Sunday, 27 November 2016 00:00

“ችግሮችን ለመፍታት ሳይሆን ምልክቶችን ለማስታገስ ነው ትኩረት የተደረገው”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ናሁሰናይ በላይ
(በአ.አ.ዩ የፖለቲካ ሳይንስ እና የፌደራሊዝም መምህር

ሹም ሽር መደረጉ፣ መንግስት የለውጥ ፍላጎት እንዳለው፣ ምልክት እንደማሳየት ነው፡፡ “የለውጥ ፍላጎት አለኝ፤ ፍላጎቴንም በዚህ በሹም ሽር እዩት” የሚል ምልክት ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን፣ ከገጠመን ችግር አንፃር ሲታይ የሚያስፈነጥዝ አይደለም፡፡
እርግጥ ነው፣ ያመጣው ነገር አለ፡፡ እውቀት እና ስራ መገናኘት አለባቸው የተባለ ይመስላል፡፡ እውቀትና ስልጣን ሲገናኙ፣ የተሻለ ነገር መስራት ይቻላል የሚል አቅጣጫ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ይሄ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን መጠንቀቅ አለብን፡፡
ኢትዮጵያ ላይ የተከሰተው ችግር፣ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ የመንግስት ቅቡልነት ቀውስ ውስጥ የገባበት ነው፡፡ በጣም ጉልህ የስራ አጥነት ችግር አለ፡፡ እንግዲህ ከገጠመን ችግር አንፃር፣ የመንግስት ጥረት በሹም ሽር የሚያበቃ ከሆነ፣ ሌላ ራሱን የቻለ ችግር ነው የሚሆነው፡፡ ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም፣ ከአገሪቱ ችግር አንፃር ትንሽ ነው፡፡
የኢህአዴግ ድርጅቶችን ግምገማ በተመለከተ፣ እኔ ከግምገማዎቹ ብዙ አልጠብቅም፡፡ ኢህአዴግ ችግሩን በቅጡ ያወቀው አልመሰለኝም፡፡ አሁን የችግሩን ምልክቶች ነው እያሯሯጠ ያለው፡፡ በሽታውን ሳይሆን የበሽታውን ምልክቶች ነው እያከመ ያለው፡፡
በዚህ ሁኔታ አሚካሄድ ግምገማና ብወዛ፣ ትልቅ ለውጥ እንዲያመጣ አልጠብቅም፡፡ በእርግጥ፣ ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል ጥሩ የመሻሻል ምልክት ታይቷል፡፡ የተማረና አቅም ያለው፣ ወጣት አመራር ለመፍጠር ዝግጁ እንደሆነ አሳይቷል፡፡ በተቃራኒው በህውሓትና በብአዴን በኩል ሲታይ ደግሞ፣ ፍላጎቱ ያላቸው አይመስልም፡፡ ወንበሩን እንደርስት የያዙ ሰዎች፣ በዚያው እንዲቀጥሉ የሚያስቡ ይመስላል፡፡
ስለዚህ ኢህአዴግም መንግስትም፣ የችግሩን መሰረታዊ ባህሪ በቅጡ ሳይረዱ፣ ችግሩን ያክማል ብለው የሚያመጡት መድኃኒት፣ ችግሩን ከማከም ይልቅ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል የሚል ስጋት አለኝ። ዋናው የኢህአዴግ ችግር የሚመስለኝ፣ ችግሩን አለማወቁ ነው፡፡ ወይ ለማወቅ አለመፈለግ፣ አሊያም ለማወቅ አለመቻል፡፡
የፌደራል ስርአቱም ሆነ ህገ መንግስቱ፣ ችግር አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡ ፖለቲካው ህገ መንግስቱን መምሰል ስላልቻለ ይመስለኛል እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ የገባነው፡፡ በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ ሊኖር የሚገባው ህግንና ህግን ብቻ መሰረት ያደረገ አሰራር፣ ገና አልተፈጠረም። ይሄ የእገሌ ወይም የእገሊት ድክመት አይደለም፡፡ ግን አሁን የተፈጠረውን ችግር ከግለሰቦች ባህሪ ጋር ያገናኙታል፡፡ ይሄ ተስፋን የሚያጨልም ነው፡፡
የፖለቲካ ስርአት ሊበላሽ የሚችለው፣ ከግለሰብ በመነጨ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ግለሰቦች ስልጣን ሲያገኙ አይበላሹም ማለቴ አይደለም፡፡ የሚበላሹ ግለሰቦች ሁሌም የትም አገር ይኖራሉ፡፡ ዋናው ነገር፣ የፖለቲካ ስርዓቱ፣ ባለስልጣናት እንዳይበላሹ የሚቆጣጠር መሆኑና አለመሆኑ ላይ ነው፡፡ ችግሩን በዚህ መንገድ አይቶ ሳይንሳዊ ጥናትና ትንታኔ መስራት ካልተቻለ፣ “እንታደሳለን፤ ቃል እንገባለን” ማለት ብዙም አያስኬድም፡፡

Read 1714 times