Sunday, 20 November 2016 00:00

በማግስቱ

Written by  አሰፋ ጫቦ - Dallas Texas USA
Rate this item
(4 votes)

    ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ሆኖ  ተመርጧል!! ይህ እውነት ነው! ማሸነፍ አልነበረበትም፤ በዚያ ምክንያት ነው፤ በዚህኛው ምክንያት ነው ያሸነፈው፤ እንዲህ፤ እንዲያ ቢደረግ ኖሮ የሚሉ አዋቂዎችም፤ አዋቂ ነን ባዮችም፤ አላዋቂዎችም፣ የኔ ቢጤዎችም ለዘመናት ይተቹታል፤ ይተቹበታል።  ያ “ጅብ ከሔደ ውሻ ጮኸ!”  ነው የሚሆነው።
የዛሬ ስንትስ አመት “የአሜሪካን ህዝብ ምንኛ ደንቆሮ ቢሆን ነው ጆርጅ ደብሊው ቡሽ የሚባል መሐይም ለፕሬዚዳንትነት የመረጠው?” የሚል ርእሰ አንቀጽ፣ አንድ የእንግሊዝ ጋዜጣ ጽፎ ነበረ።  The Daily Mail ይመስለኛል። አንዱ አንሶ ሁለቴ ተመረጠ! ይኸው ዛሬ ቡሽ ያቀጣጠለው ሰደድ እሳት መላውን መካከለኛ ምስራቅ ያጋያል! ለአፍሪቃም ተርፏል! አልሸባብ የአልቃይዳ ግልገል ነውና! አሜሪካና አውሮጳም እየተለበለቡ ነው። በሊቢያ በርሃ የተቀሉት ኢትዮጵያውያን የዚያ ቃጠሎ ወጤት ናቸው!
ትራምፕ እንዴት፣ ለምን አሸነፈ በሚባለው ላይ አሁንም ሙሉ ስራቸውም፣ የግማሽ ጊዜ ስራቸውም፤ እንደኔ ያሉ ስራቸው ያልሆነውም ጭምር ለዘመናት የሚተቹት፤ የሚተቹበት፤ ጠጉር የሚሰነጥቁበት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ። እንደኔ እንደኔ ትራምፕ ያሸነፈው በሕዝብ አመጽ ነው።  በአሜሪካን ሕዝብ አመጽ ነው።
ምን አይነት አመጽ?  አመጹ “የተቃዉሞ ድምጽ! Protest Vote” የሚሉት ነው። ማንን ነው የሚቃወሙት?  “ሥረ አቱ (The Establshmnet” የሚሉትን ነው። ስርአቱ የሚሉት የአሜሪካንን ፈዴራል መንግስት  አሰራር፤ አሜሪካንን ለዘመናት እየተፈራረቁ በገዙት፤ በነዱት የሬፑብሊካንና የዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ላይ ነው። በአጭሩ፣ ለመላው ሕዝብ  99  እጅ (99 Percent) ሳይሆን ለአንድ እጁ  (1 Percent) የሚሠሩትን ማለት ነው፡፡
ይህ ተቃውሞ እንዴት ተገለጠ? ልብ የማለት፤ የማስተዋል ወይም ለማስተዋል የመፈለግ ጉዳይ ይመስለኛል። የአሜሪካን  ሕዝብ ስለ ዶናልድ ትራምፕ የተነገረውን ጉዳ- ጉድ አልሰማሁም፣ አላየሁም አላለም! መስማት አልፈልግምም አላለም! ማጋጣ፤ ባለጌ፤ ቀጣፊ፤ ዛሬ የተናገረውን ነገ በጠራራ ፀሐይ የሚክድ መሆኑን፤ አጭበርባሪ መሆኑን፣ ዘረኛ፤ ሴት የሚንቅ፤ የሚዘልፍ፣ የሚያዋርድ መሆኑና ሌላ ሌላውንም አልሰማሁም አላየሁም አላለም! “ሰምቻለሁ አይቻለሁ፤ ሆኖም ከ እናንተ ይሻላል!” ነው ያለው። ከእናንተ  ይሻላል የሚለው “የስርአቱ  ሰዎችና ድርጅቶች (The Establishment) ከሚላቸው ነው። የዋሽንግቶን ዲ ሲ ወንበዴዎች- The D.C Mafia ይሏቸዋል። በዚሁ መሠረት ሂለሪ ክሊንተን የዚህ የወንበዴው ቁንጮ መሆኗ ነው።
እንግዲህ አንድ ዋና ነገር ልብ ማለት ያለብን ይመስለኛል። ትራምፕ ያሸነፈው ክሊንተንና ደሞክራቶችን ብቻ አይደለም። የራሱን ፓርቲ ሪፑብሊካኖችንም አሸንፏል! አልደገፉትም፤ አልፈለጉትምና! ይህ ሙያው ትችት (Critic) የሆነውንም ነገድ አሸንፏል! ትንቢት ተናጋሪዎችንም (Pollisters) አሸንፏል! መገናኛ ማእከላትንም (Mass Media) አሸንፏል! የተነበዩት፣ የተቹት አልሠመረምና!  በአጭሩ ያላሸነፈው ክፍል የለም!
