Sunday, 27 November 2016 00:00

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስለ ኢህአዴግ ግምገማዎችና ተሃድሶ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የኢህአዴግ የግምገማና የተሃድሶ ባህል ምን የኢህአዴግ የግምገማና የተሃድሶ ባህል ምን
ይመስላል? በሚለው ላይ በሽግግሩ ወቅትና ከዚያ በኋላ እስከ 1993 የተሃድሶ ንቅናቄ ድረስ የኦህዴድ እና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ይመስላል? በሚለው ላይ በሽግግሩ ወቅትና ከዚያበኋላ እስከ 1993 የተሃድሶ ንቅናቄ ድረስ የኦህዴድእና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ
ጊዳዳ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

እርሶ በመንግስት አመራርነት በነበሩ ጊዜ ግምገማዎች እንዴት ይካሄዱ ነበር?
መስሪያ ቤቶችና ተቋማት፣ መጀመሪያ ስራቸውን ለማሻሻል የስራ እቅድ ያዘጋጃሉ፡፡ ከዚያም በየጊዜው መሰረት አፈፃፀሙ ይገመገማል፡፡ እኔ የነበርኩ ጊዜ፣ የየዞኖች የስራ አፈፃፀም በየወሩ ይገመገም ነበር፡፡ የክልል ደግሞ በ6 ወር ይገመገም ነበር፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ፣ የየድርጅቶቹ ስራ አስፈፃሚ፣ በኢህአዴግ ጽ/ቤት ይገናኝና ጠንካራ ግምገማ ይካሄዳል፡፡
በአብዛኛው የስራዎች አፈፃፀም፣ ጥንካሬና ድክመት ነው የሚገመገመው፡፡ ይህ የስራ አፈፃፀም ግምገማ ይባላል፡፡ የስራ ግምገማ ከተካሄደ በኋላ፤ የፈፃሚ አካላት ግምገማ ይደረጋል፡፡ የፈፃሚው አካል (የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የክልል ቢሮዎች ወዘተ …) በስራው ጥንካሬና ድክመቶች ላይ ሚናው እንዴት ነበር? የሚለው ይገመገማል፡፡
ይህ ካለቀ በኋላ ተቋማትን የሚመሩ ኃላፊዎችና አባላት በግለሰብ ደረጃ ይገመገማሉ፡፡ በጥንካሬ ውስጥ አስተዋፅኦቸው ምን ነበረ? በድክመቱ ላይስ? የሚለው ለየብቻ በነጥብ ተለይቶ ይቀመጣል። ይህ ከተደረገ በኋላ ሰውየው (ተገምጋሚው)፣ የራሱን ሃሳብ እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ ሌሎችም ሃሳብ ይሰጣሉ። የሰውየው ጥንካሬ የሚያመዝን ከሆነ፣ በጥሩ የስራ አፈፃፀም እውቅና ይሰጠዋል፡፡ ደካማ ከነበረ ደግሞ፣ ለምንድን ነው የደከመው? የሚል ጥያቄ ይቀርባል። ግለሰቡ (ተገምጋሚው)፣ በዚህ ላይም አስተያየት ይሰጣል፡፡ ለምን ይሄን መፈፀም አቃተህ ተብሎ ሲጠየቅ፣ ስራ ስለሚበዛብኝ፣ መሳሪያዎች ስላጣሁ፣ መኪኖችን ስላጣሁ፣ ገንዘብ ስላጣሁ እና መሰል ምክንያቶችን ብዙውን ጊዜ ይዘረዝራል፡፡
ገምጋሚው አካል፣ ይሄን ምክንያት አልቀበልም፣ ያንን እቀበላለሁ ይላል፡፡ ለመሆኑ ለስራው ከልብህ እምነት ነበረህ ወይ? በስራው ታምንበት ነበር ወይ? ያ ከሆነ እንዴት መፈፀም አቃተህ? የሚሉ ጥያቄዎች ይሰነዝራሉ፡፡ አንዳንዱ፣ የምትሉትን አልቀበልም ይላል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ አምኖ ይቀበላል፡፡ ግለሰቡ የግምገማውን ነጥቦች ከተቀበለ እንዲያሻሽል ተነግሮት ይታለፋል፡፡ ካልተቀበለ ግን፣ “ይሄ ሰውዬ በስራ አያምንም፤ በስራው የማያምነው ደግሞ በድርጅቱ ስለማያምን ነው” ተብሎ ይደመደማል። ከዚያም እንደጥፋቱ አይነት ወደ ቅጣት ይገባል፡፡
ምን አይነት ቅጣት?
ገንዘብ ሰርቆ ከሆነ፣ ስራ በጣም አባላሽቶ ከሆነ፤ በሰው ላይ ጉዳት አድርሶ ከሆነ፣ እስከመባረር እና እስከ መታሰር የሚደርሱ እርምጃዎች ይወሰዳሉ። ለምሳሌ ኦህዴድ እኔም በነበርኩበት በ1989 ዓ.ም፤ በጠንካራ ግምገማ፣ የአርሶ አድር ካድሬዎችን ጨምሮ፣ ወደ 10ሺህ የሚጠጉ አባላትን አባረናል፡፡ እነዚህን ስናባርር መጨረሻ ላይ የቀረው መሃከለኛ ካድሬ 300 ብቻ ነው፡፡ 180 የሚጠጉት ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እና እንዲታሰሩ መደረጋቸውን አስታውሳለሁ፡፡ እነዚህ ሰው የገደሉ፣ ገንዘብ የሰረቁ፣ ሙስና የታየባቸው ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ በነበረ ሌላ ግምገማ፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትነት ወርዶ ነበር፡፡
አቶ ኩማ ተገምግመው ነው እንዲወርዱ የተደረጉት?
 አዎ! እነ ነጋሶን አልታገልክም ተብሎ በሚገባ ተገምግሞ ነበር፡፡ በደከሙት አመራሮች ላይ፣ በብርቱ አልታገልክም ተብሎ በ1993 ተገምግሞ ነበር፡፡ በ1989ኙ ግምገማ ከከፍተኛ አመራር እንዲወርዱ ከተደረጉት እነ ጫላ ሆርዶፋ ነበሩበት። በኋላ እንዴት እንደሆነ አላውቅም፤ ያኔ ተባረው የነበሩ ሰዎች ተመልሰው ተመልክተናል፡፡
ግምገማዎቹ ጠንካራ ነበሩ?
 አዎ! በጣም ጠንካራ ነበሩ፡፡ በኦህዴድ ውስጥ ጠንካራ ግምገማ ይካሄድ ነበር፡፡ የሌሎች እህት ድርጅቶች ሁኔታ አላውቅም ነበር፡፡ በወቅቱም የግምገማ ውጤታቸው አንሰማም ነበር፡፡ ለምን የእህት ድርጅቶች የግምገማ ውጤት አይነገረንም የሚል ጥያቄ በአንዳንድ የኦህዴድ አባላት ይነሳ ነበር። ግን የኦህዴድ ግምገማ ጠንካራ እንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡ ያለ ስስት 300 ካድሬ እስኪቀሩ ከ10 ሺህ በላይ ካድሬዎችንና አባላትን ማሰናበት መቻሉ ማሳያ ነው፡፡
በግምገማዎቹ እያንዳንዱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች የኦህዴድ፣ የብአዴን፣ የህውሓት የውስጥ ነፃነት ምን ድረስ ነበር?
አራቱም ድርጅቶች በተናጠል ግምገማ ሲያካሂዱ፣ ከዋናው የኢህአዴግ ጽ/ቤት የሚላኩ ታዛቢዎች ነበሩ፡፡ የስብሰባው አካሄድ እንዴት ነበር የሚለውን ለማየት ነው፡፡ በ1989 በነበረው ጠንካራ ግምገማ፣ እኔ እስከማስታውሰው እነ ተወልደ፣ አለምሰገድ በኦህዴድ ግምገማ ላይ ይገኙ ነበር፡፡ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ደግሞ፣ ሁል ጊዜ እንደ ረዳት ተደርጎ ወደ‘ኛ ስብሰባዎች ከኢህአዴግ ጽ/ቤት ይላክ ነበር፡፡ ወደ ሌሎቹ እህት ድርጅቶችም በተመሳሳይ ከዋናው ጽ/ቤት ሰዎች ይላኩ ነበር፡፡
ወርሃዊ እና በየ3 ወሩ የሚደረጉ ግምገማዎችን ግን ራሳችን ነበር የምናካሂደው፡፡ ሰው አይላክም ነበር፡፡ በድርጅት ተግባራዊ ግምገማ ውስጥ የሚዲያ ጉዳይም አለ፡፡ የሚዲያውን አመራሮች ግምገማ በየ2 ሳምንቱ እኔ ነበርኩ የምመራው፡፡ አመራሮቻቸውን ወደ ጽ/ቤት እየጠራሁ ጠንከር ያለ ግምገማ እናካሂድ ነበር፡፡ አልማዝ መኮ ደግሞ የኦህዴድ አባላት በፓርላማውና በዩኒቨርሲቲ ያሉትን ትከታተል ነበር። ጠንካራ ግምገማዎች ነበር የሚካሄዱት፡፡
ከኢህአዴግ ጽ/ቤት ወደየድርጅቶቹ የሚላኩት ግለሰቦች ሚና ምን ነበር?
በኢህአዴግ የጽ/ቤት ኃላፊዎች በረከት፣ አለምሰገድ እና ተወልደ ነበሩ፡፡ ይመስለኛል በረከት የሁሉንም ድርጅቶች የድርጅታዊ ስራ ይከታተል ነበር፡፡ አለም ሰገድ ደግሞ የፕሮፓጋንዳውን ዘርፍ ይከታተል ነበር፡፡ ተወልደ ደግሞ ሁለቱን ይቆጣጠር ነበር፡፡ ከነዚህ ሰዎች ስር፣ የተለያዩ ጠንካራ ካድሬ የሚባሉ ነበሩ፣ በትግሉ ውስጥ የቆዩ ሰዎች ስለነበሩ የድርጅቱ ግምገማ እንዴት እንደሚካሄድ ያውቃሉ፡፡
እነዚህ ወደየድርጅቶቹ የሚላኩት ግለሰቦች መድረክ ይመሩ ነበር? በውሳኔ ውስጥስ ይሳተፉ ነበር? ተፅዕኖአቸው ምን ድረስ ነው?
መድረክ አይመሩም፡፡ ግን ሃሳብ ይሰጡ ነበር። አቅጣጫም ያስይዙ ነበር፡፡ የነዚህ ሰዎች ሚና፣ የታዛቢነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በውሳኔዎች አይሳተፉም፡፡ መጨረሻ ላይ በግምገማው ላይ የራሳቸውን አስተያየት ያቀርባሉ፡፡ ለኢህአዴግ ጽ/ቤት ያቀርባሉ፡፡ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ደግሞ ወደ ስራ አስፈፃሚው ያቀርባል፡፡ በወቅቱ የስራ አስፈፃሚው ሊቀ መንበር አቶ መለስ ነበር፤ ፀሐፊው ደግሞ አቶ በረከት ስምዖን ነበር፡፡
በአጠቃላይ፣ ከአራቱም ድርጀቶች የተወከልን አምስት አምስት ሰዎች ነበርን - በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፡፡ በየድርጅቶቻችን የተገመገምን ቢሆንም፣ በዚህ የስራ አስፈጻሚ ግምገማ ላይ በድጋሚ ለግምገማ እንቀመጣለን። 20ዎቻችን እኩል ነበር ድምፃችን የሚሰማው። በወቅቱ በኦህዴድ በኩል እኔን ጨምሮ ኩማ ደመቅሳ፣ አሊ አብዶ፣ ዮናታን ዱቢሳ ነበር፡፡
ድምፃችን የሁላችንም እኩል ነበር፡፡ አጨቃጫቂ ጉዳይ ካለ፣ ውሳኔ ለሌላ ጊዜ እናስተላልፍ ነበር። አንዳንዴ ደግሞ አጨቃጫቂ ቢሆንም በድምፅ ብልጫ እንወስናለን፡፡ ለምሳሌ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ውሳኔ ሲተላለፍ፣ አቶ መለስና ዶ/ር ካሱ ብቻ ነበሩ በልዩነት የወጡት፡፡ ከሁለቱ በስተቀር፣ ሌሎቻችን (18) በአንድ ድምፅ ነበር በጦርነቱ ጉዳይ ውሳኔ ያሳለፍነው። ብዙ ሰው በወቅቱ አቶ መለስ ሁሉንም ነገር የሚወስን ይመስለዋል፡፡ ግን አይደለም። መለስ ራሱ በግምገማ ትችት ይደርስበት ነበር። በድርጅት ጉዳይ በተደጋጋሚ ተተችቷል። በእርግጥ፣ የመንግስት ስራን አቶ መለስ እንዴት ይመራ እንደነበር ግምገማ አይደረግም ነበር፡፡ በወቅቱ ይሄ ጉዳይ አጨቃጫቂ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኤርትራ ጦርነት ጋር ተያይዞ ነው፣ አጠቃላይ የመንግስት ስራ ይገምገም ተብሎ
የተወሰነው፡፡ በዚህ ጊዜ፣ አቶ መለስ ሌላ አጀንዳ ይዘው ብቅ አሉ፡፡ እኛ ግምገማ እናደርጋለን ብለን ስንቀመጥ፣ አቶ መለስ እነሱ የድርጅቱን የወደፊት አቅጣጫ የምታሳይ ናት በማለት “ቦናፓርቲዝም” በሚል ርዕሰ የተፃፈ ሰነድ ይዘው መጡ፡፡ የወደፊት አቅጣጫችን ምን እንደሚሆን ከወሰን በኋላ ግምገማ እናካሂዳለን አሉ፡፡ ይሄ ነበር በወቅቱ አጨቃጫቂ የነበረው፡፡ እኔ ከድርጅቱ ከወጣሁ በኋላ እንዴት እንደሚደረግ መረጃው የለኝም፡፡
አሁን የ15 ዓመት የኢህአዴግ የስራ አፈፃፀም ግምገማ እየተደረገ መሆኑና ድርጅቱና መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ ላይ መሆናቸው እየተገለፀ ነው፡፡ ከነበረዎት ልምድ በመነሳት፣ ግምገማው ውጤታማ ይሆናል ብለው ይጠብቁ ይሆን?
