Sunday, 13 November 2016 00:00

ውዳሴ ሙላቱ ወ መቋሚያ ‹‹እውቀትህን ላገርህ ህዝብ ጥቅም አውለው!››

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

ጥልቀትህ  ሙላቱ ጽናትህ ብርታቱ ማዕበል ያስንቃል
ቅላፄህ ርቅቀቱ ወርድና ስፋቱ ከአጽናፍ አጽናፍ መጥቋል
ውቅያኖስ ተሻግሮ ሥምህ ግብሩ ደምቋል
መንጸባርቅ ኃይሉ  ሺ ማሾ ያስንቃል፡፡
(መቋሚያ - ሰኔ 2000 ዓ.ም - ‹‹የፀሐይ ገበታ›› - ያልታተመ)

ባለፉት ሁለት ሳምንታት፤ በፊተኛው ቅዳሜ የሞዛርትን ህይወትና የሙዚቃ ሙያ ገድል፤ በሳምንቱ እሱን ተንተርሰን ደግሞ ሊቁን አልበርት አይንስታይንን ከአንጻራዊነት (Theory of Relativity) ንድፈ ሀሳቡ ጋር በሚወዳት ቫዮሊኑ ዜማ አጅበን መቃኘታችንን በማመስገን፤ እግረ መንገድ ‹‹ከአገር ቤትስ@›› የሚል አስተያየት ለሰነዘራችሁ አንባቢያን ወዳጆች፤ ሞልቶን! ይኸው። ያውም ከወትሮው ዘለግ ያለ፡፡ ከሙዚቃ አርዕስት ሳንወጣ፤ የአንጋፋውን የሙዚቃ ሰው የኢትዮ ጃዝ አባትን፣ ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ  ከብዙው እፍኝ ታህል ቆንጥረን፤ በተለይ አንዲት የህይወት አጋጣሚውን፤ የዚህ ጽሑፍ መክፈቻ በሆነውና ከአመታት በፊት ለውዳሴው ከተቋጠረለት ስንኝ ጋር እያሰናሰልን ለአፍታ እንቃኘው ዘንድ እነሆ...
...በጸናፅል  መቋሚያ  በበገና አውታር ላይ
መንፈስህ ተቃኝቶ በእዝልና አራራይ
ታሪክህን አዝለህ ስትል ከታች ላይ፤
ያገርክን ክቡር ቅርስ ለትውልድ ልታወርስ
በዘመን አድሰህ ለአለም ልታደርስ፤
እውነት ነው! ይኸ እኛው የራሳችንን ጸጋ ለማስተዋል የሚያቅተን ጉዳይ ግን፤ በኔ እምነት እንደ ሌሎቹ ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን ሁሉ የሺህ ዘመናት እንከኖቻችንና ተግዳሮቶቻችን ነፀብራቅ ሆኖ የሚወሰድ ነው፡፡ ይኸው በዘመናት ያልጠራ ግሳንግሳችንም ይሆናል ያገር ፈርጥና እንቁዎቻችንን ከመዳብ እምንቆጥር ያደረገንም፡፡ የራሳችንን መልክ ማስተዋል ተስኖን ባእዳኑ፤ ‹‹እነኋችሁ’ኮ ውበታችሁ፤ ሀብታችሁ፤ ታሪካችሁ...ወዘተ›› ሲሉን እጃችንን አፋችን ላይ ጭነን በመደነቅ፣አንገታችንን መነቅነቃችን ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ‹‹እንቶኔ የገባው ይመስል አንገቱን ይነቀንቃል›› እንዲል ያገራችን ተረት፤ አድሮም ያው መሆናችን እንጂ፡፡ ፊታችን ሆኖ ማየት ያቃተንን ውበት በሩቅ ሆነው አሻግረው እስኪጠቁሙን መጠበቅ መልመዳችንም በገሀድ እሚስተዋል ነው፡፡ ለዚህ ተስማሚ የሆነ የዚህ ዘመን ወግ አለ፡፡ኢትጵያዊያን ተሰባስበው ፊት ለፊታቸው የተቀመጠውን ውሀ የሞላ ብርጭቆ ከብበው ‹‹ውኃ ነው!››፤ ‹‹ቢሻን ነው!››፤ ‹‹ማይ ነው!›› ‹‹... ነው!