Saturday, 12 November 2016 13:49

ከትራምፕ ድል ማግስት...

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 - በቅስቀሳቸው ወቅት አደርገዋለሁ ያሉትን ሁሉ ያደርጉት ይሆን?...
         - ከነጩ ቤት ወደ በፊት ፍርድ ቤት ያመራሉ
         - አይሲስ እና አልቃይዳ በትራምፕ ድል ፈንድቀዋል
      በስተመጨረሻም...
አወዛጋቢው ሰውዬ ሰተት ብለው ወደ ነጩ ቤት መግባታቸውን አረጋገጡ፡፡
ዓለም የሰማችውን ለማመን ተቸገረች። ባልተጠበቀ መንገድ የተቋጨው የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ የአለማችን መነጋገሪያ ትኩስ ትንግርት ሆነ፡፡
የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ የተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ካወጧቸው ዘገባዎች የተወሰኑትን ጨለፍ አድርገን እንመልከት።
እንኳን ደስ አለዎት!...
የትራምፕ አሸናፊነት ከተሰማ በኋላ ፣ ፈጥነው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ከላኩት የዓለማችን መሪዎች አንዱ፣ “የትራምፕ ደጋፊ ነው” እየተባሉ በዲሞክራቶች ሲብጠለጠሉ የከረሙት የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው፡፡ ፑቲን ከክሪምሊን ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተኳርፈው የነበሩት ሩስያና አሜሪካ የሚታረቁበት ጊዜ እንደመጣ ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡ ቻይናም በበኩሏ፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው በክፉ ሲያነሱ ሲጥሏት የከረሙትን ትራምፕን “ስለተመረጡ ደስ ብሎኛል፤ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ለማሳደግ ከአዲሱ የአሜሪካ መንግስት ጋር ለመስራት ፍቃደኛ ነኝ” ብላለች፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል፡፡
የእንግሊዟ ቴሬሳ ሜይ፣ የአፍጋኒስታኑ አሽረፍ ጋና፣ የግብጹ አብዱል ፈታህ አል ሲሲ፣ የህንዱ ናሬንድራ ሞዲ፣ የኬንያው ኡሁሩ ኬንያታ፣ የደቡብ አፍሪካው ጃኮብ ዙማ እና የፍልስጤሙ መሃሙድ አባስ ለትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በርካታ የዓለም አገራት መሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለስልጣናት በበኩላቸው ለትራምፕ በጻፉት ደብዳቤ፣ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን ገልጸው፣ “በቻሉት ፍጥነት ሁሉ ዛሬ ነገ ሳይሉ ወደ አውሮፓ ይምጡና አስቸኳይ ስብሰባ እናድርግ” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ያሉትን ሁሉ ያደርጉታል?...
አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው አሸንፈው መንበረ ስልጣኑን መረከባቸው፣ በአሜሪካና በተቀረው አለም ላይ ምን አይነት ለውጥ ያመጣ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ሰውዬው ስልጣን ብይዝ አደርጋቸዋለሁ በሚል በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የተናገሯቸውን አስገራሚና አስደንጋጭ ጉዳዮች፣ በእርግጥ ስልጣን ላይ ሲወጡ ይተገብሯቸው ይሆን? ከተገበሯቸውስ ምን አይነት ለውጥ ይመጣ ይሆን? ብለው በጉጉት የሚጠይቁ በርክተዋል፡፡
ብዙዎች ይህን ጥያቄ ለመመለስ የየራሳቸውን አስተያየት እየሰጡ ሲሆን ቢቢሲም የትራምፕ ፕሬዝደንት መሆን አገሪቱ ከተቀረው አለም ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ይፈጥራቸዋል ያላቸውን ቁልፍ ለውጦች ዘርዝሯል፡፡
