Sunday, 20 November 2016 00:00

የኢዴፓ “ጠንካራ ተቃዋሚ” የመፍጠር ውጥን

Written by 
Rate this item
(6 votes)

• ፓርቲው ለተቃዋሚዎች ሁሉ ጥሪ አድርጓል፤ ውጥኑ ይሳካለት ይሆን?
• አንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ለመፍጠር ህልውናውን ለማፍረስ ዝግጁ ነው
• ዓላማው የህዝቡን ትግል መምራት፣ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ነው
• ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መነጋገር አለበት

ኢዴፓ ከወትሮው ለየት ያለ አቅምና ቁርጠኝነትን የሚፈታተን፣ ድፍረትም የሚጠይቅ አጀንዳ ወጥኖ ተግባራዊ ለማድረግ ተነሳሽነቱን ወስዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስታውቆ ነበር፡፡ አጀንዳው አገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ህጋዊ ፓርቲዎች ህብረት ወይም ቅንጅት በመፍጠር አንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ለመመስረት ያለመ ነው፡፡ ለዚህም የተቃዋሚዎችን፣ የምሁራንና፣ የህዝቡን ሰፊ ድጋፍና እገዛ ጠይቋል፡፡
ኢዴፓ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራትና ለመጠናከር የራሱን ህልውና ለማፍረስ ጭምር ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ አጀንዳውን ለመተግበር በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ የተመረጡት የፓርቲው መስራች አባል አቶ ልደቱ አያሌው፣ ጠንካራ ፓርቲ የመፍጠር ዓላማው የህዝቡን ትግል ለመምራት ነው ይላሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ኢዴፓ ይዞት በመጣው አዲስ አጀንዳ ዙሪያ ከአቶ ልደቱ ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

   ኢዴፓ በአሁኑ ወቅት አንድ ጠንካራ ፓርቲ ለመፍጠር የተነሳበት ዋና ምክንያት ምንድን ነው?
እንግዲህ እንደሚታወቀው ላለፉት በርካታ አመታት ተቃዋሚው ፓርቲ በሚፈለገው መጠን ጠንካራ አይደለም፡፡ የኛን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ከኢህአዴግ ግዝፈት ጋር ሲነፃፀር፣ ከህዝቡ የለውጥ ሂደት ጋር ሲነፃፀር በጣም ደካማ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ይሄን ድክመት በአግባቡ ገምግመን፣ ራሳችንን የማናስተካክል ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተቃዋሚው ጎራ ሚና ትርጉም የለሽ እየሆነ ነው የሚሄደው፡፡ የህዝቡን ትግልም አስተባብሮ መምራት አይችልም፡፡ በዚህም ኢህአዴግ ለቀጣይ 20 እና 25 ዓመታት የሚገዛበትን ሌላ እድል ነው የምንሰጠው፤ ስለዚህ ራሳችንን እናጠናክር ስንል ነው የነበረው፡፡ ነገር ግን ይሄን ጉዳይ በቅንነት የሚቀበል አልነበረም፡፡ እንደውም የተቃዋሚውን ድክመት ስናወራ፣ ብዙ ሰው ለኢህአዴግ የማሰብ አድርጎ ይመለከተው ነበር፡፡ ለምን ተቃዋሚውን ትተቻላችሁ፣ መተቸት ያለበት ገዥው ፓርቲ ነው የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፡፡ በኛ እምነት ግን ተቃዋሚውም ካልተገመገመ፣ ካልተተቸ ሊጠናከር አይችልም፤ ደካማ ሆኖ ነው የሚቀረው --- እያልን ይህ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ሊመጣ እንደሚችል ቀድመን ነው መናገር የጀመርነው፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ካየን፣ ተቃዋሚ ፓርቲ ረብ የለሽ ነው የሆነው፤ ትርጉም የለሽ ነው የሆነው፡፡ ህዝቡ ለውጥ ይፈልጋል፤ በየአካባቢው ትግል ያደርጋል፤ ነገር ግን በተደራጀ ኃይል እየተመራ አይደለም። በአካባቢ የጎበዝ አለቃ፣ በፌስቡክ ወይም ደግሞ ውጭ ባሉ የፖለቲካ ኃይሎች ነው የሚመራው፡፡ ህዝቡ ውስጥ አብረው ያሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው ድርጅቶች ትግሉን እየመሩት አይደለም፡፡ አይደለም መምራት የወረቀት መግለጫ ከማውጣት ውጪ በህዝቡ ትግል ላይ ምንም ሚና የላቸውም፡፡ ይሄ በዚህ ከቀጠለ ወዴት ነው የምንሄደው? በአንድ በኩል ህዝቡ ለውጥ ይፈልጋል፤ በሌላ በኩል ያንን ፍላጎት በስርአት መርቶ፣ ህዝቡ ወደሚፈልገው የፖለቲካ ለውጥ የሚያደርስ ፓርቲ የለም፡፡ ኢህአዴግ እንኳ በህዝብ ትግል ቢወድቅ ስልጣን ለመረከብ ዝግጁ የሆነ የለም፡፡ ይሄ ከፍተኛ ክፍተት ነው፡፡ አንደኛ፤ ህብረተሰቡ በትግሉ ውስጥ እየገባ ህይወቱን እየሰዋ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እየደረሰበት ነው። እንዲህ አይነት ጉዳይ እንዳይደርስበት የተደራጀ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ባልተደራጀ ሁኔታ ህዝቡ የሚያደርገው ትግል ለጥቃት ነው የሚያጋልጠው፡፡ ውጤታማ አይሆንም፡፡ ኢህአዴግ ቢወድቅ እንኳን በስክነት ተወያይቶ አቅጣጫ የሚያስይዝ የተደራጀ ኃይል የለም፡፡ ይሄ አደጋ ነው፡፡
በአንድ በኩል ገዥው ፓርቲ ስልጣኑን ለማጋራትም ሆነ ስልጣኑን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለመልቀቅ ፍቃደኛ ባልሆነበት ሁኔታ፣ በሌላ በኩል ህዝቡ ከፍተኛ ስሜት ውስጥ  ገብቶ ባልተደራጀ መልኩ እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ወቅት የዚህች ሀገር አጠቃላይ ህልውና አደጋ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የተቃዋሚዎች የወቅቱ ዋነኛ አጀንዳ መሆን ያለበት፣ ራሳቸውን ጠንካራ ፓርቲ አድርገው አውጥተው፣ በህዝብ ትግል ላይ ተጨባጭ የሆነ ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ እኛ ይሄን በፊትም ስንለው የነበረው ነው፤ አሁን ደግሞ ወቅቱ የበለጠ አጀንዳ አድርገን እንድንይዘው አስገድዶናል፡፡ ይሄን ጉዳይ ግን ብቻችንን የምንይዘው አይሆንም፤ ሁሉም ተቃዋሚ መምጣት አለበት፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ ዝም ብሎ ማየት የለበትም፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ እየገባ ካላጠናከራቸው የትም ሊደርሱ አይችሉም። ስለዚህ ይሄ አጀንዳ ያስፈለገው ምሁራኑ፣ ባለሀብቱ፣ ወጣቱ፣ ህብረተሰቡ በአጠቃላይ በፓርቲዎች ዙሪያ ተሰባስቦ እንዲታገል ነው፡፡ ፓርቲዎች ደግሞ ከእርስ በእርስ መናቆርና ግጭት ወጥተን፣ ህብረተሰቡን አስተባብሮ የሚመራ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ለመፍጠር መታገል አለብን፡፡ ይሄ ጠንካራ ፓርቲ በመዋሃድ፣ ህብረት በመፍጠር ሊሆን ይችላል የሚመሰረተው፡፡ ይሄን ለማድረግ አንድ ተነሳሽ ፓርቲ ያስፈልጋል፤ የኛም ጥረት ይሄው ነው፡፡ በኛ በኩል ጠቅላላ ጉባኤያችንን በ6 ወር ውስጥ እናደርጋለን፡፡ ፓርቲያችንን ወትሮ ከነበረው የበለጠ እናጠነክረዋለን፤ ከዚያም መዋሃድ የሚፈልጉ ፓርቲዎች ካሉ፣ በኛ በኩል ስያሜያችንን አፍርሰን ለመዋሃድ ዝግጁ ነን፡፡ ግን ይሄን አስተሳሰብ ሁሉም ፓርቲ ይዞ መንቀሳቀስ አለበት፡፡
ከዚህ በፊት ቅንጅት፣ ህብረት፣ ግንባር የሚሉ አደረጃጀቶች ለተቃዋሚው ጎራ እንዳልበጁት   በመግለጽ ከፍተኛ ትችት ሰንዝረው ነበር። አሁን አቋምዎትን ለወጡ? ወይስ ሁለቱን የሚያስታርቁበት መንገድ አለ ?
