማዘጋጀት የቻልነው፡፡ ባለን አቅም ግን ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማናዘጋጅበት ምክንያት አይታየኝም፡፡በኡጋንዳ ሳንቀደም የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ማዘጋጀት ነበረብን፡፡ አምልጦናል ወደፊት ግን ይህ አይነት ራዕይ እንዲኖረን ነው የምንፈልገው፡፡ እስከ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማቀድ አለብን፤ የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናን ሁሉ ማካሄድ እንችላለን፡፡ ዛሬ ታዋቂ አትሌቶች በፌደሬሽኑ አስተዳደር መግባታችን ወደፊት እነዚህን ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለማዘጋጀት የሚያፈልገውን ጥረት በተሳካ መንገድ ለማከናወን አቅም የምንፈጥርበት ይሆናል፡፡
በመጨረሻም አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በሚያካሂደው የአዲስ ፕሬዝዳንት ምርጫ ባትመረጥስ ኃይሌ….
ባልመረጥም እመረጣለሁ፡፡ እኔ ክልሎች፤ የከተማ መስተዳደሮች፤ የአትሌቶች ተወካዮች፤ የአሰልጣኞችና የዳኞች ተወካዮች ህዝቡን ማዕከል አድርገው ለአትሌቱ እና ለስፖርቱ አስበው ውሳኔ የሚያሳልፉ ከሆነ መቶ በመቶ ይመርጡኛል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ይሄን የምለው ሁሌም በአክብሮት ከምመለከታቸው ከተወዳዳሪዎቼ አንፃር የራሴን አቅም ስመዝነው ነው፡፡ በስፖርቱም ዓለምም የለመድኩት ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቼን አሳንሼ አልመለከትም፡፡ አንዳንዴ ግን የተፎካካሪህን አቅም ትገነዘብና በሩጫ ውድድር ላይ ዛሬ ለሰዓት መሮጥ አለብኝ ብለህ ነው የምትወስነው፡፡ አሁን በፕሬዝዳንትነት ምርጫ የሚሰማኝ ይሄው ነው። ካልተመረጥኩ ደግሞ ተስፋ የምቆርጥበት ሁኔታ የለም፡፡ እንደገና እሰራለሁ፡፡ በእልህ መታገሌም የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ተመረጥኩም አልተመረጥኩም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሸናፊ ሆኖ በትክክለኛ መስመር እስኪገባ ድረስ ጥረት ማድረጌን አላቋርጥም። በርግጥ ብዙዎች ኃይሌ የሚያስተዳድራቸውን ኢንቨስትመንቶች እና በርካታ የግል ስራዎቹን ትቶ እንዴት ፌዴሬሽኑን በሙሉ ትኩረት ሊመራ ይችላል ብለው ስኬታማ ልሆን እንደማልችል ጥርጣሬ ሊገባቸው ይችላል… ግን እኔ በምሰማራበት የኃላፊነት መስክ ሁሉ ከ95 በመቶ በላይ ስኬታማ መሆን እንደምችል በእርግጠኛነት ነው የምናገረው። ሁሉንም ስራዎቼ እኮ የፈጠራቸው ሩጫው ነው፡፡ ሁሌም ቅድሚያ ትኩረት የምሰጠው ለአትሌቲክሱ ስፖርት ነው፡፡ ለስፖርት ቅድሚያ የምሰጠው ለ100 ሚሊዮን ህዝብ ስኬታማ ሆኜ መስራት የምፈልገው ሃላፊነት ስለሆነ ነው፡፡
በአጠቃላይ ለሁሉም አደራ የምለው የኢትዮጵያን አትሌቲክስን እንታደገው ነው፡፡ ስፖርቱን ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ በ1 እና በሁለት ዓመት ከፍተኛ ለውጥ እናመጣለን ብዬ የምገባው ቃል የለም፡፡ በጣም የወረደውን አትሌቲክስ ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ከ3 እና ከ4 ዓመታት በላይ ተባብረን መስራት ይኖርብናል፡፡ ምናልባትም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የምናገኛቸው ድጋፎች የተጠናከሩ ከሆነ ከዚያም በፈጠነ ጊዜ የምንፈልገውን ለውጥ ማስመዝገብ እንደምንችል ነው የማምነው፡፡

Read 1431 times