Sunday, 20 November 2016 00:00

“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆንህን አትርሳ!?”

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

   “አዋጁና የኮማንድ ፖስቱ ሴክሪተሪያት ያወጣቸውን ክልከላዎች አንጥረን በማወቅ፣ ሌሎች
መብቶቻችን ሁሉ ግን አሁንም የማይጣሱ መሆናቸውን ማወቅ አለብን፡፡---

አበበ ተክለሃይማኖት (ሜ/ጄ)
   “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዳለህ አትርሳ” - ቀልድ አይሉት ማስፈራሪያ የተዘወተረ አባባል ሆኗል፡፡ አንዳንዱ እንደ ቀልድ፣ ሌላው የምሩን እየወሰደው ለብዙ ሰው መደናበር፣ ፍራቻና መደበቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ ብዙ ሰው ራስን ማቀብ (self-censorship) እያጠናከረ፣ ከነጻነት ጋር እየተፋታ ነው፡፡ በተለይ “ፖለቲካ በሩቁ” የሚሉ ሰዎች፣ ትንፍሽ ለማለት እንኳን እየፈሩ ነው። ሲያወሩ ወፍ እንኳን እንዳትሰማቸው ማንሾካሾክ አመላቸው ሆኗል፤ ልክ በደርግ ጊዜ እንደነበረው፡፡
ለዘመናት በአገራችን የመሸገው ኢ-ዴሞክራሲያዊና ለመብት እስከ መጨረሻ ያለመታገል ባህል፣ በመጀመሪያ በሽግግር ቻርተር፣ በኋላም በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት አማካኝነት በተወሰነ ደረጃ መቀረፍ ጀምሮ ነበር፡፡ ህዝቦች መብታቸውን ለማረጋገጥ በመደራጀት በሁሉም መልክ መታገል የጀመሩበት፣ የፕሬስ ውጤቶች እንደ አሸን የፈሉበት፣ ሰላማዊ ሰልፍ በየቀኑ የምናየው ትእይንት የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሮም ነበር፡፡ በተለይ በ1997 ምርጫ አጥቢያ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ፣ ኢትዮጵያችን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እመርታ ልታሳይ ተቃርባ ነበር፡፡ በ97 ምርጫ ማግስት በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስና በተወሰደው ቀጣይነት ያለው እርምጃ፣ ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ በመጥበቡ፣ራስን የማቀብ (self-censorship) ሁኔታ ዳግም በከፍተኛ ደረጃ እያንሰራራ መጥቷል፡፡
‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ››ከታወጀ በኋላ፣‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› እንዲሉ፣ በሕብረተሰቡ በአጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ በፖለቲካ ልሂቃኑ፣ በጋዜጠኞች፣ በማተሚያ ቤቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሚለው ክልከላ በላይ ራስን ማቀብ በከፍተኛ ደረጃ እየተለመደ መጥቷል፡፡ አዋጁ የታወጀው በሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ መብቶቻችንንና ፍላጎታችንን ማረጋገጥ ስላልቻልን፣ የህዝቦችን ተቀባይነት ያለው ትግል ፅንፈኞች ወደ ሁከት ስለቀየሩት፣ ለጊዜውም ቢሆን ወደ ኋላ ተመልሰን አገራችንንና አደጋ የተጋረጠበትን ጅምር ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ማዳን ስለነበረብን ነው፡፡ ሽንፈቱ  አማራጭ የሌለው እንኳን ቢሆን እኛ ግን በሽንፈት ዓለም ለመኖር መፍቀድ የለብንም፡፡
