Sunday, 20 November 2016 00:00

ገራገር ወሬዎች - በአሜሪካ ምርጫ ዙሪያ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“ስፒል ጫማ ካደረገች ዝንጀሮ” እስከ “ትራምፕ ፊርማ”

         በአፍ ይጠፉ፣ በለፈለፉ
በዌስት ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የክሌይ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ቤቨርሊ ዋሊንግ እና ክሌይ ካውንቲ ኮርፖሬሽን የተባለ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ፓሜላ ቴለር፣ ከሰሞኑ የሚያጠፋቸውን አጉል ነገር በፌስቡክ ገጻቸው በኩል ለፈለፉ፡፡
መጀመሪያ...
“ስፒል ጫማ ያደረገች ዝንጀሮ!...” ሲሉ በገደምዳሜ ወረፏት ቴለር - የክቡር ፕሬዚዳንቱን ሚስት ሚሼል ኦባማን፡፡ ይሄን የፌስቡክ ዘለፋ ያነበቡት የከተማዋ ከንቲባ ዋሊንግም፣ ዘለፋውን የሚደግፍ አስተያየት ዝቅ ብለው አሰፈሩ፡፡
ዳይሬክተሯና ከንቲባዋ በቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ ላይ እንደዋዛ የሰነዘሩት ዘለፋ፣ በፍጥነት ከፌስቡክ ወደ መሬት ወርዶ አሜሪካውያንን ክፉኛ ያስቆጣ የዘረኝነት ንግግር ሆነ፡፡ ብዙዎች በዳይሬክተሯ ዘለፋና በከንቲባዋ ምላሽ በንዴት ጦፉ፡፡ የሁለቱ ሰዎች የዘረኝነት ፖስት ያስቆጣቸው አሜሪካውያን፣ በድረገጽ አማካይነት በጀመሩትና ሁለቱም ሴቶች ከስራቸው እንዲባረሩ በሚጠይቀው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ፣ ከ170 ሺህ በላይ ሰዎች ፊርማቸውን አሰፈሩ፡፡
ዳይሬክተሯ እና ከንቲባዋ በሁኔታው እጅግ ደነገጡ። ሁለቱም ያንን ጦሰኛ ጽሁፍ ከፌስቡክ ገጻቸው ላይ ቢሰርዙትም፣ ቀድሞ በሺህዎች ተባዝቶ ምድረ ፌስቡክን አዳርሶት ነበርና፣ እንዳሰቡት አላመለጡም፡፡ በርካታ አሜሪካውያን ክፉኛ ያብጠለጥሏቸው ያዙ፡፡
ዳይሬክተሯ ሊያስተባብሉ ሞከሩ፡፡
“ለማለት የፈለግሁት አልገባችሁም!... እኔ እኮ ስፒል ጫማ ያደረገች ዝንጀሮ ያልኩት ሚሼልን ሳይሆን...” በሚል የጀመሩትን ማስተባበያ የሚቀበላቸው አላገኙም፡፡
ከንቲባዋም ዘረኝነትን የማራመድ ሃሳብ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ ለሆነው ነገር ሁሉ ይቅርታ ቢጠይቁም፣ ጆሮ እሚሰጣቸው አልተገኘም፡፡
በስተመጨረሻም...
ከንቲባዋ ባለፈው ሰኞ በገዛ ፈቃዳቸው ስራ መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለከተማዋ ምክር ቤት አስገቡ፡፡ ዳይሬክተሯም ከስራ መባረራቸውን የሚገልጽ አስደንጋጭ ደብዳቤ ደረሳቸው - ይላል ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ፡፡
የራሷ ሲያርባት የሰው ያማሰለቺው ቱርክ
መንበረ መንግስቴን ለመንጠቅ አሲራችኋል በሚል ከመቶ ሺህ በላይ ዜጎቿን ከስራ በማባረር፣ ... ሺህ ያህሉን በጅምላ እያፈሰች ወደ ወህኒ በመወርወር፣ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማዋከብ የአለም መነጋገሪያ የሆነቺው ቱርክ፤ የራሷን ጉዳይ መላ መምታት ትታ፣ ወደ አሜሪካ ዞር አለችና የሰሞኑ ተቃውሞ ያሰጋኛል አለች፡፡
ዘ ኢንዲፔንደንት ማክሰኞ እንደዘገበው፣ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎቿን ማሰርና መግደል የማይታክታት ቱርክ፣ በትራምፕ ላይ የተጀመረው ተቃውሞ ሊባባስ ይችላልና አደራችሁን ወደዚያ ድርሽ እንዳትሉ ስትል ዜጎቿን አስጠንቅቃለች። አሜሪካ በቱርክ መዲና ኢስታምቡል የሚገኙ የቆንስላ ሰራተኞች የሆኑ ዜጎቿን፣ የሽብር ጥቃት ሰለባ እንዳትሆኑ ወደ አገራችሁ ተመለሱ ስትል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቋን ያስታወሰው ዘገባው፣ የቱርክ መንግስትም ለአሜሪካ ምላሽ ለመስጠት፣ ወግ ደርሶት ለዜጎቹ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ማስተላለፉን ገልጧል። የቱርክ መንግስት ከሰሞኑ ባወጣው በዚህ መግለጫ፣ በአሜሪካ የሚገኙና ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ያቀዱ ዜጎቹን፣ የጸረ-ትራምፕ ተቃውሞው ሰለባ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ ማለቱንም አስረድቷል፡፡
