Print this page
Sunday, 27 November 2016 00:00

የአዲሱ ካቢኔ ተስፋዎችና ፈተናዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግንቦት 2009 ምርጫ ማግስት ያቋቋሙትን ካቢኔ በመበተን፣ ምሁራንን
በርከት አድርገው አዲስ ካቢኔ ሾመዋል፡፡
ፖለቲከኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችስ ምን ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በአዲሱ
ካቢኔ ዙሪያ የአንጋፋ ፖለቲከኞችን አስተያየት እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

“ተቃዋሚዎችና ኢህአዴግ መወያየት አለባቸው”
አቶ ሙላቱ ገመቹ (የኦፌኮ አመራር)

የህዝቡ ጥያቄዎች በአብዛኛው፤ የ“ሲስተም” ለውጥን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ከኢህአዴግ የምንሰማው የለውጥ አይነት ግን ሌላ ነው፡፡ በውስጡ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ሙስኞች እንዳሉ ይናገራል፡፡ እናም፣ እነዚህን አባርሬ፣ በአዲስ መንፈስ የህዝብን ፍላጎት አሟላለሁ ነው የሚለው፡፡ እንደ‘ኔ፣ በዚህ የኢህአዴግ ሃሳብ ከሄድን፣ ለምሳሌ ምርጫ ቦርድን ሙሉ ለሙሉ በመቀየር አሰራሩን የማስተካከል፤ ከዚያም በቁርጠኝነት ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የማካሄድ፤ ሀሳብ ሊነሳ አይችልም፡፡ ህዝቡ ጋ ግን፣ እንዲህ አይነት የለውጥ ጥያቄ ያለ ይመስለኛል፡፡
ኢህአዴግ፣ በዚህች ሀገር የዶክተሮችና የፕሮፌሰሮች እጥረት ያለ አስመስሎ ነው፣ እንደ አዲስ ካቢኔውን በዶክተሮችና በፕሮፌሰሮች ያዋቀረው፡፡ ግን ይሄ ብቻውን መልስ አይሆንም፡፡ ከስልጣን የተነሱት ሰዎችኮ፣ በግላቸው የፈጠሩት አሰራር የለም፡፡ በተዘረጋላቸው ሲስተም ውስጥ ሆነው ነው የሰሩት፡፡ ከዚያ መውጣት አይችሉም፡፡ አዲሶቹ ተሿሚዎችም፣ በዚያው ሲስተም እንዲሰሩ ነው የሚጠበቀው፡፡ ስለዚህ አዲሱ ነገር ምንድነው? የሚለው ጥያቄ አስቸጋሪ ነው፡፡ በቀጣይ የምናየው ይሆናል፡፡
በግጭቶች ሳቢያ የበርካታ ሰዎች  ህይወት አልፏል፤ ንብረት ወድሟል፡፡ በአንድ በኩል፣ መንግስት፣ የብልሹ አመራር ችግር ነው ብሏል፡፡ ግን እስካሁን በህግ የተጠየቀ ሰው አላየንም፡፡ ታዲያ፣ ከስልጣን የተነሱ ሰዎች ምንድን ነው ጥፋታቸው? ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ ህይወት ያጠፉ ፍ/ቤት መቅረብ አለባቸው፡፡
ሌላው ጥያቄ፣ የአመራሮች ግምገማ ጉዳይ ነው፡፡ ከኢህአዴግ ግምገማ ምን ውጤት ነው የሚፈለገው? በኦሮሚያ የአመራር ለውጥ ከተደረገ በኋላ፣ ምን ውጤት መጣ? ይሄን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ባለስልጣናት ስራቸውን በአግባቡ ካልሰሩ ራሳቸው ናቸው አልቻልኩም ብለው መልቀቅ ያለባቸው። እዚያው ቦታ ተቀምጠው ተሃድሶ አድርገናል፣ ተሻሽለናል ቢሉ፣ የሚያመጣው ውጤት የለም። የፖሊሲ ለውጦች ያስፈልጋሉ፡፡ ሰዎች ከወንበር ወንበር መዘዋወራቸው ብቻ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ስለዚህ፣ ሲስተሙ፣ አሰራሩ መፈተሽ አለበት፡፡
ሰላም አለ የሚባለው፣ ህዝብ ነፃ ሆኖ ሲወያይ፣ ለተፈጠሩት ችግሮች የራሱን መፍትሄዎች ሲያስቀምጥ ነው፡፡ አሁን ኢህአዴግ በር ዘግቶ የሚያደርጋቸው ግምገማዎችና ስልጠናዎች የሚያመጡት ለውጥ ብዙም አይታየኝም፡፡ ተቃዋሚዎች እዚሁ ሀገር አሉ፡፡ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን ከኢህአዴግ ጋር እንዴት መወያየት አንችልም? ቅሬታ ያላቸው ግለሰቦች እንኳ ሳይቀሩ፣ የውይይት አካል መሆን አለባቸው፡፡ ኢህአዴግ በቁርጠኝነት ለዚህ መዘጋጀት አለበት፡፡ ተቃዋሚዎችን ጠርቶ፣ እስቲ ምንድን ነው የምትሉት? አማራጫችሁን አምጡና እንወያይ ማለት አለበት፡፡
ለሀገራችን ስንል፣ በአማራጮቻችን ላይ በሰፊው መነጋገር አለብን፡፡ ስለዲሞክራሲ መምከር አለብን፡፡ የኢህአዴግ ሹም ሽር ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ አስተማማኝ አይሆንም፡፡

