Sunday, 20 November 2016 00:00

“ለአገራችን ሙዚቃ ተስፋዎቹ እኛው ነን”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

    ተወልዶ ያደገው መሀል ፒያሳ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በራስ አበበ አረጋይ፣ ሁለተኛ ደረጃን በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተከታትሏል፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ለአራት አመት ፒያኖ ተምሮ፣ በ93 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ ለጥቂት ዓመታት ከተለያዩ የሙዚቃ ባንዶች ጋር ከሰራ በኋላም፣ የዛሬ አስር ዓመት ከአራት ወንድሞቹ ጋር “መሀሪ ብራዘርስ” የተሰኘውን ባንድ ማቋቋሙን ይናገራል፡፡ በቅርቡ ለአድማጭ ጆሮ የደረሰው “790” የተሰኘ አልበሙ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወዳጅነትን የተቀዳጀለት ሲሆን በአገር ውስጥም በአህጉር ደረጃም ለሽልማት በቅቷል፡፡
ከሙዚቀኛ ቤተሰብ የወጣው ሄኖክ፤ ከአንድ ሳምንት በፊት በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው የ“ኦል አፍሪካ ሚዩዚክ አዋርድ (አፍራማ)” ሥነ-ሥርዓት ላይ ታድሞ ነበር፡፡ መታደም ብቻ ግን አልነበረም፡፡ ከዓመቱ የ”አፍራማ” ተሸላሚ አፍሪካውያን ሙዚቀኞች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ሰሞኑን ከድምጻዊ ኄኖክ መሃሪ ጋር በነበራት ቆይታ በሙዚቃ ህይወቱ ዙሪያ በስፋት አውግቷታል፡፡ የሚያስደምመውን፣ የሚያስደስተውን፣ የሚያበግነውን፣ የሚያረካውን፣ የሚያልመውን፣ የሚተቸውን፣ የሚያደንቀውን------በአጠቃላይ አስደማሚ ህይወቱን ይተርክልናል፡፡

      ‹‹790›› የመጀመሪያ አልበምህ መጠሪያ ቢሆንም ከዚያ በፊት በግልህ አንድ አልበም ያወጣህ ይመስለኛል። ትክክል ነኝ ?
ልክ ነው፡፡ ያኔ ገና ከቤተ-ክርስቲያን እንደወጣሁ፣ ከየትኛውም ባንድ ጋር መስራት ሳልጀምር ያሳተምኩት፣ ‹‹የእውቀት ፍቅር›› የተሰኘ አልበም ነበረኝ፡፡ በ1996 ይመስለኛል የወጣው፡፡ ይህ አልበም ብዙ ሳልበስል የሰራሁት፣ ብዙ ተምሬ ያለፍኩበት ሥራ ነው፤ ስኬታማ አልነበረም፡፡
አዲሱ አልበምህ ከርዕሱ ጀምሮ አነጋጋሪ ነው፡፡ ‹‹790›› የድሮ ቤታችሁ፣ ቁጥር ነው አይደል? ግን እንዴት ለአልበምህ ስያሜ  መረጥከው? በጣም ያልተለመደ ነው...
እውነት ነው::  ‹‹790›› ተወልደን ያደግንበት የቤታችን ቁጥር ነው፡፡ ስያሜውን “790” ያልኩበት ምክንያት ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ቤተሰባችን በሙዚቃ ውስጥ ያለ ቤተሰብ ነው፡፡ ለአልበሜ ርዕስ ማውጣት ሳስብ ምን ልበለው አልኩኝ፤ የሆነ ፍልስፍና እንዲኖረውም ፈልጌያለሁ፡፡ ዝም ብሎ የአንዱን ዘፈን ስም የአልበሙ መጠሪያ ማድረግ ይቻላል፡፡ ደግሞ ይህን ቤተሰብ የሚገልፀው፣ ታሪካችንን የሚወክል መሆን እንደሚገባው ወሰንኩ፡፡ ብዙ ካሰብኩና ከተጨነቅኩ በኋላ፣ “እኛ ከየት ነው የመጣነው? እኛነታችን ከየት ነው የጀመረው?” ብዬ ራሴን ስጠይቅ፣ የተወለድንበት ቤት ትልቁ ነገር ነው። ሁሉን መማር ማወቅ የጀመርነው፣ የተወለድነው ያደግነው፣ “790” የሚል ቁጥር ባለው ቤታችን ውስጥ ነው፡፡ በቃ ርዕሱን “790” ለማድረግ ወሰንኩ፡፡
አልበሙ ውስጥ የተካተቱት 15 ዘፈኖች መንፈሳዊና ሞራላዊ እሴታቸውን የጠበቁ እንደሆኑ ነግረኸኛል፡፡ ግጥምና ዜማውን ማን ሰራልህ?