ሕገ-መንግስታችንንና የሕግ መርሆዎችን መሰረት በማድረግ በአዋጁ ምክንያት የሚፈጠረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመቀነስ፣ (በአጭር ጊዜ አዋጁ ይነሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ) ያሉንን መብቶች ተጠቅመን፣ የአገራችን የልማት፣ የዴሞክራሲ ግንባታ መልሰን ለማረጋገጥ፣ ሁላችንም በሰላማዊ መንገድ መታገል ይኖርብናል። መሰረታዊ ችግሮቻችንና መፍትሔዎቹ ከአንድ ፓርቲ አቅም በላይ ሆነዋል፡፡ ኢህአዴግ እታደሳለሁ ማለቱ እሰየሁ ነው፤እስኪታደስ ያውም “በጥልቀት” መጠበቅ ግን ሞኝነት ነው፡፡ በኔ እምነት ኢህአዴግ መታደስ የሚጀምረው በይፋ፣” ችግሩ የሁላችንም ነው፤ ለመፍትሔውም በጋራ እንስራ” በማለት በይፋ ያወጀ ዕለት ነው፡፡
‹‹ማናቸውም ጉዳይ በግልፅ በሕግ ካልተከለከለ እንደተፈቀደ ይቆጠራል›› የሚለው የህግ መርህ፣ ለዜጎች እንደ ዋነኛ የፖለቲካዊ ነፃነት መሳሪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሶስቱ ትውልድ የሰብዓዊ መብቶች ያረጋገጠ ሕገ-መንግስት አለን፡፡ ሰፊ እና የተሟላ ነው፡፡ አዋጁና የኮማንድ ፖስቱ ሴክሪተሪያት ያወጣቸውን ክልከላዎች አንጥረን በማወቅ፣ ሌሎች መብቶቻችን ሁሉ ግን አሁንም የማይጣሱ መሆናቸውን ማወቅ አለብን፡፡ የተከለከሉት ውሱን መብቶች መሆናቸውን ካለማወቅና ከፍራቻ የተነሳ መብቶቻችን አሳልፈን መስጠት አይገባንም፤ ሌላ ሽንፈት ይሆናልና፡፡
አዋጁ በዋናነት የሕገ-መንግስታችን አንቀፅ 30 ማለትም፤ ‹‹የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብትን” በከፊል ነው የከለከለው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ከልክሏል፣ ስብሰባ በማስፈቀድ ማድረግ ይቻላል፡፡ አቤቱታ ማሰማትን ግን የከለከለ አይመስልም፡፡ አንቀጽ 31 ማለትም፤ ‹‹የመደራጀት መብት ክልከላ ውስጥ አላስገባውም፡፡ የአመለካከት እና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብትን እንዳለ አልከለከለም፡፡ የፅንፈኞች የመረጃ ምንጭ ቢከለክልም። ከመጀመሪያውም ቢሆን ሕገ-መንግስታችን በአንቀፅ 29፤ ‹‹… የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በሕግ የሚከለከሉ ይሆናል›› ይላል፤ በኔ እምነትም መከልከል ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በአንቀፅ 29፤ ‹‹የአመለካከት እና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት›› በመደንገግ የተሟላ ነፃነት ያረጋግጥልናል፡፡ በተለይ በንዑስ አንቀፅ 3/ሀ፤ ‹‹የቅድሚያ ምርመራ በማናቸውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን” ስለሚያስቀምጥና በክልከላው ስለሌለ፣ ራሳቸውን እያቀቡ ያሉ (ቅድመ ምርመራ እያደረጉ) መብታቸውን በገዛ እጃቸው እያፈኑ ነውና ጉዳዩን ሊያጤኑት ይገባል። በእኔ አመለካከት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና  ማስፈፀሚያ መመሪያዎቹ፣ ሕገ-መንግስቱን ይፃረራሉ የሚል አካል ካለ፣ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ የመታገል መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ በተረፈ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስካልተነሳ ድረስ የማክበር ግዴታ አለብን፡፡
እኩልነት የሕገ-መንግስታችን እምብርት
አንቀፅ 93/2/ሐ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የሚወጡት ድንጋጌዎችና የሚወሰዱ እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ በሕገ-መንግስቱ የተወሰኑት አንቀፆችና የተቀመጡ መብቶች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም ይላል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንቀፅ 25፤ የእኩልነት መብት ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም አይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው››
