Sunday, 20 November 2016 00:00

የውጭ ተጨዋቾች በኢትዮጵያ እግር ኳስ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 • በፊፋ ስር ዝውውራቸውን ህጋዊ የሚያደርግ ዲፓርትመንት ተቋቁሞ መንቀሳቀስ ከጀመረ 6 ወራትተቆጥረዋል፡፡
    • በፕሪሚዬር ሊጉ ብዛታቸው ከ10 የተለያዩ አገራት 32 ተጨዋቾች ናቸው፡፡

                   
          በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተጨዋቾች የደሞዝ መረጃ በከፊል
  ስም  ክለብ  ወርሃዊ ደሞዝ

ታደለ መንገሻ አርባ ምንጭ ከነማ 125,000.0
እንዳለ ከበደ አርባ ምንጭ ከነማ 104,166.0
ጌታነህ ከበደ ደደቢት 100,000.0
ሳሙኤል ሳኑሚ ኢትዮ.ቡና 100,000.0
አስራት መገርሳ ደደቢት 83,333.0
ተሾመ ታደለ አርባ ምንጭ ከነማ 79,166.7
አማኑኤል ጎበና አርባ ምንጭ ከነማ 79,166.0
ወንድወሰን ሚልኪያስ አርባ ምንጭ ከነማ 72,916.7
ሳምሶን ጥላሁን ደደቢት 68,205.0
አንተነህ መሳ አርባ ምንጭ ከነማ 66,666.0
አመለ ሚልኪያ አርባ ምንጭ ከነማ 66,666.0
ምንተ ስኖት አበራ አርባ ምንጭ ከነማ 66,666.0
ተመስገን ካስትሮ አርባ ምንጭ ከነማ 66,666.0
ተካልኝ ደጀኔ አርባ ምንጭ ከነማ 66,666.0
ወንድሜነህ ዘሪሁን አርባ ምንጭ ከነማ 66,666.0
ገብረ ሚካኤል ያእቆብ አርባ ምንጭ ከነማ 62,500.0
በረከት ቦጋለ አርባ ምንጭ ከነማ 62,500.0
ወርቅይታደስ አበበ አርባ ምንጭ ከነማ 62,500.0
አንድነት አዳነ አርባ ምንጭ ከነማ 62,500.0
ዳዊት ፈቃዱ ደደቢት 61,795.0
ስዩም ተስፋዬ ደደቢት 61,795.0
ዘሪሁን ታደለ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
ፍሬው ጌትነት ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
አሉላ ግርማ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
አንዳርጋቸው የላቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
አበባው ቡጣቆ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
መሃሪ መና ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
አይዛክ ኢሴንዴ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
አሰቻለው ታመነ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
ሳላሃዲን ባርጌቾ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
በሃይሉ አሰፋ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
ተስፋዬ አለባቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
ምንተስኖት አዳነ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
ምን ያህል ተሾመ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
አዳነ ግርማ ቅዱስ ጊዮርጊስ 58,333.3
አብዱልከሪም መሃመድ ኢትዮ.ቡና 58,333.0
አይናለም ሃይሉ ደደቢት 55,385.0
አክሊሉ አየነው ደደቢት 52,780.0
ብርሃኑ ቦጋለ ደደቢት 52,178.0
ጃክሰን ፊጣ አርባ ምንጭ ከነማ 50,000.0
ሰለሞን ሃብቴ ደደቢት 42,564.0
ዘካሪያስ ቱጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ 41,666.7
ደጉ ደበበ ቅዱስ ጊዮርጊስ 41,666.7