ያም ሁኖ ትራምፕ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? እንዴታ!  አሁን የአሜሪካን መንግስት ልክ እንደ ኢህአዴግ የአንድ ፓርቲ መንግስት ነው። ምክር ቤቱንም (Congress) ተቆጣጥረዋልና! በአሜሪካን መንግስት ዘላቂ ለውጥ የሚያመጣው ፕሬዚዳንቱ ወይም ምክር ቤቱ (Congress) ሳይሆን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ (Supreme Court) ነው። አሁን 8 ዳኞች ብቻ ስለአሉ አንዱን ትራምፕ ይሠይማል! አንድ ሶስቱ በምርኩዝ ስለሚሔዱ በአራት አመት ውስጥ ሌላው ቢቀር ሶስት ዳኛ የመሠየም እድል አለው። ዳኞች አንዴ ከተሠየሙ  ሞት ብቻ ነው የሚገላግላቸው።  ስለዚህም ትራምፕ በአለም ላይ ለውጥ ማምጣት መቻል አለመቻሉ የሚያነጋግር ቢሆንም አሜሪካን ላይ ለውጥ ማምጣት መቻሉ ብዙም አያነጋግርም። ሁሉንም “ታውቁኛላችሁኮ !አርፋችሁ  ተቀመጡ!” ማለት ይችላል። ማንም ውለታ የሰራለት የለምና!
ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ሊኖር ይችላል? ይህ የሚያነጋግር ነው። እንደኔ እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ላይ ለውጥ ያመጣ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ስለሌለ ትራም የተለየ የሚሆንበት ምክንያት አይኖረውም። እኔ አይታየኝም! የአሜሪካን መንግስት፤ የማንኛውም መንግስት፣ መሠረታዊ መርሆ ለራሱ ሕዝብና መንግስት ብቻ ነው። ከጥቅሙ ጋር ሲገናኝ ይተባበራል። ወይም የሚተባበር ይመስላል!!
በተለየ ኢትዮጵያን በሚመለከት ሁሌ የምታዘበውና የሚገርመኝም አለ። ባራክ ኦባማ የኢህአዴግ ደጋፊ ነው የሚል ጽሑፍ በድረ ገጾችም ላይ፤ ሰልፍ ላይ በሚያዙ መፈክሮችም ላይ አያለሁ። ምሁራን ነን የሚሉ፣ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች ጭምር ስለ ኢትዮጵያ ሲጽፉ፣ የአሜሪካንን ሕገ መንግስት ጠቅሰው፤ “አሜሪካ የሰው ልጅ መብት የተከበረባት አገር” አድርገው ያቀርባሉ። አብዛኞዎቹ እንዲህ ባዮች፤ ማለትም ጸሐፊዎቹ፣ እዚህ አሜሪካ ያሉ፤ በተለምዶ ዳያስፖራ ተብሎ የሚታወቁቱ ናቸው። በአይናቸውን የሚያዩትን ትተው  የሚያነቡትን ያምናሉ እንደ ማለት ይመስለኛል። ማን ይሙት አሜሪካ የራሱን ጥቁር በአብዛኛው ከሰው ልጅ በታች አድርጎ የሚያኖር፤ በነጋ በጠባ በፖሊስ ጥይት የሚዘርር፤ ወህኒ ቤቶችን ሌላው የጥቁሮች መኖሪያ አገር ያደረገ፤ እዚያ ከዉቂያኖስ ማዶ ላለች ኢትዮጵያ በተለየ ሊያስብ ይችላል ማለት፤ ወይ ከንቱ ምኞት፤ ወይም እውነትን ማየት አለማቻል፤ ወይም አይቶም መቀበል አለመፈለግ ይመስለኛል።
አሜሪካ ለጥቅሟ ስትል ኢትዮጵያን ትፈልጋለች። መካከለኛው ምስራቅ ላላት ጥቅም ማስከበሪያ፣ ለጦር ሰፈርነት (Military Base) ብቻ ነው። ልክ ጁቡቲን የምትፈልገውን ያክል ማለት ነው። አንስተውታል ሲሉ የሰማሁ መሰለኝ እንጅ አሜሪካ አርባ ምንጭም የጦር ሰፈር ነበራት።
እዚህ ቦታው ስለአልሆነ አልገባበትም እንጅ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ በአሜሪካና በኃይለ ሥላሴ መካከል የነበረው ግንኙነት ትንሽ ራሱን የቻለ ድራማ ነበር።   John Spencer, Ethiopia at Bay   በሚለው መጽሐፋቸው፤ በኒክሰን ዘመን የኃይለ ሥላሴን ጉብኝት አስመልክተው የጻፉት የሚያሳፍር አይነት ባህርይ ያለው ነው።  
ሁሌ ስለ አሜሪካ ተሞክሮዬ (Experience) እጽፋለሁ እልና እዘነጋለሁ። አሁን መጀመሬ የሚቀር አይመስለኝም!
የዚያ ሰው ይበለን!  “መልካም የትራምፕ ዘመን “አይባል ነገር!!

Read 1590 times