ትራምፕ በያዙት የንግድ ፖሊሲ የሚገፉበት ከሆነ፣ አሜሪካ ከተቀረው አለም ጋር ባላት የንግድ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱ አይቀሬ ነው ይላል ቢቢሲ፡፡ ለስራ አጥነት ምክንያት ሆነዋል ያሏቸውንና አገሪቱ ከሌሎች አገራት ጋር የገባቻቸውን ነባር የነጻ የንግድ ስምምነቶች ሊያፈርሱ፤ ከአለም የንግድ ድርጅት አባልነቷ እንድትወጣ አደርጋለሁ ያሉትን እቅዳቸውንም ተግባራዊ ካደረጉ እጅግ ትልቅ ለውጥ ይፈጠራል ይላል፡፡
አሜሪካ አምና ከ195 የአለማችን አገራት ጋር የተፈራረመቺውን የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንደሚያፈርሱና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሙቀት መጠን መጨመር ፕሮግራሞች የምትሰጠውን ገንዘብ እንደሚያቋርጡ መናገራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ እንዳሉት የሚያደርጉ ከሆነ ሌላ ለውጥ ሊታይ ይችላል ብሏል።
አገሪቱን ከሜክሲኮ የሚያካልል የግንብ አጥር የመገንባት፣ ከኔቶ ጋር ያለመቀጠልና ከሩስያ ጋር የነበረውን የተካረረ ግንኙነት የማለዘብ እቅዶቻቸውም፣ የመተግበር ዕጣቸው እውን ከሆነ ተጽዕኗቸው እጅግ የጎላ ይሆናል ይላል፤ ቢቢሲ። ኒውዮርክ ፖስት ግን፣ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገቧቸውን ጉዳዮች በእርግጥም ስልጣን ላይ ሲወጡ ተግባራዊ ስለማድረጋቸው ይጠራጠራል፡፡ ዘገባው እንደሚለው፤ ትራምፕ በተለይ ዋና ዋናዎቹን ቃል የገቧቸው ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ፣ የኮንግረሱን ድጋፍና ይሁንታ ማግኘት ግድ ይላቸዋል፡፡ እርግጥ ሪፐብሊካኖች በሁለቱም ምክር ቤቶች አብላጫ ድምጽ ያላቸው መሆኑ፣ ጉዳዩን ያን ያህል ፈታኝ ላያደርገው ይችላል።
ይሄም ሆኖ ግን፣ ትራምፕ የተወሰኑ ለውጦችን የማድረግ ስልጣንና አቅም ባያጡም፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል የገቡትን የወፈፌ ሃሳብ የሚመስል ዕቅድ ሁሉ፣ መንበረ ስልጣኑን ስለተቆናጠጡና የእሳቸው ሃሳብ ስለሆነ ብቻ ያለ ከልካይ ተግባራዊ ያደርጉታል ብላችሁ አትስጉ ያለው ደግሞ ዋሽንግተን ፖስት ነው፡፡
እዚያም ምርጫን ተከትሎ አመጽ...
አሁን...
የምርጫ ውጤት ይፋ መደረግን ተከትሎ የሚመጣ አመጽና ተቃውሞ የእነ አፍሪካ መገለጫ ብቻ አይደለም! ልዕለ ሃያል አሜሪካም፣ የምርጫ ውጤትን በጸጋ ከመቀበል ወደ አመጽና ተቃውሞ ወርዳለች፡፡ ትራምፕ ማሸነፋቸው ከታወቀ በኋላ በካሊፎርኒያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ በምርጫው ውጤት ያልተደሰቱት ከ500 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ረቡዕ ማለዳ አደባባይ በመውጣት ጸረ- ትራምፕ መፈክሮችን ማሰማታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ በበርክሌይ፣ ኤርቪንና ሳንጆሴ አካባቢዎችም ተመሳሳይ አነስ ያሉ ተቃውሞዎች መደረጋቸውን ገልጧል፡፡ የትራምፕን አሸናፊነት አምነው ለመቀበል ያልፈለጉ በሺህዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በርካታ አሜሪካውያን ማንሃታን ውስጥ ወደሚገኘው ግዙፉ የትራምፕ ህንጻ በማምራት ሰውዬው በስደተኞችና በሙስሊሞች ላይ የያዙትን አቋም በመንቀፍ፣ ለመሪነት አይበቁም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ በኦክላንድም 6 ሺህ ያህል የትራምፕ ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጥተው የትራምፕን ፎቶግራፍ አቃጥለዋል፣  የመደብሮችን መስኮቶች ሰባብረዋል፡፡ ወደ ትራምፕ ኢንተርናሽናል ሆቴል ሲያመሩ የነበሩ 1 ሺህ 800 ተቃዋሚዎችም በፖሊስ እገዳ ተመልሰዋል፡፡