ጠቅላይ ሚኒስትራችንና ሚኒስትሮቻችን፣ ጄኔራሎቻችን ከማንኛውም ዜጋ ጋር በሕግ ፊት እኩል ናቸው፡፡ ባለስልጣናት የመላው ህዝቦቻችንን መብቶች የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህን ግዴታ ለማክበርና ለማስከበር ብቻ እንደ ሁኔታው የሚቀያየር ስልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ሳይሆን በሕግ ብቻ እንዲገዛ ያዛል፡፡ ካልሆነም እንደማናቸውም የሚጠየቁበት ይሆናል፡፡
የኢህአዴግ ድርጅቶች በ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ሰበብ ለወራት በስብሰባና በግምገማ ተወጥረው ተይዘዋል። መቋጫው መቼ እንደሆነ ለማወቅ አዳጋች ቢሆንም ጋዜጣዊ መግለጫዎችንም እስኪበቃን ድረስ እየተጋትን ነው፡፡ ቢሆንም መብታቸው ነው፡፡ መቼም ከአዋጁ በኋላ ስብሰባቸውንም ሆነ ጋዜጣዊ መግለጫቸውን የሚያደርጉት ፈቃድ እየጠየቁ ነው ብለን እንገምታለን፡፡ (ኮማንድ ፖስቱና ገዢው ፓርቲ ለየቅል ናቸውና!!) በሌላ በኩል ኢዴፓ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ከኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ አላገኘሁም ሲል የሰማሁት መሰለኝ። ወይም ዘገባውን በጋዜጣ አንብቤ ይሆናል፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ፓርቲው ስብሰባ ለመጥራት ወይም ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ፈቃድ ቢጠይቅስ? መብት በመሆኑ ልክ እንደ ኢህአዴግ መስተናገድ ይገባዋል፡፡ መሰረቱ የህግ የበላይነት በመሆኑ፣ሁላችንም የማክበር ግዴታ አለብን፡፡
በአዋጁ ማግስት፣ ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ.ም፣ ‹‹የፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከየት ወዴት? ፈተናዎች እና መልካም እድሎች›› በሚል ርዕስ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የውይይት መድረክ ተካሂዶ ነበር፡፡ ፈር-ቀዳጅና ገንቢ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት መድረክ በመሆኑ ፋና ምስጋና ይገባዋል፡፡ በነገራችን ላይ ውይይቱን ኢቢሲ ያስተላልፈዋል ብለን በጉጉት ብንጠብቅም፣‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሆኑን አትርሳ›› የሚል ተግሳፅ ደርሶት ይሁን ወይም ራሱን በማቀብ (self-censorship) እስካሁን ውይይቱን አላቀረበውም። ነገር ግን አዋጁ ውይይቱን እንዳያስተላልፍ ፈጽሞ አይከለክለውም፡፡ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29/5፣ እንደውም እንደ ህዝብ ሚዲያ፣መረጃውን የማሰራጨት ሃላፊነት ይጥልበታል፡፡   
ለማጠቃለል የአዋጁ ድንጋጌዎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን ቢያጠቡትም፣ ሕገ-መንግስቱንና የሕግ መርሆዎችን መሰረት አድርገን፣ ሰላማዊ ትግላችንን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ በዚህም አገራችንን ልንታደጋት እንችላለን፡፡ ራስን ማቀብ ለራስም ሆነ ለማህበረሰብ እንዲሁም ለአገር የሚበጅ ነገር የለውም፡፡ ሰላማዊ ትግሉ ብዙ መስዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ ግን ደግሞ ሌላ አማራጭ ያለን አይመስለኝም፡፡
አዲስ ወይን በአሮጌ አቁማዳ!!
