Sunday, 20 November 2016 00:00

የግብ ጠባቂውና የልጆቹ ሞት ሀዋሳን አስደንግጧል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(9 votes)

ባለቤቱ በፖሊስ እየተመረመረች ነው ተብሏል

   የሃዋሳ ከነማ ግብ ጠባቂ ክብረአብ ዳዊት ከሁለት ህፃናት ልጆቹ ጋር ባለፈው ማክሰኞ ማታ በቃጠሎ መሞታቸው ብዙ የሃዋሳ ነዋሪዎችን ያስደነገጠ ሲሆን፤ ባለቤቱ ወ/ሮ ቤቴል በላይ፣ በፖሊስ እየተመረመረች ነው፡፡
በሀዋሳ ተወልዶ ያደገው የ22 ዓመቱ ግብ ጠባቂ፤ ሰኞ እለት ከነበረው የኳስ ጨዋታ በኋላ፤  ማክሰኞ አመሻሽ የክለቡ ስብሰባ ላይ እንደነበረ  የቅርብ ጓደኛው የክለቡ ተጫዋች አስጨናቂ ሉቃስ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ በጓደኛዬና በልጆቹ አሰቃቂ ህልፈት ልቤ ተሰብሯል ሲልም ተናግሯል፡፡ ወጣቱ ግብ ጠባቂ ዓለም አቀፍ እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ህልሙን ለማሳካት ራሱን በደንብ ሲያዘጋጅ እንደነበር የጠቀሰው ጓደኛው፤ ጓደኛው፤ ከነ ህልሙ በለጋነቱ መቀጨቱ እንዳሳዘነው ጨምሮ ገልጿል፡፡
ወጣት ክብረአብ ዳዊት፤ ከአራት ዓመት በፊት  ለሲቲ ካፕ ጨዋታ አርባ ምንጭ በሄደበት ወቅት ነው ከባለቤቱ ወ/ሮ ቤቴል ጋር የተዋወቀው ብሎናል-ጓደኛው፡፡ ከሱቋ እቃ ሲገዛ አይቷት በዚያች ቅፅበት እንደወደዳትና ወደ ሀዋሳ መጥተው አብረው መኖር መጀመራቸውን ጓደኛው ተናግሯል፤  ግን ሰላም አልነበራቸውም ብሏል፡፡ “የመጀመሪያ ልጃቸው ከተወለደች በኋላ  ሦስት ጊዜ  ተጣልተው ታርቀዋል” ብሏል ጓደኛው፡፡
ሳጂን ማሞ ማናሞ፤ የሟች ባለቤት በጉዳዩ ተጠርጥራ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀው፤ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የምርመራ ውጤት መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ቤቴል እጅና እግሯ ላይ ቃጠሎ እንደደረሰባት ጠቅሰው፤ በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል በአራት ፖሊስ ታጅባ እየታከመች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ባለትዳሮቹ እስከ ፍርድ ቤት የደረሰ ጠብ እንደነበራቸው በመጥቀስ፣ ከሰሞኑም ንግግር አልነበራቸውም ያሉት ሳጂን ማሞ፤ የቀብር ስርዓት ላይ የቁጭት አስተያየት ሲሰነዝሩ አይቻለሁ፤ የምርመራ ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ ግን ተጠርጣሪ እንጂ ወንጀለኛ ናት ብሎ መናገር አይቻልም ብለዋል።
ከፌደራል ወንጀል ምርመራ ከመጡ የፎረንሲክ ባለሙያዎች ጋር በመሆን በተቃጠለው ቤት ላይ ፍተሻ መካሄዱን ሳጅን ገልፀው፤ ቤቱ ውስጥ ቤንዚን እንደነበርና ለቃጠሎው ድርሻ እንዳለው ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡
ቃጠሎ ከመድረሱ በፊትም ሆነ በኋላ፣ በአካባቢው የነበሩ ምስክሮች ያዩትንና የሰሙትን በመግለፅ፣ ለፖሊስ መረጃ እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በቦታው የነበረች የቤት ሰራተናም በፖሊስ እየተመረመረች ነው ብለዋል ሳጂን ማሞ፡፡




Read 8646 times