የ12ቱን ዜማና ግጥም የሰራሁት እኔ ነኝ፡፡ የሶስቱ ዘፈኖች ዜማና ግጥም በዘሪቱ ነው የተፃፈው፡፡ ከሰራኋቸው 12 ግጥሞችና ዜማዎች አንዱን ከዘሪቱ ጋር፣ አንዱን ከቤቲ ጂ ጋር ነው ያዜምነው፡፡ ባንዱ ይህን አልበም በማጀብና በማቀናበር ከፍተኛ ሚና ነበረው - በሙሉ ባንድ ነው የሰራነው፡፡ የትራምፔትና ሳክስፎን ተጫዋቾችን ከባንዱ ውጭ በመጋበዝ፣ አንዲት ኦኬት የተባለች የአውሮፓ ዜጋ ቫዮሊን አንድትጫወት በማድረግ፣ የተሟላና የተቀናጀ የባንድ ድምፅ እንዲኖረው በመጣር፣ ኪሩቤል ተስፋዬ፡- ሳውንድ ኢንጂነር ሆኖ፣ ግሩም ስራ ሰርተናል ብለን እናምናለን፡፡ ተቀባይነቱም ጥሩ ሆኖ አግኝተነዋል። ይዘቱን በተመለከተ በጣም ጥሩ መልዕክት ያለው፣ ስሰማው የምኮራበት፣ ለሁልጊዜ መኖሩ የሚያኮራኝ፣ መናገር የምፈልገውን መልዕክት ያስተላለፍኩበት ነው፡፡ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሰጠን ብዙ ፀጋዎች አንዱና ዋነኛው ፍቅር ነው፤ የህይወት ፍቅር፣ የአገር ፍቅር፣ የሚስትና የልጅ ፍቅር፡፡ ይህ ሁሉ በአልበሜ ውስጥ አለ። የሰው ልጅ በህይወቱ ደስተኛ ሆኖ ለማለፍ መፋቀር፣ መተሳሰብ፣ መተባበርና መከባበር እንዳለበት የሚመክር፣ ጠቅለል ያለ ሀሳብ የሚያስተላልፍ ነው፤ አልበሙ፡፡
በዚህ አልበም በተለይ ‹‹እወድሻለሁ›› የተሰኘው ዘፈን በአገር ውስጥም በአፍሪካ ደረጃም ተሸልሟል፡፡ የተለየ ጥረትና ትጋት ተደርጎበታል ወይስ አጋጣሚ ነው?
አልበሙ ከወጣ ስድስት ወሩ ነው፡፡ በቅርቡ ዲጂ ቤቢ ባዘጋጀው የ‹‹አዲስ ሚዩዚክ የአድማጮች ምርጫ›› ሽልማት ላይ በ ‹‹ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ›› ዘርፍ አሸናፊ ሆኗል፡፡ የሙዚቃ ቪዲዮው የተሰራው በጣሊያናዊው ወዳጃችን፣ አሌሳን ድሮግራፊ ነው፡፡ ሙዚቀኛም፤የፎቶ ባለሙያም ነው፡፡ ፌስቲቫሎችን ይቀርፃል፤ አብሮም ይሳተፋል፤ ሁሌ ቪዲዮ ሊሰራልኝ እንደሚፈልግ ይነግረኝ ነበር፡፡ ይህን ቪዲዮ በቃሉ መሰረት በ15 ቀን ውስጥ ሰርቶልኝ ተመለሰ፡፡ ይህ ዘፈን፤ ቪዲዮውም መልዕክቱም ሙዚቃውም ተወዷል፤ የተሳካ ስራ ነው፡፡
ናይጄሪያ ሌጎስ በቅርቡ በተካሄደው “ኦል አፍሪካ ሚዩዚክ አዋርድ (አፍሪማ)” ላይም ያሸነፍከው በዚሁ ዘፈን ነው አይደል----!?