›› እያሉ ሲሟገቱ፣ ድንገት በሩን ከፍቶ የሚገባ እንግዳ ‹‹This is water.” ብሎ አስማማቸው፡፡ ባእዳኑን ለባለውለታነታቸው እያመሰገንን፤ ሆኖም ‹‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል›› ነውና የማይደገሙ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርስና አንጡራ ሀብቶቻችንን በጉዲፈቻ ስያሜ መልሰው ለኛው ሲያቀብሉን በዝምታ መመልከቱና የእነሱ አውራጅ የእኛ ተቀባይነቱ፣ ‹‹ባይቆጭ ያንገበግባል›› ያሰኛል መቸም፡፡
የምድሩ የሰው ዘር መገኛ (Cradle of human kind) መሆናችንን ሲያረጋግጡልን፤ ከአፋር ምድር ስር ቆፍረው ያወጧትን ቅሪተ አካል (Australopithecus afarensis) ስሟን ‹‹ሉሲ›› ብለው ሲያስተዋውቁን፤ መጠሪያው የእነሱን ምድር የሙዚቃ ቡድን The Beatles ዜማን “Lucy in the Sky with Diamonds” አስከትሎ አየሩን መናኘቱንና አሁንም ድረስ መዝለቁን ልብ ይሏል፡፡ ከተነሳው አርእስተ ጉዳይ ጋር ሙዚቃም ስለተሸረበ፣ እንደ ጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ ያሉ የእትብት ቀዬአችን ጠቢባን እዚህ ብናነሳም፤ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሉትንም፤ ለየእድሜ ልክ ትጋትና ርእያቸው ተፈፃሚነት፤ የተቸገሩ፡ የተነፈጉት ቦታና ክብር ጉዳይም ጎትጓች ጥያቄ ሆኖ መወሳቱ ግድ ይላል። (‹‹ወይ ደግሞ በዚህም ሆነ በአንድ ሌላ ጉዳይ ላይ በጥቅሉ ነጩን ወይም ጥቁሩን ሁለቱንም ጥግ አለቅጥ ከመደገፍ አስታራቂው ግራጫው “Grey Scale” እንኳ ቢሆን መልካም ነው እላለሁ››) ወደ ክቡር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ የዜማ ጸጋና ጉዞ ስንቀጥል...
...በጸጋህ  ስትተጋ ስለ ዜማ ማቅቀህ
ለፈውስህም ተስፋ ባገር ፍቅርህ ጠበል በዜማ ተጠምቀህ፤
የእንቢልታ ፡ መለኸት ትንፋሽ ሽቅብ መጥቆ ለዓለም እስኪወጣ
ዜማ ጓዝ ሸክፈህ እድሜ ዘመንህን ጠጉርህ እስቲነጣ
የቅኝትን ዳገት የኪንን በረሃ ስትኳትን ‹በነጻ›፤
እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ፤ በአንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያነቱ በሩቁ ከማደንቀው፤ ከጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርበት ትውውቅ የፈጠርኩት፤ ለዚሁ እድሜ ዘመኑን ለገበረለትና ላቅ ያለ ሀገራዊ ፋይዳ ላለው የጥበብ ካቡ፣ ያቅሜን አንዲት ጡብ ለማቀበል ታላቅ እድል ባገኘሁበት ወቅት ነበር፡፡ ከአስር አመታት በፊት። ዛሬም ይቺኑ ያንዲት ጡብ አጋጣሚ ተታክኬ ጥቂት ለማለት ያህል ደፈርኩ እንጂ፤ የእሱ ህይወትና ሙያዊ ገድል በኔ ብእር የሚከተብ ሆኖ፤ እኔም እሱን የመተረክ ብቃት ኖሮኝ አይደለም፡፡ ብቻ ግን በቃ ገና ያኔውኑ፤ ቅርበቴና መረዳቴ የገለጠልኝን ያህል ባይመጥንም እንዲህ ብዬ ከማወደስ አልታቀብኩም...
