Sunday, 20 November 2016 00:00

ቦብ ዳይላን፤ “ስራ ስለበዛብኝ” የኖቤል ሽልማቴን መቀበል አልችልም አለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ጃኪ ቻን ከ56 አመታት በኋላ ኦስካር ተሸለመ፤
              ከ200 በላይ ፊልሞችን ለእይታ አብቅቷል
    የ2016 የኖቤል የስነጽሁፍ ተሸላሚው አሜሪካዊው ድምጻዊና የሙዚቃ ግጥም ጸሃፊ ቦብ ዳይላን፣ በመጪው ታህሳስ ወር መግቢያ በስቶክሆልም በሚከናወነው የኖቤል ሽልማት ስነስርዓት ላይ እንደማይገኝ ባለፈው ረቡዕ አስታውቋል፡፡
የ75 አመቱ ቦብ ዳይላን፣” በስነስርዓቱ ላይ ተገኝቼ ሽልማቱን ብቀበል ደስ ይለኝ ነበር፤ ሆኖ ግን ሌሎች ፋታ የማይሰጡ ጉዳዮች ስላሉብኝና ስራ ስለበዛብኝ ልገኝ አልችልም” ሲል ለኖቤል አካዳሚ በላከው ደብዳቤ ማስታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የሽልማት አካዳሚው የቦብ ዳይላንን ውሳኔ እንደሚያከብር ገልጾ፣ እንዲህ ያለው ውሳኔ ያልተለመደ ቢሆንም ሽልማቱን በአካል ተገኝቶ ባለመቀበል፣ ቦብ ዳይላን የመጀመሪያው ሰው አለመሆኑን ጠቁሞ፣ ድምጻዊውን በመወከል ሽልማቱን የሚቀበለው ሰው ማንነት ገና አለመታወቁን ዘገባው ገልጧል፡፡
አካዳሚው የቦብ ዳይላንን ተሸላሚነት ይፋ ያደረገው ከአንድ ወር በፊት ቢሆንም፣ ተሸላሚውን ለማግኘት እጅግ ተቸግሮ መቆየቱና ዳይላንም ባልተለመደ መልኩ ሽልማቱን በተመለከተ ለሳምንታት ምንም አይነት አስተያየት አለመስጠቱ ብዙዎችን ያነጋገረ ጉዳይ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡ በተያያዘ ዜና ላለፉት 56 አመታት በፊልሙ ኢንዱስትሪ ውስጥ የቆየውና አለማቀፍ ተወዳጅነትን ያተረፈው የፊልም ተዋናይ ጃኪ ቻን፣ ገቨርነርስ አዋርድ የተባለውን የኦስካር የክብር ሽልማት ባለፈው ሳምንት መቀበሉ ተዘግቧል፡፡ ጃኪ ቻን በየአመቱ በፊልሙ ኢንዱስትሪ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሙያተኞች የሚሰጠውን ገቨርነርስ አዋርድ የተባለውን የኦስካር የክብር ሽልማት ባለፈው ቅዳሜ በሎሳንጀለስ በተካሄደ ስነስርዓት መቀበሉን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በረጅም አመታት የሙያ ቆይታው ከ200 በላይ ፊልሞችን በተዋናይነትና በዳይሬክተርነት ለእይታ ያበቃው የ62 አመቱ የፊልም ተዋናይ ጃኪ ቻን፣ አካዳሚ ኦፍ ሞሽን ፒክቸርስ አርትስ ኤንድ ሳይንስስ ባዘጋጀው ስነስርዓት ላይ ተገኝቶ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡ ጃኪ ቻን በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረገው ንግግር፤ በሽልማቱ መደሰቱን ገልጾ፣ ከ56 አመታት በላይ በዘለቀው የፊልም ስራ ቆይታው፣በርካታ ፈተናዎችን እንዳለፈ በማስታወስ፣ ለወደፊትም ሌሎች አዳዲስ ፊልሞችን መስራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

Read 767 times