ትክክል ነው፤ በአፍሪማ፤ የአፍሪካ ‹‹ምርጥ RandB ሶል”በሚል ዘርፍ ነው ያሸነፍኩት፡፡ እኔም የምኖረውን የምሆነውን ነው፣ወደ ግጥምና ዜማ የማመጣው፡፡ እንደሚታወቀው ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ። ዘፈኑን የፃፍኩት ለባለቤቴ ነው፡፡ የተሰማኝን ቀለል ባለ መልኩ፣ ጥሩ የፍቅር ዘፈን አድርጌ ስለሰራሁት ይመስለኛል የተወደደው፡፡ ብዙ ሽልማቶችን፤ ብዙ አድናቆቶችን እያመጣ ነው፡፡
በሽልማቱ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተህል፡፡ ሽልማቱን ግን አልጠበቅህም ነበር፡፡ ለምን? አሸናፊ መሆንህ ይፋ ሲደረግ ምን ተሰማህ?
በነገራችን ላይ ሽልማቱ ትልቅ ሽልማት ነው፡፡ የሌጎስ አስተዳዳሪ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት ነው ያዘጋጀው፡፡ በሚዲያም በኩል ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት ነበር፡፡ የአፍሪካን አርቲስቶች በአንድ አዳራሽ አገናኝቶ፣ አክብሮና ሸልሞ፣ የሶስትና የአራት ቀን ፕሮግራሞች ዘርግቶ፣ እራት ጋብዞ … ምን ያልተደረገ አለ፡፡ በአጠቃላይ ለአርትና ለአርቲስት ክብር የተሰጠበት፣ የሚያስቀና፣ በአገሬ ቢኖር--- ብለሽ የምትመኝው አይነት ነበር፡፡
በዚህ ዝግጅት ላይ እንኳን መሸለም መታደምም ያኮራል ነው የምትለው?
በጣም እንጂ! እኔ ለፍቅርአዲስም፣ ለአንተነህም ስላቸው የነበረው ይህንኑ ነው፡፡ መታጨት በራሱ እንደ ማሸነፍ ነው፡፡ ሽልማቱን አልጠበቅሁም ነበር፡፡ አዎ አልጠበቅሁም፤ ምክንያቱም ለውድድር አብረውኝ የቀረቡት በዓለም አቀፍ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚታወቁ 7 ናይጄሪያዊያን፣ ታዋቂ ደቡብ አፍሪካዊያን ሙዚቀኞች ነበሩ፡፡ አስበሽዋል? … እነዚህን አሸንፎ መሸለም ምን ስሜት እንደሚሰጥ? ይሄ ሽልማት የሁሉም የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ሽልማት ነው፤ ኢትዮጵያ ናት በዚያ ቦታ ላይ የተወከለችው፡፡ ሽልማቱ አስደንግጦኛል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቃ በተዳከመበት በአሁኑ ወቅት የእናንተ በአህጉር ደረጃ መሸለምና መታጨት ምን ስሜት ይሰጣል?
