Sunday, 27 November 2016 00:00

የትራምፕ መመረጥ በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን?!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

የዘረኝነት ጥቃት ይደርስብናል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገለፁ
    የዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንትነት መመረጥ ተከትሎ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ እንባረራለን በሚል ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ለአዲስ አድማስ ተናገሩ፡፡ የዘረኝነት ጥቃት ይደርስብናል የሚል ፍራቻ እንዳለባቸውም ገልፀዋል፡፡  
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ህገ ወጥ ስደተኞችን ከአገራቸው እንደሚያስወጡ የተናገሩ ሲሆን በዚህም የተነሳ በርካታ በሀገሪቱ የሚኖሩ ስደተኞች እሳቸው እንዳይመረጡ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ የትራምፕን ያልተጠበቀ የምርጫ ድል ተከትሎ ኢትዮጵያውያንን  ጨምሮ በርካታ ስደተኞችን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡  
መቅደስ ተኮላ የተባለች የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ ትራምፕ ይመረጣሉ ብላ እንዳልጠበቀችና መመረጣቸውንም ማመን እንደተሳናት ትገልጻለች። በተለይ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አሜሪካንን በስራ ቀጥ አድርገው የያዙትን ስደተኞች “አስወጣለሁ፣ ግንብ እገነባለሁ፣ ሙስሊም እዚህ ሀገር አይገባም” ማለታቸው በአሜሪካ ከተለመደው ነፃነት ጋር የተቃረነ እንደሆነባት ተናግራለች፡፡
“እኔ የመኖሪያ ፍቃድ ስላለኝ ያስወጡኛል የሚል ስጋት የለኝም” ያለችው መቅደስ፤ “ጉዳያቸው ያላለቀና በእንጥልጥል ላይ ያሉትን ስደተኞች ሊያባርሯቸው ይችላሉ ብዬ እሰጋለሁ” ብላለች፡፡  
በአሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ ነዋሪ የሆነው ሌላው ኢትዮጵያዊ የአይቲ ባለሙያ መሳይ ሀሰንም በትራምፕ መመረጥ አለመደሰቱን ይገልጻል፡፡ “የሰውየው መመረጥ ጉዳዩ ያልገባቸው ኢትዮጵያውያንን ካልሆነ በቀር ሌላውን ሊያስደስት አይችልም” ብሏል። ዘረኝነት በሰፊው እየተንሰራፋ መምጣቱን የጠቆመው መሳይ፤ የመጀመሪያ ተጎጂ የሚሆኑትም ጥቁር አፍሪካውያን ናቸው ይላል፡፡
በተለይ ዘረኛ የሆኑ ሰዎች በሚበዙባቸው ቦታዎች ፊት ለፊት የሚታዩ ግልፅ መገለሎችና ጥላቻዎች ሊፈጠሩ እንደሚችልና ልጆች ትምህርት ቤት ውስጥ መገለል ሊደርስባቸው እንደሚችል መሳይ ይናገራል። “በአጠቃላይ ምን እንደሚፈጠር ለወደፊት የምናየው ቢሆንም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በጥላቻ ንግግር የተሞላ ሰው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ ማየቴ እጅጉን አሳዝኖኛል” ብሏል፤ የአይቲ ባለሙያው፡፡  
አሜሪካ ከገባ 10 ዓመት ያስቆጠረው የሜሪላንዱ ነዋሪ ቢኒያም አያልቅበት፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን ትራምፕ መመረጡ እንዳስከፋው አልሸሸገም፡፡ ያለምክንያት ግን አይደለም፡፡  “ሰውየው  ፖሊሲ የሌለው መሆኑና በተለይ በስደተኛ ሙስሊሞች ላይ ያለው አቋም በእጅጉ ያበሽቀኛል፤ ይሄ ሀገሪቱን ወደ ኋላ የሚጎትት ነገር ነው” ይላል፡፡   በቴክሳስ ነዋሪ የሆነው ሌላው ኢትዮጵያዊ ወጣት፣ አሜሪካ ብዙም አልቆየም፡፡ ገና አንድ ዓመት ከ5 ወሩ ሲሆን የምርጫውን ሂደት በአንክሮ ሲከታተል እንደነበርና ትራምፕ እንዳይመረጥ ፀሎት ቢያደርግም እንዳልተሳካለት ይናገራል፡፡ የመኖሪያ ፍቃድ በማውጣት ሂደት ላይ እንደነበር የሚገልፀው ወጣቱ፤ የትረምፕ መመረጥ በሀገሪቱ የመቆየት እድሉ ላይ ጥላ እንዳጠላበት ይናገራል፡፡ “እስካሁን የሰራሁትና የተከሰስኩበት ምንም አይነት ወንጀል የለም፤ የጠየቅሁት የፖለቲካ ጥገኝነት ነው፤ውጤቱን በተስፋ እየተጠባበቅሁ ነው” ብሏል ወጣቱ፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም በተመሳሳይ በትራምፕ መመረጥ ደስተኞች እንዳልሆኑና የሃይማኖትና የዘረኝነት ጥቃት ይደርስብናል ብለው እንደሚሰጉ ተናግረዋል፡፡  
እዚያው ተወልደው ሙሉ የአሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው፣ ከኢትዮጵያ ሄደው ዜግነት ያገኙና እንዲሁም ዜግነት ሳያገኙ በመኖሪያ ፍቃድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግን ከሀገሪቱ እንባረራለን የሚል ስጋት እንደሌላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡   
ከሀገሪቱ የመባረር ስጋት ያደረባቸው የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው የተከለከሉና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያለ፤ ጥያቄያቸው በፍርድ ቤት ተቀባይነት ሳያገኝ ከሀገር እንዲወጡ ተብለው ተደብቀው የሚኖሩና ጥገኝነት ጠይቀው የስራ ፍቃድ ብቻ ተሰጥቷቸው ጉዳያቸው በእንጥልጥል ላይ ያለ ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሏል፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ50 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄ በእንጥልጥል ላይ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ካቢኔያቸውን በማዋቀር ላይ ሲሆኑ አንዳንድ ተመራጭ የካቢኔ አባሎቻቸው ዘረኛ አቋም ያራምዳሉ መባሉ በስደተኞች ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረ ታውቋል፡፡


Read 4884 times