Sunday, 13 November 2016 00:00

የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ልዩ መለያዎች

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

   አሜሪካ ነጻነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ እስከ ዛሬ 44 ፕሬዚዳንቶች ሐገሪቱን አስተዳድረዋል፡፡ በያዝነው ሣምንት አጋማሽም 45ኛ ፕሬዚዳንቷን መርጣለች። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን የተመረጡትም ዶናልድ ትራምፕ ናቸው፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ፍጹም የተለዩ ሰው መሆናቸውን፤ በምርጫ ውድድሩ አሸናፊ የመሆናቸው ዜና በተገለጸ ቅጽበት በዓለም ህዝብ ዘንድ የተፈጠረውን ግራ መጋባት በመመልከት መረዳት ይቻላል፡፡
ትራምፕ ወጣ ያለ ሰብእና ያላቸው ናቸው። ከሌሎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የተለየ አድርጎ ሊያቆሟቸው የሚችሉ በርካታ ነገሮች አሉ። ለምሣሌ፤ ትራምፕ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሴናተርነት ከማገልገላቸው በቀር፤ የዳበረ የፖለቲካ ልምድ የሌላቸው የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ናቸው። እንዲሁም በህዝብ ምርጫ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን በተሰጠው ማግስት በመላ የሐገሪቱ ግዛት የህዝብ ተቃውሞ የተነሳበት የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ናቸው፡፡ እጩ አድርጎ ለውድድር ባቀረባቸው በራሳቸው ፓርቲ አባላት ተቃውሞ የገጠማቸው ፕሬዚዳንትም ናቸው። በምረጡኝ ዘመቻ ሂደት ግልጽ የፖሊሲ ሐሳብ ሳያቀርቡ አሜሪካን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የተዘጋጁ የመጀመሪያው ሰው ናቸው። በሐገሪቱ የምርጫ ታሪክ ለሪፐብሊካን ፓርቲ እጩዎች ድምጽ በመስጠት ከማይታወቁ የምርጫ ክልሎች የመራጮችን ድምጽ በማግኘት ለማሸነፍ የበቁ ብቸኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሊባሉም ይችላሉ። የህዝብ አስተያየት መረጃ አጠናቃሪ ተቋማትንና የመገናኛ ብዙሃንን ትንበያ እርባና የለሽ ባደረገ የምርጫ ሂደት ያሸነፉ የመጀመሪያው ሰው ናቸው፡፡ ዝርዝሩ ሊቀጥል ይችላል፡፡