አሁንም ቢሆን እያልን ያለነው አስፈላጊው ሆኖ ከተገኘ፣ ለፓርቲዎች መጠናከር የሚጠቅም ከሆነ ህልውናችንን አሳልፈን ለመስጠት ዝግጁ ነን፡፡ ይሄንን በተግባርም ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ኢዴፓ የአራት ፓርቲዎች ውህድ ነው፡፡ በውህደት ስሙንም የቀየረባቸው ጊዜዎች ነበሩ፡፡ ይሄን ሁሉ ያደረግነው አብሮ ለመስራት ካለን ፍላጎት ነው። ግን አንዳንድ ጊዜ የተቃዋሚ ጎራ እንዲጠናከር በቅንነት ስንሰራ፣ አጋጣሚውን ለተለየ የቡድን ስሜት ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ በፓርቲ ደረጃ ተንቀሳቅሰው፣ ህዝቡ ውስጥ ገብተው ተጨባጭ ስራ መስራት ሲያቅታቸው፣ ተቃዋሚው ፓርቲ ካልተባበረ የትም መድረስ አይችልም በሚል ምንም ጥቅም በሌለው ስብስብ ውስጥ ሁሉንም እያስገቡ፣ ተቃዋሚ የሚያዳክሙበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁንም በኛ እምነት እስካሁን ድረስ የነበረው የተቃዋሚ ትግል መጠናከር ያልቻለው፣ እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ተቃዋሚዎች ስላሉ ነው፤ ህብረት መፍጠርን ለመጠናከር ሳይሆን የግል የፖለቲካ አላማን ለማሳካት የሚጠቀሙበት ወገኖች አሉ፡፡ ይሄ ጉዳይ ለወደፊትም እንቅፋት ሆኖ ሊቀጥል ይችላል፡፡
ህብረት የምንፈጥረው፣ የምንዋሃደውና ህልውናችንን አሳልፈን እንሰጣለን የምንለው ለማይረባ ነገር አይደለም፡፡ ለቡድን ጥቅም ወይም  ራሳቸውን ወደ ስልጣን ለማውጣት ለሚፈልጉ ግለሰቦች ጥቅም አይደለም፡፡ በዚህ መልክ ለሚመጣ ጥያቄ ፍላጎቱ የለንም፡፡ ያለፈውን ስህተትና ጥፋት ለመድገም ሳይሆን የመጠናከር አስፈላጊነትን ከልብ በማመን ለሚመጣ ግን ዝግጁ ነን፡፡ ስለዚህ ይሄ ተለይቶ መታየት አለበት፡፡
ጥሪ የተላለፈው ለማን ነው? በሀገር ውስጥ ላሉት ነው? በውጭ የሚንቀሳቀሱትንስ  ይጨምራል?