...ኗሪ ምልክትህ ያንተ ህይወት የኖርካት ጸንተህ በዚህች ምድር
በአፍሪካ ከበሮ በኢትዮጵያ መሰንቆ ቶምቶም ክራር ድርድር
የሰሜን የደቡብ የምስራቅ ምዕራብ ድምፁን አጣጥመህ
ያገርክን ከወዲያኛው ምት ስታበራይ ህዝብህ መሀል ኖረህ፤
ከጋሽ ሙላቱ ጋር፤ በ1999 ዓ.ም ገደማ ቦሌ ከአትላስ ሆቴል ጀርባ ተከራይቼ በኖርኩበትና በመንደሩ ዙሪያ ባሉ ዛፎች የሰፈሩት አእዋፍ ዝማሬ ብቻ ኩልል ብሎ በሚሰማበት ጸጥታ የነገሰበት ባለ ሁለት ክፍል መኖሪያ ቤቴ ውስጥ፤ ረዥም ጊዜ የደከመበትንና ገና ሰርቶ ያጠናቀቀውን፤ ቅኝቱ የድምጽ ሰረገላ አቆናጥጦ፡ በሽምጥ ደንገላሳ ግልቢያ የህዋውን ሞገድ የሚያሳብር፡ በዜማ አክናፍ እያንሳፈፈ ሰማየ ሰማያት የሚያመጥቅ አይነት ስሜት ያሳደረብኝን የረቂቅ ሙዚቃ ስራውን fusion Jazz? አክብሮ ጋብዞኝ በጋራ አደመጥን፡፡ ጸጥታው መልሶ ሲነግስም፤ ስለ ስራው መነሻ፡ ምንነትና ይዘት እኔ ብዙ ያልተረዳኋቸው ሙያዊ ትንታኔዎቹን እየጨለፈ፣ ከህይወት ዘመኑ የሙዚቃ ፍልስፍናውም ቆንጠር እያደረገ አውግቶኝ ሲያበቃ፤ በቤቴ ውስጥ መደርደሪያ ላይ ተዘበራርቀው የተቀመጡትንና በወለሉ ዙሪያ እዚህም እዚያም ተዝረክርከው፡ ከባዶ የወይን ጠርሙሶች ቂጥ ስርም ተዳብለው ተበታትነው የወዳደቁትን አሮጌ መጽሐፍቶቼን ገርመም አድርጎ፤ በተለመደ እርጋታው ስለ ንባብና የጥበብ ህይወት አርእስት አንስቶ፤ በተራዬ ቅኝቱ እንደፈራረሰ ክራር ኳኳታ ዜማ ያለው በሚመስል የፍንዳታነት እድሜ እርግብግቢቱ የተጣደፈ ድምፄ ሳላቋርጥ የዘበዘብኩለትን ‹ጠጠር መጣያ ያልነበረውን› የተንዛዛ ምላሼን በትእግስት እያደመጠ፤ እንደ ወላጅ አባት በየዋህ አይኖቹ ትክ ብሎ በሀዘኔታ ሲያስተውለኝ ቆይቶ፤ ‹‹ዋናው ቁም ነገር፤በራስህ ፍለጋ ተመራምረህ የደረስክበትንም ሆነ ከውጪ ሀገራት የቀሰምከውንም ቢሆን፡ በእድሜህ ያካበትከውን ሁሉ፤ ማንኛውንም እውቀትህን ላገርህ ህዝብ ጥቅም እንዲውል ለማድረግ መቻል ነው›› አለኝ፡፡
...ዛሬም ትሰማለህ ጆሮ እምብርት ድረስ ሳትናጠብ ተምመህ
ጽናትህ ሙላቱ በቅኝት አንሳፍፎ በጥበብ ያከረመህ
ሱባዔህ ቢረዝምም በግብርህ ለምልመህ
ነገንም ነው እምትኖር ስለ ውበት ቀድመህ፡፡
ይህ የአንጋፋው ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ሰው አባባል፣ የሰውየውን ማንነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይም ነው፡፡ ህይወቱን ሙሉ የኢትዮጵያን የሙዚቃ መሳሪያዎችና ቅኝቶች ሲቆፍርና ሲመራመር መኖሩን፡፡ የተገናኘነውም በኢትዮጵያ ቤተ ክህነት ዜማ ላይ ተመርኩዞ ላቀናበረው ዘመናዊ ረቂቅ ሙዚቃ ......... የቪዲዮ ክሊፕ ለማዘጋጀት ነበር። ያ አጋጣሚም ታላቁ የሙዚቃ ሊቅ ማህሌታይ ያሬድ በተመስጦ የኖረበትንና የኢትዮጵያ ቤተ ክህነት ሊቃውንት፣ የዜማ እውቀት የሚቀስሙበትን ዙራምባ ማርምን ገዳም እንድጎበኝ አስቻለኝ። ለክብሩ እምበቃም ባልሆን የቅዱስ ያሬድን መቋሚያና ጸናፅልንም በእጄ እንድዳስስ፡፡ በስፍራው የተገኘነው የወርኃ ጽጌ ወቅት ላይ ስለነበር፤ ሌሊት ካህናቱ ማህሌት ቆመው የሚያወጡትን አንዳች መለኮታዊ ግርማ የተላበሰ ዜማ ሳደምጥ፤አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ በ”ፍቅር እስከ መቃብር” ገጽ መሀል እንዳሰፈሩት፤ ወደ ዲማ እንግዳ ሆኖ የመጣውን በዛብህን ቅኔ ቤት በር ላይ በጥያቄ ያፋጠጠውን ተማሪ አይነት አሁን ቢገጥመን ምን መልስ ሊወጣን ነው እያልኩ አሰላስል ነበር፡፡ የበዛብህ ምላሽ ግን ጠያቂውንና አብረውት የነበሩትን ጓደኞቹንም ያስደመመ ነበር፡፡ በመሀሉም ይህቺን ታሪካዊ ቅዱስ ስፍራ ከዜማ ጋር አብሮ ያነሳታል...
‹‹መጽሀፍ ለመቀጸል ነው? ወይስ ለቅኔ ትምህርት ነው የመጡ?››
‹‹ቅኔ ለመማር ነው፡፡›› አለ በዛብህ፡፡
‹‹እህ፡-ለማለዘብ ነው? ወይስ ለመጀመር?››
‹‹ለማለዘብ››
‹‹ወዴት ነው መጀመሪያ የተቀኙ?››
‹‹ዋሸራ››
‹‹መቸ?››
‹‹ከአራት አመት በፊት፡፡››
‹‹ከዚያ ወዲህስ?››
‹‹ሁለት አመት ያክል ዙራምባ ዝማሬ መዋሲት አሄድሁ፤ ሁለት አመት ተኩል ያክል ደብረ ወርቅ መጽሀፍ እቀጽል ነበር፡፡››
እነሆ ጥንታዊውን የሀገራችንን መንፈሳዊ ዜማ መነሻ አድርጎ፣ ከዘመናዊው የጃዝ ቅኝት ጋር አዋህዶ ላረቀቀው ለጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ የረቂቅ ሙዚቃ ቅንብር፤ ከፊልም ባለሙያ ጓደኞቼ ጋር ሆነን በጎልዳፋ እውቀታችንም ቢሆን፤ አቅማችን በፈቀደልን መጠን ‹‹መቋሚያ›› የሚል አጭር ቪዲዮ ክሊፕ ሰራን፡፡ እውነት ለመናገር ከዜማው እምቅነት አኳያ የኛ ምስል ወ ድምጽ ረጋ ሰራሽ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ያም ሆኖ ውሎ አድሮ  ጋሽ ሙላቱ፤ በጸጥታዋ የተነሳ ከሚወዳትና ከሚያዘወትራት ስፍራ፣ ግዮን ሆቴል ዩኒቲ መናፈሻ ተገናኝተን እንዳጫወተኝ፤ በየሄደበት ሀገር ከረቂቅ ሙዚቃው ጋር ሊያሳየውና በተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተቀንጭቦ ለመቅረብም እድል አግኝቷል፡፡ አርእስቱ ‹‹መቋሚያ›› የተሰኘበት ምስጢርም እንዲሁ ክቡር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ፣ አለም ስለ ኢትዮጵያ ያውቀው ዘንድ በስፋት ሊያስተዋውቀው የተነሳው ብርቱ ጉዳይ ነው፡፡