የ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ መንደርደሪያ የተባለው አዲሱ ካቢኔ፤ የመወያያ አጀንዳ እንደሆነ ቀጥሏል። ብዙዎች፤” አገር በምሁራን ይመራ” የሚለውን የመንግስት ሹመት አሰጣጥ (መስፈርት) ቢያንስ በመርህ ደረጃ ይስማሙበታል። የአዲሶቹ ሚኒስትሮች የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት፣ በአብዛኛው የሚያጠግብ ይመስላል። ስለ እያንዳንዱ ሚኒስትር ሰብዕና እንዲሁም የፖሊሲ አቅጣጫ መረጃውና ዕውቀቱ ባይኖረኝም፣ በጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሹመት መስፈርት መርካቴን አልደብቅም፡፡ በ2008 በተዋቀረው የጠ/ሚኒስትሩ ካቢኔ ያፈርኩበትን ያህል፣ ዘንድሮ የተካስኩ ይሰማኛል፡፡ ካቢኔው የተስፋ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ አዲሶቹ ምሁራን ሚኒስትሮች፤ አገሪቱን በጥናትና ምርምር የተመሰረተ እውቀት ባለው መንገድ ሊመሯት ይችላሉ፡፡ ይህ አሰራር እስከ ታች ከወረደና፣ የፓርቲው አደረጃጀት በየደረጃው ካላደናቀፈ፣ በብዙ ዘርፎች ውጤታማ ለመሆን አያቅተንም፡፡
በየደረጃው የሚመደቡ የመንግስት ሃላፊዎች በተመሳሳይ መልኩ፣ በብቃት መስፈርት ብቻ ከተመዘኑ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ፓርቲና መንግስት ለየቅል መሆናቸው እየጎላ ይመጣል፡፡ ለፓርቲ ታማኝ ከሆኑት ይልቅ ብቃት ያላቸው ሹመኞች በበረከቱ ቁጥር  ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ብቃት የሌላቸውና አፋቸውን ብቻ አሹለው ለጌቶቻቸው ለማደር የሚሽሎከሎኩ ጥገኞችም እየተሽመደመዱና ቦታ እያጡ ይሄዳሉ፡፡  
አንዳንድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከጠ/ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ሹመት በኋላ እንደገለፁት፤ በእርግጥም የተከበሩ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ያቀረቡት የካቢኔ ጥንቅር በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡ አንዳንዶች “የምሁራን ካቢኔ” ብለውታል፡፡ በሌላ በኩል፤ ‹‹ቀለም ያልዘለቀውም ቢሆን ፖለቲካዊ ታማኝነት እስካለው ድረስ ሚኒስትር ሊሆን ይችላል›› የሚለውን እጅግ ኋላቀር አስተሳሰብ አሽቀንጥሮ በመጣል፣ በአዲስ አስተሳሰብ የተካ የካቢኔ ሹመት ነው፡፡
አዲሱ ካቢኔ ሲፀድቅ ከሌላው ጊዜ በተለየ የተወካዮች ምክር ቤት ለ”ጥልቅ ተሃድሶ”  መንደርደሪያ ያደርገዋል ብለን ጠብቀን ነበር፡፡ የተከበሩ አፈ ጉባኤና ሌሎች ጥቂቶች  በፓርቲው ውስጥ ባላቸው ስልጣን መሰረት፣ የሚኒስትሮች ሹመት ላይ በአንድ ወይ በሌላ መንገድ ተሳትፈዉበት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ እንደ ተቋምና የተለያዩ ኮሚቴዎች ከምር ስልጣናቸውን ተጠቅመው ነው ሹመቱን ያጸደቁት? ያስብላል፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት ገደማ ምክር ቤቱ የሚኒስትሮች፣ ወይም ኮሚሽነሮች አሊያም ዳኞች ሹመትን እንዲያፀድቅ ሲቀርብለት፣ (ተቃዋሚዎች የሚያሰሙት ድጋፍ ወይ ተቃውሞ ካልሆነ በቀር) አንድም ጊዜም እንኳን አይሆንም ብሎ ሲከራከር፣ ሲያስቆም ወይም ሲያስለውጥ አላየንም። ከአሁኑ ምክር ቤታችንም በሹመቱ ዙሪያ ልብ የሚሞላ ጥያቄ ይሁን አስተያየት አልያም ትችት ሲሰነዘር አልተሰማም፡፡ የም/ቤቱ አባላት እንደተለመደው፣ በ100 ፐርሰንት ነው ሹመቱን ያፀደቁት፡፡ (ይህች 100 ፐርሰንት ለመደችብን!)