እውነት ለመናገር እኔ ሙያዬን ባልወደው ኖር፣ ብዙ ገንዘብ ማግኛ ስራዎችን እመርጥ ነበር፡፡ ሙያዬን በመውደዴ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ባሉበት ተስፋ ባለመቁረጥና ተግቶ ቢመስራት እስከ መሸለም መድረስ ለተተኪዎቻችን ፅናትን ያስተምራል፡፡  ለወደፊቱ የአገራችን ሙዘቃ ተስፋዎቹ፣ እኛው ሙዚቀኞች ነን፡፡ አሁንም የምንጨነቀው፣ የምንለፋው እኛው ሙዚቀኞች ነን እንጂ ዘርፉ በመንግስት ችላ የተባለ፣ ብዙ ክፍተቶች ያሉበት ነው፡፡ ይህ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ የሌጎስ ከተማ አስተዳዳሪ ያልኩሽ ሰው አንድ ነው፤ግን ለውጦችን አምጥቷል፤ አንድ ሰው ነው፡፡ አፍሪካ ህብረትን የሚያክል ትልቅ የአህጉር ድርጅት አሳምኖ፣ ዝግጅቱን ስፖንሰር አስደርጓል፡፡ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የት ነው? ኢትዮጵያ!! እኛ ህብረቱን ተጠቅመንበት አናውቅም። ለምን? ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ፡፡ መንግስታችን በቂ እገዛ እያደረገ አይደለም፡፡
በቅርቡ ሙዚቀኞች ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር አንድ ስብሰባ አድርጋችሁ ነበር፡፡ ሙዚቃ በCRBT ስለ መሸጥ ጉዳይ ነበር ውይይቱ፡፡ እንዴት ነው ተስፋ አለው?
CRBT ሙዚቃን በስልክ ላይ የመሸጥ ፕላትፎርም ነው፤ ቴሌ 85 በመቶውን ወስዶ ለአርቲስቱ 15 በመቶ ነበር የተወሰነለት፡፡ ይህ በዓለም ላይ ያሉ ፕሮዲዩሰሮችን  ያስደነገጠ ነበር፡፡ ከሞራልም አኳያ አርቲስቱን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ተብሎ ነበር፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በአገራችን ብቸኛውና ዘርፉን በሞኖፖል የያዘ የመንግስት ተቋም ነው፡፡ እንግዲህ ሂደቱ ቴሌ ነጋዴዎችን ያጫርትና አሸናፊዎቹ ነጋዴዎች፣ ከሙዚቀኞች ጋር ተደራድረው ገበያውን ወደ ቴሌ የሚወስዱበት አሰራር ነው፡፡ ከ3 ዓመት በፊት ቴሌ 85 በመቶ የሚያመጣልኝን “አሸንፈህ ግባ” ብዬዋለሁ ብሎ ሙዚቀኞች ተጭበርበረንና ሰለባ ሆነን ነበር፡፡ ከ15 ቀን በፊት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በነበረን ውይይት፣ ይህን እንደሚቀይሩና የሙዚቀኛውን ሞራል እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ ያንን ተግባር ላይ ሲውል የምናየው ይሆናል፡፡ ቴሌ እንደተናገረው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ 47 ሚሊዮን የስልክ ተጠቃሚ አለ፡፡ ይህ ትልቅ ገበያ እንዳለ ያሳያል፡፡ በቃላቸው መሰረት ከሰሩ አንደኛ ዳታ እንሰበስባለን፡፡ ሁለተኛ በተገቢው መልኩ ድርሻችንን እናገኛለን፤ ከመዘረፍ እንድናለን፡፡ ለዚህ ደግሞ የመጣው ሶፍትዌርና ፕሮግራም፣ ዘፈኖች በቀላሉ ኮፒ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ነው፡፡ አልበማችንን በስልክ ስንሰጥ ጥበቃም የገንዘብ ጥቅምም አለው፡፡ ተጠቃሚው ደግሞ ገጣሚው የዜማ ደራሲው፣ አቀናባሪው፣ ድምፃዊው … ሁሉም ናቸው፡፡ መንግስት ማግኘት የሚገባውን ያገኛል፤ አገርም ታድጋለች፤ ይህ በሌለበት ሁኔታ ሙዚቃ፣ ሙዚቀኛና አገር እንዲያድግ መጠበቅ ዘበት ነው፡፡
የሚገርምሽ እኔን በፊት ያስፈረመኝ ድርጅት፣ እኔ 85 በመቶ፣ ድርጅቱ 15 በመቶ እንደሚያገኝ  አድርጎ ነበር ያስፈረመኝ፡፡ በዚህ ስምምነት ውስጥ ቴሌ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ገንዘብ ልወስድ ስሄድ፣ በሳንቲም ደረጃ ነው ያለው፡፡ ለምን? ብዬ ጠየቅሁኝ “አይ ቴሌ 85 በመቶውን ከወሰደ በኋላ፣ የ15 በመቶውን 85 ፐርሰንት ታገኛለህ ነው ያልንህ” አሉኝ፡፡ ይሄ ተራ ማጭበርበር ነው፡፡ ግጥሙ፣ ዜማው፣ ቅንብሩና ሌላው ሁሉ ስራ የኔ ሆኖ፣ ቴሌ ምን ስለ ሰራ ነው 85 በመቶ የሚወስደው? የእውነት ያበሳጭ ነበር፡፡ ይህ ድርጅት በርካታ ሙዚቀኞችን ዘርፎ የት እንደገባ አላውቅም፡፡
ድርጅቱ ምን ይባላል? ከዚህስ በፊት ይሰራ ነበር?
