Sunday, 20 November 2016 00:00

ውብስራ

Written by  ቅዱስ ሰውነት
Rate this item
(22 votes)


ቅዳሜ ።
ወንደላጤ ነኝ።
በግራ እጄ ጫቴን፣ በቀኜ የዕለቱን ጋዜጣ አንጠልጥዬአለሁ። ወደ ቤቴ እየተንደረደርኩ ነበር::  
“ሄይ!” - ታክኬው ካለፍኩት የቆመ ዘመናዊ መኪና ውስጥ  በመስኮቱ አንገቱን አስግጎ ጠራኝ::
ዞርኩኝ። ባለ መነጽር ጎልማሳ። ዝም ብዬው ልሄድ ነበር:: በግራ እጁ ጣቶች በምልክት  ጠራኝ። እየሱሳዊ አጠራር።
ማነው እሱ?
ሄድኩኝ። “አቤት ጌታዬ”  አልኩት። “መንገድ የጠፋው ቀብራራ” እላለሁ  በሆዴ።
ተንጠራርቶ የጎኑን በር ከፍቶ እንድገባ ጋበዘኝ።
ማነው ይሄ ዘንካታ?
ገባሁ። መነጽሩን አውልቆ  የካኔቴራው አንገት ላይ በቄንጥ አንጠለጠለው።
“ማነው ይሄ ጉረኛ?” ራሴን እጠይቃለሁ:: የበርጫ ሰዓቴን በውስጤ አሰላለሁ። ሙሉ በሙሉ ወደ እሱ ዞሬ አየሁት።
የት ነበር የማውቀው? የት ነበር? የት ነበር? ወደ ትዝታዬ ጎጆ በረርኩ።
ግራ እጁን አንስቶ መሪው ላይ በስታይል አኖረው። ‘ማነው ይሄ ቄንጠኛ ትርፍ ጣት!?’
ፈገግ አለ። የሆዴን  የሰማኝ መሰለኝ።አፍሬ አንገቴን ደፋሁ። ድንገት ግን ዞሬ አየሁት። ሚጢጢ ሰያፍ ሸራፋ።
ጮህኩኝ። “ውብ ስራ!”
አንገት ለአንገት ተጠማጠምን።
 አናቴን ደባበሰኝ።
“ይሄ ሁሉ ሽበት ምንድን ነው?”

“ቦስ!”
 በእሱ በኩል ባለው መስኮት፣ አንድ ዘናጭ ወጣት ቆሞ ኖሯል::
“እዚህ ያለው ጉዳይ ትንሽ ጊዜ ሳይወስድ አይቀርም:: በአንድ ሰዓት ውስጥ መልሼ እደውላለሁ። ምሳ ማድረግ ይችላሉ እስከዚያው”
“ኦ! መልካም!  እኔም ደውዬ እሱኑ ልልህ ነበር። ደውል::”
የድምጹ ግርማ ሞገስ! ወይ ጊዜ! ይሄ አሁን እውን ‘ውብስራ ትርፍ ጣት’ ነው? ማን ያምናል?
“እሺ ሰር”
ወጣቱ ሄደ።
“ታዲያ ምሳ የት ነው እየበላን የምናወጋው?” ወደኔ ዞረ፡፡
መኪናውን አስነሳ።
“ሽሮ ጥጄ ነው የወጣሁት። እሷን መቋደስ እንችላለን” አልኩት::
“ሃሃሃሃ! ግዴለም ለእራት ተጋቢኖ ሆና ትቆይህ፤ ዛሬ እኔ ነኝ ጋባዥ”
ጋዜ አሳዘነችኝ።

