Sunday, 27 November 2016 00:00

ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ በህይወትና በንብረት ላይ አደጋ አደረሰ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

የ10 እና 16 ዓመት ልጆች ህይወት አልፏል

   ትላንት ማለዳ 11 ሰዓት ገደማ በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 11፣ በተለምዶ ቡልጋሪያ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በንግድ ሱቆች ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ፣ የሁለት ወንዶች ልጆች ህይወት ሲያልፍ አራት ሱቆች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ በአንደኛው ሱቅ ውስጥ የ10 እና የ16 ዓመት ልጆች ተኝተው እንደነበረ የገለፁት በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን፣ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ሱቁ ከውጭ ተቆልፎ ስለነበር ከቃጠሎው ማምለጥ አልቻሉም ብለዋል፡፡ የ10 ዓመቱ ህፃን ከክፍለ ሀገር ከመጣ ገና 10 ቀናት ብቻ እንዳስቆጠረና የ16 ዓመቱ ታዳጊ ከባለሱቁ ጋር አብሮ ይሰራ እንደነበር አቶ ንጋቱ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ቃጠሎው የተነሳው ከማለዳው 11፡05 ገደማ እንደነበር የተናገሩት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው፤ አደጋው ለባለስልጣኑ የተጠቆመው ዘግይቶ ስለነበር የአደጋ ሰራተኞች በስፍራው የደረሱት 12፡25 አካባቢ ሲሆን የህፃናቱን ህይወትም ሆነ በአራቱ ሱቆች የነበረውን ንብረት ማትረፍ አለመቻሉን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ህፃናቱ የተኙበት ሱቅ በተንጠልጣይ ጋኖች ከውጭ የተቆለፈ ስለነበር የአደጋ ሰራተኞቹ በውስጡ ሰው ይኖራል ብለው እንዳልገመቱ የገለፁት አቶ ንጋቱ፤ ህፃናቱ ከውጭ ሱቁን ቆልፈው ከስር ባለች ጠባብ በር ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ያችን ትንሽ በር ከውስጥ ዘግተው መተኛታቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከሱቆቹ ጀርባ የነበሩ አራት ቤቶችም የመለብለብ አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን በተለይ ሱቆቹ ከቆርቆሮና ከላሜራ የተሰሩ በመሆናቸው እሳቱን መቋቋም እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
የአደጋው መንስኤና በአደጋው የጠፋው የንብረት መጠን ገና እየተጣራ መሆኑን አቶ ንጋቱ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

Read 1758 times