Sunday, 20 November 2016 00:00

“ዶ/ር... ቁልፉን መልሰሽ መቆለፍ እንዳትረሺ”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(4 votes)

 ትንሽ ዘግየት ብሎአል። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በተለይም የሴት ልጅ ብልት ግርዛትትልተላ ን በሚመለከት አንድ አለም አቀፋዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዶ ነበር። በጊዜው ሴት ልጆች የመገረዛቸውን አስከፊ ገጽታ ለማሳየት በርከት ያሉ ሳይንሳዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን በተግ ባርም ድርጊቱ ምን እንደሚመስል በቪድዮ ታይቶ ነበር። የዚህ አምድ አዘጋጅ ትውስታ እጅግ ዘግናኝ መሆኑ እና ተሰብሳቢዎቹም ይሰጡ የነበረው አስተያየት የሚረሳ አይደለም።
 “...ድርጊቱ የተፈጸመው በኢትዮጵያ በሱማሌ ክልል ነው። አንዲት ሴት ልጅ የመረረ ልቅሶ እና ዋይታ እያሰማች እግርዋ እንዳይገናኝ ተደርጎ የመንደሩ ገራዥ የተባሉ ሴት መቁረጫቸውን ይዘው ወደብልትዋ ቀረቡ። ወዲያውም ልጅቱ ደም በደም ሆነች። ሴትየዋም ስራቸው ከባድ ነው መሰል... ቶሎ አልለቀቅዋትም። ልጅቱ ከታች ደም በደም ከላይ ደግሞ በላብ ተዘፍቃ ትንፋሽዋ ቁርጥ ቁርጥ ብሎ አይንዋ ብቻ ነበር ደም ለብሶ የሚጉረጠረጠው። ከዚያ በሁዋላ ቪድዮው መታየቱን አልቀጠለም።”
ወዲያውኑ ብዙ ተሰብሳቢዎች በተለይም ነጮቹ አዳራሹን ጥለው ነበር የወጡት። ግማሾቹ ነፋስ ለማግኘት ስለጨነቃቸው ...ግማሾቹ ደግሞ እንባቸውን ይጠራርጉ ነበር። ከአዳራሹ ተከትላ የወጣችው የዚህ አምድ አዘጋጅ ጥያቄዎችዋን አቀረበች። እነዚህ ተሰብሳቢዎች ከሰጡአቸው መልሶች ጥቂቱ የሚከተለው ነበር።
 መ/1/ ምን አይነት አረመኔያዊ ድርጊት ነው? ይህንን ዝም ብሎ መመልከት ይቻላል አንዴ?
 መ/2/ እኔን የገረመኝ እናትየው አብራ ቆማ ልጅዋን በስለት ማስቆረጥዋ ነው። ይህች ምን እናት ነች? ጨካኝ እንጂ...
 መ/3/ የልጅቱ አባትኮ ምንም ጎጂ ነገር እንዳልተፈጸመ ሁሉ ገራዥዋን ሴት ሲሸኝ ነበር። በጣም ነው የሚገርመው...ወዘተ...