የትራምፕ ፊርማ ሲነበብ
“የስልጣን ጥም ያንገበገባቸው ሰው ናቸው!...” አለች ትሬሲ፡፡
እንግሊዛዊቷ ትሬሲ ትሩሴል፣ ስለ ዶናልድ ትራምፕ ነው እንዲህ በእርግጠኝነት ያወራቺው፡፡
ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው፣የብሪቲሽ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ግራፎሎጂስትስ ባልደረባ የሆነቺው ትሬሲ ትሩሴል፣ ከሰሞኑ በአነጋጋሪው ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባህሪ ላይ ጥናት ድርጋለች። እሷና ባልደረቦቿ እንደሚያደርጉት፣ ጥናቷን የሰራቺው በትራምፕ የእጅ ጽሁፍ እና ፊርማ ላይ ነበር። የትራምፕን ፊርማ እና የእጅ ጽሁፍ አጣጣል በትኩረት ስታጤን የሰነበተቺው ትሬሲ፣ ከሰሞኑ ብቅ አለቺና እንዲህ አለች...
“ፊርማቸውን ልብ ብዬ ሳጤነው፣ ትራምፕ የስልጣን ጥም የሚያንገበግባቸው ሰው እንደሆኑ አረጋግጫለሁ!...”
እንዲህ ብላም አላበቃችም፡፡
የማይጨበጥ ምኞት የሚያጠቃቸው ትራምፕ፣ ምንም እንኳን ሃይለኝነት ቢጠናወታቸውም በተለይ ለቤተሰባቸው ጥላ ከለላ መሆን የሚያስደስታቸው ሰው እንደሆኑ ከፊርማቸው መረዳት መቻሏን ተናግራለች፡፡ እምብዛም ሌሎችን እንደማያደምጡና በድርድር ወቅት ፈርጠም ማለት የሚቀናቸው እንደሆኑም ገልጻለች፡፡
ዙክበርግ እንደ ጲላጦስ
ቀጣዩዋ የአሜሪካ መሪ እንደሚሆኑ ብዙዎች በልበ ሙሉነት ቢናገሩላቸውም ያልተሳካላቸው ሄላሪ ክሊንተን፣ ባልታሰበ መልኩ ለመሸነፋቸውና ያልተጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ ለመመረጣቸው ብዙ ምክንያቶች መጠቀሳቸው እንደቀጠለ ነው፡፡
ሁሉም የየራሱን ሰበብ ሲሰነዝር ታዲያ፣ ለሄላሪ መሸነፍ ምክንያቱ ፌስቡክ ነው የሚሉም አልታጡም፡፡
በርካታ አሜሪካውያን ፌስቡክ ትራምፕ እንዲመረጥ የራሱን ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለው እንደሚያስቡ የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፣ በሄላሪ ዙሪያ ያልተጨበጡ አሉባልታዎችን በማናፈስ ተወዳጅነቷን ቀንሶታል በሚል ፌስቡክን ማብጠልጠል የያዙ እንደበረከቱ ገልጧል፡፡
ምርጫው ጥቂት ቀናት ሲቀሩት፣ በፌስቡክ ከ560 ሺህ ጊዜ በላይ ሼር የተደረገውንና የሄላሪን የኢሜል ቅሌት ሚስጥር ያወጣው የኤፍቢአይ መርማሪ ሞቶ እንደተገኘ ዘ ዴንቨር ጋርዲያን ዘገበ የሚለውን ጽሁፍ ለአብነት የሚጠቅሱት እነዚህ አሜሪካውያን፣ ቆየት ብሎ ግን ዘ ዴንቨር ጋርዲያን የተባለ ጋዜጣ እንደሌለ መረጋገጡንና መረጃው ሄላሪን ለማጥላላት ሆን ተብሎ የተሰራጨ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
ለትራምፕ ድል እና ለሄላሪ ሽንፈት ምክንያት ሆኗል በሚል ፌስቡክን የሚወነጅሉ መበራከታቸውን ተከትሎ ታዲያ፣ የኩባንያው መስራችና ባለቤት ማርክ ዙክበርግ፣ ከሰሞኑ አደባባይ ወጥቶ እንደ ጲላጦስ “ከደሙ ንጹህ ነኝ” ሲል በይፋ ማስተባበሉን ዘገባው ገልጧል፡፡
“ፌስቡክ ትራምፕ እንዲያሸንፍ ረድቶታል ብሎ መናገር የማይመስል ነገር ነው!... ሰዎች ለማን ድምጻቸውን እንደሚሰጡ የሚወስኑት፣ ተጨባጭ የህይወት ልምዳቸውን መሰረት አድርገው ነው!...” ብሏል ዙክበርግ፡፡
ትራምፕ እና ሂትለር ምን እና ምን ናቸው?...
