Sunday, 20 November 2016 00:00

ሙሉጌታ አባተ - በወዳጆቹ አንደበት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

    አንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ ሙሉጌታ አባተ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ የባንዶችን መፍረስ ተከትሎ በኦርጋን ብቻ ሙዚቃን በማቀናበር ፈር ቀዳጅ መሆኑ የሚነገርለት አርቲስት ሙሉጌታ፤ የሰራውን ያህል ዕውቅና ያላገኘ ሙያተኛ መሆኑን የሙያ አጋሮቹ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡  የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ዳዊት ይፍሩ ‹‹ዛሬ ለከፍተኛ እውቅና የበቁ ድምፃውያንን ወደፊት ያመጣ፤ ለሙዚቃ ብዙ ውለታ የከፈለ ባለሙያ ነው›› ብሏል፡፡
“ሙሉጌታ አባተ ለኔ ሁሉ ነገሬ ነበር” የሚለው ድምፃዊ ግዛቸው ተሾመ በበኩሉ፤ “ለሙዚቃ ባለሙያዎችም ትልቅ አጋዥና ለሙዚቃ የተፈጠረ ትክክለኛ ሰው ነው” ሲል ይገልፀዋል፡፡
ሙሉጌታ የራሱን የጥበብ ዘመን የፈጠረ ትልቅ ባለሙያ መሆኑን የጠቀሰው አርቲስት አሸብር በላይ በበኩሉ፤ “ሙሉጌታ በቅንብር፣ በዜማና ግጥም ከ500 በላይ አልበሞች የሠራ ቢሆንም  ያልተዘመረለትና የሚገባውን እውቅና ያላገኘ ሙያተኛ ነው” ብሏል፡፡
ከአርቲስቱ ጋር የረጅም ጊዜ የስራ ግንኙነት እንደነበራት ያስታወሰችው አርቲስት ፍቅር አዲስ ነቃ ጥበብ፤ “ሙሉጌታ በጣም ታታሪ የማይደክመው፤ በሙያው የቆረበ ሰው ነው፤ አመሉም በጣም ትሁትና ሰው ወዳድ ነው” ስትል አድናቆቷን ገልፃለች፡፡
በወሎ በ1957 ዓ.ም የተወለደው ሙሉጌታ አባተ፤ ሙዚቃ መስራት የጀመረው ከሀረር ምስራቅ ጎህ የኪነት ቡድን ጋር ሲሆን ህይወቱን በሙሉ ከሙዚቃው ጋር እንደተቆራኘ ኖሮ አልፏል፡፡ የስድስት ልጆች አባት የነበረው አርቲስቱ፤ በማጅራት ገትር ህመም በምኒልክ ሆስፒታል ሲረዳ ቢቆይም ህመሙ እየባሰ ሲሄድ በወዳጆቹ ትብብርና ድጋፍ ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ገብቶ በህክምና ሲረዳ ቢቆይም፤ ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት በተወለደ በ52 ዓመቱ ህይወቱ አልፏል፡፡ በነጋታው እሁድ ህዳር 4 ቀን 2009 ዓ.ም በሰሚት ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አድናቂዎቹ፣ ቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት ስርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል፡፡

Read 1746 times