Sunday, 13 November 2016 00:00

‹‹ፋልከን ኮች›› አዳዲስ አውቶቡሶች አገልግሎት ይጀምራሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    ፋልከን የትራንስፖርት ድርጅት፣ ከቻይናው ዞንግ ቶንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር ‹‹ፋልከን ኮች›› የሚል ስያሜ ያላቸው አገር አቋራጭ አውቶቡሶችን ለትራንስፖርት ሊያሰማራ ነው፡፡ ምቾት፣ ጥራትና ደህንነታቸው የተረጋገጡ የመጀመሪያዎቹ አውቶቡሶች አገር ውስጥ የገቡ ሲሆን ዛሬ ረፋድ ላይ ቦሌ ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ በሚገኘው “ራማዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል” ይመረቃሉ ተብሏል፡፡
22 አውቶቡሶች በምስራቁ የአገሪቱ ክፍሎች፡- ከአዲስ አበባ ድሬደዋ፣ ከአዲስ አበባ ሀረርና ከአዲስ አበባ ጅጅጋ ህዝብ በማመላለስ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የገለጹት የዝግጅቱ አስተባባሪ የኤልሻዳይ ማስታወቂያና ኮሚዩኒኬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሮቤል ቢኒያም፤ድርጅቱ በቀጣይ ተጨማሪ አውቶቡሶችን በማስመጣት በመላ አገሪቱ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አክለው ገልፀዋል፡፡
በአገር አቋራጭ የአውቶቡሶቹ የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የዞንግ ቶንግ ኩባንያ ተወካዮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ባለሀብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተው አውቶቡሶቹን እንደሚጎበኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፋልከን የትራንስፖርት ድርጅት፣ከአምስት አመት በፊት ተመስርቶ፣በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ስራ ላይ የተሰማራ ሲሆን አገር አቋራጭ አውቶብሶችን ሲያስመጣ የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነ አቶ ሮቤል ቢኒያም ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

Read 1147 times