ይኸውም፤ የቤተ ክርስቲያን መቋሚያ በረዥሙ የቅዳሴ ጸሎት ጊዜ ለምእመናንና ካህናት ከመደገፊያነቱ ባሻገር፤ የካህናት ዜማ መምሪያ በመሆን እንደሚያገለግል ማሳወቅ ነው። እኛም ይህንኑ መገለጥ (ምስሉን እዚህ በቃላት መከሰት ባይቻልም ለአንባቢያን የስዕሉን መልክ በደብዛዛውም ቢሆን ለማስጨበጥ ያክል) ገና በአለም ላይ የሙዚቃ ኖታ ሳይፈጠር ብዙ መቶ አመታት አስቀድሞ፣ ማህሌታይ ያሬድ ከነደፋቸው የሀገራችን የዜማ ምልክቶች ተነስተን፤ በሮሀ ላሊበላ ሜሙ ዳገት ላይ በየአመቱ በልደት/ገና በአል የሚቀርበውን የካህናት ወረብና አዲስ አበባ  ሚካኤል አጥቢያ በሌሊት ታድመን ያየነውን፡ የዜማው አወራረድ መርቀቅ እምንሆነው ያሳጣንን በመቋሚያ የሚመራውን መርግድ፡ በእንጦጦ ኤልያስ ደብር ዋሻ ውስጥ የቀረፅነውንና በአኒሜሽን በመታገዝም ልዩ ልዩ ግብአቶች አካትተን፤ በመዝጊያው ላይም የአለም ሲምፈኒ ኦርኬስትራ ሳይጀመር በፊት ኢትዮጵያዊያን በመቋሚያ እንዴት ዜማ መምራት እንደጀመርን መቋሚያችንን ከዘመናዊው የሙዚቃ መሪና መምሪያ  (conductor stick) ጋር መሳ ለመሳ በማሳየት፣ ተወራራሽነቱን ለመጠቆም ሙከራ አድርገናል፤ጋሽ ሙላቱ የፈለገውን ያህል ባይሆንም፡፡ እርግጥ ነው አቅማችን ቢፈቅድ ማህሌታይ ያሬድ በአራቱ የአመቱ ወቅቶች እንዲዜሙ ያደራጃቸውንም (ድጓ antiphonary ዝማሬ antiphonal chants ምእራፍ collection of hymns) መንፈሳዊ መዝሙራት ሁሉ በየአውዱ የምናሳይበት ደረጃው ከፍ ያለ ጥናታዊ የምስል ወ ድምጽ (Experimental Video) ስራ ቢኖረን በወደድን ነበር፡፡ ቦ ጊዜ ለኩሉ፡፡ አሜን፡፡
...የጥንቱን ቁፋሮ ወረቡ ሲመራ መርግድ ሲረገድ ማህሌት ታድመህ
ከርሞን አሸብሽበህ የዘንድሮን ትዝብት በዝማሜ ዘምመህ
በያሬድ መቋሚያ ተደግፈህ ቆመህ፤
ቪዲዮ ክሊፑን  በምእራብ አፍሪካ ላገኘሁት ፈረንሳዊ ሳሳየው፣ በሙዚቃው እንደ እብድ አያደርገው መሰላችሁ! ገና የሙላቱ አስታጥቄን ስም ሲሰማ ነው ጸጉሩ የቆመው፡፡ በአለም ዙሪያ ኢትዮጵያ ከሚለው ስም ይልቅ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ወይም ሙላቱ አስታጥቄ የሚሉትን ስሞች የሚያውቁ ይበዛሉ የሚባለው እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ፈረንሳዊው ቤቤህ አንድ ማድ ሲቲን እውቆቹ ጆንትራ ቮልታና ደስቲን ሆፍማን የተጫወቱትን መሰል ታላላቅ ፊልሞችን ያቀናበረ ሰው ነውና ሙዚቃ ቀላል ያውቃል መሰላችሁ፡፡ ከሁሉ የደነቀኝ ደግሞ ላፕ ቶፑን ከፍቶ ዘርግፎ ያሳየኝ የኢትዮጵያዊያን ሙዚቃ ዝርዝር ነው፡፡