ታሪካዊው ምርጫ፣ በታሪክ መምህሩ ታሪክ ላይ የራሱን አሻራ ጣለ ይላል፤ ዘ ቴሌግራፍ፡፡
የዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ፣ ላለፉት 40 አመታት በካሊፎርኒያው ማውንቴን ቪው አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተግተው ታሪክ ባስተማሩት መምህር ፍራንክ ናቫሮ ላይ በተለየ መልኩ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንደፈጠረ ዘገባው ያስረዳል፡፡ መምህሩ ሰሞኑንም እንደወትሯቸው ታሪክ ሊያስተምሩ ወደ ክፍል ገቡ፡፡
ማስተማርም ጀመሩ፡፡ በመሃል ላይ ግን፣ የሚያስተምሩትን ርዕሰ ጉዳይ በምሳሌ ማስደገፍ ነበረባቸው፡፡ ምሳሌ ፈለጉ። አገኙ። እንደዋዛ ጉዳያቸውን በምሳሌያቸው እያዋዙ ለደቀመዝሙራናቸው ማስረዳት ቀጠሉ፡፡
የዕለቱ የታሪክ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ተጠናቀቀና፣ መምህር ናቫሮ ተማሪዎቻቸውን ተሰናብተው ከክፍል ወጡ፡፡
ከቀናት በኋላ...
እኒሁ መምህር ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው። የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ከተማሪዎች ወላጆች ቅሬታ እንደቀረበባቸው ነገራቸው፡፡ የቅሬታውን ሰበብ ለማወቅ ጓጉተው ሲጠይቁ ታዲያ፣ ከቀናት በፊት ሲያስተምሩ የሰጡት ምሳሌ መሆኑ ተነገራቸው፡፡ ደንግጠው ሊያስታውሱ ሞከሩ፡፡
እውነት ነው፡፡ መምህሩ በዕለቱ ታሪክ ሲያስተምሩ በሰጡት ጦሰኛ ምሳሌ፣ ተመራጩን ዶናልድ ትራምፕ እና የናዚውን ጨፍጫፊ አዶልፍ ሂትለርን እያነጻጸሩ ሲያስተምሩ ነበር። ሁለቱም በምርጫ ለማሸነፍ ባደረጓቸው ቅስቀሳዎች ለአናሳዎች ያላቸውን አመለካከትና የዘረኝነት መንፈሳቸውን ማንጸባረቃቸው እንደሚያመሳስላቸው፤ ሁለቱም ዳግም ታላቅ ስለማድረግ ቃል መግባታቸው አንድ እንደሚያደርጋቸው ለተማሪዎቻቸው አስረድተው ነበር፡፡
በመሆኑም ትራምፕን ከሂትለር ጋር ማመሳሰል አግባብ አይደለም በሚል ተወነጀሉ፤ መምህሩ፡፡
“እኔ የፈለግኩት እንኳን፣ የ20ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን ታሪክና አሁን እየሆነ ያለውን ታሪክ ለማስተሳሰር እንጂ ታላቁን መሪያችንን ከዚያ ሰው በላ ጋር ለማመሳሰል አልነበረም!...” በማለት የልባቸውን ተናግረው ለማስተባበል ሞከሩ፡፡
የሚሰማቸው አልተገኘም - “ላልተወሰነ ጊዜ ከስራ ታግደሃል!...” ተባሉ፡፡
ይህን የሰሙ ከ30 ሺህ በላይ አሜሪካውያን ባሰባሰቡት ፊርማ፣ መምህሩ ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ስራቸው እንዲመለሱ የትምህርት ቤቱን አስተዳደር መጠየቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ከቀናት እገዳ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ እንደተፈቀደላቸው ገልጧል፡፡

Read 3683 times