በአጭሩ ዶናልድ ትራምፕ የተለየ ሰብእና ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ በርግጥ የሁሉንም የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ህይወት በደንብ ከፈተሽን፤ ሁሉም ፕሬዚዳንቶች መለያ የሚሆን አንድ ወጣ ያለ ነገር አያጡም፡፡ በአደባባይ ከሚታወቀው የተለየ ነገር የማይዛመድ ወይም አስገራሚ ሆኖ ሊታይ የሚችል ባህርይ ወይም ልዩ ችሎታ ያላቸው በርካታ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች አሉ፡፡ ቤተሰብ ወይም የቅርብ ሰው ብቻ የሚያውቃቸው ልዩ ባህርያት ወይም ችሎታ ከነበራቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የአንዳንዶቹን እያነሳን መጫወት እንችላለን፡፡ ጨዋታውን ከመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከጆርጅ ዋሽንግተን እንጀምር፡፡
ጆርጅ ዋሽንግተን
ጆርጅ ዋሽንግተን ምርጥ ዳንሰኛ ነበሩ፡፡ ጆርጅ ዋሽንግተን ለቁጥር አታካች በሆኑናየዳንስ ዕድል በሚፈጥሩ ‹‹ፓርቲዎች›› ወይም የጭፈራ ድግሶች ታድመዋል፡፡ ከጭፈራ ድግሶች ሄደው እየደነሱ ያነጋሉ። ግን ዘወትር ከአንዲት ሴት ጋር ሲደንሱ አይገኙም። ከጭፈራ ድግስ ሄደው ለዳንስ ሲወጡ በክንዳቸው የሚይዟት ሴት አያጡም፡፡ ጆርጅ ዋሽንግተን ለፓርቲ ከታደሙት ሴቶች መካከል ምርጥ ደናሽ ከምትባለው ሴት ጋር የዳንስ መድረኩን ይውረገረጉበታል፡፡
አንድሪው ጃክሰን
አሜሪካ የሽጉጥ ፍልሚያ የሚወድድ ፕሬዚዳንትም ነበራት፡፡ እኒህ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አንድሪው ጃክሰን ይባላሉ፡፡ ጃክሰን የሽጉጥ ፍልሚያ አርበኛ ናቸው፡፡ አንጋፋ የጦር ሰው ተደርገው ይታዩ የነበሩት አንድሪው ጃክሰን፤ በጦር አውድማ ብቻ ሳይሆን በከተማም ሲዘዋወሩ ከትከሻቸው ጠብመንጃ አይጠፋም። በህይወት ዘመናቸው 100 ጊዜ ሸማ ተታጥለው፤ ከባላንጣቸው ጋር ለፍልሚያ ተሰልፈዋል፡፡ ብዙ ጊዜ በጥይት ቆስለዋል፡፡ አንድሪው ጃክሰን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት፤  እ.ኤ.አ በ1806 ዓ.ም ከአንድ ታዋቂ ሰው ጋር ፍልሚያ አድርገው ነበር፡፡ ከተፋላሚያቸው ጋር በፈረስ ግልቢያ ውርርድ አድርገው፤ ተወራራጁ ሰው ለማጭበርበር በመሞከሩና ሚስታቸውን ወ/ሮ ጃክሰንን በመሳደቡ፤ሰውዬው ጋር ፍልሚያ ለማድረግ ቆረጡ፡፡ ይህ ሰው ቻርልስ ዲከንስ ነው። ጃክሰን ከታዋቂው እንግሊዛዊ ደራሲ ቻርልስ ዲከንስ ጋር ፍልሚያ አድርገው ገደሉት፡፡
ጆን ታይለር
በዳንስ ዝግጅቶች መደነስ የማይታክተውንና ከሞት ፊት መቅረብ የማይሰለቸውን ፕሬዚዳንት አይተን ስንገረም፤ ሙዚቀኛው ፕሬዚዳንት ጆን ታይለር ይመጣሉ፡፡ ፕሬዚዳንትነት እንጀራዬ ይሆናል ብለው አስበው የማያውቁት 10ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆን ታይለር፤ ፊታቸውን ወደ ህግ ጥናት ከማዞራቸው በፊት፤የኮንሰርት የቫዮሊን ተጫዋች ለመሆን የሚያስችል ትምህርት መማር ጀምረው ነበር። በኋላ የሙዚቃ ትምህርቱን ትተው የህግ ተማሪ ቢሆኑም ‹‹ደግሞ መሸ አምባ ልውጣ›› የሚያሰኝ የሙዚቃ ፍቅር አድሮባቸው፤ ልክፍቱ ‹‹ኋይት ሐውስ›› ድረስ ተከትሏቸዋል፡፡ እናም ነሸጥ እያደረጋቸው፣ በ‹‹ኋይትሐውስ›› በተከወኑ የሙዚቃ ድግሶች ቫዮሊን እየተቀበሉ ይጫወቱ ነበር፡፡