እማሆይ ጽጌ፣ ሽሽግ ቸኮል፣ ሙላቷ ከልካይ፣ ግርማ በየነ፣ አሰለፈች አሽኔ፣ አስናቀች ወርቁ፣ መሀሙድ አህመድ...ለዚህ መቸም ኢትዮፒኪዩስ (Ethiopiquies) በሚሉ ተከታታይ የአልበም ህትመቶች፣ ሙዚቃችንን በአለም ያስተዋወቀውን ፈረንሳዊ ፍራንሲስ ፋልሴቶን ዝቅ ብለን እጅ መንሳት ይገባናል፡፡  በአለም ላይ ያሉ የፊልም ሙያተኞች፣ ሙዚቃ በፊልም የድምጽ ግብአት ውበት ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ ስለሚያውቁም ነው የጋሽ ሙላቱ የሙዚቃ ስራ በሌላ አጋጣሚ ያውም በድንገት ታክሲ ውስጥ ተሳፍሮ ባደመጠው ዳይሬክተሩ ተመርጦ፣ሆሊዉድ ውስጥ ለተሰራው “Broken Flowers” ፊልም ማጀቢያ ለመሆን የበቃውም፡፡ በተለይ ፈረንሳዊው ኤዲተር ባንድ ወቅት የጋሽ መሀሙድ ኮንሰርት መኖሩን ዘግይቶ ሰምቶ፣ እንዴት በሶስት ባቡር አቆራርጦ ሌላ ከተማ ደርሶ የመዝጊያ ዘፈኑን ለማየትና ተመልካቹን ተጋፍቶ የጋሽ መሀሙድን እጅ ለመጨበጥ እንደታደለ በትዝታ ሰመመን ተንሳፍፎና፣ ‹‹አረ መላ መላ››ን በኮልታፋ አንደበቱ በተመስጦ እያንጎራጎረ ሲያወራልኝ፤ የእውነት ኢትዮጵያዊያን አብረውን ያሉትን ጸጋዎቻችንን፡ እንቁዎቻችንን እናውቃቸዋልን? ያሰኛል፡፡ እኔም ከፈረንሳዊው ኤዲተር ጋር ሆኜ አጭሩ የፊልም ስልጠናችን ሲጠናቀቅ የክርስቶስ ሳምራን ሰይጣንን ከእግዜር ለማስታረቅ መሻት ገድል መነሻ በማድረግ፤ ‹‹ከሚስቴ ካስታረቅከኝ ለሰይጣን ጋቢ አለብሳለሁ›› ብሎ ለእግዜር ስለት በተሳለው ሰውዬ ዙሪያ በኢትዮጵያ ተረት ላይ ተመርኩዤ በዋጋዱጉ ለሰራሁትና አሜሪካዊያን፡ ናይጄሪያዊን፡ ፈረንሳዊያን፡ቡርኪናቤ፡ ደቡብ አፍሪቃና ኢትዮጵያዊያን ለተሳተፉበት ‹‹ሰይጣንን ፍለጋ›› In Search of the Devil ለተሰኘ አጭር ፊልም ይህንኑ የጋሽ ሙላቱን ረቂቅ ሙዚቃ በማጀቢያነት ተጠቀምንበት፡፡ In Search of the Devil -(You Tube - IMAGINE FILM TRAINING INSTITUTE 2009)
የተደገፍከውን ስትባዝን ኖረህ
የጥንቱን መቋሚያ በእድሜህ አቅም አግንነህ
ለአድማስ ወዲያ ምድርም በጥበብ አሻግረህ በሳይንስ ከሽነህ
የጥልቅ ተመስጦውን ትሩፋት  ለእትብቱ
ለቀዬህ ሣር ቅጠል መሻትህ ለከርሞ
ጩኸቱ  ለወረረህ ለሚንጣጣው  ዘመን ፊትህ ተደንቅሮ፤