ናትናኤል ዘለቀ ቅዱስ ጊዮርጊስ 41,666.7
ራምኬል ሎክ ቅዱስ ጊዮርጊስ 41,666.7
ሮበርት ኦዱንግካራ ቅዱስ ጊዮርጊስ 40,000.0
ያሳር ሙገረዋ ቅዱስ ጊዮርጊስ 40,000.0
አብዱልከሪም ዞኮ ቅዱስ ጊዮርጊስ 40,000.0
ሶፎኒያስ ሰይፈ ደደቢት 38,462.0
ታገስ አበበ አርባ ምንጭ ከነማ 33,333.2
ጸጋዬ አበራ አርባ ምንጭ ከነማ 33,300.0


       የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፕሪሚዬር ሊግ  ክለቦች የውጭ ተጨዋቾችን ቅጥር አስመልክቶ የሚሰራ ክፍል አቋቁሞ መስራት ከጀመረ ስድስት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ የፌደሬሽኑ ዲፓርትመንት የአይቲሲ፤ የቲኤምኤስ እና የፊፋ ቲኤምኤስ ተግባራትን የሚያከናውን ሲሆን ሃላፊው አቶ ሚካኤል እምሩ ይባላል፡፡ አቶ ሚካኤል እምሩ ለስፖርት አድማስ እንደተናገረው ዲፓርትመንቱ በፊፋ ማኔጅመንት ሲስተም ስር የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ የውጭ ተጨዋቾች ዝውውርን ተከታትሎ ይመዘግባል፡፡ ከሌሎች አገራት ፌደሬሽኖች  ግንኙነት መፍጠር መረጃዎችን ያሳውቃል፤ ይመረምራል፤ የውጭ ተጨዋቾች ቅጥሮችን በፊፋ የማኔጅመንት ሲስተም ደንቦችና መመርያዎች መሰረትም ያረጋግጣል በመጨረሻም የሊጉ ክለቦች የሚፈፅሟቸውን ዝውውሮች የውጭ ተጨዋቾች ፓስፖርት በመስጠት ያፀድቃቸዋል፡፡
በየሊጉ ክለቦች የውጭ ተጨዋቾችን ለመቅጠር መፈለጋቸውን  በግልፅና ዝርዝር መረጃዎች ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የፌደሬሽኑ ዲፓርትመንት ደግሞ የውጭ ተጨዋቾቹ ከሚመጡባቸው አገራት ፌደሬሽኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ህጋዊ ምዝገባ መከናወኑን ይጠይቃል። ከዚያም የሚገኘውን ምላሽ በዝውውሩ የሚያስፈልጉ የተጨዋቹ የቀድሞ ክለብ እና አዲስ ሊዛወርበት የፈለገው ክለብ የኮንትራት ውሎችና ሌሎች መረጃዎች ተገቢነትን ሙሉ ለሙሉ በመመርመር በድጋሚ ከሌላኛው አገር ፌደሬሽን በሚያደርገው ግንኙነት የሚያረጋጥ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም በፊፋ የማኔጅመንት ሲስተም መረብ ተጨዋቹን ያስመዘግባል፡፡
በአጠቃላይ  የውጭ አገር ተጨዋቾች ለአንድ ክለብ ተገቢ ሆነው መጫወት የሚችሉት የፊፋ የዝውውር ስርዓት በሚጠብቅ አካሄድ ሆኗል፡፡
ተጨዋቹ የሚጫወትበትን ክለብ በደብዳቤ ጠይቆ   ስምምነት   ሲያገኝ፤ የሚጫወትበት ክለብ ለሀገሩ ፌዴሬሽን ስምምነቱን ሲያሳውቅ፤ ተጫዋቹ የሚጫወትበት አገር ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ የዝውውር መልቀቂያ ወረቀት እንዲልክለት የኢት/እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ሲጠይቅና በዚህ ጥያቄ መሰረትም ፌዴሬሽኑ ተጨዋቹ የሚገኝበትን ሀገር ፌዴሬሽን በጽሁፍ ሲጠይቅ፤ ተጫዋቹ የሚጫወትበት አገር ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ የዝውውር መልቀቂያ ወረቀት /ITC/ በቀጥታ ሲልክ፤ ከሚጫወትበት ኢትዮጵያዊው ክለብ ጋር በዘመን የተደረገ የውል ስምምነት ለፌዴሬሽኑ ሲቀርብ ከሚመለከታቸው የመንግስት መ/ቤቶች የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ክለቡ አሟልቶ ሲያቀርብ የዝውውሩ ሂደት ህጋዊና በፊፋ ማኔጅመንት ሲስተም የተተገበረ ይሆናል ማለት ነው፡፡
