Sunday, 20 November 2016 00:00

አለማቀፉ የቀውስ ማዕበል፣ በትራምፕ አያበቃም!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(12 votes)

 ከBriexit እስከ ዶናልድ ትራምፕ... አውሮፓና አሜሪካ የምር ጉዳቸው ፈልቷል።
                ሲጠራቀም የቆየ፣ የቅይጥ ኢኮኖሚ መዘዝ፣ አስደንጋጭ ማዕበል እየሆነ ነው። እንዴት?
                 የአሜሪካና የአውሮፓ ፋብሪካዎች፣ ተዳክመዋል - በመንግስት ታክስ፣ ቁጥጥርና ክልከላ።

         • ከ15 ዓመት በፊት፣ በአሜሪካ የፋብሪካ ሰራተኞች ቁጥር 20 ሚ. ነበር። ዛሬ በ5 ሚ. ቀንሷል፡፡
   • የእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ የጣሊያን የፋብሪካ ምርትም ቀንሷል፤ 15 አመት ወደ ኋላ ተመልሷል።
በፈረንሳይ፣ 4 ሚ. ሰዎች በፋብሪካ ውስጥ የስራ እድል ያገኙ ነበር፡፡ ዛሬ ግን 3ሚ. ብቻ!
ለኢንዱስትሪው ውድቀት ሦስት መንስኤዎች
   • የአውሮፖ ህብረት፣ እያንዳንዱን ምርት ለመቆጣጠር ለቁጥር የሚታክቱ ህጎች አውጥቷል፡፡ ቁመቱ ከ14 ሴሜ. ያነሰ ሙዝ፤ ህገወጥ ሙዝ ነው፡፡ ለጥቅል ጎመንም በርካታ ህጎች
   • በአሜሪካም የቁጥጥር ህጎች በየአመቱ ይራባሉ፡፡ በ180 ሺ ገፅ ጥቅጥ ተደርገው የተፃፉ ህጎች፤ በ237 መፃህፍት ተጠርዘዋል፡፡ ህጎቹ፣ በየአመቱ ዜጎች ላይ የ2 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ያደርሳሉ፡፡
   • ከአገር ኢኮኖሚ ውስጥ፣ የመንግስታት ድርሻ 10% አይደርስም ነበር፡፡ አሁን 50% ገደማ ሆኗል፤ በዚያው ልክ የታክስ ጫናው ጣሪያ ነክቷል፡፡ ታክስ መጨመር   የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
   • ታክስ አልበቃ ሲላቸው ብድር ጨመሩበት፤ ለዚህም ነው በብድር የተጥለቀለቁት። ግን፣ መቀጠል አይችሉም - የብድር ጣሪያ እየነኩ ነው።
  • የአውሮፓ መንግስታት እዳ፣ በ15 ዓመት፣ እጥፍ ሆኗል። የፈረንሳይ ከ$1.2 ትሪሊዮን ወደ 2.4 ትሪሊዮን ‹‹አድጓል››።
የአሜሪካ መንግስት እዳም፣ በባራክ ኦባማ ዘመን ብቻ፣ ከ10 ትሪሊዮን ወደ 20 ትሪሊዮን! ‹‹በደብል ድጅት ፈጣን እድገት››!
   • በቁጥጥርና በታክስ ጫና ላይ፣ ‹‹የአካባቢ ጥበቃ›› በሚል ሰበብ፣ ፋብሪካዎችን የማዳከምና የመዝጋት ዘመቻ ሲጨመርበት፣ የአሜሪካና የአውሮፖ ኢንዱስትሪ ቢፍረከረክ ያንሰዋል?
