Sunday, 27 November 2016 00:00

ኢቢሲና የትራምፕ ምርጫ - አራምባና ቆቦ!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(12 votes)

   “ዶናልድ ትራምፕ፣ በቅርቡ እንደሚታሰሩ ታዋቂው ፕሮፌሰር ተናግረዋል” … ይሄ ከሳምንት በፊት በኢቢሲ የተላለፈ ዜና ነው። የኢቢሲ ዜና፣ በሌጣው የተሰራጨ አይደለም። በቪዲዮ ታጅቧል። ዝነኛው ፕሮፌሰር አለን ሊክማን፣ በገዛ አንደበታቸው ሲናገሩ ታይተዋል - በኢቢሲ ዜና። ዜናው፣ በጣም ያስደንቃል። አለምን የሚያናውጥ ትልቅ ዜና፣ መሆን አለበት።
እንግዲህ፣ ፕሮፌሰሩ የታሪክ ተመራማሪ ናቸው።
ላለፉት 20 ዓመታት በተደረጉ ምርጫዎች ላይ፣ የተወዳዳሪዎችን ጥንካሬና ድክመት እየዘረዘሩ፣ የትኛው ፓርቲና የትኛው ተፎካካሪ ብልጫ እንደሚያገኝ የሚያሳይ ትንታኔና ትንበያ በማቅረብ ይታወቃሉ - ፕሮፌሰሩ። የአገር ውስጥና የውጭ የፖለቲካ ሁኔታዎችን በማገናዘብ፣ እንዲሁም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከአገር አቀፍና ከአለማቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር እያመዛዘኑ ይተነትናሉ። ከትንታኔው በመነሳትም ትንበያ ይሰጣሉ - በምርጫ ማን እንደሚያሸንፍ አስቀድመው ይናገራሉ። ለበርካታ ጊዜያት፣ የፕሮፌሰሩ ትንበያ መሬት ጠብ አላለም። በዘንድሮ ትንበያም፣ እንደወትሮው ተሳክቶላቸዋል።
“90 በመቶ፣... 98%... ዶናልድ ትራምፕ፣ በሂላሪ ክሊንተን ይሸንፋሉ” የሚል የትንበያና የትንታኔ ዶፍ፣ በየእለቱ በሚዘንብበት ወቅት ነው፣ ፕሮፌሰሩ ትንበያቸውን በይፋ የገለፁት። ምርጫው ከመካሄዱ በፊት፣... ለዚያውም ከበርካታ ሳምንታት በፊት።
ታዲያ፣ ፕሮፌሰሩ ያቀረቡት ትንበያ፣ በየአቅጣጫው ሲዥጎደጎድ ከነበረው መዓት ትንበያ ይለያል። አብዛኛው ትንበያ፣ የዶናልድ ትራምፕን አስከፊ አወዳደቅ የሚያውጅ ነበር። ፕሮፌሰሩ ግን፣ ያንን ሁሉ በመቃረን፤ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው እንደሚያሸንፉ ነበር ግምታቸውን የተናገሩት። እውነትም፣ ትራምፕ አሸንፈዋል። ይህንን ውጤት አስቀድሞ መገመት፣ አስገራሚ እውቀት፣ ድንቅ ችሎታ ነው።
ኢቢሲ ግን፣ ሌላ ጉድ ይዞ መጣ። በምርጫው ማግስት፣ “ዶናልድ ትራምፕ፣ በቅርቡ መታሰራቸው አይቀርም” በማለት ፕሮፌሰሩ እንደተናገሩ ዘገበልን። “አጃኢብ ነው” ብትሉ አይፈረድባችሁም። ግን ምን ዋጋ አለው?
የፕሮፌሰሩን ንግግር በቀጥታ ስንሰማው፣… ለካ ነገሩ፣ ሌላ ነው። ዶናልድ ትራምፕ “impeached” የመሆን እጣ ሊገጥማቸው እንደሚችል ይገልፃል - የፕሮፌሰሩ የእንግሊዝኛ ንግግር። ምን ማለት ነው?
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ የስልጣን ዘመኑ ሳያበቃ፣ ከስልጣን እንዲወርድ፣ በአገሪቱ ፊደራል ምክር ቤት (በኮንግረስ) ከተወሰነበት፣ … “impeached” ሆነ ይባላል። ይህንን መራራ ውሳኔ የቀመሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሁለት ናቸው። አንደኛው የቆየ ታሪክ ነው - ከመቶ ሃምሳ አመት በፊት የተከሰተ። ሁለተኛው ግን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው - በቢል ክሊንተን ላይ የደረሰ።
“ቢሮ ውስጥ ከተለማማጅ ሰራተኛ ጋር ማግጠዋል” በሚል የተጀመረ ምርመራ፣ ቀስ በቀስ እየተወሳሰበና እየተደራረበ፣ ቢል ክሊንተንን ጉድ አደረጋቸው። በኮንግረስ፣ ተወሰነባቸው። ነገር ግን፣ ይሄ... የመጀመሪያ ደረጃ ውሳኔ ነው። ኮንግረስ ስለወሰነ ብቻ፣ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ይባረራል ማለት አይደለም።
ጉዳዩ፣ ወደሌላኛው ምክር ቤት (ወደ ሰኔት) ያመራል። በዚሁ የመጨረሻ ፍርድ፣ ከመቶ የሴነት አባላት መካከል፣ 67ቱ ወይም ከዚያ የሚበልጡ ