Sunday, 27 November 2016 00:00

የኢህአዴግ ግምገማ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንዳለበት ፖለቲከኞች አሳሰቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(28 votes)

   ኢህአዴግ ህዝብ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ “ጥልቅ ተሃድሶ” ለማድረግ ቃል መግባቱን ተከትሎ በፓርቲው 4 ግንባር ድርጅቶች ለወራት የዘለቀ ግምገማና ሹም ሽር እየተካሄደ ሲሆን ግምገማዎች ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንዳለባቸው ፖለቲከኞችና ምሁራን አሳሰቡ፡፡
ኢህአዴግ ከአመራሮች ግምገማ ምን ውጤት እንደሚጠብቅ በግልፅ አለማስቀመጡንና ግለሰቦችን የመቀያየር ስራ ብቻ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት የመድረክ አመራር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ ፖሊሲዎች፣ አሰራሮችና አስተሳሰቦችም መለወጥ አለባቸው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የፌደራሊዝም መምህር አቶ ናሁሰናይ በላይ በበኩላቸው፤መንግስት የህዝቡን ችግር በቅጡ አላወቀውም ይላሉ፡፡ መንግስት በሽታውን ሳይሆን ምልክቶቹን ለማከም እየተሯሯጠ ነው ሲሉ የተቹት መምህሩ፤ በዚህ ሁኔታ የሚካሄድ ግምገማና ሹም ሽር ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብዬ አልጠብቅም ብለዋል፡፡   
“አሁን የሚደረጉት ግምገማዎች ፋይዳቸው አይገባኝም” ያሉት የህውሃት አንጋፋ ታጋይ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ፤ እስካሁን በግምገማ የመጣ ውጤት አላየሁም ብለዋል፡፡ የፖለቲካውን ችግር ሊፈታ የሚችለው ምህዳሩን በማስፋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ ቀድሞ የነበረው ግምገማ ጠንካራ እንደነበር ያስታወሱት የታሪክ ምሁርና አንጋፋ ፖለቲከኛ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤የአሁኑ ግምገማ በሙስና እና በመልካም አስተዳደር ላይ ብቻ የሚያነጣጥር ከሆነና የዲሞክራሲና የፖለቲካ ጉዳይን ከዘነጋ ውጤታማነቱ አጠራጣሪ ነው ባይ ናቸው። የእስካሁኖቹ ግምገማዎች በተለይ በመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምና በዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ ብዙም አላተኮሩም ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ በዋናነት ህዝብ ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡   መንግስት የሚያደርጋቸው ሹም ሽረቶች ግልፅነት እንደሚጎድላቸው የገለፁት የዛሚ ኤፍኤም ሬዲዮ መስራችና ባለቤት አቶ ዘሪሁን ተሾመ በበኩላቸው፤በአዲሱ የካቢኔ አወቃቀር የተነሱ ሚኒስትሮች ከስልጣናቸው የተነሱበት ምክንያት ለህዝብ በግልፅ ተዘርዝሮ መነገር አለበት ይላሉ - ግምገማዎችም በዚህ መልኩ መቃኘት እንዳለባቸው በመጠቆም፡፡
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከ27 ሺህ በላይ አመራሮች በግምገማ ላይ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን ጥፋት በተገኘባቸው አመራሮች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡ በኦሮሚያ ከክልሉ ፕሬዚዳንት ጀምሮ በበርካታ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ሹም ሽር የተደረገ ሲሆን በትግራይ፣ በደቡብና በአማራ ክልሎች ነባሮቹ ፕሬዚዳንቶች በስልጣናቸው እንደቀጠሉ ታውቋል፡፡   

Read 5617 times