   • ቀውሱን ለማድበስበስ እንጂ፣ አብጠርጥሮ ለማሳየትና ለመፍታት የሚጥር ሚዲያና ፖለቲከኛ ጠፋ።
   • የፖለቲከኛና የሚዲያ ላይ ሰብከት፣... ሰሚ አጣ። በቁጣ መደናበር በዛ። Briexit ተከሰተ፣ ዶናልድ ትራምፕ ተመረጠ።
    
    የአውሮፓና የአሜሪካ ቀውስ፣ በስድስት ወራት ልዩነት፣ በእንግሊዝና በአሜሪካ ፈንድቶ፣ እንደ ድንገተኛ ጎርፍ ብዙዎችን ቢያስደነግጥም፣ ዱብዳ ክስተት አይደለም። ባለፉት አስር ዓመታት፣ ቀስ በቀስ እየጎላ የመጣ፣ ነባር አለማቀፍ ክስተት ነው። የዛሬ ስምንት አመት የተከሰተው “የፋይናንስ ቀውስ” መች ተረሳ? የግሪክ፣ የጣሊያን፣ የስፔን መንግስታት የእዳ ቀውስስ? የአውሮፓና የአሜሪካ ኢኮኖሚኮ፣ ገና እስካሁን ከቀውሱ ማገገም አልቻለም። ታዲያ፣ የነሱ ብቻ አይደለም - ቀውሱ። የባሰባቸው አገራት፣ ሲፈራርሱ አይተናል፡፡  አንዳንዶቹም እየፈራረሱ ነው - ቬንዝዌላ፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣... እነሶሪያና ሊቢያን ተከትለው።
የአውሮፓና የአሜሪካ የኢኮኖሚ ስርዓት፣ ከሌሎቹ የአለማችን አገራት የተሻለ ስለሆነ ነው፤ እስከ ዛሬ  ሳይፈራርሱ የተንገታገቱት። “የተሻለ” ማለት ግን፣ “እንከን የለሽ” ማለት አይደለም። ምን እንከን ብቻ! የለየለት አጥፊ በሽታ ተጠናውቷቸዋል እንጂ። የዚህ ጥፋት ስም፣ “ቅይጥ ኢኮኖሚ” ይባላል።
በኢኮኖሚ ውስጥ፤ የመንግስት ድርሻ፣ ቁጥጥር እና ክልከላ... በየሰበቡ እየገነነ ከመጣ፣... የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ የትኛውም አገር ቢሆን፣ ወደ ቀውስ ማምራቱ አይቀሬ ነው። የዛሬ 25 ዓመት ገደማ፣ ምን እንደተፈጠረ አስታውሱ። ኢኮኖሚን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ሲሞክሩ የነበሩ ከ50 በላይ ሶሻሊስት መንግስታት፣ በኢኮኖሚ ቀውስ ተናግተው ፈራርሰዋል - በጥቂት አመታት ውስጥ። ኢኮኖሚን ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን፣ በከፊል ብቻ ለመቆጣጠር መሞከርስ? ነፃ ገበያም የመንግስት ጣልቃ ገብነት የተቀላቀሉበት ቅይጥ ኢኮኖሚ ያዛልቃል?
በከፊል ነፃ ገበያ፣ በከፊል የመንግስት ቁጥጥር የተቀላቀለበት፣... በከፊል የግል ቢዝነስ፣ በከፊል የመንግስት ገናና ድርሻ የተዳቀለበት፣... በከፊል የብልፅግና ፍላጎት፣ በከፊል “የአካባቢ ጥበቃ” (ማለትም የድህነት ጠበቃ) የተደባለቀበት ...  እንዲህ አይነት ቅይጥ ኢኮኖሚ ያዛልቃል? ያዛልቃል ብለው ያሰቡ ወይም የተመኙ እጅግ ብዙ ናቸው። እጅግ ከመብዛታቸው የተነሳም፣ የቅይጥ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ያለተቀናቃኝ በመላው አለም ለበርካታ አመታት ተንሰራፍቷል። ግን፤ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ ከመቃወስ አያመልጥም፤ … ለተወሰነ ጊዜ ለመንገታገት ያስችላል እንጂ፣ አያዛልቅም። ለምን?
የባሰባቸውን አገራት ትተን፣ ደህናዎቹን አገራት እንመልከት (አሜሪካና አውሮፓን)።
ከከፊል ነፃ ገበያ ጋር የመንግስት ቁጥጥር የተቀላቀለበት ቅይጥ ኢኮኖሚ፡
የአውሮፓ ህብረት፣ በትራስ እና በትራስ ጨርቅ ምርቶች ላይ ቁጥጥር ለማካሄድ የሚያስችሉ ከመቶ በላይ ህጎችን አውጥቷል። የሙዝ አመራረት ላይ የቁጥጥር ህግ፤ ከዚያም በአዝመራው ላይ ማለትም በሙዝ ምርት ላይ የቁጥጥር ህግ፣ ሙዝ ወደ ገበያ የሚጓጓዝበትን ሁኔታ ለመቆጣጠር ሌላ ህግ፤ የሙዝ ግብይት ላይም ሌላ የቁጥጥር ህግ... ለሙዝ የወጣው የግብይት ህግ እንዲህ ይላል፡፡ እያንዳንዱ ዘለላ፣ አራት ወይም ከዚያ በላይ ሙዞች ሊኖሩት ይገባል፡፡ 3 ወይም 2 ሙዞችን ብቻ የያዘ ዘለላ፣ ህገ ወጥ ዘለላ ነው … የሙዝ ቆዳ ላይ፣ መልክ የሚያበላሽ ጠቃጠቆ መኖር የለበትም፡፡ የጠቃጠቆው ስፋት ተለክቶ ከአንድ ካሬ ሴሜ ከበለጠ፣ ጉድለቱን የሚገልፅ መረጃ በሙዙ ላይ መለጠፍ ግዴታ ነው … ወዘተ ወዘተ
የአውሮፓ ህብረት፣ በየአመቱ እልፍ አእላፍ ህጎችንና የቁጥጥር መመሪያዎችን የሚፈለፍል ተቋም ነው።
በአሜሪካስ? ያው፣ በየአመቱ በሺ የሚቆጠሩ የቁጥጥር ገፆች እየተጨመሩ፤ ለቁጥር አስቸጋሪ ሆነዋል። ኢንሳይክሎፒዲያ የሚያካክሉ፣ 237 መፃሕፍት፣ በቁጥጥር ህጎች ታጭቀዋል። ጥቅጥቅ ተደርጎ የተፃፈባቸው፣ 180ሺ ረዣዥም ገፆች! የገፆቹ ብዛት፣ በእጥፍ የጨመረው ባለፉት 30 ዓመታት ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ‘ነፃ ገበያ’ እየቀነሰ፣ የመንግስት ቁጥጥጥ ሽቅብ ይመነጠቃል።
እና ይሄ ሁሉ ቁጥጥር፣ ያለ መዘዝ እስከወዲያኛው መቀጠል ይችላል? አምራቾችን ተብትቦ የሚያስቀር እልፍ ገመድ በየአመቱ እየቋጠርን፣ በየአመቱ የምርት እድገት እያገኘን ለመቀጠል ብናስብ ያስኬዳል? የማይመስል ነገር!
