Sunday, 13 November 2016 00:00

አንከር የወተት ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

    ተቀማጭነቱ ኒውዚላንድ የሆነው አንከር የኢትዮጵያ የወተት ምርት ድርጅት የአገር ውስጥ የወተት ኢንዱስትሪውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሳደግ ከኢትዮጵያ የወተት አቀራቢዎች ማኅበረር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
 የኢንዱስትሪ ሚ/ር ዴኤታ ዶ/ር መብራህቱ መለስ በተገኙበት ከትናንት ወዲያ በራማዳ አዲስ ሆቴል በተደረገው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት በወተት አሰባሰብና የትራንስፖርት ሂደት፣ በሁሉም የቅብብሎሽ ሰንሰለት የወተት ጥራት እንዲጠበቅ፤የወተት አመራረት መጠን ለመጨመርና የገበሬውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚሠሩ ተፈራራሚዎቹ ገልጸዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት አንከር ከገበሬዎች ወተት የሚሰበሰብበት ጣቢያ በጫንጮ የሚገነባ ሲሆን፣ ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የወተት መሳሪያዎች ማለትም የብረት (ስታንለስ ስቲል) ወተት ማጠራቀሚያ ባልዲዎች፣ ቀዝቃዛ የወተት ማከማቻና ሬፍሪጂሬተሮች ይኖሩታል ተብሏል፡፡
አቶ ዜኮ ቃሲም በኢትዮጵያ የአንከር ወተት አምራች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ድርጅታቸው በብዙ ትውልድ የኒውዚላንድ የወተት አምራች ገበሬሮች የተመሠተ መሆኑን ጠቅሰው ‹‹ይህ ዛሬ የተፈራረምነው ትብብር የውጪውንና የአገር ውስጡን ልምዳችንን በማቀናጀት የአገር ውስጡ የወተት ኢንዱስትሪ እንዲያድግ፣ የበለጠ ትርፋማና ዘለቄታ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ እንዲሁም በአቅርቦት ሰንሰለቱ የሚታዩ ችግሮችን በማስወገድ የአገር ውስጥ የወተት ምርት እንዲጨምር፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፤ የገበሬው ገቢ ከፍ እንዲልና በኢትዮጵያ ጥራቱ የተጠበቀ የወተት ኑትሪሽን እንዲኖር እንሰራለን›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የወተት አቅራቢዎች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን መኮንን ባደረጉት ንግግር የሁለቱ ድርጅቶች ትብብር ለገጠሩ ወተት አምራቾች ኅብረተሰብ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ጠቅሰው ‹‹ከኒውዚላንዱ በኢትዮጵያ ወተት አምራች ድርጅት ጋር በመሆን ለገጠሩ ወተት አምራቾች፣ ወተት እንዴት እንደሚመረት፣ እንዴት እንደሚሰበሰብና የአቅርቦት ሰንሰለቱ እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው እናስተምራለን፡፡ ምርት የበለጠ እንዲጨምር፣ የተሻለ ጥራት ያለው ወተት እንዲመረትና የወተት ብክነት እንዲቀንስ እናደርጋለን›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች የክብር እንግዳው ዶ/ር መብራህቱና ሁለቱ ተፈራራሚ ድርጅቶች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Read 1887 times