Sunday, 13 November 2016 00:00

አዋሽ ባንክ ዛሬ “ባልቻ አባነፍሶ” ህንፃን ያስመርቃል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ያስገነባውን ባለ 10 ፎቅ “ባልቻ አባነፍሶ” ዘመናዊ ህንፃ ዛሬ ያስመርቃል።
ግንባታው 257 ሚ. ብር መፍጀቱን የጠቀሱት የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የብራንዲንግ፣ ፕሮሞሽንና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ መቻል በዳዳ፤ “ባልቻ አባነፍሶ” ህንፃ ከአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ፌርማታ ጋር የተገናኘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከአዋሽ ኢንሹራንስ እህት ኩባንያ ጋር በትብብር የተሰራው ሁለገብ ህንፃ፤ የባንኩና የኢንሹራንሱን ልደታ ቅርንጫፎች የያዘ ሲሆን የተቀረው በአብዛኛው ሞል (የገበያ አዳራሽ) መሆኑን የገለፁት አቶ መቻል፤ ባቡር ተሳፋሪው ፌርማታው ላይ ሲወርድ በቀጥታ የሚያገኘው የህንፃውን 4ኛ ፎቅ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ተሳፋሪው በህንፃው ውስጥ የተለያዩ ዘመናዊ ሱቆች ስላሉ እየተዘዋወረ ይጎበኛል፡፡ ከዚያም ከአዋሽ ኤቲኤም ወይም አዋሽ ልደታ ቅርንጫፍ ገንዘብ አውጥቶ ልቡ የፈቀደውን ነገር ይገዛል፤ በካፌና ሬስቶራንቶቹ ይዝናናል” በማለት አብራርተዋል፡፡
በ486 ባለአክሲዮኖችና በ24.2 ሚ. ብር ካፒታል ከ22 ዓመት በፊት የተመሰረተው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ በአሁኑ ወቅት የባለ አክሲዮኖች ቁጥር ከ3,600 በላይ፣ የተከፈለ ካፒታል ከ2.3 ቢ. ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፤ በቅርቡም ወደ 3 ቢ. ብር ለማድረስ ታቅዷል፡፡
ከምስራቅ አፍሪካ 10 ታላላቅ የግል ባንኮች ተርታ ለመሰለፍ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ያለው ባንኩ፤በአገር ውስጥ ተደራሽነቱን በማስፋት ደንበኞቹ ሁሉ በፈለጉበት እንዲያገኙት የቅርንጫፎቹን ቁጥር 250 ያደረሰ ሲሆን ይህም ከግል ባንኮች ቀዳሚ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ ባንኩ፣ ንብረት በማፍራትም ረገድ ጠንክሮ እየሰራ ነው፡፡
በአዲስ አበባ በተለምዶ “ሰንጋ ተራ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ካለው ባለ 18 እና 16 የዋና መ/ቤት ህንፃ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ባለ 8 ፎቅ ህንፃ አስመርቋል፡፡ በአዳማ ባለ 8 ፎቅ፣ በአጋሮና ግምቢ ባለ 4 ፎቅ፣ በሻሸመኔ ባለ 3 ፎቅ፣ በነቀምቴ ባለ 3 እና ባለ 1 ፎቅ ህንጻዎች ሲኖሩት፣ ወደፊት በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ፣ ከዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ባለ 12 ፎቅ ህንፃ ለመገንባት ዕቅድ አለው

Read 1758 times