ግምገማው ትክክለኛ ከሆነ መልካም ነው። ይመስለኛል የስራ ግምገማ ከተደረገ በኋላ፤ የግለሰቦች አስተዋፅኦ ጥንካሬና ድክመት ይገመገማል። እንደማስታውሰው በስራ ድክመት ከድርጅት የሚባረር አልነበረም፡፡ ለመባረር ዋናው ምክንያት፣ የአመለካከት ግምገማ ነው፡፡ በስራ ግምገማ ደካማ ውጤት ያገኘ ግለሰብና ከስራ ቦታው ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወር፣ ከስልጣን ዝቅ እንዲል ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ አቶ ሙክታር ከድር እና ወ/ሮ አስቴር ማሞ ከስልጣን ወርደዋል ተብሏል፡፡ ግን በዞኖች ግምገማ ላይ መድረክ ሲመሩ ታይቷል፡፡ ይሄን ስመለከት፣ እነዚህ ሰዎች በግምገማ የተገኘባቸው ጥፋት፣ የስራ ድክመት ብቻ ነው? የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡ ነገር ግን በስራ ድክመቱ የተነሳ‘ኮ ግጭት ተፈጥሯል ተብሏል፡፡ የሰው ህይወትና ንብረት ጠፍቷል ተብሏል፡፡ ይሄ ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡ ግን እንዳልኩት የስራ ድክመት አያስቀጣም፡፡
ከአሁኑ ግምገማ ምን ይጠብቃሉ?
የአሰራርና የአመለካከት ግምገማ ተካሂዶ፣ “የተቃዋሚ አመለካከት አለው፤ በዚህ ነው ስራውን መስራት ያልቻለው” ተብሎ ከተገመገመና ጥፋቱ አስከፊ ከሆነ የሚወሰዱት እርምጀዎች፣ ከማሰር፣ ከማባረር እና ከቦታ ቦታ ማዘዋወር የትኛው እንደሚሆን፣ በቀጣይ የምናየው ይሆናል፡፡ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡ ቀድሞ በነበረው አሰራር ግን፣ እርምጃ ሳይወሰድ ቀድሞ አይነገርም ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ግምገማው ምናልባት ስራቸውን ለማሻሻል ይጠቅማቸው ይሆናል፡፡
ህዝቡ ያቀርባቸው ብዙ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎች እንዳሉ ሁሉ፣ የፖለቲካና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችም አሉ፡፡ እኔ የምፈራው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮችን ብቻ ለማሻሻል ጥረት አድርገው፤ በሚዲያና በዲሞክራሲ ረገድ፣ በተለይ ሰፊው ህዝብ የሚሳተፍበት መድረክ ሳይከፍቱ እንዳያልፉት ጥርጣሬ አለኝ፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይ፤ ብዙ ሲናገሩ አይደመጡም፡፡ የሰብአዊ መብት አያያዝና የዲሞክራሲ ጉዳይ ካልተሳሻሻለ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኩን ማስተካከል፣ ብቻውን ውጤት ላያመጣ ይችላልና ቢያስቡበት ጥሩ ነው፡፡
እኔ ትንሽ የተስፋ ፍንጭ ያየሁት፣ የምርጫ ስርአቱ ላይ ማሻሻያ ይደረጋል የተባለው ላይ ነው። ይሄ ደግሞ ህገ መንግስት ማሻሻልን ይጠይቃል። ያንን ያደርጋሉ አያደርጉም የሚለው ለወደፊት የሚታይ ነው፡፡ በሚዲያ በኩል ደግሞ፣ ሬዲዮ ፋና ውይይት ማዘጋጀቱ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በመንግስት ሚዲያ ላይ አንቀፅ 29 እየተሰራበት ነው ወይ የሚለውን ማየት አለብን፡፡  

Read 3664 times