=====================================

“ሚዲያዎች ለውይይት ክፍት መሆን አለባቸው”
አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ (የህውሓት መስራች አባል የነበሩ)

በቅርቡ የተካሄደው ሹም ሽር፣ ኢህአዴግ ከህዝብ እና ከራሱ ስርአት ተናቦ የፈፀመው አይመስለኝም፡፡ አዲሱ ካቢኔ፣ በትምህርታቸው የላቁና ሲቪሎችን ያሰባሰበና ብሄራዊ ተዋፅኦን ያገናዘበ መሆኑ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን፣ ዋናው የፖሊሲና የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ ያ ካልሆነ፣ አዲሶቹ ተሻሚዎች ወደ ነባሩ ሲስተም የገቡ በመሆ ናቸው፣ ያልተመጣጠነውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ሊያስተካክሉ ይችላሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
ኢህአዴግ በራሱ ላይ የጨከነበት የካቢኔ ለውጥም አይደለም፡፡ ቢጨክን ኖሮ፣ ብዙ ነገር ላይ መቁረጡ አይቀርም ነበር፡፡ ዋናው ነገር፣ ለውጥ የሚመጣው፣ ዜጎች በተስተካከለ ምርጫ ላይ በሚያደርጉት ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ትርምስና ችግር፤ ካለፈው ምርጫ ጋር ይያያዛል፡፡ በምርጫው ኢህአዴግ 100 በመቶ መመረጡ፣ ብዙ ጉድለት አስከትሏል፡፡ ሌላው ችግር፣ የህግ የበላይነት አለመከበሩ ነው፡፡ ይሄን እናስተካክላለን ብለው ካሰቡ፤ ብዙ ነገር መነካካት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይሄን ያደርጋሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
የአመራር ግምገማውን በተመለከተ፣ በኢህአዴግ ውስጥ በነበርኩ ጊዜ የሚደረጉትን ግምገማዎች አውቃቸዋለሁ፡፡ ያኔ በትግሉ ጊዜ የስራ ግምገማ ተደርጎ፣ ወዲያውኑ ወደ ተግባራዊ ለውጥ እንገባ ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ደርግን የሚያህል ግዙፍ ኃይል ደምስሰናል፡፡
ወደ ስልጣን ከተመጣ በኋላ ግን፣ ግምገማ የስልጣን ማጠናከሪያ መሳሪያ ሆኗል፡፡ በትግሉ ወቅት የነበረው ግምገማ በአንፃራዊነት ጥሩ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የተበላሸው፡፡ በ1984 በተደረገው ግምገማ፣ 32ሺ ታጋይ ተባሯል፡፡ ግምገማው ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማምጣት ሳይሆን፣ ስልጣንን ለማጠናከር የተደረገ ነበር፡፡ ይሄ አካሄድ አሁንም የተለወጠ አይመስለኝም፡፡ ከህዝብ ጥያቄ ሲነሳ ስልጣናቸው አደጋ ላይ ስለሚወድቅ፣ የማይፈልጉትን ሰው ለማባረር ግምገማዎችን ይጠቀሙ ነበር፡፡
በኋላም ተሃድሶ የሚል ግምገማ መጥቷል፡፡ ቀጥሎ መተካካት የሚባል ነገር መጣ፡፡ ግን ተተኪ ሰው አብስለው አላዘጋጁም፡፡ ምሁራን ተተኪ ሆነው እንዲገቡ አልተደረገም፡፡ በአገልጋይነት መስፈርት ነው ተተኪዎች የተመደቡት፡፡ ይሄ ውጤት ያመጣ አይመስለኝም፡፡ በዚህ መሃል ልክ የለሽ ስልጣን በግለሰቦች እጅ ገብቶ ሙስና ተስፋፍቷል፡፡ ይሄ ትልቁ ችግር ነው፡፡
አሁንም፣ አዲሱ ግምገማ ምን ፋይዳ ያመጣል የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ድርድር ማድረግ፣ የፖለቲካ እስረኞች ተፈተው የሀገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት ፎረም ተዘጋጅቶ፣ የወደፊት አቅጣጫ ቢተለም መልካም ነው፡፡ የህዝብ ፍላጎትንም በትኩረት ማንበብና ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ ፕሬስና ሌሎች ሚዲያዎች ለውይይት ክፍት መሆን አለባቸው፡፡ አፉ የተዘጋ እንቁላል መሆን የለበትም፡፡