 የፌደሬሽኑ  የአይቲሲ፤ የቲኤምኤስ እና የፊፋ ቲኤምኤስ  ሃላፊ አቶ ሚካኤል እምሩ ለስፖርት አድማስ እንደተናገሩት ዲፓርትመንታቸው መንቀሳቀስ በጀመረባቸው ባለፉት 6 ወራት 45 የውጭ ተጨዋቾች በኢትዮጵያ የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች የዝውውር እንቅስቃሴ ተሳትፈዋል ሲሆን በተጨማሪም ዲፓርትመንቱ 4 የውጭ ተጨዋቾች ከኢትዮጵያ የለቀቁበትን ዝውውር ህጋዊነት መረጋገጡንና  በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ህጋዊ የውጭ ተጨዋች ፓስፖርታቸውን ያገኙ የውጭ ተጨዋቾች ብዛት 32 እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች ከ10 የተለያዩ አገራት ማለትም፤ ከጋና፤ ናይጄርያ፤ አይቬሪኮስት፤ ብሩንዲ፤ ሴራሊዮን፤ ናይጄርያ፤ ኬንያ፤ ኡጋዳ፤ ቶጎና ቤኒን የመጡ ናቸው፡፡
ባለፈው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ እግር ኳስ የክለቦች ውድድር ከአፍሪካ 6 አገራት የተውጣጡ ከ26 በላይ የውጭ ተጨዋቾች በ7 ክለቦች ህጋዊ እውቅና  አግኝተው በመቀጠር ተጫውተዋል፡፡ ያኔ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ለሚዲያው አሰራጭቶት በነበረው ዝርዝር መሰረት በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሲጫወቱ የነበሩት 26 የውጭ ተጨዋቾች 8 ከካሜሮን፤ 7 ከናይጄርያ፤ 6 ከጋና፤ 3 ከኡጋንዳ እንዲሁም የተቀሩት ከኬንያ እና ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ነበሩ፡፡ ከ26ቱ ተጨዋቾች ጊዮርጊስ 7፤ መብራት ኃይል እና ሀረር ቢራ እያንዳንዳቸው 5፤ ደደቢት 4፤ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከነማ እያንዳንዳቸው 2 እንዲሁም ኒያላ ለ1 ተጨዋች ቅጥር ፈፅመው በፌደሬሽኑ የእውቅና ማረጋገጫ በማግኘት የውድድር ዘመኑን አሳልፈዋል፡፡
“ሜዳዎች ለስላሳና ምቹ ሳር ቢነጠፍባቸው…”
ባሪ ሊድዮም ከናይጄርያ
በሙሉ ስሙ ባሪ ሌድዮም ተብሎ ይታወቃል። የ24 ዓመቱ ናይጄሪያዊ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ነው፡፡ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከተቀላቀለ ዘንድሮ 5ኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት በናይጄርያ ትውልድ ከተማው ፖርት ሃርኮት በሚገኝ ክለብ በመጫወት አሳልፏል፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ ህንድ በማቅናት በሙምባይ ኤፍ.ሲ ክለብ ለ1 ዓመት ተጫውቶ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣው፡፡  የመጀመሪያ ክለቡ የሆነው በብሄራዊ ሊግ የሚወዳደረው ወልቂጤ ከነማ ሲሆን  ለ1 ዓመት ከ6 ወራት ተጫውቷል፡፡ ሁለተኛ ክለቡ በ2006 ዓመት በብሄራዊ ሊግ የነበረው የጂማ አባቡና ክለብ ሲሆን 1 ዓመት በዚያው አሳልፏል።  በሁለቱ ክለቦች በብሔራዊ ሊግ የ2 ዓመት ከ6 ወር ቆይታው የነበረውን አጠቃላይ ልምድ ባሪ ሌድዮም ለስፖርት አድማስ ሲናገር፣ የብሔራዊ ሊግ ተሳትፎ ወደ ፕሪሚዬር ሊግ ለመግባት ለሚፈልጉ ተጨዋቾች ከፍተኛ ልምድ የሚያስገኝ መሆኑን ገልፆ፤ ተወዳዳሪ ክለቦች በቂ የሚዲያ ሽፋን አለማግኘታቸውና በተሟሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች የሚንቀሳቀሱ ባለመሆናቸው የተጎዱ ናቸው ብሏል፡፡
