Saturday, 12 November 2016 12:39

ሴት ሕጻናት የብልት ፈሳሽ ሊኖራቸው ይችላል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(23 votes)

 ተፈጥሮአዊው የማህጸን ወይንም የብልት ፈሳሽ ልክ የመኖሪያ ቤትን ለመንከባከብ የሚደረገውን የጽዳት አገልግሎት በሴቶች የስነተዋልዶ አካል ላይ እንደሚፈጸም የሚቆጠር ነው። በብልትና በማህጸን በር አካባቢ የሚፈጠረው ፈሳሽ የሞቱ ሴሎችንና ባክሪያዎችን ጠራርጎ ስለሚያስወጣ በዚህም ምክንያት ብልት ንጹህ እንዲሆንና Infection መመረዝ እንዳይደርስበት ይከላከላል። ብዙ ጊዜ መመልከት እንደሚቻለው የብልት ፈሳሽ ተፈጥሮአዊ ነው። መጠኑም በተለያዩ ምክንያቶች ከፍና ዝቅ ሊል የሚችል ሲሆን መጠነኛ ሽታ ያለው እና ቀለሙም ንጹህ ውሀ ከመምሰል እስከ ወተት መምሰል ሊደርስ ይችላል። ለምሳሌም ከማህጸን እንቁላል በሚወጣበትና ለእርግዝና ዝግጁ በሚሆንበት ጊዜ ፣በጡት ማጥባት ወቅት ወይንም ለወሲብ ግንኙነት ዝግጁ በሚኮንበት ጊዜ የፈሳሽ መጠኑ ከፍ ሊል ይችላል። ሽታውን በሚመለከትም በእርግዝና ወይንም የግልን ጽዳት ካለመጠበቅ የተነሳ የተለያየ ይሆናል።
ከላይ የተጠቀሱትና መሰል ምክንያቶች በሌሉበት የፈሳሹ ቀለምም ሆነ ሽታ ወይንም መጠኑ ከተለመደው ውጭ ሆኖ ሲታይ እና የብልት ማሳከክ ወይንም ማቃጠል ስሜት ሲኖረው በቸልታ የማይታይ ስለሆነ ሐኪምን ማማከር ይጠቅማል።
ተፈጥሮአዊ ያልሆነ የብልት ፈሳሽ ለምን ይከሰታል?
ተፈጥሮአዊ የሆነው የብልት ፈሳሽ በተለያዩ ምክንያቶች ቀለሙን ወይንም ሽታውን እንዲለውጥ የሚገደድበት ሁኔታ አለ። በተከታይ የተጠቀሱት ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።
ባክሪያን ለማጥፋት የምንወስዳቸው መድሀኒቶች (Antibiotic)፣
አንዲት ሴት በእርግዝና ጊዜ ወይንም ከአንድ ሰው በላይ የግብረስጋ ግንኙነት በምታደርግበት ጊዜ የሚፈጠር ባክሪያ፣
ለእርግዝና መከላከያ የሚወሰዱ ኪኒኖች፣
የማህጸን በር ካንሰር፣
የአባለዘር በሽታዎችበግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚፈጠሩ፣
የስኩዋር ሕመም፣
ውሃና ሳሙና ተቀላቅሎ ከፍተኛ አረፋ ባለበት መዘፍዘፊያ ውስጥ ገብቶ መቆየት፣
በብልት ውስጥና በአካባቢው የሚኖር ቁስለት...ወዘተ
 ምንጭ www.womenshealth.gov/
ከላይ ያስነበብናችሁ የብልት ፈሳሽ ተፈጥሮአዊና ተፈጥሮአዊ አይደለም የሚያሰኘው ልዩነት በምን ምክንያት እንደሚከሰት ነው። ባለፈው ሳምንት በዚህ ነጥብ ዙሪያ የተወሰኑ ቁምነገሮችን ከጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስቱ ዶ/ር ሙህዲን አብዶ ያገኘነውን አስነብበናችሁዋል። ዛሬም ዶ/ር ቀሪውን ነጥብ ለአንባቢ ይደርስ ዘንድ አጋርተውናል።