ይህ ድርጊት ምናልባትም ወደ ሀያ አመት ይሆነዋል። በጊዜውም በዚህ ይብቃ የሚል ስሜት የነበረው ይህ ስብሰባ ሲዘጋ በየሀገራቱ ያሉት በጊዜው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አስወጋጅ ይባሉ የነበሩት ቢሮዎች ብዙ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ብዙ ስራዎችን የሰሩ ቢሆንም ዛሬም ስለ ሴት ልጅ ግርዛትብልት ትልተላ ማውራት ግን አልቀረም። ድርጊቱ አልተወገደም።
ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት መምህርት እና ዶ/ር ሽፈራው ነጋሽ ተባባሪ ፕሮፌሰር የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት መምህር ለዚህ አምድ በስራቸው አጋጣሚ የተመለከቱትን ያብራራሉ። በቅድሚያም የዶ/ር ማህሌትን እናስነብባችሁ።
“...ጊዜው ትንሽ ቆየት ብሎአል። እኔም የጠቅላላ ሐኪም ነበርኩ። አንዲት እናት በምጥ ተይዛ ከወደሐረር እኔ ወደነበርኩበት ሆስፒታል መጣች። በጊዜው ላዋልዳት ስዘጋጅ አንድ አዲስ ነገር ተመለከትኩ። ብልትዋ ከወርቅ በተሰራ በተንጠልጣይ ቁልፍ ተቆልፎአል። የልጁ ፀጉር ከቁልፉ ጀርባ ታያል። ሊወለድ ደርሶአል። ሴትየዋ ምጥ ስለያዛት ትገፋለች። ትጮሃለች። በሁዋላም ይሄ ነገር ምን ድነው? እንዴት ነው የሚከፈተው? ወይንስ ቁልፉ የገባበትን ቦታ ብልትሽን በኦፕራሲዮን እንክፈተው? ስላት...ሴትየዋ...አ...አ...ይ ቁልፍ አለው ...ባለቤን ጠይቁት አለች። እራሴ ወደኮሪደር ወጥቼ ሁኔታውን አስረዳሁዋቸው። ባልተቤትዋም ...በጣም በኩራት... ከደረት ኪሳቸው ውስጥ የቁልፉን መክፈቻ አውጥተው ሰጡኝ። ከዚያም ተቀብዬ አቸው ስመለስ...ስሚ ዶ/ር አሉኝ... ሳዳምጣቸውም ካዋለድሻት በሁዋላ ቁልፉን መልሰሽ መቆለፍ እንዳትረሺ ...አሉኝ ። ሐኪሞቹ በጣም ነው የተገረምነው። እኛ ግን ያደረግነው ካዋለድናት በሁዋላ ቁልፉን ከነመ ቆለፊያው ለወላድዋ ለእራስዋ ነው የሰጠናት። ምክንያቱም ሴቶች ሲወልዱ ምን ያህል ሰውነ ታቸው እንደሚቆጣ እንዲሁም ፈሳሽ የሚበዛበት ስለሆነ ለኢንፌክሽን በጣም የተጋለጠ ነው። ስለዚህም ለሴትየዋና ቤተሰብዋ ከስድስት ሳምንት በፊት ምንም እንዳያደርጉ እና ከወሊድ በሁዋላ ወደሐኪም ቀርበው ከታዩ በሁዋላ የሚወሰን እንደሆነ ነገርናቸው። በዚያውም ባልተቤት የውንም ሆነ ወላድዋን በትዳር ተማምነው አብረው ያሉ ሰዎች ሆነው ሳለ ባልየው የሚስት የውን ብልት በቁልፍ ዘግቶ መክፈቻውን ይዞ መንቀሳቀስ ምን ያህል ትዳርን አለማክበር መሆ ኑን ለማስረዳት ሞክረናል። ምክንያቱም ትዳር የመግባባት ፣የመተማመን ፣የመፋቀር ፣ኃላፊ ነትን የመወጣት ድርሻ ያለው ስለሆነ ያንን ሁሉ ዘንግቶ አልፎ ተርፎ ብልትን በተን ጠልጣይ ቁልፍ መቆለፍ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አልነበረም። ስለዚህም እኔ በወቅቱ የተረዳሁት... የአመለካከት ችግር መኖሩን...ሴትየዋ ምን ያህል በባልዋ ቁጥጥር ስር እንደሆነች ...ሰውየው ሚስታቸው ብልት ላይ የወርቅ ቁልፍ በማንጠልጠላቸው ኩራት የሚሰጣቸው መሆኑን ...የበላይነታቸውን በሚስታቸው ላይ ማረጋገጥ መቻላቸውን የሚያሳይ ድርጊት ነበር። ሰውየውን በምናነጋግርበት ወቅት ያገኘነው መልስ ይሄ ባህላችን ነው...የሚል ነበር።”