ጥሬ ስጋና ጥብስ ጋበዘኝ። ወጣቱ ጋ ራሱ ደውሎ ቀጠሮውን አራዘመ። አንዲት ቡና ቤት ደጃፍ፣ ዛፍ ያረበባት ጥላ ስር፣ እኔ ቢራ፣ እሱ ስሙ የማይያዘኝ አልኮል አዘን ተቀመጥን።
ንግግሩ ቀጥተኛ ዓይነት ነው። “ምን ትሰራለህ?” አለኝ ወሬ እንደ ጀመርን።
“አስተምራለሁ”
“ምን?”
“ታሪክ”
“የት?”
“አንድ ሃይ ስኩል ውስጥ”
ስለ ደሞዝ፣ ስለ ኑሮ፣ ስለ ትዳር፣ ስለ ሃይማኖት አከታትሎ ጠየቀኝ። በሁሉም መምከኔን ነገርኩት፡፡  ስለ እሱ እንዲያወራኝ ጓጓሁ።
“ያንተን ታሪክ አልረሳውም”  አልኩት፡፡
አቋረጠኝ።
“ያ እስክንድርስ? ለመሆኑ አለ?” ጠየቀኝ።
“እሱማ ሞቶ”
“ተው እንጂ!  ያ ተንኮለኛ ጓደኛው እንዳሻውስ?”
“እሱ ባክህ ያለበት አይታወቅም…..ወይ አንተ! ትምህርት ስታቋርጥ ትዝ ይልሃል?”
መልሱን ዘለለው።
“ስለ መስታወትስ ሰምተህ ታውቃለህ?”
“እሷ እንኳን ጎብዛለች አሉ። እንደውም ምን የሚባል ከተማ፣ ግሩም ሆቴል ከፍታ ትሰራለች አሉ። ትዝ ይልሃል? አንተ እና እሷ...... ”
አላስጨረሰኝም።
 “ያ’ሳ  ‘ኡስታዝ’ የምንለው፣ ካንተ ጋር ሁሌ ትምህርት ቤት ጓሮ እየዞራችሁ  ይሰግድ የነበረው፣ ጂኒየስ ልጅ? ማን ነበር ስሙ?”
“ ሃይከል፤ ኑሮውን ሳውዲ አረቢያ ካደረገ ስንት ጊዜው”

