Sunday, 20 November 2016 00:00

ኢትዮጵያ የአለም የፖስታ ህብረት ጉባኤን እንድታዘጋጅተመረጠች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ የአለም ፖስታ ህብረት ልዩ ጉባኤ እንድታዘጋጅ የተመረጠች ሲሆን ከ1 ሣምንት በላይ በሚዘልቀው ጉባኤ ከ3 ሺህ በላይ እንግዶች ከዓለም ዙሪያ እንደሚሳተፉ  ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግደይ ገ/ዮሐንስ ከትላንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በቅርቡ በቱርክ በተካሄደው 26ኛው የአለም የፖስታ ህብረት ኮንግረስ ላይ ኢትዮጵያ ከ2 አመት በኋላ የሚደረገውን የህብረቱን ልዩ ጉባኤ እንድታዘጋጅ በከፍተኛ ድምፅ መመረጧን አስታውቀዋል፡፡
ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ የሃገሪቱን ገፅታ ለመገንባት፣ ሃገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ፣ በአለማቀፍ ቱሪዝም አገሪቱን ለማስተዋወቅ ሃገሪቱ በፖስታ አገልግሎት ያላትን አቅም ለዓለም ለማሳየት ይጠቅማል ተብሏል፡፡
በጉባኤው ላይ ከ192 አባል ሃገራት የተውጣጡ የፖስታ አገልግሎት ሚኒስትሮች፣ ዋና ዳይሬክተሮች፣ የፖስታ ኤክስፐርቶች፣ ታዛቢዎች፣  አለማቀፍ ተቋማትና ህብረቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በፖስታ አገልግሎት ኢትዮጵያ 4 አለማቀፍ እውቅናዎች ማግኘቷን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ በአገልግሎት ጥራት የ ‹‹ቢ›› ደረጃ ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡
በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት 16 ሺህ ያህል የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ለመክፈት እየተንቀሣቀሰ መሆኑን የጠቀሡት አቶ ግደይ፤ በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥም ለግለሰብ ደንበኞች የቤት ለቤት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ድርጅቱ አምና ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱንና በዘንድሮ ዓመትም ወደ 1.2 ቢሊዮን ብር ገደማ ብር ለማግኘት ማቀዱን ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ የፖስታ ድርጅት ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎችን ለመወዳደር የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመው፤ በየአመቱም ገቢውን በከፍተኛ መጠን እያሣደገ ለመጓዝ እንዳቀደ ተናግረዋል፤ አቶ ግደይ፡፡

Read 1474 times