በዋናነት የሚያካትተው በህጋዊ መንገድ በሰላማዊ አግባብ፣ በሀገር ውስጥ ተቀምጠው ትግል የሚያካሂዱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ጠንካራ ናቸው፣ ደካማ ናቸው የሚል ፍረጃ ውስጥ አንገባም፡፡ በኛ እምነት፣ እኛንም ጨምሮ ሁላችንም ደካሞች ነን፡፡ ያም  ነው ወደዚህ አይነቱ አጀንዳ እንድንሄድ የገፋፋን፡፡ ሀገር ውስጥ ያለ ማንኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ በዚህ ሂደት ተሳታፊ መሆን አለበት፡፡ ለሁሉም ነው ጥሪያችን። በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲ መነጋገር አለበት፡፡ በዚህ ሂደት የሚገለል አካል አይኖርም፡፡ አንዱ ትልቅ ችግር የነበረው፣ “እኔ ከእነ እገሌ ጋር አልሰበሰብም” የሚለው ነው፡፡ ይሄ ተገቢ ያልሆነ ፍረጃ ነው እንቅፋት እየሆነ ያለው፡፡ ውጭ ሀገር ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን በተመለከተ፣ አሁን ባለው ሁኔታ፣ በህገ ወጥ መንገድ በጠመንጃ መንግስትን ለመለወጥ ጥረት ከሚያደርጉ ጋር ልንተባበር አንችልም። ተባብረንም እዚህ ሀገር ውስጥ ህልውና ሊኖረን አይችልም፡፡ በአጠቃላይ የሀገሪቱን ችግር ከመፍታት አንፃር ግን ውጭ ያሉም ኃይሎች ሀገር ውስጥ ገብተው በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መመቻቸት አለብን ብለን እናምናለን። በራሳቸው ፍላጎት ብቻ አይደለም ወደ ውጭ የሄዱት፤ ሀገር ውስጥ ባለው ሊያሰራ በማይችል ሁኔታ ተገፍተውም ነው፡፡ ተገፍተው ስለሄዱ የጠመንጃ ትግል ማድረግ አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ አንደኛ እዚሁ ሀገር ውስጥ ተቀምጠው መታገል አለባቸው ብለን እናምናለን። ይህ ሁኔታ ቢመቻችላቸው መልካም ነው የሚል እምነት አለን። ግን እኛ አሁን የምንተባበረው ሀገር ውስጥ ካሉት ጋር ብቻ ነው፡፡ በውጭ ካሉት ጋር እንስራ ብንልም፣ አሁን ባለው ሁኔታ አደጋ ውስጥ ነው የምንገባው። ሀገር ውስጥ ከገቡና ህጋዊ ከሆኑ፣ ከነሱም ጋር የማንሰራበት ምክንያት የለም፡፡
ለመፍጠር ያሰባችሁት አንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ዋነኛ አላማው ምንድን ነው?
ዋናው ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ተፈጥሮ፣ የህዝቡን ትግል መምራት አለበት። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ህዝቡን የስልጣን ባለቤት በሚያደርግ መልኩ መስተካከል አለበት፡፡ እንዲስተካከል ግን ትግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ባለፉት 25 ዓመታት እንዳየነው፣በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ለህዝብ ማስረከብ የሚፈልግ መንግስት አይደለም። ይሄ መንግስት ይሄን ጥያቄ መቀበል የሚችለው፣ በጥያቄ ብቻ ሳይሆን በትግል ነው፡፡ ስለዚህ ታግለን ህብረተሰቡንም አታግለን፣ ህዝቡ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ አለብን፤ዞሮ ዞሮ አላማው የስልጣን ጥያቄ ነው። ግን ህዝቡን ነው የስልጣን ባለቤት የምናደርገው። ዋናው ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ማድረግ ነው፤ ይሄን ለማድረግ ግን የተደራጀ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡ ያልተደራጀ ኃይል ውጤት ቢቀዳጅም ችግር ይዞ ነው የሚመጣው፡፡
የምትፈጥሩት ፓርቲ እቅዱ አሁን ያለውን እንቅስቃሴ ለመምራት መዘጋጀት ነው?
 ትክክል! ህብረተሰቡ ለውጥ እንደሚፈልግ ባለፉት ሁለት ዓመታት ህይወቱን መስዋዕት በማድረግ ጭምር አሳይቷል፡፡ ያ የለውጥ ፍላጎትና የሚመጣው ለውጥ ግን ወደ እርስ በእርስ ግጭት የሚከተን መሆን የለበትም፡፡ አንድን መንግስት ከስልጣን ሲወርድ፣ ሀገሪቱ መንግስት የለሽ መሆን የለባትም፡፡ ዲሞክራሲያዊ መንግስት የሚተካበት ሁኔታ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ያለ መሪ ድርጅት ትግል፣ የሚፈለገው ለውጥ አይመጣም፡፡ በኃይለ ሥላሴ ዘመን የተማሪው ትግል የተደራጀ ኃይል የሚመራው ባለመሆኑ፣ ስልጣን የወደቀው በወታደሩ እጅ ነው፡፡ አሁንም ተመሳሳይ ታሪካዊ ስህተት እንዳንሰራ ነው፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር ሆኖ ይሄን እንቅስቃሴ ማድረግ አያዳግትም?