 ///////
በተከታይነት የምናስነብባችሁ የዶ/ር ሽፈራው ነጋሽን የሴት ልጅ ግርዛት የስራ አጋጥሚ ነው።
በህክምና አለም እያለሁ ከሴት ልጆች እና ሴቶች ግርዛት ጋር በተያያዘ በጣም ብዙ ገጠመኞች አሉኝ። ነገር ግን ከዘ ውስጥ በጣም የማልረሳው በአንዲት ሴት ላይ የተፈጸመውን ድርጊት ነው። በማለት ነበር ዶ/ር ሽፈራው ወደ ትውስታቸው የገቡት።
“...እኔ ያጋጠመኝ ምናልባትም በመጽሐፎች ከተጻፈው በላይ ሆኖ ስላገኘሁት ሁልጊዜም በምሳሌነት ለተማሪዎቼ የምገልጸው ነው። እድሜዋ በግምት ወደ ሀያ አመት የሚሆን በአፋር አካባቢ የምትኖር ሴት ነች። ባለትዳር ናት። ነገር ግን በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ የህመም ችግር ያለባት ሲሆን እርግዝናም አልሞከራት። ስለዚህም ከአፋር ክልል ሪፈራል ተሰጥቶአት ወደጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነበር የመጣችው። ምርመራ በምናደርግበት ወቅትም ያጋጠመን ነገር እጅግ የሚገርም ነው። ብልትዋ ሙሉ በሙሉ ዝግ ነበር። ይህች ሴት የወር አበባዋን በጣም ትንሽ በሆነ ቀዳዳ የምታይ ነች። የተተወላት ክፍተት የግብረስጋ ግንኙነት ለማድረግ ግን ፈጽሞ የማያስችላት ነው። ይህች ሴት ኦፕራሲዮን ከመደረግ ውጭ ሌላ ምንም አማራጭ አልነበ ራትም። ስለሆነም አብሮኝ ከነበረ ሲኒየር ሐኪም ጋር በመሆን በጣም ከበድ ያለ ኦፕራሲዮን እንደተሰራላት አስታውሳለሁ። ከኦፕራሲዮኑም በሁዋላ ምናልባትም ክፍተቱ ተፈጥሮአዊ መጠኑን እንዲይዝ ስለተደረገ የወር አበባ እንደልብ እንዲፈስና በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት ሕመም እንዳይሰማት ከማድረግ ውጪ ለእርግዝና የሚያስችላት ሁኔታ ግን መፍጠር አል ተቻለም። ይህች ሴት ባሳለፈቻቸው ችግሮችና ዘላቂ በሆነውም ልጅ ማርገዝ አለመቻል እን ዲሁም የወሲብ ስሜት የሌላት በመሆኑ እራስዋን ከሌሎች ሴቶች ዝቅ አድርጋ መመልከት ታዘወትር ነበር። በትዳር ሕይወትዋም ለመቀጠል ጥርጣሬ ያላት ሲሆን በህብረተሰቡም ዘንድ ልጅ ባለ መውለድዋ ስለምትናቅ እኔ.. ሴት የምታሟላውን ነገር አላሟላም የሚል ሀሳብ እንደሚኖራት የታወቀ ነው። ሌሎችም በርካታ ሴቶች ወደሆስፒታላችን መጥተው እርዳታ ተደርጎላቸዋል። ብዙ ጊዜ የብልት ትልተላው በሚፈጸምባቸው ወቅት መንገድ ማጥበብ የሚሉት አሰራር አላቸው። ስለዚህም ወደ ትዳር አለም በሚገቡበት ጊዜ የግብረስጋ ግንኙነት ለማድረግ በጣም ይቸገራሉ። እንደነዚህ አይነት ሴቶች