እንግዲህ የም/ቤት አባላት ሥራቸው፣ የቀረበላቸውን ሁሉ በ100 ፐርሰንት የድጋፍ  ጭብጨባ ማጽደቅ ብቻ ከሆነ፣ ለምን አንዳንድ ለውጦች አይደረጉም? ለምሳሌ፤ “ጠ/ሚኒስትሩ የሚሾሟቸውን እጩዎች፣ ፓርላማ ይዘው ከመቅረብ ይልቅ ለምን እዚያው ቢሯቸው ተቀምጠው፣ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለህዝቡ ይፋ አያደርጉትም?” መቼም የካቢኔ አባላት ፓርላማ ቀርበው የሚሾሙት ለክብር ወይም ለፕሮቶኮል ተብሎ አይደለም። ቃለ መሃላ ለመፈፀም እንዲመቻቸው ተብሎ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያታቸው እኒህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ጠ/ሚኒስትሩ ፓርላማ ድረስ መምጣት አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ ለማንኛውም ግን ም/ቤቱ ከማንም በላይ “ጥልቅ ተሃድሶ” እንደሚያስፈልገው ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ከ10 ወራት በላይ በተቃውሞ ሲናጥ የከረመው የኦሮሚያ ክልል መንግስት፣ የፌዴራሉን ካቢኔ ለማዋቀር ስራ ላይ የዋለውን መስፈርት በማሟላት (ያውም አስቀድሞ) የራሱን ካቢኔ መመስረቱ አይዘነጋም። በሌላ በኩል ድምፃቸውን ያጠፉ ክልሎችም አሉ። በተለይ የትግራይና የአማራ ክልል መንግስታት፣ ምን እያሉ ይሆን? ወይስ እነሱን “ጥልቅ ተሃድሶ” አይመለከታቸውም!? በጣም ሲዘገዩብንና ድምጻቸው ሲጠፋብን እኮ ነው፡፡
የሆነስ  ሆነና  የሁለቱ  ክልሎች  መንግስታት፣ የኦሮሚያን መስፈርት ተጠቅመው፣ ሹም ሽር ያደርጋሉ ወይስ “እኛ  በትጥቅ ትግል መስዋዕትነት ስለከፈልን፣ ብቃትና ዝግጅት ባይኖረንም፣ የተወሰነ የስልጣን ማሸጋሸግ አድርገን መምራቱን እንቀጥላለን” ይሉን ይሆን? ወይም ደግሞ፤ “እኛ በቂ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች ስሌሉን ቀድሞ በስልጣን ላይ የነበሩትን የተማሩ ሹማምንት ባሉበት  እንዲቀጥሉ እናደርጋለን” ሊሉም ይችላሉ፡፡ ሆኖም ብቃትና ወኔ የሌላቸው፣ በፀረ-ዴሞክራሲያዊነትና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም በትምክህት ያበዱ ግለሰቦች በሕግ የማይጠየቁ ከሆነ፤ አልቻላችሁም ይባሉ!! በክብር ይሰናበቱ!! የመንግስት ስልጣን ፈጽሞ ዳረጎት አይሁን!! በአቅም ማነስ፣ በዳተኝነት፣ በሙስና፣ በኢ-ዲሞክራትነት ወዘተ---የተገመገሙ የመንገፍስት ባለሥልጣናት ሳይወገዱ ወይም ሹም ሽር ሳይካሄድ ለህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት አዳጋች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ክልሎቹ እስካሁን እየሰሩ ያሉትን ሪፖርት ቢያደርጉ ሸጋ ነው፡፡ ህዝብ፤ ምለው ተገዝተው ሥልጣን ላይ የወጡ የመንግስት ሃላፊዎች፤ በስሙ እየወሰኑ ስላሉት ጉዳይ የማወቅ መብት አለው፡፡
ፖለቲካ ሲቀዛቀዝ (ሃሳብ መጠቅለያ)
ሰው ያለ ኦክስጅን አይኖርም። ኦክስጂን ካጠረው ይታመማል፣ ኦክስጅን ከእነ አካቴው ከተነፈገ ደግሞ በሰከንድ ይሞታል። አገርም እንዲሁ ነው፤ ፖለቲካ የአገር ኦክስጂን ነው፤ እየተነፈሱ የሚያቃጥሉት የህይወት ምንጭ። ፖለቲካ ሲቀዛቀዝ አገር ትታመማለች፤ ህዝቦችዋ፣ ተቋሞችዋ፣ ሁለመናዋ ክፉኛ ይጎዳሉ። ቅዝቃዜው ወደ በረዶነት ከተቀየረ ግን አደጋ ላይ ነን። የፈንጂ ዞን ውስጥ ገብተናል፡፡ በዘመናዊት ኢትዮጵያ የሁሉም ፖለቲካ እምብርት ዴሞክራሲ ነው። የዴሞክራሲ እጥረት ፖለቲካን ያውከዋል፡፡
መንግስት ሕገ መንግስቱ ያስቀመጠለትን ግዴታ ያለማወላወል በመተግበር፣ ይቺ በምጥ ላይ ያለችን አገር በማዳን የድርሻዉን ይወጣ። እኛ ዜጎች ደግሞ መብቶቻችን አሳልፈን ሳንሰጥና በተሟላ መንገድ እየተጠቀምን፣ ወሳኝ ሚናችንን እንወጣ። ሁሉንም ልማትና ጥፋት የመንግስት እያደረግን፣ ራሳችንን ከሃላፊነት በማራቅ  አገራችንን አንጉዳ። በተለይ ወጣቱ በትንሽ ኦክስጂንም ቢሆን ብዙ መራመድ ስለሚችል፣ እየታገለ የተሟላ ኦክስጂን እንዲረጋገጥ በማድረግ፣ አገሩን የማዳን ሃላፊነቱን ይወጣ።

Read 2541 times