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በግልፅ እንደተነገረው ፍቃድ ያስፈልጋል፡፡ ለአደባባይ ስብሰባ ፍቃድ ያስፈልጋል፤ ለመደበኛ የስራ ስብሰባ ፍቃድ አያስፈልገውም ነበር የተባለው፡፡ አሁን ግን በተግባር እንዳየነው፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠትም ፍቃድ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ መሰረታዊ የህዝብ መብቶችም እገዳ እየተጣለባቸው ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ መታገል አለብን፡፡ ካልታገልን ይሄ አዋጅ ቋሚ አዋጅም ሊሆን ይችላል፡፡ ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነገሮችን ማፈን ነው የተፈለገው፡፡ ስለዚህ ፊት ለፊታችን አደጋ አለ ማለት ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መጠናከርና መታገል አስፈላጊነት እዚህ ላይ ነው፡፡ የሀገር ህልውና መጠበቅ አለበት። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሀገር፣ ለህዝብ የምናስብ ከሆነ፣ ከዚህ ጊዜ በላይ ጠንካራ ሆነን ለመስራት የሚጠበቅብን ጊዜ አይኖርም፡፡
ይሄን ፓርቲ የመፍጠር አጀንዳ እስከ መቼ ይሳካል ብላችሁ ነው ያቀዳችሁት?
እዚህ ላይ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ አያስፈልግም። እኛ በህገ ደንባችን በ6 ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ አለብን፡፡ ግን የተቃዋሚዎችን ጉዳይ ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የኛ ጉዳይ ብቻ አይደለም። መግለጫችን በሚዲያዎች ከወጣ በኋላ በህብረተሰቡ ዘንድ በጎ ተነሳሽነት እያየን ነው። ወቅታዊ ነው፤ ግፉበት የሚል ግፊት እያየን ነው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት የተከለከለውን ፍቃድ አግኝተን፣ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው። ፍቃዱን እንደምናገኝ ተነግሮናል፡፡ ጠንካራ ፓርቲ ኢትዮጵያ ውስጥ የመኖሩ ጉዳይ ለህዝብም ለተቃዋሚዎችም ለመንግስትም ይጠቅማል። ሲያጠፋ የሚጠየቅ ድርጅት ትግሉን ቢመራው መንግስትም ይጠቀማል። አለበለዚያ ግን በድንጋይ ውርወራ የሚደረግ ትግል መንግስትንም ያልሆነ ነገር ውስጥ ይከተዋል፡፡ ያ ደግሞ ለሀገርም የማይጠቅም ነው፡፡
እስከ አሁን ተቃዋሚዎችን በጉዳዩ ላይ አነጋግራችኋል?