ናይጄሪያዊው ባሪ በብሄራዊ ሊግ የነበረውን ቆይታ ካጠናቀቀ በኋላ ባለፈው የውድድር ዘመን በፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊ የሆነውን ሲዳማ ከነማን ተቀላቅሏል፡፡ በሲዳማ ከነማ ክለብ ባሳለፈው የመጀመሪያ የውድድር ዘመን ከሊጉ ጋር ለመላመድ መቻሉን ጠቅሶ፣ ዘንድሮ ከክለቡ ጋር በሊጉ ጠንካራ ብቃት ለማሳየት ተስፋ ማድረጉን ገልጿል፡፡  በሊጉ ክለቦች ናይጄሪያዊ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ብዛት እየቀነሰ መምጣቱን የገለፀው ባሪ፣ ከእሱ ሌላ ሁለት ተጫዋቾች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ሌላ ተጨዋች በቡና እንደሚገኙ አውቃለሁ ይላል፡፡ ባሪ ሊድዮም ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው አሁን በሚጫወትበት የሲዳማ ቡና ክለብ ሁለት ኬንያውያን አንድ የሃይቲ ተጫዋቾች ይገኛሉ፡፡ ደጋፊዎች በክለቡ ለሚገኙ የውጭ ተጫዋቾች ልዩ ማበረታቻ እና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጾ፤ በየጊዜው ውጤታማ እንድንሆን መፈለጋቸው ጥሩ ሞራል እንደሚፈጥር ተናግሯል፡፡
ባሪ ሉድዮም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ባሳለፈው ልምድ ዙሪያ ለስፖርት አድማስ አስተያየቱን ሲሰጥ በአፍሪካ ደረጃ ሁሉም ነገር ተሟልቶ እንዲገኝ መጠበቅ አያስፈልግም ብሎ በተለይ የሊግ ውድድሩ በፉክክር ደረጃው መሻሻል እየታየበት መሆኑን ገልጿል፡፡  በተለይ ግን የሊጉ ተወዳዳሪ ክለቦች ለጨዋታ የሚጠቀሙባቸው ሜዳዎች ለስላሳና፣ ምቹ ሳር ቢነጠፍባቸው በማለትም ምክሩን ለግሷል፡፡
‹‹የማልያ ቁጥር መቀያየር የለበትም››
ሱሌማን አሊ ከጋና
የ31 ዓመቱ ሱሌማን አሊ በዜግነቱ ጋናዊ ነው፡፡ ዘንድሮ በሊጉ ተወዳዳሪ በሆነው መብራት ኃይል  ክለብ በግብ ጠባቂነት በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ሱሌማን ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት በታዋቂ የሞዛምቢክ ክለብ ለ5 ዓመታት ተጫውቷል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የመጀመርያ ክለቡ ደደቢት የነበረ ሲሆን ለ6 ወራት ከተጫወተ በኋላ ኢትዮጵያን ለቅቆ በመውጣት በማልዲስ ለሚገኝ ክለብ ለ6 ወራት በመጫወት በኤሽያን ካፕ የመሳተፍ እድል ነበረው፡፡ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የተቀላቀለው መብራት ኃይልን ሲሆን የፈረመው ኮንትራት  ለ2 ዓመት ነው፡፡ በውድድር ዘመኑ መጀመርያ  ክለቡ የሲቲ ካፕ ዋንጫውን ማሸነፉ አስደሳች እንደሆነ የገለፀው ሱሌማን፤ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን የሚያነሳሳ ሲሆን  መነሻ እንደሚሆንና ከ1-5 ባለው ደረጃ ለመጨረስ ተስፋ ማድረጋቸውን ለስፖርት አድማስ አስተያየት ሰጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ገና የሁለት አመት ልምድ ያለው ግብ ጠባቂው ቀስ በቀስ እድገት እያሳየ የሚሄድበትን አቅጣጫዎች መታዘቡን ተናግሯል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንዳንድ የክለብ ተጨዋቾች የማልያ ቁጥራቸውን በየጊዜው መቀያየራቸው ልክ እንዳልሆነ ያመለከተው ሱሌማን፤ ማንኛውም ተጨዋች ውድድር ዘመኑ ሲጀመር የለበሰውን የማልያ ቁጥር ዓመቱን ሙሉ ሳይቀይር እንዲጫወት የሚያስገድድ መመርያ መኖር አለበት ብሏል፡፡ በተጨማሪም የሊጉን የፉክክር ደረጃ ለማሳደግ ጨዋታዎችን በዝርዝር በመዘገብ ሚዲያዎች ሽፋን መስጠት ይኖርባቸዋል ብሎ ይህ አሰራር ለውጭ ተጫዋቾቹ የመተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድቷል፡፡
“የኢትዮጵያ ሊግ ተሻሽሏል …”  