ጀምስ ኬ. ፖልክ
አሜሪካ ብራንዲ መጎንጨት የሚወድ ፕሬዚዳንትም ነበራት፡፡ ፕሬዚዳንት ጀምስ ኬ. ፖልክ፤ ‹‹ወይን ያስተፌስህ ልበሰብ›› የሚሉ ናቸው። ከሐኪም አልጋ ተጋድመው እንኳን የብራንዲ ጽዋቸውን ይይዛሉ። ፖልክ በልጅነታቸው በሽታ የሚያጠቃቸው ነበሩ፡፡ 17 ዓመት በሆናቸው ጊዜ የሽንት ወይም የኩላሊት ጠጠር ተገኝቶባቸው ታመሙ፡፡ ታዲያ ጠጠሩ እንዲወጣ የቀዶ ጥገና ባደረጉ ጊዜ ‹‹ማደንዘዣቸው›› ብራንዲ ነበር። ጽዋቸውን አንስተው፤ ብራንዲ ቀማምሰው፤ የሐኪሙን መቀስ ፉጨት እየሰሙ፤ ከብራንዲው ፉት እያሉ፤ ቀዶ ጥገናውን አድርገዋል፡፡
ፍራንክሊን ፒርስ
በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ በልዩ የማስታወስ ችሎታ የሚጠቀሱ ሰው አሉ፡፡ እኒህ ሰው ፍራንክሊን ፒርስ ናቸው፡፡ ፒርስ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ ያደረጉትን ንግግር አንድ ጊዜም ወረቀት ሳያዩ በማቅረባቸው በአንክሮ ይጠቀሳሉ፡፡ ንግግራቸው 3 ሺህ ቃላት ያሉት ንግግር ነበር፡፡ አንዳችም የማስታወሻ ካርድ ሳይዙ በቃል ዘልቀውታል፡፡
አብርሃም ሊንከን
ብዙዎች በፍቅር የሚያነሷቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን ይመስሉኛል፡፡ አብርሃም ሊንከን፤ ‹‹የአሜሪካን የነጻነት አዋጅ›› (Emancipation Proclamation) ሰነድን ለመጻፍ ከመቀመጣቸው በፊት የአልኮል መጠጥ ቸርቻሪና የቡና ቤት አስተጋጅ ነበሩ፡፡ ሊንከን ከአንድ ሰው ጋር ሽርክና ገብተው በኢሊኖይስ (Illinois) የከፈቱት መጠጥ ቤት  አትራፊ አልነበረም፡፡ ቡና ቤቱ በብድር ተዘፍቆ ብዙ ሳይቆይ በኪሳራ ተዘጋ፡፡ አብርሃም ሊንከንም የአልኮል መስፈሪያ መለኪያቸውን ጥለው የህግ መጽሐፍ አነሱ። ‹‹የአሜሪካን የነጻነት አዋጅ›› የተጻፈው አልኮል በመለኪያ ሲሰፍር በነበረ ሰው ነው፡፡
ጀምስ ጋርፊልድ
በያዝነው ሣምንት 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ፤ ‹‹በአንድ ራስ ሁለት ምላስ›› ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ ልሳነ-ብዙው ፕሬዚዳንት ጀምስ ጋርፊልድ ደግሞ በሁለት እጃቸው፤ በአንድ ጊዜ፤ በሁለት ቋንቋዎች ደብዳቤ መጻፍ የሚችሉ ነበሩ፡፡ ጋርፊልድ በቀኝ እጃቸው ግሪክኛ እየጻፉ፤ በግራ እጃቸው ላቲን መጻፍ የሚችሉት ቢሆኑም ግራኝ ናቸው፡፡
ቸስተር ኤ. አርተር ውድ
ሽቅርቅር ማለት የሚወዱት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቸስተር ኤ. አርተር ውድ ናቸው፡፡ አርተር ውድ ‹‹አሸር ባሸር›› ነገር አይወዱም፡፡ ሁሉም ነገር የምርጥ ምርጥ ካልሆነ ንክች አያደርጉትም፡፡ የሚያምራቸውና የሚወዱት ነገር ሁሉ ኪስ የሚያራቁተውን ነገር ነው። በዚህ የተነሳ ቅጽል ሥም ወጥቶላቸዋል፡፡ ‹‹ሽቅርቅሩ አለቃ›› (Gentleman Boss) ይሏቸዋል፡፡