ከግል ንብረት ባለቤትነት ጋር፣ የመንግስት ድርሻ የተቀላቀለበት ቅይጥ ኢኮኖሚ፡
በ20ኛው ክፍለዘመን የመጀመሪያ ዓመታት፣ የአሜሪካ መንግስት፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የነበረው ድርሻ 5% ገደማ ነበር። የአውሮፓ መንግስታት ድርሻም፣ ከ10% በታች ነበር። ዛሬ፣ የፈረንሳይ መንግስት፣ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ 57% ያህሉን እንደራሱ ድርሻ እየቆጠረ በጀት ያወጣል። የጣሊያን መንግስት ድርሻም፣ 50% ገደማ ነው። የእንግሊዝ፣ ከ45% በላይ። የአሜሪካ እንኳ፣ 40% ደርሷል።
ተቃራኒ ነገሮችን አቀላቅሎ የያዘ ቅይጥ ኢኮኖሚ በጊዜ ካልታረመ፣ በሽታው ስር እየሰደደ፣ ቀስ በቀስ ነፃ ገበያ እየኮሰመነ፣ መንግስት እየገነነ ይመጣል። ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ግማሽ ያህሉን እንደድርሻው የሚቆጥር መንግስት፣… እንደ ተራራ አብጦ፣ በአገር ምድሩ ተለጥቶ፣ አዳሜን ደምጥጦ ይቀመጣል፡፡ ያው… እንዲያ የሚያሳብጥ ገንዘብ የሚያገኘው ከታክስ ነው። ድርሻው እያበጠ የሚሄደው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ላይ በላዩ በሚጭነው ታክስ ነው- በአምራቾች አናት ላይ።
ታዲያ፣ የታክስ ጫና እየከበዳቸው፣ ከስር ተደፍጥጠው፣ በአጭር እየተቀጩ ከገበያ የሚወጡ አምራቾች መበራከታቸው ይቀራል? ይሄ አንዱ አይቀሬ መዘዝ ነው። የፋብሪካዎች ትርፋማነት እየቀነሰ፤ የስራ እድልም እየጠበበ ሲመጣ፣ እንደ ልብ ታክስ መጫን አስቸጋሪ ይሆናል። ግን ችግር የለውም፡፡ መንግስት፣ ቦንድ እየሸጠ፣ ብድር ማግበስበስ ይችላል።
በባራክ ኦባማ ዘመን፣ የአሜሪካ መንግስት፣ በየአመቱ በአማካይ ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ተበድሯል፡፡ በስምንት አመት ውስጥ፣ 10 ትሪሊዮን ዶላር ተጨማሪ ብድር በማግበስበስ፤ የእዳ ክምችቱን 20 ትሪሊዮን አድርሶታል። ከዚህ በላይ ለተወሰነ ጊዜ መቀጠሉ አይቀርም። ግን ብዙም ሊቀጥል አይችልም። ለወለድ ብቻ፣ በአመት ግማሽ ትሪሊዮን ዶላር መክፈል ቀላል አይደለም። 500 ቢሊዮን ዶላር ማለትኮ ነው። ማለትም በየአመቱ፣ 100 የህዳሴ ግድብ! ለወለድ ክፍያ ብቻ!
የነፈረንሳይና የነጣሊያን እዳም፣ ጫፍ ደርሷል። እንደ ግሪክ፣ የአምና የካቻምና እዳ ለመክፈል፣ ዘንድሮ ተጨማሪ ብድር እየጠየቁ…፣ ብዙ መጓዝ አይችሉም። ይሄ ሁሉ መዘዝ፣ ድንገት የተፈጠረ ሳይሆን፣ ለሰላሳና ለአርባ አመታት፣ ሲጠራቀም ሲከማች በየቆየ ጥፋት ሳቢያ የመጣ መዘዝ ነው።
በቢዝነስ የመበልፀግ ፍላጎትና፣ ፀረ ብልፅግና “የአካባቢ ጥበቃ” ዘመቻ፡