አዳሙ አህመድ ከጋና
ጋናዊ አዳሙ አህመድ   የመሀል ተከላካይ መስመር ላይ የሚጫወት ሲሆን ላለፉት 7 ዓመታት በኢትዮጵያ የክለብ እግር ኳስ ከፍተኛ ልምድ አካብቷል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት በጋና ፕሪሚየር ሊግ  ለ3 የተለያዩ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን በቱርክ ክለብ ለ1 ዓመት፣ በአልቤንያ ክለብ ለ6 ወራት፣ በእስራኤል ክለብ ለ6 ወራት የተጫወተበት ልምድ ነበረው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ ደደቢትን በመቀላቀል ለ6 ዓመታት የተጫወተ ሲሆን የፕሪሚየር ሊግ የሻምፒዮናነት ክብር ከማጣጣሙም በላይ፤ በሁለት የውድድር ዘመናት በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ እና በአንድ የውድድር ዘመን በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ በቅቷል፡፡
በደደቢት ክለብ የነበረውን ቆይታ ከጨረሰ በኋላ ወልዲያ ከነማን ተቀላቀለ፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በሱፐር ሊግ ስኬታማ የውድድር ዘመን ያሳለፈ ሲሆን   ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ እየተጫወተ ነው፡፡ ባለፉት 5 እና 6 ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በየውድድር ዘመኑ መሻሻል እየታየበት ነው በማለት ለስፖርት አድማስ አስተያየቱን የሰጠው አዳሙ፤ በተለይ ክለቦች የፋይናንስ አቅማቸውን በማጠናከርና የስፖርት መሰረተ ልማታቸውን በማሳደግ ላይ መሆናቸው የሚበረታታ እንደሆነም ጠቅሷል፡፡
‹‹ የተጨዋቾች ማጓጓዣ አውቶብሶች ደረጃን ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡››
 ጋብሬል አህመድ ከጋና
የ26 ዓመቱ ጋናዊ ጋብሬል አህመድ የአማካይ መስመር ተጨዋች ሲሆን በደደቢት ክለብ ለ3 ዓመታት በመጫወት አሳልፏል፡፡ ከደደቢት ክለብ ጋር 1 ጊዜ የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃ ሲሆን፤ በሁለት የውድድር ዘመናት ክለቡ በሁለተኛ ደረጃ ሊጉን ሲያጠናቅቅ አስተዋፅኦም ነበረው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ካለው ልምድ ባሻገር በስዊድን ክለብ ለ2 ዓመታት እንዲሁም በዴንማርክ ክለብ ለ5 ወራት ለመጫወት ችሏል፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የሚያስታውሰው አገር ትመስለው የነበረችው የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ከተማ መሆኗን መገንዘቡ አስገርሞት እንደነበር የሚያታውሰው ጋብሬል፤ ከእንግሊዘኛ ተናጋሪ አገር በመምጣቱ በቋንቋ በኩል ከቡድን አጋሮቹ ጋር በቀላሉ ለመግባባት ቸግሮትም ነበር። ሌላው የውጭ ተጨዋች ፈተና የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች ከመላመድ አንፃር ነውም ብሏል፡፡
ጋብሬል አሁን በተያዘው የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጨዋች ነው፡፡ ክለቡ በጣም ጥሩ አደረጃጀት እና ብቁ የአስተዳደር ሃላፊዎች ያሉበት፤ በልምምድ ሜዳ ደረጃ ያለውን መሰረተልማት ያሟላ በመሆኑ ደስተኛ ነው፡፡ የተጨዋቾች ማጓጓዣ አውቶብሶችን ደረጃ ማሻሻል እንደሚያፈልግ ግን ጠቁሟል፡፡ ክለቦች ለሌሎች የመሰረተልማቶች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ያህል ለተጨዋቾች ምቹ የሆኑ የትራስፖርት