መጀመሪያ ሃሳቡን በጋዜጣዊ መግለጫ እናሰራጨው፤ ቀጥሎ የህብረተሰቡን ሁኔታ እያየን ለህዝቡ እንቀጥላለን ብለን ነበር፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ሳምንት ጉዳዩን ለሁሉም መገናኛ ብዙኃን ካብራራን በኋላ በሙሉ እንቅስቃሴ የምንገባበት ይሆናል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል እንጂ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ሁሉ እያዘጋጀን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ከህዝብ ጋር ለመወያየት ዝግጁ ነን፡፡ መንግስት ይሄን ለማስተናገድ ምን ያህል ፍቃደኛ ነው የሚለውን በሂደት የምናየው ነው የሚሆነው፡፡
ከ97 ምርጫ በኋላ አንዳንዶች ኢዴፓን በለዘብተኝነት፣ ሌሎች ደግሞ በ“ኢህአዴግ ጥገኛነት” ይፈርጁታል፡፡ እንዲህ ያለው አመለካከት የተአማኒነትና የተቀባይነት ችግር አይፈጥርባችሁም?  አጀንዳችሁን ለመተግበር ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ይሁንታ ማግኘት ያስፈልጋችኋልና -----
ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይሄ ነገር ግን ተገቢ እንዳልሆነ ያለፉት ሂደቶች በደንብ የሚያሳዩ ይመስለኛል፡፡ ህብረተሰቡ እኛ ባለን መረጃ፣ የኛን ጉዳይ በደንብ ተረድቷል፡፡ 97 ምርጫ ላይ ኢዴፓ ያለውን ቅንጅት ተቀብሎ፣ ፓርላማ ቢገባና በሙሉ ኃይሉ አዲስ አበባን ተረክቦ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ አሁን ካለበት ብዙ ርቀት የተለየ ነበር የሚሆነው፡፡
ኢዴፓ ከመጀመሪያ አንስቶ ትክክለኛ አቅጣጫ ይዞ፣ ትክክለኛ ነገር ሲያመላክት እንደነበር፣ በተለያዩ ምክንቶች ግን ለአሉባልታዎች ሰለባ እንደሆነ ሰው በደንብ ገብቶታል፡፡ “አሁን ገብቶናል ተረድተናል” ይሉናል፤ ሰዎች፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ ተቃዋሚዎች የተባለው ዓይነት  አስተሳሰብ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ግን በኛ ላይ ከፍተኛ የአሉባልታ ዘመቻ ያካሄዱ ሰዎች ዛሬ  በመድረኩ የሉም፤ ወይ ቤታቸው ተቀምጠዋል ወይ ተሰደዋል፤ ትግሉን በፅናት እየመራን ያለነው እኛው ነን፡፡ ህብረተሰቡ እስከተረዳ ድረስ ተቃዋሚዎቹም ወደዚህ አስተሳሰብ ይመጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ሌሎች በዚያው መቀጠል የሚፈልጉ ይኖራሉ፡፡ እነሱን እንግዲህ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡
የምትፈጥሩት ፓርቲ በቀጣዩ የአዲስ አበባ መስተዳድር እና የማሟያ ምርጫ ላይ ሊሳተፍ ይችላል? ምንድን ነው እቅዳችሁ?
የአስፈላጊነቱን ጉዳይ ሁሉም ፓርቲዎች ተገንዝበውት፣ ፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ህብረተሰቡም ተገንዝቦት፣ በፓርቲዎቹ ዙሪያ ተሰባስቦ ገንዘብ፣ ጊዜ፣ ጉልበት እያዋጣ ተሳትፎ ካደረገ፣ አንድ ዓመት ቀላል አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ምርጫ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እናመጣለን፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ እሱን ተጠቅመን ከሶስት ዓመት በኋላ ተቃዋሚው ኃይል ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ መንግስት እንኳ መሆን ቢያቅተን በቂ የሆነ የፓርላማ መቀመጫ አሸንፈን፣ ሲቻል በ97 እንዳደረግነው አዲስ አበባን አሸንፈን፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የራሳችን ሚና እንዲኖረን ማድረግ እንችላለን፡፡ ይሄ እድል ከፊታችን ነው ያለው፡፡ ይሄን እድል ለመጠቀም ደግሞ አሁን ጥሩ አጋጣሚ ነው። መንግስት አሁን ሀገር በበቂ አቅም ማስተዳደር ባለመቻሉ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። ህብረተሰቡ ደግሞ ለለውጥ ተዘጋጅቷል። ይሄን እድል የመጠቀም ያለመጠቀም ጉዳይ የኛ ፋንታ ነው፡፡ ይሄ እድል ካልተጠቀምንበት አደጋ ነው፡፡ ይሄን የተፈጠረውን አደጋ፣ ወደ እድል የመቀየር ጉዳይ በኛ እጅ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የሚመጡትን ሁለት ምርጫዎች፣ ትርጉም ባለው መልኩ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ ለመለወጥ ልንጠቀምባቸው እንችላለን፡፡

Read 4149 times