እንደ ዶ/ር ሙህዲን አብዶ ማብራሪያ ተፈጥሮአዊው የብልት ፈሳሽ ተፈጥሮአዊ ወደአልሆነው ከሚሸጋገርባቸው ምክንያቶች በኦፕራሲዮንም ይሁን በተፈጥሮአዊው መንገድ ከወለዱ በሁዋላ ወይንም ከግብረስጋ ግንኙነት ጋር በተያያዘ የሚከሰተው አንዱ ነው። በተጠቀሱት ምክንያቶች የሚኖር ፈሳሽ እና በብልት አካባቢ የማሳከክ ሁኔታ ከተከሰተ እንዲሁም በተለምዶ የምናው ቃቸው ቂጥኝ፣ ጨብጥ የመሳሰሉት በቫይረስ የሚመጡ ሕመሞች የሚያስከትሉት ሽታ ያለውና ብጫ የሆነ ፈሳሽ ተፈጥሮአዊ ያልሆነ ይባላል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በታችኛው ሆድ ክፍል ሕመም ወይንም ሰውነትን ብርድ ብርድ የሚል ስሜት ሊፈጠር ይችላል።
 ከእድሜ ጋር በተያያዘ በተለይም ትንንሽ ልጆች ላይ ፈሳሽ የሚታይ ከሆነና በተለይም ሽታ ያለው ከሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሕጻናት ሕጻናት ናቸውና በጨዋታ ወይንም በአንዳንድ ምክንያት ባእድ አካል ወደሰውነታቸው ሊያስገቡ ስለሚችሉ መጠራጠር ተገቢ ይሆናል።ሕጻናት አንዳንድ ጊዜ ጉንፋን ሲይዛቸውም የማህጸን ፈሳሽ ሊታይባቸው ይችላል። ይህ ግን እንደችግር የሚቆጠር አይደለም።
በመውለጃ እድሜ ክልል ያሉ እንደ ኢንፌክሽን ባሉ ምክንያቶች ፈሳሻቸው ተፈጥሮአዊ ያልሆነውን አቅጣጫ ሊይዝ ሲችል በተለይም እድሜአቸው እየጨመረ ሲሄድ እና የወር አበባ ሲቋረጥ የሚስተዋለው ፈሳሽ አብዛኛውን ጊዜ በከፋ ሁኔታ የሚታይ ነው። የወር አበባ ከተቋረጠ በሁዋላ ብልትንና ማህጸንን የሚንከባከቡት ባክሪያዎች ስለሚቀንሱ ማህጸንም ስለሚሳሳ ወይንም ስለሚሟሽሽ በቀላሉ ለኢንፌክሽን የመጋለጥ እድል ያጋጥማል። እንዲሁም የማህጸን በር ካንሰር ወይንም ቅድመ ካንሰር ምልክት ካለ እንዲያውም ፈሳሹ ከደም ጋር ተቀላቅሎ ይታያል። ስለዚህ በማንኛውም ጊዜ ከተፈጥሮአዊው ፈሳሽ ለየት ያለ ሁኔታ ሲስተዋል ወደሕክምና ተቋም መሔድ ያስፈልጋል።
ተፈጥሮአዊው የብልት ፈሳሽ ተፈጥሮአዊ ወደአልሆነው እንዳይቀየር መከላከያ መንገዶች፡-
ብልትን በተወሰነ ሰአት ምናልባትም በቀን አንድ ጊዜ ወይንም ሁለት ጊዜ በተለይም ውጫዊውን የብልት አካባቢ ብዙ ኬሚካል በሌለውና ጉዳት በማያሰከትል ሳሙና እና ሞቅ ባለ ውሀ መታጠብ፣
የመታጠቢያ ውሀው በከፍተኛ ኃይል የሚረጭ እና ሰውነትን እስኪሰማ በሚማታ ውሀ ከመታጠብ መቆጠብ ያስፈልጋል። እንዲሁም ሽታ እና ቀለማቸው በተለያዩ ኬሚካሎች የተሰሩ ሳሙናዎችን አለመጠቀም፣
ወደመጸዳጃ ቤት ከሄዱና ከተጠቀሙ በሁዋላ መጠራረግን ወይንም መታጠብን ከፊት ወደሁዋላ ማድረግ ይመረጣል።
በተጨማሪም፡-
ቆሻሻን ለማስወገድ የምንጠቀምባቸውን መጸዳጃ ሳሙናዎች የመሳሰሉትን መለወጥ
 ምናልባ ትም ያጸዳል ተብሎ የሚጠበቀው መጸዳጃ ይበልጡኑ ተፈጥሮአዊውን ነገር የሚያስወግድና ወደሕመም ሊያሸጋግር ስለሚችል
ስኩዋር የበዛባቸውን ምግቦች መቀነስና እንደ ኦቾሎኒ ወይንም ለውዝ የመሳሰሉትን ጠቃሚ ነገሮችን መመገብ፣
የብልት አካባቢ ቁስለት ወይንም የማሳከክ ሁኔታ ቢከሰትበት እርጎ እና ማርን እንደ ክሬም መቀባት ሕመሙን ሊያስታግስ ይችላል።