የላመ - የጣመ፤ ያማረ- የከበረ ነገር ብቻ የሚወዱት  አርተር ውድ፤ በዚህ ዓመላቸው የመንግስት ካዝናን ያስደነግጡ ነበር፡፡ ዘወትር በ‹‹ኋይትሐውስ›› የሚያደርጉት ግብዣ፤ ‹‹12 ኮርስ›› ያለው የተትረፈረፈ ዓይነት ግብዣ ነበር፡፡
በአዋቂ እጅ የተሠራ ከ80 በላይ ሙሉ ልብስ ነበራቸው፡፡ ለማህበራዊ ጉዳይ የሚሄዱበት ነገር ከገጠማቸው፤ ሽቅርቅር ብለው በተጌጡ ፈረሶች በሚጎተት ሰረገላ እየተንፈላሰሱ መሄድ ምርጫቸው ነው፡፡
ጂሚ ካርተር
በድንቅ ችሎታቸው ወይም በእንግዳ ጠባያቸው የሚታወቁ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችን መጥቀስ ከጀመርን፤ጂሚ ካርተር ሊነሱ ይገባል፡፡ ካርተር የሚታወቁት በፈጣን አንባቢነታቸው ነው፡፡ የፈጣን ንባብ ችሎታ በኦሎምፒክ የስፖርት መድረክ ውድድር የሚደረግበት ስፖርት ቢሆን ኖሮ፤ አሜሪካንን በመወከል ለውድድር የሚቀርቡት ጂሚ ካርትር ይሆኑ ነበር፡፡  ጂሚ ካርትር ይህን ችሎታ ያገኙት ተምረው ነው፡፡ የፈጣን ንባብ ትምህርቱን የተማሩት ከሚስታቸው ጋር ቢሆንም ሚስቲቱ እንደ ባልዬው የተሳካላቸው አይደሉም፡፡ ካርት በደቂቃ ሁለት ሺህ ቃላት የማንበብ ችሎታ ነበራቸው፡፡ ታዲያ ዝም ብሎ ማንበብ ብቻ አይደለም፡፡ ካነበቡት ነገር 95 በመቶውን በትክክል ከመረዳት ብቃት ጋር እንጂ ዝም ብሎ ሩጫ አይደለም፡፡
ቴዎዶር ሩዝቬልት
በጂሚ ካርተር (Jimmy Carter) ነገር መገረም ካቃታችሁ፣ ቴዎዶር ሩዝቬልት (Theodor Roosevelt) አሉላችሁ፡፡ ሩዝቬልት ከሥራ ፋታ ባገኙ ጊዜ በ‹‹ኋይትሐውስ›› ምድረ ግቢ ድልድይ መስለው በተሰሩ ጠባብ አግዳሚ እንጨቶች ላይ ሚዛን ጠብቀው ለመራመድ ሲጣጣሩ ታገኟቸዋላችሁ። በእርግጥ በዚህ ነገር የሚዝናኑት ሩዝቬልት ብቻ አይደሉም፡፡ ሁሉም የቤተሰባቸው አባላት የየራሳቸው ድልድዮች እንደነበሯቸው ይነገራል፡፡
እነ ዊድሮው ዊልሰን
በርካታ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሙዚቃና ዘፈን ይወዱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ዊድሮው ዊልሰን (Woodrow Wilson) ናቸው፡፡ ዊልሰን ዘፋኝ ነበሩ፡፡ ‹‹የመንግስታቱ ማህበር›› መስራች የነበሩት ዊድሮው ዊልሰን፤ በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ በሚማሩበት ወቅት የኮሌጁ የኪነት ቡድን ዘፋኝ ነበሩ፡፡ በዚህ ጎራ የሚገኙ ሌላው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሐርዲንግ (William Harding) ናቸው፡፡ ሐርዲንግ መጫወት የማልችለው አንድም መሣሪያ የለም ባይ ቢሆኑም፤ በልዩ ችሎታ የሚጫወቱት፤ የሐገራችን የፖሊስ ማርሽ ባንድ የሚጫወትበት ከወገብ ተጠምጥሞ የሚያዝና፣ ‹‹Sousaphone›› የሚሉት የትንፋሽ መሣሪያን ነው። ዊልሰን በ‹‹ኋይትሐውስ›› ልምምድ ከሚያደርግ የሙዚቃ ባንድ ሙዚቃ ሲሰሙ፤ ከአጠገባቸው ያገኙትን መሣሪያ አፈፍ አድርገው ከባንዱ ጋር ለመጫወት ሲሞክሩ በተደጋጋሚ ማየታቸውን የግቢው ሰራተኞች ይናገራሉ፡፡
