Sunday, 27 November 2016 00:00

በአ.አ.ዩ ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ ያስቆጠረ ታቦት ተገኘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

      በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ካምፓስ ሙዚየም ውስጥ ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ ያስቆጠረ ታቦት የተገኘ ሲሆን ታቦቱ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እንደተመለሰ ታውቋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ግቢ ታቦት ስለመኖሩ ራዕይ ታይቶኛል የሚሉ ግለሰብ ለቤተ ክህነት ባስታወቁት መሰረት ጥናት ተደርጎ መኖሩ በመረጋገጡ፣ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ብዙ ድርድር ከተደረገ በኋላ ህዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም ታቦቱ ለቤተ ክህነት መመለሱን በጉዳዩ ተሳታፊ የነበሩት መምህር ብሩክ አሳመረ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
“ታቦቱን አፄ ኃይለሥላሴ እንዳሰሩትና የሚካኤል ታቦት መሆኑን የሚገልፅ ማስታወሻ ተገኝቷል። ታቦቱ ከ68 ዓመት በላይ እድሜ እንዳለውም ታውቋል” ብለዋል - መምህር ብሩክ፡፡
ታቦቱ በዩኒቨርሲቲው ስለመኖሩ አቶ በለጠ ዘነበ የተባሉ ባህታዊ በራዕይ ታይቶኛል በሚል በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደነበር የጠቆሙት መምህር ብሩክ፤ “ቅዱስ ሚካኤል ሚዛንና ሰይፍ ይዞ በዩኒቨርሲቲው ካምፓስ 1ኛ በር በኩል እየወሰደ ያሳየኛል” እያሉ ይናገሩ እንደነበርና ይህንንም በ2003 አካባቢ ለፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ መግለጻቸውን፣ነገር ግን ትኩረት የሚሰጣቸው ሳያገኙ መቅረታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ግለሰቡ በ2007 ዓ.ም ይሄንኑ ራዕይ  ለአቡነ ማትያስ ማሳወቃቸውንና የሚመለከታቸው የቤተ ክህነቱ የስራ ኃላፊዎች ጉዳዩ እንዲጠና ማዘዛቸውን የጠቆሙት መምህሩ፤ በጥናቱም ፅላቱ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ መኖሩ መረጋገጡን መምህር ብሩክ አውስተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ዩኒቨርሲቲው ታቦቱን ለቤተ ክርስቲያኗ እንዲመለስ በርካታ የደብዳቤ ልውውጦች የተደረጉ ሲሆን መጀመሪያ ላይ ዩኒቨርሲቲው መንግስታዊ የእውቀትና ምርምር ተቋም እንደመሆኑ፣ ቅርሶችን ተንከባክቦ የመያዝና ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለው በመግለጽ፣ታቦቱን ለቤተ ክርስቲያኗ ለማስረከብ በእጅጉ ተቸግሮ ነበር ይላሉ፡፡ ሆኖም ፅላት ለቱሪስቶች ክፍት ሆኖ መታየት የሌለበት የእምነት መገለጫ በመሆኑ፣ በዩኒቨርሲቲው ሙዚየም ውስጥ ቢቀመጥ ትርጉም እንደሌለው ስምምነት ላይ በመደረሱ፣ የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በአደራ ተረክቦ እንዲያስቀምጥ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ታቦቱ አልተርስቶን በሚል ስያሜ በመዝገብ ቁጥር 1761 ተመዝግቦ የተገኘ ሲሆን ሚስተር ስቲፈን ራይት በተባለ ሰው እ.ኤ.አ ሰኔ 12 ቀን 1961፣ ወደ ሙዚየሙ መግባቱ እንደታወቀ መምህሩ ይናገራሉ፡፡
ነገስታት ታቦትን አስቀርፀው በቤተ መንግስታቸው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የማስቀመጥ ልምድ እንደነበራቸው የጠቀሱት መምህሩ፤ ምናልባት አፄ ኃይለሥላሴም ይህን ታቦት ለተመሳሳይ ዓላማ ሳያስቀርፁት እንዳልቀረ ግምት መኖሩን አመልክተዋል። “ታቦቱ በዩኒቨርሲቲው ሙዚየም 3ኛ ምድር ቤት ውስጥ ለብቻው በተሰራ ቤት ውስጥ ተደብቆ ነው የተገኘው፤የሙዚየሙ ሰራተኞች እንኳ ታቦቱ መኖሩን አያውቁም ነበር” ብለዋል - መምህሩ፡፡
ከሰኔ 12 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ከመላኩ ቅዱስ ሚካኤል ጋር ይገናኙ እንደነበር የገለጹት  ታቦቱን በራዕይ አይተዋል የተባሉት አቶ በለጠ ዘነበ፤በተደጋጋሚ ወደ ፓትርያርክ ጽ/ቤት እየሄዱ ስለ ጉዳዩ ቢናገሩም ትኩረት አለማግኘታቸውን አስታውሰው፣በኋላ የቤተ ክርስቲያኗ ልማታዊ ተራድኦ ኮሚሽንና የቤተ-መዛግብትና ቅርስ ክፍል ኃላፊዎች ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ታቦቱን ከዩኒቨርሲቲው መረከብ መቻሉን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቪርሲቲ የታሪክ ምሁር የሆኑትን ፕ/ር አህመድ ዘካሪያን ስለ ጉዳዩ ጠይቀናቸው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል - “አሁን ብዙም የምገልፀው ነገር የለም” በማለት፡፡    
በዩኒቨርሲቲው ሙዚየም የተገኘውን የቅዱስ ሚካኤል ታቦት አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃንና ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ለጥር 9 ቀን 2009 ዓ.ም መርሃ ግብር መያዙን መምህር ብሩክ ገልጸዋል፡፡  
አሁን ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት ግቢ የአፄ ኃይለ ሥላሴና ቤተሰቦቻቸው መኖሪያ እንደነበርና ንጉሱ ለትምህርት ተቋምነት በስጦታ እንዳበረከቱት ይታወቃል።   



Read 9687 times