====================================

“የጥልቅ ተሃድሶው ይዘት ግልፅ አይደለም”

ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ (አንጋፋ ታጋይና የአረና አባል)

አዲስ የተሾሙትን ሰዎች አንድ በአንድ አላውቃቸውም፡፡ ምናልባት እነዚህ ሰዎች ህዝባችንን እናገለግላለን የሚል ከፍተኛ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የህዝቡ ጥያቄ አንዱን አውርዶ ሌላውን ለመተካት ብቻ የተሰነዘረ ጥያቄ አይደለም፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉዳይም ቢሆን፣ ሰዎችን በመቀያየር ብቻ መፍትሄ አይገኝም፡፡
የህግ ልዕልና ይከበር የሚል ጥያቄ አለ፡፡ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ ነፃነቶች ይከበሩ የሚል ጥያቄ አለ፡፡ ነፃና ግልፅ የሆነ ምርጫ ይደረግ፣ አንድ ፓርቲ መቶ በመቶ የሚያሸንፍበት ሳይሆን ሁሉም በነፃነት መርጦ የሚሳተፍበት ምርጫ መኖር አለበት የሚል ጥያቄም ይነሳል፡፡
ከዚያ ላይ፣ የሙስና ጉዳይ አለ፡፡ በፖለቲካም በኢኮኖሚም ሙስና የተበራከተበት ሀገር ሆኗል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጥያቄዎች ሳይስተካከሉ፣ በሹም ሽር ሰዎች ቢለዋወጡ፣ በየትኛው ምህዳርና ፖሊሲ ውስጥ ሆነው ነው ሊያስተካክሉ የሚችሉት? ይሄን ስል፣ አዲሶቹ ተሿሚዎች የተለያዩ ችግሮችን ለማስተካከል ጥረት አያደርጉም ወይም ፍላጎት የላቸውም ማለቴ አይደለም፡፡ ግን ምህዳሩ ካልተስተካከለ፣ እነሱ ለውጥ እናመጣለን ብለው ቢሞክሩ እንኳ፣ ብቻውን መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም፡፡
በእርግጥ፣ የምርጫ ስርአቱን እናስተካክላለን ተብሏል፡፡ እንደኔ ግን ወሳኙ መፍትሄ ይሄ አይደለም። አሁን እየተጠየቀ ያለው፣ የምርጫ ስርአት ለውጥ አይደለም፡፡ ምርጫው ራሱ በግልፅነትና ነፃነት የሚካሄድ አለመሆኑ ነው ችግር የሆነው፡፡ መስተካከል ያለበት የምርጫ በነፃነት፣ ፍትሃዊነትና ገለልተኝነት ነው፡፡ አሁን የሚደረጉ ግምገማዎች፣ ፋይዳቸው አይገባኝም፡፡ ከዚህ በፊት ሲደረጉ የነበሩ ግምገማዎች፣ አነሰም በዛም፣ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ ውጤት ያስገኙ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን በግምገማ የሚመጣ ውጤት አላይም፡፡ ተሃድሶ የሚባለውም ፋይዳው አይገባኝም፡፡
እንደውም በ1993 ዓ.ም ተሃድሶ የሚባል ነገር ከተጀመረ ወዲህ ነው፤ ሁሉም ነገር እየጠበበ የመጣው፡፡ ከዚያ በፊት ስንመለከት፣ የተሻለ የዲሞክራሲ ሂደት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን እየጠበበ ነው የመጣው፡፡ ተሃድሶ የሚለው ቃል መልካም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን በተጨባጭ የሚታይ መልካም ውጤት ሲያመጣ አላየሁም፡፡
አሁን፣ ጥልቅ ተሃድሶ የሚባለው ነገርም ለኔ ፋይዳው ግልፅ አይደለም፡፡ ለመሆኑ፣ ከዚያ በፊት የነበረው ተሃድሶ፣ ምን ስለጎደለበት ነው አሁን ጥልቅ የተባለው?

Read 3687 times