በተለያየ ዘመን ሐገሪቱን የመሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች አንድ ላይ ቢሰባሰቡ አንድ ጥሩ ባንድ ይወጣቸው ነበር፡፡ ዘፋኝና የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች የሆኑ ፕሬዚዳንቶች መኖራቸውን አይተናል፡፡ አሁን ደግሞ የዘፈን ግጥም ደራሲው ሊመጣ ነው፡፡ ኸርበርት ሁቨር (Herbert Hoover) ከወደ ውሃው የሚበረቱ ገጣሚ ነበሩ፡፡ ሁቨር በዕድሜ ሃያዎቹ ግድም ሳሉ፤ የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ ኢንጂነር ሆነው ይሰሩ ነበር። በዚሁ ጊዜ ለአንዲት አውስትራሊያዊት የቡና ቤት አስተናጋጅ የፍቅር ግጥም ጽፈውላት ነበር፡፡ ይህ ግጥም ዛሬም ድረስ ፕሬዚዳንቱ ከአስተናጋጇ ጋር በተገናኙበት ሆቴል ተሰቅሎ ይገኛል፡፡
ሐሪ ቱሩማን (Harry Truman) ደግሞ ፒያኖ ተጫዋች ናቸው፡፡ በርግጥ አንዳንዶች የትሩማንን የፒያኖ ችሎታ ጥያቄ ውስጥ ይከቱታል፡፡ ትሩማን የኮንሰርት ፒያኖ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት ይዘው፤ በየዕለቱ ለሰዓታት ልምምድ የሚያደርጉ ነበር፡፡ ሆኖም ብቃቸውን ብዙ ለማዳበር አልቻሉም፡፡
ሪቻርድ ኒክሰንም (Richard Nixon) በሙዚቃ ፍቅር የተለከፉ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ለጊዜው የ‹‹ወተርጌት›› ቅሌትን እንርሳው፡፡ ኒክሰን፤ ሳክስፎን፣ ክላሪኔት፣ አኮርዲዮንና ፒያኖ መጫወት ይችላሉ። የራሳቸውን የሙዚቃ ድርሰትም ጽፈዋል፡፡ አሳዛኙ ነገር፤ አንዲት ሐረግ የሙዚቃ ዐ. ነገር እንኳን ማንበብ አይችሉም፡፡ መቼም አሁን አንድ የሙዚቃ ባንድ ለመመስረት በቂ ሰዎች ያገኘን ይመስለኛል። ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ባንድ ፈጥረው ሙዚቃ ከሰሩ፤ ሥራቸውን ለህዝብ ለማስተላለፍ አንድ የሬዲዮ ዲጄ አለን፡፡ ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ. ጆንሰን (Lyndon B. Johnson) የሬዲዮ ዲጄ ነበሩ። የቴክሳስ ገዢ ሳሉ በሚስታቸው የውርስ ገንዘብ የሬዲዮ ጣቢያ ገዙ፡፡ እናም በጥቂት አስርት ዓመታት ጣቢያው በሚሊየን የሚቆጠር ሐብት ማካበት ቻለ፡፡ የሬዲዮ ጣቢያው ዛሬም ድረስ አለ። KLBJ-FM እየተባለ የሚጠራ ነው፡፡ ይህ የሬዲዮ ጣቢያ በደቡብ ምዕራብ አሜሪካ የሚገኝ የሮክ ሙዚቃ የሚያቀርብ ግንባር ቀደም የሬዲዮ ጣቢያ ነው፡፡
