Sunday, 27 November 2016 00:00

ቤተ ክህነት በ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ላይ ያቀረበችውን ክስ አሻሻለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የክስ ሂደቱ በሚዲያ እንዳይዘገብ ቢጠየቅም ተቀባይነት አላገኘ

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ፅ/ቤት፣ በ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፍሬው አበበ ላይ ያቀረበውን የስም ማጥፋት ክስ አሻሽሎ ያቀረበ ሲሆን የፍርድ ሂደቱን ጋዜጠኞች እንዳይዘግቡ የቀረበውን ጥያቄ ፍ/ቤቱ አልተቀበለውም፡፡
ክሱ የተሻሻለው ፍ/ቤቱ ህዳር 5 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ቀደም ሲል የጠ/ቤ/ክህነት ጽ/ቤት በጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፍሬው አበበ ላይ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም “ፓትርያርኩ ለኢትዮጵያ የደህንነት፣ ለምዕመናን የድህነት ስጋት” በሚል ርዕስ በዲ.ዳንኤል ክብረት ተፅፎ በጋዜጣው የታተመው መጣጥፍ “የፓትርያርክ አቡነ ማትያስን ስም ያጠፋ ነው” በሚል ያቀረበውን ክስ በተመለከተ ተከሳሹ የፓትርያርኩ ጉዳይ በቀጥታ ጠ/ቤ/ክህነትን የሚመለከት አይደለም የሚል የክስ መቃወሚያ ማቅረቡን ተከትሎ፣ ፍ/ቤቱ ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብ በሰጠው ትዕዛዝ ጽ/ቤቱ ክሱን አሻሽሎ አቅርቧል፡፡
ተከሳሽ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ፤ የተሻሻለውን ክስ ተመልክቶ ምላሽ ለመስጠት በጠየቀው ቀጠሮ መሰረት ፍ/ቤቱ ለታህሳስ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በእለቱ ተከሳሽ “ሰንደቅ” ጋዜጣን ጨምሮ ሌሎች እየዘገቡ ክስ ያቀረቡበት ጉዳይ በየጊዜው እየተደጋገመ ቤተ ክህነትን መጉዳቱን በመጥቀስ ፕሬሶች በሂደት ላይ ያለውን ክስ ጉዳይ እንዳይዘግቡ እንዲደረግ አቤቱታ ቀርቧል፡፡
ተከሳሹ ሂደቱን እየተከታተሉ ፕሬሶች መዘገባቸው ህጋዊ ሂደት መሆኑን ያስረዳ ሲሆን ፍ/ቤቱም ሚዲያዎችን እንዳትዘግቡ ማለት እንደማይቻል፣ ሚዲያዎችም ቢሆኑ በዘገባ ወቅት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ በመስጠት ቀጣዩን ሂደት ለመከታተል ለታህሳስ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

Read 1740 times