እንደሰማሁት ጨረታ አሸንፎ፣ በቴሌና በሙዚቀኛው መሀል ሆኖ ሙዚቃ በመግዛት፣ ለቴሌ የሚያስረክብ ነበር። ስሙ ክሬዶክስ ይባላል፡፡ ቴሌ “ለእኔ ተስማምተኸኛል” ብሎ አቅፎ ተቀብሎት ነበር፡፡ እኛን እያታለለ ለቴሌ ዘፈን ይሸጥ ነበር፡፡ እኔ እንደውም እንደ ሌሎቹ ብዙ አልተጎዳሁም፡፡ ሁለት ዘፈን ብቻ ነበር የተስማማሁት፤ ለሙከራ ብዬ፡፡
አሁን ከ15 ቀን በፊት ደግሞ እኔ፣ ኤሊያስ መልካ፣ ጆኒ ራጋና ሀይሌ ሩት የሚመሩት ትልቅ ቡድን ተፈጥሮ ስብሰባው ተካሄደ፡፡ ቴሌም ጨረታውን ትቶና ለባለፈው ይቅርታ ጠይቆን፣ ብዙ ተስፋ ሰጪ ነገሮች ሰምተናል፤ አብረን እናያለን፤ ተግባራዊ ከሆነ የአርቲስቱን ጥቅምና ሞራል የሚያስከብር፣ አርቲስቱ ብዙ ፐርሰንት የሚያገኝበት ነው፡፡ በኬኒያ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ፤ ሙዚቃቸውን ያሳደገላቸው የሽያጭ ስርዓት ነው፡፡
በቅርቡ ‹‹ሚዩዚክ ኢን አፍሪካ›› የተሰኘ ፕሮጀክት ውስጥ መግባትህን ሰማሁ----
ሰሞኑን ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ሙዚቀኞች፣ የተሳተፉበት የፓናል ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ ፓናሉ “ሚዩዚክ ኢን አፍሪካ” በተባለ ፕሮጀክት ነው የተካሄደው፡፡ እኔም ፕሮጀክቱ ውስጥ ተካትቻለሁ፡፡ በውይይቱም ላይ ተሳትፌያለሁ፡፡ የናይጄሪያው ተወካይ፤ የኢትዮጵያ ቴሌ በCRBT ላይ ያለው ልምድ ምን ያህል ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ነበር፡፡ “እኛ አገር ናይጄሪያ፣ ሲዲ መሸጥ አቁመናል” ነው ያለው፡፡
ወደ ‹‹ኮክ ስቱዲዮ›› እንምጣ … አመራረጣችሁ በውድድር ሳይሆን በራሱ በኮካ ኮላ ነው፤ ትክክለኛዎቹ ሙዚቀኞች ተመርጠናል ትላለህ?
ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ “ኮክ ስቱዲዮ” ኢትዮጵያ ሲገባ የመጀመሪያው ነው፡፡ የገበያ ባለሙያዋ ወ/ሪት ትዕግስት ስትናገር እንደሰማነው፤ በሌላው ዓለም ለ”ኮክ ስቱዲዮ” የሚሆኑ አርቲስቶች የሚመረጡበት መንገድ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያንን ለማድረግ አመቺ አልሆነልንም ነው ያለችው፡፡ እኔ በኋላ እንደተረዳሁት፣ የኢትዮጵያ ኮክ ስለመረጠን ብቻ አይደለም የተሳተፍነው፡፡ በርካታ የግምገማ ጊዜ ነበራቸው፡፡ ሙዚቃዎቻችንን...ቪዲዮዎችን ሰምተው፣ ተመልክተውና ገምግመው እንጂ ስማችን ስለሄደ ብቻ አይደለም፡፡ እነሱም ለስቱዲዮው የማይመጥን፣ አለም አቀፍ እይታ የሌለው ሊያሰሩ አይችሉም፡፡ ከዚህ አንጻር የተመረጥነው አርቲስቶች፣ በጣም ይገባናል፡፡ ብዙ እየለፋን ራሳችንን እያሳደግን፣ ከአለም አቀፍ ሙዚቃ ጋር ራሳችንን ለማዘመን እየሮጥን፣ በመሆኑ፣ ይገባናል፡፡ ትክክለኛዎቹ ሙዚቀኞች ነን ብዬ አምናለሁ፡፡
በቆይታችንም አገራችንን፣ ባህላችንን፣ ሙዚቃችን ያለበትን ደረጃ ለሌሎች አሳውቀናል፡፡ እኛም ከፍተኛ ልምድ ቀስመን ተመልሰናል፡፡ እኔ ለምሳሌ “ሆያ ሆዬ”ን ስዘፍን፣ “ለምን ሆያ ሆዬ” እንደሚባል ኮርኪ ቀጥቅጬ፣ ሰርቼ፣ አለባበሱን ሁሉ አስረድቼ ነበር፡፡ ስለዚህ “ሆያ ሆዬ” የ”ኮክ ስቱዲዮ” ሲዝን አራት ማስታወቂያ ሆኖ ቆይቷል፤ ይሄ ትልቅ ነገር ነው፤ ለአገራችን ሙዚቃ፡፡
በ”ኮክ ስቱዲዮ” ቆይታህ በጣም ያስደመመህ ምንድን ነው?
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሙዚቀኞች፣ በእኛ ባህል ሲደመሙ ተመልክቻለሁ፡፡ እኔ ከናይጄሪያዊቷ ዘፋኝ ጋር ስገናኝ ያስደመመኝ ግን የናይጄሪያ የሙዚቃ ገበያ ነው፣ አብዛኛዎቹ የዓለም ሙዚቃን እየተቀላቀሉ ነው፤ በጣም ሄደዋል፡፡ ይሄ በጣም አስደምሞኛል፡፡ ምክንያቱም በአሜሪካ ገበያ የቢል ቦርድ ቻርት ውስጥ የገቡ ብዙ ናይጄሪያውያን ዘፋኞች አሉ፡፡ እነ ዴቪድ ከጎዳና፣ ከዝቅተኛ ኑሮ የተነሱ ናቸው፡፡ በአሁን ሰዓት በአንድ ሾው 200 ሺህና 300 ሺህ ዶላር የሚከፈላቸው ተወዳጅ አርቲስቶች ሆነዋል፣ ይሄ አያስደምም? በጣም ታታሪ ናቸው፡፡
ከ”ኮክ ስቱዲዮ” መልስ በማሪዮት ሆቴል በሰጣችሁ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቃ የጓሮ ድመት ይባላል›› የሚል ነገር ተናግረሃል ተብሎ መነጋገሪያ ሆነህ ነበር፡፡ ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
እኔ ለማለት የፈለግሁት በቀደመው ጊዜ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የጓሮ ድመት ይባል ነበር ነው፡፡ የትም የማይደርስ ነው ሲባል እኔም ቁጭት ነበረኝ፤ የአገራችን ሙዚቃ የጓሮ ድመት እንዳልሆነ ይሄው ለአህጉርና ለዓለም እያስተዋወቅን ነው ለማለት ነው እንጂ እኔ ራሴ የጓሮ ድመት ይባላል አላልኩም፤ መባሉም ይቆጨኛል፡፡
ለሙዚቃው ኢንዱስትሪው ዋና ዋና ፈተናዎች የሚባሉት ምንድ ናቸው?