ይህን መሰል ስሜት አድሮብኝ የሚያውቀው በኢየሩሳሌም ከተማ ህንፃ ቤተ ክርስቲያኗ በአፄ ዮሐንስ ዘመን ተጀምሮ  በአፄ ምኒልክ ዘመን በተጠናቀቀው  የኪዳነ ምህረት ገዳም በጠባብ ክፍላቸው ውስጥ ፒያኗቸውን በስስት እያስተዋሉ፡ስለ ግሸን ደብረ ከርቤ ገዳምና የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጉዳይ በጽኑ የጠየቁኝን የእድሜ ባለጸጋዋን እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩን ባገኘኋቸው ጊዜ ነበር፡፡ እማሆይ (አንድ ቀን በሰፊው እናስባቸው ይሆናል) የመጀመሪያዋ በመሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃን በሸክላ ያሳተሙ አንጋፋ ኢትዮጵያዊት የሙዚቃ እናት ናቸው፡፡ ልክ እንደ ጋሽ ሙላቱ ሁሉ እሳቸውም የአብነት ትምህርት ቤት ኢትዮጵያዊያን እንቦቃቅላዎች የዜማ ክህሎት ጉዳይ ያሳስባቸዋል፡፡ እናም በዚህ በእድሜያቸው አመሻሽ ላይ ሆነውም አንዲት ቀን፣ ለመጨረሻ ጊዜም ቢሆን ሙዚቃ መጫወት ቢችሉ ያላቸውን ጉጉት ባወጉኝ ጊዜ፤ እማሆይ ‹‹የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው›› ነበር ያሉኝ፤ ከግማደ መስቀሉ መገኛ ከግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም ወጥተው ነው አስቀድመው በግብጽ ሀገር በቀን ውስጥ ለስምንት ሰአታት ቫዮሊንና ፒያኖ በማጥናት የተካኑበትን የዜማ ተሰጥኦ ለመቼውም ጊዜ እንዲሆነን አስቀርጸው የተዉልንን የህይወት ዘመናቸውን ድንቅ አጋጣሚ፡፡ ዘር ከገዳም ያወጣል ማለት ይኸው ነው፡፡ ጋሽ ሙላቱም ለሌላ ትምህርት ተልኮ በውጪ ሀገር ሙዚቃን ተምሮ መመለሱ እንዲሁ፡፡ የዜማ ዘር፡፡
ታዲያን ዛሬ ጋሽ ሙላቱ በአለም ዙሪያ ዝናው ገንኖ በተለያዩ የክብርና አድናቆት ሽልማቶች ሲንበሸበሽ ሀሴት እያደረግኩ፤ሆኖም ግን በብርቱ ጽናት አሁን የደረሰበት እርከን ላይ ሆኖ ሊያደርገው ካቀደው መሻቱ ምን ያህሉ  ሞልቶለታል? እላለሁ። ቢሆን በአይነቱ ልክ ስመ ጥሩው ሙዚቀኛ ያኒ  በጥንታዊው የግሪክ አክሮፖሊስ ግምብ ስር የአለም ሙዚቀኞችን ሰብስቦ እንዳቀረበው ሰፊ ኮንሰርትና Acropolis ከዚያም በላይ፤ እሱም ጋሽ ሙላቱ ተስፋ እንደሚያደርገው፤ እድሜ ዘመኑን የገበረላቸውንና በተለይም በኢትዮጵያ መንፈሳዊ ዜማ ላይ ተመርኩዞ የሰራውን ረቂቅ ሙዚቃውን በሮሀ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አምባ (ወይም በአክሱም ሀውልቶች ስር፣ ጢያ ትክል ድንጋይ፣ ዳሎል አዘቅት፣ ኮንሶ ሀውልት፣ጢስ አባይ፣ አዋሽ፣ ኦሞ፣ ግሸን፣ ፋሲለደስ፣ ጣና ቂርቆስ፣ ሀይቅ እስጢፋኖስ፣ ቢሾፍቱ፣ ሀዋሳ፣ ጋምቤላ፣ ማንኪራ፣ ደቡብ፣ ሀረር፣ ግምብ ስር፣ ...