ሞቅ እያለን ሄደ። በሞቅታችንም ውስጥ አንዳች የሚሽሽው ጨዋታ እንዳለው ታዘብኩ።  አልለቀውም!
“ከድሮ ጓደኞቻችን ማንን ታገኛለህ?” ጠየቅኩት።
“ማንን አገኛለሁ ብለህ ነው?”
 “አስታውሳለሁ፣ እየጎረመስን ስንመጣ፣ስላንተ ሲነሳ፣ሁላችንም እናዝን ነበር።” አልኩት
“ምን ታዝናላችሁ።” አለ “ የእብደት ዘመን:: የተማሪውስ ይሁን የመምህራኖቹ መባስ:: እንደዚያ ሲያሰቃዩን፣እናንተም ያንን ችላችሁ  በትምህርት መግፋታችሁ  ይደንቃል።”
እውነት ነው፡፡ ልጅነት ጋርዶን  እንጂ ቦታው ግማሽ ሲዖል ነበር፡፡ ግማሽ ገነት።
“ከትምህርት ከወጣህ ወዲያ ምን ጀመርክ?” አልኩት።
እንዴት ትምህርት እንደተወ አውቃለሁ።
ትዝ ይለኛል፡፡ ትምህርት ቤታችን ግቢ ውስጥ እሱ፣መስታወትና ስማቸውን አሁን የረሳኋቸው ጥቂት የሌላ ክፍል ልጆች፣ በተማሪዎች መግቢያና መውጫ ሰዓት ከረሜላ፣ ማስቲካና  የተጠበሰ እንደ ብይ ድቡልቡል ሰሊጥ ይሸጡ ነበር። አስተማሪዎቻችን ይህን ስራቸውን ይከለክሏችው ነበር። እነሱ ግን እየተደበቁ ስራቸውን ይቀጥሉ ጀመር። የሆነ ቀን በየክፍሉ ፍተሻ ተደረገ፡፡ ውብስራ ከነሰሊጡ  ተያዘ። እኛ ማቲዎቹ እየተሻማን ሰሊጦቹን በላናቸው:: ውብስራ በትምህርት ቤቱ ዩኒት ሊደር ጭንቅላቱን እንደ እባብ በሸንበቆ እየተቀጠቀጠ ከክፍል ተባረረ። ቅጣቱ እንኳ ጊዜያዊ ነበር፡፡ እሱ ግን ትምህርቱን እስከ ወዲያኛው አቋርጦት ቀረ። የልጅነት ለቅሶውን በሳቃችን አጅበን ሸኘነው::
ከዚያስ? እራሱ ውብስራ ይንገረን።
“ያው ሰምታችሁታል። ከትምህርት ቤቱ  ፊት ለፊት ከተዘረጋው አስፓልት ማዶ፣ የቀበሌው ጽህፈት ቤት አጠገብ ካለው የሸንኮራ አገዳ ማከፋፈያ ቤት ከመኪና አውራጅ ሆኜ ተቀጠርኩ። በሳምንት ትንሽ ብር እያገኘሁ፤ ግማሿን እየቆጠብኩ፣ ግማሿን ለእናቴ እየሰጠሁ፣ ኑሮዬን  ቀጠልኩ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ በብድርና በዱቤ መለስተኛ ቦታ ተከራይቼ  የራሴን ሸንኮራ አውርጄ መስራት ጀመርኩ።”
ይሄንን እሰማ ነበር።  እኛ ያን ጊዜ ሃይ ስኩል ገብተናል።
“እናንተ ያን ጊዜ ሃይ ስኩል ገብታችኋል።” አለ ውብስራ ደግሞ “የእግራችሁን ዳና ማዳመጤን አላቆምኩም። አንድ ቀን ተስፈንጥሬ ከፊታችሁ እንደምቆም አውቅ ነበር። መንገዴን ቀጠልኩ። ጊዜው ወደፊት ሄደ። ቆይቶ፣ የገጠር እህል አምራቾችን ከከተማ ነጋዴ ጋ የማገናኘት የኮሚሽን ስራ መስራት ጀመርኩ። ብዙ ገንዘብ አገኝ ጀመር። እያደር የራሴን የንግድ ስራ የምጀምርበት እድል አገኘሁ። ህይወቴ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ።”
“የትምህርትህስ ነገር?”
“ተውኩታ! እውነት ልንገርህ? እስከ ጉልምስናዬ መባቻ ድረስ፣ እያንዳንዳችሁ የክፍሌ ልጆች ሞታችሁ፣ ያ በልባችሁ  ያለው አሳዛኝ ታሪኬ አብሯችሁ መቃብር እንዲወርድ ምኞቴ ነበር። በኋላ፣ ከብዙ ጊዜ በኋላ፣ ለስራ በየሄድኩበት ከተማ እንደ ሃዋርያት ተበትናችሁ የምትገፉትን የተበደለ ኑሮ ሳይ፣ ሁላችሁንም ይቅር አልኳችሁ።”
‘ይህን ሰው በድለነዋል’ አልኩ፤ ለራሴ። ልቤ ሃዘንና ጸጸት  ጸነሰ።
ከሃሳቤ መለሰኝ።
ድንገት ተነሳ።
“ኋለኞች ፊተኞች ፣ ፊተኞች ኋለኞች ይሆናሉ” አለ እየሳቀ።
ከብዙ ብሮች መሃል ቆጥሮ፣ ሂሳባችንን ከፈለ።
ግማሽ መንገድ በመኪናው ሸኘኝ።
ጫቴንና ጋዜጣዬን  ይዤ ተሰናብቼው ወረድኩ።
“በዚህ አግኘኝ” ብሎ ትንሽዬ የአድራሻ ካርድ በመስኮቱ በኩል አቀበለኝ።
መኪናው አቧራ ረጭቶኝ ተሰወረ።
ወደ ካርዷ አቀረቀርኩ::    
ቆሜ ቀረሁ።

Read 3814 times