አገልግሎቶችን በማከናወን መስራት እንዳለባቸው ሲመክርም፤ የተጨዋቾች ማጓጓዣ አውቶብሶች በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በደደቢት ክለቦች እንደሚታየው ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ባሶች መሆን እንዳለባቸው፤ የክለቦችን ብራንድ የሚያስተዋውቁ ስለሆኑ በዚያ አቅጣጫ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በየዓመቱ ለውጥና መሻሻል እየታየበት ቢሆንም በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራት በኬንያ፤ በታንዛኒያ እና በሱዳን የሚታዩ እንቅስቃሴዎችን ለመስተካከል ጥረት መደረግ አለበት ብሎ ምክሩን የሚለግሰው ጋብሬል አህመድ፤ የኬንያ ሊግ በዲኤስቲቪ መተላለፉ የታንዛኒያ እና የሱዳን ሊጎች በስፖንሰርሺፕ መንቀሳቀሳቸው ጠቃሚ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ሲል ተናግሯል፡፡ በሌላ በኩል  መገናኛ ብዙሓናት ለውጭ አገር የሊግ ውድድሮች የሚሰጡት ሽፋን ለአገር ውስጥም ማድረግ እንዳለባቸው የጠቆመው ጋብሬል፤ በየትኛውም አገር ቅድሚያ የሚሰጥበትን አሰራር በኢትዮጵያም መተግበር ይገባል ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ የፕሪሚዬር ሊግ ደረጃ መሻሻል በአፍሪካ ደረጃ ለሚኖረው ተፎካካሪነት አስተዋፅኦ እንዳለው መታወቅ አለበት የሚለው ጋሬል አህመድ፤ የኢትዮጵያ ክለቦች በአፍሪካ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች እስከምድብ ድልድል ለመድረስ ከበቁ ከፍተኛ ስኬት ላይ መደረሱን ያረጋግጣል ብሏል፡፡
‹‹የውጭ ተጨዋቾች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ተቋቁመው ማለፍ አለባቸው››
ሳሙኤል ሳኑዊ ከናይጄርያ
ናይጄርያዊው ሳሙኤል ሳኑዊ በኢትዮጵያ የክለብ እግር ኳስ የ6 ዓመታት ልምድ ያለው ሲሆን፤ በትልልቅ ክለቦች በመጫወት ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ነው፡፡
በቤኒን ክለብ ልምድ የነበረው የ24 ዓመቱ የአጥቂ መስመር ተሰላፊ በኢትዮጵያ የመጀመርያ ክለቡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲሆን ለ2 የውድድር ዘመና በዚያ ክለብ ካሳለፈ በኋላ በቀጣይ ለ1 የውድድር ዘመን በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በመጫወት የሲቲ ካፕ እና የፕሪሚዬር ሊግ ሁለት ዋንጫዎችን መጎናፀፍ ችሏል፡፡ ከጊዮርጊስ በኋላ ያለፉትን ሁለት የውድድድር ዘመና በደደቢት ሲጫወት ያሳለፈ ሲሆን አሁን የሚገኝበት ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢነት ከፍተኛ ዝና ያለው ሳሙኤል ሳኑዊ ሊጉ በየዓመቱ በተለያያየ የፉክክር ደረጃ የሚቀያየር መሆኑን ገልፆ ከውጭ የሚመጡ ተጨዋቾች እግር ኳስ ሙያችን ነው ብለው ከተነሱ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ተቋቁመው ማለፍ እና ውጤታማ ለመሆን በትጋት መስራት አለባቸው ሲል ምክሩን ለስፖርት አድማስ ሰጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ እያገኘ ያለው ልምድ በቀጣይ የፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱን የማሳደግ ህልሙን እንደሚያጠናክርለት እምነት አለኝ የሚለው ሳሙኤል ሳኑዊ፤ እቅዱ ወደ አውሮፓ ክለብ ማቅናት እንደሆነና በተለይ አርሰናልን መቀላቀል ፍላጎቱ እንደሆነ  ተናግሯል።

Read 715 times