ሲመጡ በተለይም ከባሎቻቸው ጋር በመነጋገር የማስተካከል ስራ የተሰራላቸው ብዙ ናቸው። ከዚህ ውጪ በተለይም እርግዝና ተከስቶ ለመውለድ በምጥ ከተያዙ በሁዋላ ወደሆስፒታል ሲመጡ ብልታቸው ዝግ ስለሆነ ያንን ኦፕራሲዮን አድርገን ልጁን ለማዋለድ በሚደረገው ጥረት በርካታ እናቶች ልጆቻቸውን ያጡ ነበር። ምክንያቱም በነበሩበት ቦታ በምጥ ተይዘው የሚቆዩ ስለሆነ ልጃቸው ታፍኖ የሚሞት በርካታ እናቶች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ልጁን ለማዋለድ ሲባል በኦፕራሲዮን ብልታቸው ሲከፈት የሚፈሰው ደም ብዙ ስለሆነ ሴቶቹ ጉዳት ላይ የሚወድቁበትን አጋጣሚም አስተውዬአለሁ። ከዚህም በተጨማሪ በተፈጸመባቸው ትልተላ ምክንያት የማህጸን መንገድና የሽንት ፊኛ መንገድ ተገናኝቶ የመጡ እናቶች አጋጥመውኛል። በአጠቃላይም ይህ የሴት ልጅ ግርዛት ስብእናን የሚነካ ተፈጥሮአዊ እና ሰብአዊ መብትን የሚጋፋ ምንም የህክምና ባህርይ የሌለው ጎጂ ነገር መሆኑን አለም የሚስማማበት ይመስለኛል። “
ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የሴት ልጅ ግርዛት የሚለውን ቃል መጠቀም የለብንም ...ምክንያቱም ግርዛት ለበጎ ነገር የሚውል የህክምና ስርአትን ጠብቆ የሚደረግ ነገር መገለጫ ቃል ነው ብለዋል። እንደዶ/ር ማህሌት ማብራሪያ ግርዛት የሚለው ቃል ይህ የሴት ልጅ ብልት ትልተላ እስከአሁን ድረስ እንዲቆይ ሽፋን የሆነው ይመስላል ብለዋል። ዶ/ር ሽፈራው ነጋሽም ግርዛት የሚለው ለድርጊቱ ትክክለኛ መገለጫው አይደለም። ግርዛት ለበጎ ድርጊት የምንጠቀምበት ቃል ሆኖ ሳለ ይህ ሴቶችን በእጅጉ የሚገዳ እና ሰብአዊ መብታቸውን የሚጥስ የብልት ትልተላ በግርዛት መገለጽ አይችልም ነበር ያሉት።
ዶ/ር ማህሌት አክለውም ይህ ድርጊት ማህበራዊ ሽፋን ሊሰጠው አይገባም። የሴት ልጆችን ገላ አለአግባብ እየቆራረጡ ከጥቅም ውጭ ማድረግ በሕግ ሊያስጠይቅ ይገባል። አንድ ሰው እጁን ወይንም አይኑን ወይንም ሌላ አካሉን እንደዚህ አይነት ድርጊት ይፈጸምብህ ቢባል አይስማ ማም። እሱም ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡም አይቀበለውም። ታዲያ ሴቶች ተፈጥሮአዊ አካላቸውን ሲያጡ ለምን በዝምታ እንመለከታለን? ሲሉ ጠይቀዋል።
ዶ/ር ሽፈራው ነጋሽ በበኩላቸው ይህ በሴት ልጅ ብልት ላይ የሚደርሰው ትልተላ ለሴት ልጆች ጥቅምን የማይሰጥና ጉዳት ብቻ የሚያስከትል ድርጊት መሆኑን አለምአቀፍ ህብረተሰብ ይስማማ በታል። በዚህ ድርጊት የሚከሰተው ችግር ሰፋ ያለና በጊዜ የተከፋፈለ ነው። ወዲያው ትልተ ላው ሲፈጸምባቸው፣ ወደትዳር አለም ሲገቡ እና ልጅ በመውለድ ጊዜ እንዲሁም በዘለቄታው ሕይወታቸው የሚደርስባቸው የስነልቡና ጫና ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መግለጽ ይቻላል ብለዋል።  ይቀጥላል

Read 3207 times