ትራምፕ ፕሬዝዳንታችን አይደለም የሚል መፈክር ያነገበው ተቃውሞው፤ ወደ ሎሳንጀለስ፣ ፖርትላንድ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ፊላዴልፊያ፣ ቦስተን፣ ሲያትል፣ ሳን ፍራንሲስኮና ሌሎች የአሜሪካ አካባቢዎች መዛመቱን ቢቢሲ የዘገበ ሲሆን፣ ዘረኝነትን የሚያወግዙ 200 ያህል እንግሊዛውያንም ለንደን በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ደጃፍ ባደረጉት ተቃውሞ ትራምፕን አውግዘዋል ብሏል - ዘ ኢንዲፔደንት፡፡
አይሲስና አልቃይዳ በደስታ ፈንጥዘዋል
“ላሸንፍ እንጂ ሙስሊሞች የአገሬን ምድር አይረግጡም!...” የሚለው የትራምፕ ንግግር ብዙዎችን አስደንግጦ ነበር፡፡ ይህ ንግግር ብዙዎችን ቢያስደነግጥና ቢያስከፋም፣ አይሲስን ለመሳሰሉ ጽንፈኛ ቡድኖች የተለየ ትርጉም ነበረው። የሰውዬው ንግግር በሙስሊሞች ላይ ቁጣን የሚቀሰቅስ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለእነዚህ ቡድኖች አዳዲስ አባላትን መመልመያ ፕሮፓንዳ ሆኖላቸው ነበር። የአይሲስ እና የአልቃይዳ አጋሮች የሆኑ አክራሪ ቡድኖች ባለፈው ረቡዕ የዶናልድ ትራምፕን ማሸነፍ ሲሰሙ፣ እንደ አንድ የሪፐብሊካን ደጋፊ በደስታ ነበር የፈነጠዙት፡፡
ዋሽንግተን ፖስት እንደ ዘገበው፤ ከአይሲስ ጋር ግንኙነት ያለው አል ሚንባር ጂሃዲ የተባለ ሚዲያ፣ “በፈጣሪ ድጋፍ አሜሪካን በገዛ እጃቸው የሚያጠፏት ሰው በፕሬዚዳንትነት ተመረጡ!... የእሳቸው መመረጥ ሙስሊሙ በአሜሪካ ላይ ጥላቻ እንዲኖረው ያደርጋል” ብሏል፡፡ የአይሲስ ጂሃዲስት ታጣቂዎች፣ “አህያው ትራምፕ መመረጡ የአሜሪካ ውድቀት ምልክት ነውና በማሸነፉ ደስተኛ ነን” ሲሉ መናገራቸውንም ዘ ዴይሊ ሚረር ዘግቧል፡፡
ዘ ሰን በበኩሉ፤ አሸባሪው ቡድን አል ቃይዳም የትራምፕ ማሸነፍ ለአሜሪካ ጥፋት በር የሚከፍት በመሆኑ እንዳስደሰተው መግለጹን በመጠቆም፣ ቡድኑ በምርጫው ሰሞን በአሜሪካ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም አቅዶ እንደነበር ደርሼበታለሁ ሲል ኤፍቢአይ አስታውቆ እንደነበርም ዘግቧል፡፡
ሄላሪን በሚሼል?
በርካታ አሜሪካውያን ለሄላሪ ክሊንተን ድምጻቸውን በመስጠት በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት ወደ ስልጣን ለማምጣት ቋምጠው ነበር ይላል፤ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ፡፡ ያልተጠበቀው የምርጫ ውጤት ግን፣ ለሄላሪ የታጨውን መንበር ለትራምፕ አሳልፎ በመስጠት ህልማቸውን አጨናገፈው፡፡
በዚህ ዱብ እዳ የተናደዱት ሴት መሪ ናፋቂ አሜሪካውያን፣ ዘንድሮ በሄላሪ ያጡትን ስኬት ከአራት አመታት በኋላ በሚሼል ኦባማ ከእጃቸው ለማስገባት አቅደዋል ተብሏል፡፡አንደበተ ርዕቱዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ፣ ከአራት አመታት በኋላ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዲሞክራትን ወክለው ቢወዳደሩ ለድል ሊበቁ እንደሚችሉ አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሜሪካውያን በርካታ መሆናቸውን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
እነዚህ በሄላሪ በለስ ያልቀናቸው ሴት መሪ ናፋቂ አሜሪካውያን፣ ዛሬ ነገ ሳይሉ በትዊተር ድረገጽ ሚሼል2020 የሚል የድጋፍ ዘመቻ መጀመራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ዘመቻውን የሚቀላቀሉ ዜጎች ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም አስረድቷል፡፡
የዝነኞች ኩርፊያ
የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሂደት፣ ዝነኞች ከወትሮው በተለየ ፖለቲካዊ አቋማቸውን በአደባባይ ያንጸባረቁበት ነበር፡፡ ታላላቅ ድምጻውያን፣ የፊልም ተዋንያን፣ ደራሲያንና የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ከዋክብት፣ የሚደግፉትን ዕጩ ተወዳዳሪ ማንነት በይፋ ከመናገር አልፈው፣ አድናቂዎቻቸውም እነሱ ለሚደግፉት ዕጩ ድምጻቸውንእንዲሰጡ በይፋ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ተሸናፊዋ ሄላሪም፣ ወደ ዋይት ሃውስ የሚገቡበትን ጎዳና ይጠርጉልኛል በሚል ቢዮንሴና ጄይዚን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ድምጻውያንን ከጎናቸው አሰልፈው የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ሲያጧጡፉት ከርመው ነበር - አልሆነም እንጂ፡፡
የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ምድረ ዝነኛ በድንጋጤ ክው ማለቱን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
“አሜሪካ ሆይ... ተግተሽ ጸልይ!...” ብላለች፤ የሰማችው ነገር ከአቅሟ በላይ የሆነባት ሌዲ ጋጋ፡፡
ከቀናት በፊት ሄላሪን አቅፋ የምርጫ ቅስቀሳ መድረክ ላይ ስትፈካ የታየቺው ድምጻዊት ኬቲ ፔሪ ግን፣ ከጸሎት ይልቅ አብዮት ያዋጣል ባይ ናት። “አብዮት ሊፈነዳ ነው!...” ብላለች፤ ድምጻዊቷ የሄላሪን መሸነፍ ከሰማች በኋላ በትዊተር ገጽ ላይ ባሰፈረቺው ጽሁፍ፡፡“ምንድን ነው እየሆነ ያለው?...” በማለት ግራ መጋባቱን የገለጸው ታዋቂው ራፐር ስኑፕ ዶግ ሲሆን፣ ክሪስ ኢቫንስ በበኩሉ፤ “አሳፋሪ  ነው፤ በጥላቻ የተሞላ ሰው ታላቂቷን አገር ይመራ ዘንድ ፈቅደንለታል!...” በማለት በምርጫው ውጤት መበሳጨቱን ጠቁሟል፡፡
ከትራምፕ ያልተናነሰ የፈነደቀው እንግሊዛዊ
የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ እጅግ ከፍተኛውን ደስታ ያጎናጸፈው ለአሸናፊው ትራምፕ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ አንድ እንግሊዛዊ ግን ከትራምፕ ያልተናነሰ በደስታ ፈንድቋል፡፡ ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው፣ ነዋሪነቱ በለንደን የሆነውና ስሙ ያልተጠቀሰው እንግሊዛዊ፣ የምርጫውን ውጤት ከትራምፕ ባልተናነሰ እጅግ በከፍተኛ ጉጉትና ጭንቀት ሲጠባበቅ ነበር፡፡ ሰውዬው የምርጫ ውጤቱን በጉጉትና በጭንቀት የጠበቀው፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በእሱ ህይወት ላይ ያን ያህል ተፅዕኖ የሚፈጥር ስለሆነ አልነበረም፡፡
በምርጫው የሚያሸንፈው ሰው ካሸነፈ በኋላ የሚፈጥረው ነገር ሳይሆን፣ ማሸነፉ በራሱ ነበር እንግሊዛዊውን ያጓጓውም ያስጨነቀውም፡፡ እየጓጓና እየተጨነቀ የምርጫውን ውጤት ሲጠብቅ አመሸ፡፡ በስተመጨረሻም የትራምፕን ድል ሰማና፣ በደስታ ፈነጠዘ፡፡
ትራምፕ ያሸንፋል ብሎ ባስያዘው የቁማር ጨዋታ፣ 200 ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ በላ!
ከነጩ ቤት በፊት፣ ፍርድ ቤት
ሮይተርስ ደግሞ፣ ዘግየት ብሎ አጉል ዘገባ አመጣ...
የታላቂቷ አሜሪካ ቀጣዩ ታላቅ መሪ ዶናልድ ትራምፕ፣ ወደ ነጩ ቤት ከማምራታቸው በፊት ወደ ፍርድ ቤት ማምራታቸው አይቀርም ይላል፤ ሮይተርስ። ዘገባው እንዳለው፣ ዶናልድ ትራምፕ አገልግሎቱን ባቆመው የቀድሞው ትራምፕ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተመሰረተባቸውን ክስ ለመከታተል፣ ካሊፎርኒያ ውስጥ ወደሚገኝ የፌዴራል ፍርድ ቤት በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ያመራሉ፡፡
ምንም እንኳን የአገሪቱ ህግ ፕሬዚዳንቶች ከስራቸው ጋር በተያያዘ ክስ እንዳይመሰረትባቸው ጥበቃ የሚያደርግላቸው ቢሆንም፣ ከስልጣን በፊት በሰሯቸው ጥፋቶች ሊከሰሱ እንደሚችሉ ይደነግጋል ብሏል ዘገባው፡፡
ትራምፕ ከተለያዩ የንግድ ኩባንያዎቻቸው ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት የተመሰረቱባቸውና ያልተዘጉ ሌሎች የፍርድ ቤት ክሶች እንዳሉባቸው የዘገበው ዩኤስ ቱዴይ በበኩሉ፣ ዶናልድ ትራምፕና የሚያስተዳድሯቸው ኩባንያዎች ባለፉት 30 አመታት ከ4ሺህ በላይ ክሶች እንደተመሰረቱባቸው አስታውሷል፡፡

Read 1940 times