በከፊል የመበልፀግ ምኞት ይዞ በከፊል ደግሞ “የድህነት ጠበቃ” መሆን፣…እንዲህ አይነት ቅይጥ ኢኮኖሚ፣ ለተወሰነ ጊዜ እንጂ አያዛልቅም። (የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፣ “የድህነት ጠበቃ” ቡድኖች ናቸው በማለት የተናገሩት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መሆናቸው ይገርማል)። የሆነ ሆኖ፤ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፣ ፈታ በማይሰጥ ዲስኩር፣ “ፋብሪካ፣ የአለምን አየር ይበክላል” የሚል ዘመቻ እያቀጣጠሉ፤ “የኪዮቶ ፕሮቶኮል”፣ “የፓሪስ ስምምነት”... ምናምን እየተባለ፣ ፋብሪካዎችን የሚያከሰር፣ ከነአካቴው ስራ እንዲያቆሙም የሚያስገድድ፣ መዓት ህግና መመሪያ እለት በእለት እየታወጀ፤... ወንዝ እንዳይገደብ እየተከለከለ፣ በተቃራኒው ግማሽ ያህል የኤሌክትሪክ ሃይል ለማያመነጩ የነፋስ ተርባይኖች እጥፍ ያህል ወጪ እየፈሰሰና ሃብት እየባከነ፤... ይሄ ሁሉ ፀረ ብልፅግና የድህነት ጥብቅና አለምን ከዳር ዳር እየወረረ፣... ይሄ ሁሉ ጥፋት፣ እንዲሁ ያለ መዘዝ እንዲቀጥል ማሰብ ሞኝነት ነው።
መዘዙን እያየነው ነው። ከአሜሪካ እስከ ኢትዮጵያ፣ ከእንግሊዝ እስከ የመን፣ ከፈረንሳይ እስከ ቱኒዚያ... ደረጃው ቢለያይም፣ በዚህ ጥፋት ውስጥ ያልተሳተፈ አገር የለም ማለት ይቻላል። የጥፋታቸውንም ያህል መዘዙን እየቀመሱ፣ እየተናጉ፣ እየደናበሩ ወይም እየፈረሱ ናቸው።
የመዘዙ ዋና ዋና ምልክቶች፣ የኢንዱስትሪ ድንዛዜና ውድቀት፣ እንዲሁም በስራ አጥነት የሚባባስ የኑሮ መናጋትና  የኑሮ ምሬት... ናቸው። ገና በኢንዱስትሪ ጎዳና፣ ‘ሀ’ ብለው መጓዝ ያልጀመሩ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገራት... ብዙዎቹ የአፍሪካና የአረብ አገራት ጭምር፣ በድንዛዜና በኑሮ ምሬት ይቃወሳሉ። በብልፅግና ጎዳና ሲራመዱ የነበሩ አሜሪካና አውሮፓ ደግሞ፣ በኢንዱስትሪ ውድቀትና በኑሮ መናጋት ይቃወሳሉ።
የእንግሊዝ እና የአሜሪካ የምርጫ ውጤቶች፤ በኢንዱስትሪው ውድቀት ከተከሰተው የኑሮ መናጋት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ፣ ገና ብዙዎችን ያተራምሳል!
እንግሊዝ፣ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ትቀጥል ወይስ ትውጣ በሚል በተካሄደው ምርጫ፣ አብዛኛው ሰው፣ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ለመቀጠል ይመርጣል ተብሎ ነበር የተጠበቀው፡፡ ለምን? ሁለቱ አውራ ፓርቲዎችን ጨምሮ፣ በፓርላማ ወንበር ያላቸው ፓርቲዎች በሙሉ፣ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ መቆየትን ነበር የሚሰብኩት። አለበለዚያ፣ በምርጫው ማግስት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ይንኮታኮታል፡፡ ቁልቁል እየተምዘገዘገ እንጦሮጦስ ይወርዳል … የማስፈራሪያ መዓት አዥጎድጉደዋል - አብዛኞቹ የሚዲያ ተቋማት፣ አለማቀፍ ድርጅቶችና አንጋፋ መሪዎች፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው?