ስለሚወስዱዋቸው ክሬሞች ወይንም ዘይታማ ፈሳሾች እና መድሀኒቶች አስቀድሞ ከሕክምና ባለሙያ ምክር ማግኘት ጠቃሚ ነው።
ዶ/ር ሙህዲን አብዶ ስለጽዳት እና ሕክምናን በሚመለከት የሚከተለውን ብለዋል።
አንዳንድ ጊዜ ችግሩ የገጠማቸው ሴቶች ለሕክምና ሲመጡ ለሐኪማቸው የሚሰጡት መልስ እንደሚከተለው ነው።
ሕመሙ ሲገጥመኝ ምናልባትም ... ሊሆን ይችላል ብዬ ...የተባለውን መድሀኒት ተቀባሁ ወይንም ዋጥኩ፣
ሕመሙ ሲገጥመኝ ለጉዋደኛዬ አማከርኩዋትና ለእሱዋ የታዘዘ መድሀኒት ተጠቀምኩ፣
እና ወይንም እህ...በዚህ አይነት ሕመም ሲቸገሩ ስለነበር እና ይጠቀሙበት የነበረ መድሀኒት በቤት ውስጥ ስለነበር እሱን ወሰድኩ፣
ከብል ወይንም ከማህጸኔ የሚወጣ ፈሳሽ ሽታው ጠረኑ እና መልኩ እጅግ ዘግናኝ ሰለነበር ባለቤ እንዳያይብኝ በቀን ብዙ ጊዜ በሳሙና እየታጠብኩ ፓንት እየቀየርኩ ነው የኖርኩት...ወዘተ
ከላይ ያነበባችሁዋቸው መልሶች ታካሚዎች ለሐኪሞቻቸው ከሚሰጡዋቸው መካከል ሲሆኑ ሁሉም ትክክል ያልሆኑ መልሶች ናቸው። ምክንያቱም
ለአንዱ የታዘዘ መድሀኒት ለሌላ ሰው አይሆንም፣
የብልት ፈሳሽ ሽታ እና ቀለሙ ትክክል አይደለም በሚል በቀን ብዙ ጊዜ በሳሙና መታጠብ ይበልጡኑ ሰውነትን ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ነው።
የብልት ፈሳሽ መልኩና ጠረኑ እንዲሁም መጠኑ ሲቀየር በፍጥነት ወደሐኪም መሔድ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ግን ፡-
ሴቶች መካከለኛና የተመጣጠነ የአየር ጸባይ ባለው የአኑዋኑዋር ሁኔታ ቢኖሩ ይመረጣል።
መንገድ መሄድ ወይንም ስራ ጎንበስ ቀና እያሉ መስራት እና የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ይመከራል።
በሙቀት አካባቢ የሚሰሩ ከሆነ እና ረዥም ጊዜ መቀመጥ በሚኖርበት ጊዜ የአካባቢውን ንጽሕና መጠበቅ የማያስችል ሁኔታ ስለሚፈጠር ተፈጥሮአዊ ያልሆነ ፈሳሽ ሊከሰት ይችላል። በተወሰነ ጊዜ የመታጠብ ልምድ ከሌለ የኢንፌክሽን መፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል።
እንደአቅም የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የማህጸን ወይንም የብልት ፈሳሽ ተፈጥሮአዊ እንደሆነ እንዲቆይ ይረዳል።
አለባበስን በሚመለከት ፡-
ሴቶች የማህጸን ፈሳሻቸው ተፈጥሮአዊ ወደአልሆነ እንዳይለወጥባቸው ለሰውነት ተስማሚ ያልሆኑ ልብሶችን ማለትም በጣም ሰውነትን የሚያጣብቁ ሱሪዎችና ሙታንታዎች አለመልበስ ይመከራል። እንዲሁም ከጥጥ የተሰሩ የውስጥ ሱሪዎችን መልበስ ጠቃሚ ነው።
ሴቶች የሚጠቀሙባቸውን የውስጥ ሱሪዎች እንደፈሳሻቸው ሁኔታ ማለትም በአንድ ቀን ወይንም በሀያ አራት ሰአት ውስጥ አለዚያም ውለው አድረው መቀየር ይችላሉ። ነገር ግን ይህንን የሚወስነው ከሰውነታቸው የሚወጣው ፈሳሽ መጠንና ጠረን ይሆናል።
የውስጥ ሱሪን በማጽዳት ረገድ ሞቅ ባለ ውሀ እና ሳሙና ቢታጠብ ይመረጣል።

Read 12256 times