Sunday, 20 November 2016 00:00

ሕብረት ባንክ ባለፈው ዓመት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከታክስ በፊት ከ428 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ
       ሕብረት ባንክ ያለፈው ዓመት 2008 (ጁን 30 2016) የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአገሪቱ ላሉ ባንኮች ፈታኝ ሆኖ ቢያልፍም፣ ባንኩ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 13.63 ቢሊዮን ብር በማድረስ ከግል ባንኮች 4ኛ ደረጃ ሊይዝ መቻሉን አስታውቋል፡፡
ባንኩ የባለ አክሲዮኖች 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከትናንት በስቲያ በሂልተን ሆቴል ያደረገ ሲሆን የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ ዛፉ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ ከቀደመው ዓመት  ጋር ሲነፃፀር 25 በመቶ ዕድገት ማሳየቱና፣ ከግብር በፊት የተኘው ትርፍም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 358.2 ሚሊዮን ብር ጋር ሲተያይ ወደ 428.5 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ከቀደመው ዓመት (2007) ከነበረው 11.7 ቢሊዮን ብር 16.2 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 13.63 ቢሊዮን ብር መድረሱን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፣ በብድር የተሰጠው ገንዘብ ከቀደመው  ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ1.7 ቢሊዮን ብር ወይም የ24.4 በመቶ ዕድገት በማሳየት 8.53 ቢሊዮን ብር በመድረሱ የተገኘው ውጤት አመርቂ ነው ብለዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአገሪቷ ወጪ ንግድ በመቀነሱ ከዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት ዘርፍ የተገኘው ገቢ ከካቻምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ ቀንሷል፡፡ አምና ከዓለም አቀፍ ባንክ ዘርፍ የተገኘው ገቢ 2.98 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የበጀት ዓመቱ 4.71 በመቶ ቀንሶ 2.84 ቢሊዮን ዶላር ወይም 400.9 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህም የባንኩን አጠቃላይ ገቢ 23 በመቶ እንደሚሸፍን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አያደር ሲብስበት እንጂ ሲሻሻል የማይታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለሥራቸው እንቅስቃሴ ስጋት መፍጠሩን የጠቀሱት አቶ ዛፉ፤ ስጋቱን ግምት ውስጥ በማስገባት ከዚህ በፊት ከነበረው በተጨማሪ ከሁለት ዓለም አቀፍ የካርድ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማለትም ከቪዛ ኢንተርናሽናልና ከቻይና ዩኒየን ፔይ ጋር መሥራት ጀምረናል፡፡ የእነዚህ ድርጅቶች የባንኩ አጋር መሆን ለንግድ ተጓዦችና ቱሪስቶች የምናቀርበውን አገልግሎት ምቹና ቀልጣፋ ከማድረጉም በላይ የውጭ ምንዛሬ ከማሳደግ አኳያ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ባንኩ ጁን 30 2016 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ በተከፈለ አክሲዮን ላይ 25 በመቶ የትርፍ ክፍያ አንዲደረግ የዲሬክተሮች ቦርድ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 17.3 ቢሊዮን፤ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል 1.25 ቢሊዮን ብር ሲሆን ባንኩ 2,998 ባለአክሲዮኖች እንዳሉት ታውቋል፡፡
ተደራሽነትን ከማስፋፋት አኳያ ባንኩ 161 ቅርንጫፎች ሲኖሩት፣ የሰው ኃይሉም 3,123 ደርሷል፡፡ በበጀት ዓመቱ 438 ሠራተኞ የተቀጠሩ ሲሆን ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ በ289 ሰራተኞች ብልጫ አለው፡፡ 149 ሠራተኞች ደግሞ ባንኩን ለቀዋል፡፡

Read 1940 times