ለ15 ዓመታት፣ እልፍ ፋብሪካዎች እየከሰሩና እየተዘጉ የሚሊዮኖች ኑሮ ሲናጋ፣… በታክስ ጫና፣ በቁጥጥር ብዛትና በክልከላ የፋብሪካ ስራ ሲንኮተኮት … ነገሩን ለማድበስበስና ለመሸፋፈን ሲጥሩ የነበሩ ፓርቲዎች፣ የሚዲያ ተቋማትና አለማቀፍ ድርጅቶች፤ ድንገት ተነስተው “እሪ” ቢሉ ሰሚ ለማግኘት አልቻሉም፡፡
እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ፣ በድምፅ ብልጫ ተወሰነ፡፡ ከዚያ፣ “ባልተጠበቀ ሁኔታ”፣ ለBriexit ድምፅ የሰጡ እንግሊዛዊያን፣ በአብዛኛው የኢንዱስትሪ መነሃሪያ በነበሩ  አካባቢዎች የሚኖሩ ናቸው ተባለ። ባልተጠበቀ ሁኔታ? ወይ ጉድ! በፋብሪካዎች አጠገብ የተስፋፉና ባለፉት 15 አመታት ክፉኛ የተዳከሙ አነስተኛ ከተሞች ውስጥ፣ ብዙ የተናጋ ኑሮ፣… ብዙ የተጠራቀመ ምሬት መፈጠሩ፣... “ያልተጠበቀ ሁኔታ” ነው?
ዶናልድ ትራምፕ፣ “ባልተጠበቀ ሁኔታ”፣ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማሸነፍ የቻሉትም፣ እንደቀድሞው በገጠራማ አካባቢዎች ሰፊ ድጋፍ በማግኘታቸው አይደለም። በገጠራማ አካባቢዎች፣ ብዙ ድጋፍ እንደሚያገኙማ፣ ቀድሞውኑም ታውቋል። ይልቅስ፣ የፋብሪካ መነሃሪያ በነበሩ አካባቢዎች፣ ዶናልድ ትራምፕ፣ “ያልተጠበቀ ድጋፍ” በማግኘታቸው ነው ያሸነፉት ተባለ። ያልተጠበቀ? ቅይጥ ኢኮኖሚ፣ ውሎ አድሮ፣ የቀውስ መዘዝ ማምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ወደፊትም አይቀርም።
በአጭሩ፣ የኋላቀር አገራት ቀውስ፣ በሊቢያና በሶሪያ ወይም በቻድና በቬንዝዌላ እንደማያልቅለት ሁሉ፤ በአሜሪካና በአውሮፓም፣ የቀውሱ ማዕበል፣ በBriexit ወይም በዶናልድ ትራምፕ አያበቃም። ለምን?
አንደኛ፣ ቀውሶቹ፣ መዘዝ እንጂ ሰበብ አይደሉም። የቀውሱ ሰበብ፣ በመላው አለም የተንሰራፋው ቅይጥ ኢኮኖሚ ነው። ሁለተኛ፣ ቅይጥ ኢኮኖሚ ዋነኛ የቀውሱ መንስኤ እንደሆነ ለመገንዘብ፤ ይህንን ጥፋት ለማረም የሚደረግ ብዙም ጥረት አይታይም።
በኢኮኖሚ ውስጥ፣ የመንግስትን ድርሻና የታክስ ጫናዎችን ለመቀነስ፣ ዘመቻ የጀመረ መንግስት ታውቃላችሁ? እስካሁን የለም።
የተቆለለውን የመንግስታት እዳ፣ በአንዳች መንገድ ለማቃለል ዘዴ የሚያበጅና የሚጣጣር አንጋፋ ፓርቲ ወይም መንግስት አለ? እስካሁን የለም።
እልፍ አእላፍ የተሳከሩ የመንግስት ቁጥጥሮችን ጠራርጎ ለማስወገድና አጥፊ ‘የአካባቢ ጥበቃ’ ዘመቻዎችን ለማክሰምስ፤ ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው? በተቃራኒው፣ ከእስከዛሬው ሁሉ የከፋ የአካባቢ ጥበቃ ዘመቻ ለማካሄድ፣ የክልከላና የገደብ ህጎችን እንደ አሸን ለማፍላት፣ ጉባኤ ተያይዘውታል - ከሰሞኑ በሞሮኮ እንደምናየው።

Read 3208 times