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ የመንግስት ድጋፍ አንሶናል እላለሁ፡፡ ለምሳሌ በባህልና ቱሪዝም የሞያና የንግድ ፈቃድ አለኝ፡፡ ግብር እከፍላለሁ፤ እኔ ግዴታዬን ስወጣ መብቴ እንዲከበር እፈልጋለሁ፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከብዙ አናዳጅ ህጎቹ ጥቂቶቹን ልጥቀስልሽ፡- ለምሳሌ አንድ ዘመናዊ ባንድ ስምንት ተወዛዋዦች መያዝ ግዴታ ነው ይላል፡፡ እኛ ሙዚቃ የምንጫዎተው አምስት ሆነን ነው፡፡ አምስት ሰው ለማስተዳደር የሚከብደኝ ሰውዬ ስምንት ተወዛዋዥ ካልቀጠርክ አታሟላም ተብያለሁ፡፡ በምን ሂሳብ ይሄ እንደተጫነብኝ አላውቅም። እኔ ያጠናሁት ፒያኖ እንጂ ውዝዋዜ አይደለም፡፡ ተወዛዋዥ ቅጠር ተብዬ ቀንበር በላዬ ላይ ተጭኖብኛል። ሳክስፎን የሌለው ባንድ፣ ባንድ ሊባል አይችልም ይላል፤ ይህ ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ኤክስፐርት ተብለው ተቀምጠው ይህንን ህግ የሚያወጡት ሰዎች፣ ሙዚቃ ካቆሙ ብዙ አመታቸው ነው፡፡ ከሙዚቃ ጋር አይገናኙም፤ ቢሮ ቁጭ ብለው ሙዚቀኛው ላይ ቀንበር መጫን ነው ስራቸው፡፡ ይሄ ለእኔና ለሙያዬ ትልቅ ጫና ነው፡፡ ማን መልስ እንደሚሰጥበት አላውቅም፡፡ እነዚህን ሰዎች ማን ኤክሰፐርት እንዳላቸው በምን እንደተሾሙ አላውቅም፡፡ ስምንት ተወዛዋዦችም አልባሳት ያስፈልጋቸዋል ይላል፤ እኔ እንግዲህ ሙዚቃውን ትቼ አንድ ትልቅ ቴአትር ቤት ከፍቼ ማስተዳደር አለብኝ ማለት ነው፤ ራሴ ላይ የተጫነብኝ ቴአትር ቤት ነው። በሰለጠነ ዘመን ይህንን ውስብስብ ችግር የሚያቃልል የመንግስት አካል ማጣት ያሳዝናል፡፡ ለማን እንደምንጮህ አላውቅም። በታክስ በኩል ውስኪ በነፃ ይገባል፤ ለሙያዬ ማሳደጊያ የማመጣው ኪ-ቦርድ 200 ፐርሰንት ይቀረጣል። ህዝብ የሚያጠፉ አልኮሎች ይበረታታሉ። እነ ኪቦርድ የሚጫንባቸውን ተመልከቺ ይህ ፍትሀዊ አይደለም፡፡
በመጨረሻ?
በስራዬ ከጎኔ የነበሩትን ቤተሰቦቼን ጓደኞቼን አመሰግናለሁ፡፡ በሙዚቃውን ጉዞ ብቻዬን አይደለሁም፤ ብዙ የረዱኝ አሉ፡፡ ሁሉንም ሚዲያውን ጨምሮ አመሰግናለሁ፡፡ ሽልማቱም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው እላለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡

Read 1561 times