እስከ አሁን ከተጠቀሱት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሁሉ ለየት ያለ የህይወት ልምድ ያላቸው ገራልድ ፎርድ (Gerald Ford) ናቸው፡፡ ገራልድ ፎርድ የሃያ ዓመት ወጣት ሳሉ የፋሽን ሞዴል ነበሩ፡፡ በ1942 ዓ.ም (እኤአ) ‹‹ኮስሞፖሊታን››(Cosmopolitan) በተባለ ዝነኛ መጽሔት የሽፋን ገጽ ላይ ምስላቸው ወጥቶ ነበር። ይህ የሞዴል ሥራቸው ሞዴል ከነበረች የወደፊት ሚስታቸው ጋር የመተዋወቅ ዕድልን ፈጥሮላቸዋል፡፡
ሮናልድ ሬጋን
ሮናልድ ሬጋን (Ronald Reagan) በፊልም ተዋናይነት ዝና ከማግኘታቸው በፊት፤ እንደ ደምሴ ዳምጤ በሬዲዮ ጨዋታዎችን የሚያስተላልፉ ጋዜጠኛ ነበሩ፡፡ በአንድ ጨዋታ 10 ዶላር ይከፈላቸው ነበር። በዚህች ላይ ለትራንስፖርት ትንሽ ገንዘብ ጣል ይደረግላቸዋል፡፡ ሆኖም ከ10 ዓመታት በኋላ የፊልም ተዋናይ ሲሆኑ፤ ደመወዛቸው ወደ 11 ሚሊየን ዶላር አደገ፡፡
ቢል ክሊንተን
ቢል ክሊንተን (Bill Clinton) በጋዜጣ የሚወጡ የቃላት ሰንጠረዥ ጨዋታ ሊቅ ናቸው፡፡ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የምርጫ ውድድር አድርገው፣ በአስገራሚ ሁኔታ የተሸነፉት የሂላሪ ክሊንተን ባለቤት ቢል ክሊንተን፤ በ‹‹ኒውዮርክ ታይምስ›› የሚወጡ የቃላት ሰንጠረዥ ጨዋታዎችን እንቆቅልሽ በጥቂት ደቂቃዎች የመፍታት ችሎታ ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ ታዲያ ይህን ሲያደርጉ ኮስታራ የፖለቲካ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡
ጆርጅ ደብሊው. ቡሽ
የ‹‹በረሃው ማዕበል›› አዝማች የሆኑት ጆርጅ ደብሊው. ቡሽ ደግሞ አማተር ሰዓሊ ሆነዋል፡፡ በ2008 ዓ.ም (እኤአ) የፕሬዚዳንትነት መንበሩን ካስረከቡ በኋላ የ‹‹ካውቦይ›› ባርኔጣቸውን አውልቀው የስዕል ብሩሽ አነሱ፡፡ ቡሽ የሚሰሩትን ስዕል፤ ዳላስ በሚገኘው ‹‹የጆርጅ ቡሽ ፕሬዚዳንታዊ ማዕከል›› ውስጥ ለህዝብ ዕይታ ያቀርቡታል፡፡ ከቭላድሚር ፑቲን ጀምሮ እስከ አንጌላ ሜርክል ድረስ የበርካታ የዓለም መሪዎችን ምስል በዘይት ቀለም ስለዋል፡፡
በቅርቡ መንበረ ሥልጣኑን ለዶናልድ ትራምፕ የሚያስረክቡት ባራክ ኦባማ ደግሞ የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኙ ደራሲ ናቸው። ኦባማ የኖብል የሰላም ሽልማት አልበቃቸውም። በ2007 ዓ.ም (እኤአ) የ‹‹ግራሚ ሽልማት›› አሸናፊ ሆነዋል - ‹‹Dreams My Father›› በሚል መጽሐፋቸው፡፡
ይህ ሁሉ ነገር የተነሳው በዶናልድ ትራምፕ ሰበብ ነው፡፡ የዶናልድ ትራምፕ መመረጥ ዓለምን ግራ አጋቢ ሁኔታ ውስጥ ጥሏታል፡፡ ይህ ግራ አጋቢ ነገር በግልጽ የሚናገረው አንድ ግልጽ ነገር አለ፡፡ ዓለም ገና ውሉ ባልታወቀ የለውጥ ሂደት ውስጥ እያለፈች መሆኑን በግልጽ የሚናገር ክስተት ነው፡፡ ይህ ሐቅ ዓይኑን አፍጥጦ፤ ቃሉን ረጋግጦ፣ በትምክህት እና በንቀት ስሜት ሆኖ አፍ አውጥቶ፤ ዓለም በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኗን እየተናገረ ነው፡፡

Read 2856 times