Sunday, 20 November 2016 00:00

አቢሲኒያ ባንክ ከ487 ሚ. ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ አገኘ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

 - ጠቅላላ ካፒታሉን ወደ 4 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ
            - ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች 500 ሺህ ብር ሰጠ

      አቢሲኒያ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ ያልተጣራ 487.23 ሚ. ብር ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው 2007 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር የ113.27 ሚ. ብር ወይም የ30.28 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
ባንኩ፣ የዛሬ ሳምንት በሂልተን ሆቴል ባደረገው 20ኛው የባለ አክሲዮኖች መደበኛና 11ኛው አስቸኳይ ጉባኤ፣ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሰረት ታዬ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ አቢሲኒያ በ2008 ዓ.ም ባደረገው ከፍተኛ ጥረት፣ ግብርና አስፈላጊ ወጪዎች ከተቀነሱ በኋላ 374.78 ሚ. ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በባንኩ 11ኛው ድንገተኛ ጉባኤ የዲሬክተሮች ቦርድ የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል 4 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ባለአክሲዮኖች በሙሉ ድምፅ መቀበላቸውን፣ እንዲሁም የዲሬክተሮች ቦርድ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ በየጊዜው ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በዓመቱ ካገኘው ትርፍ ግማሽ ሚሊዮን ብር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲሰጥ መወሰኑን የባንኩ የገበያ የኮሙኒኬሽንና የኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ አስቻለው ታምሩ ገልፀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ 13.63 ቢ. ብር መድረሱን የጠቀሱት የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ2.52 ቢ. ብር ወይም የ22.6 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ካቻምና 478 ሺህ የነበረው የገንዘብ አስቀማጮች ቁጥር በ108ሺህ ጨምሮ 586 ሺህ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኩ የብድርና ቅድሚያ ክፍያዎች መጠን ወደ 8 ቢ. ብር ያደገ ሲሆን ከካቻምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ2.1 ቢ. ብር ወይም የ35 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል፡፡ ይህም ከፍተኛ ዕድገት ሊገኝ የቻለው በጊዜ ገደብ የተሰጠ ብድር 1.56 ቢ. ብር ወይም 38.7 በመቶ፣ ኦቨርድራፍት ብድር 108 ሚ. ብር ወይም 8.1 በመቶ፣ እንዲሁም የቅድሚያ ክፍያ ብድር 48.3 ሚ. ብር ወይም 80.8 በመቶ በማደጉ እንደሆነ አቶ መሰረት ገልጸዋል፡፡
ከስምንት ስመ-ጥር ገንዘብ አስተላላፊዎች ጋር እንደሚሰሩ፣ ባለፈው ዓመት ደግሞ ከሌሎች ሁለት አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር መፈራረማቸውን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፤ ከወጪ ንግድ ከዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊዎችና ከውጭ ምንዛሬ ግዢ የተገኘው ዶላር፣ ከዚህ በፊት ከነበረው ትልቅ እመርታ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ የባንኩ የውጭ ምንዛሬ መጠን 7.3 ቢ. ብር መድረሱን፣ ይህም ከካቻምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ2.3 ቢ፣ ብር ወይም የ45.7 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 1.74 ቢ. ብር መድረሱንና ከካቻምናው ጋር ሲነፃፀር የ468 ሚ. ብር ወይም የ37 በመቶ ብልጫ እንዳለው፣ ጠቅላላ ወጪው ደግሞ 1.26 ቢ. ብር መሆኑንና ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ354.9 ሚ. ብር ወይም የ39.33 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል 2.1 ቢ. የደረሰ ሲሆን ይህም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የ314 ሚ. ብር ወይም የ17.3 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን፤ የተከፈለ ካፒታል ከአምናው 155 ሚ. ወይም 13.8 በመቶ ብልጫ በማሳየት፣ 1.27 ቢ. ብር መድረሱን አመልክተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከተገኘው 347.78 ሚ. የተጣራ ትርፍ ውስጥ ሕጋዊ መጠባበቂያ 93.94 ሚ. ብር እንዲሁም የዲሬክተሮች ቦርድ ዓመታዊ ክፍያ 450 ሺህ ብር ከተቀነሰ በኋላ ቀሪው 280.63 ሚ. ብር ባለአክሲዮኖች ባላቸው ድርሻ እንዲከፋፈል፣ 100 ብር ዋጋ ያለው አንድ የአክሲዮን ዕጣ የትርፍ ክፍያ 31.45 ብር መሆኑ ታውቋል፡፡
የሰራተኞች ቁጥር 4,144 ሲሆን ከዚህ ውስጥ ሴቶች 36.3 በመቶ ድርሻ ያላቸው መሆኑ፣ ሲሆን በበጀት ዓመቱ 53 አዳዲስ ቅርንጫፎች ተከፍተው፣ ቁጥሩ ወደ 185 ማደጉና ዘንድሮና በሚቀጥለው ዓመት የቅርንጫፎችን ቁጥር 220 ለማድረስ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Read 1453 times