ብዙ...ወዘተ)፤ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ የሙዚቃ መሳሪያዎች፤ በሀገር ውስጥ ያሉትና በአለም ዙሪያ የተበተኑ ኢትዮጵያዊያንና አለማቀፍ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሁሉ ተሰባስበው፤ ስፍር ቁጥር በሌላቸው በሀገራችን የዜማ ቅኝቶች እየተራቀቁ ቢያስደምሙን! እማሆይ ጽጌ ፒያኖ ተጫውተው ሲያበቁ ብድግ፡ ሮጥ ብለው (ሙዚቃ ውስጥ እርጅና የለምና) ቫዮሊናቸውን አንስተው ሲያስነኩት ይታያችሁ፡፡
ከሁሉም ሙዚቀኞች ፊት በሚቀመጠው አትሮነስ ላይ የአለማቀፉ የሙዚቃ ኖታ ገፆች ከማህሌታይ ያሬድ የዜማ ምልክቶች ጋር መሳ ለመሳ የተፃፉ ይሆናሉ፡፡ (እዚህ አካባቢ በለው! ፋንታሲ! ማለት ይቻላል፡፡ ምን ይደረግ ቅኝቱ ነው!) ሙዚቀኞቹ በኢትዮጵያዊያን ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦችና በአፍሪቃዊያን፤ ከፍ! ሲል በአለም ህዝብ ሁሉ አልባሳት (የሰው ዘር መገኛ ምድር ነንና) በሕብር ተውበው የሚታዩበት፡፡ እናም አስቡት እስቲ፤ እዚያ መሀል ክቡር ዶክተር ጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ - የኢትዮ ጃዝ አባት፤ በኢትዮጵያ የሀገር ባህል ልብስ ተሽቀርቅሮ፤ በአጋፋሪነት (conductor) ጃኖውን አገልድሞ ቆሞ፤ ሙዚቃው ጸጥ ሲል ሁላችንም በምናውቀው ወርቃማ ድምጹ፤ ‹‹ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ የሰው ዘር መገኛነቷ ሁሉ፤ የአለም የዜማ ቅኝቶች ሁሉ መሰረትም ናት›› ብሎ ንግግር ሲያደርግ፤ ረ....ዥ..ም የጋለ ጭብጨባ ተሰምቶ ሲያበቃና ጸጥ እረጭ ብሎ እንደገና ሙዚቃው ድንገት ተግ ሲል ደግሞ፤ ጋሽ ሙላቱ በተመስጦ አይኖቹን ጨፍኖ፤ እጥፍ ዘርጋ፡ ወደ ቀኝ ወደ መሀል፣ ወደ ግራ ወደ ፊት ወደ ኋላ፡ ወዲህ ወዲያ፡ ቀስ ረጋ፣ ዝግ ፈጠን፣ ረገብ ፡ሞቅ ቀዝቀዝ፡ ዝቅ ከፍ...! ከፍ...! ከፍ.....! ....... በአለማቀፍ የሙዚቃ ቅኝት ጥበብ ክህሎቱ እጆቹን እያወናኘ ዜማ ሲመራ - በመቋሚያ፡፡
ጆሮ ደዌ ታምመህ የሚጠልዝ ምቱን ዲቃላ ቅኝቱን!
እንደ ፋና ወጊ ዜማ ፈውስ ማርከሻ ዳንኪራ ልክፍቱን
የትናንቱን ጸጋ የአበውን ጽሙና ለዛሬ ጠቁመህ
እንዲሰክን ነገ ‹‹መቋሚያ እንያዝ›› አልክ በማምሻህ አቀርቅረህ
ከኳኳታ ጥድፊያው ቆሞ ራሱን እንዲያይ ትውልድ አስደምመህ፡፡

Read 2531 times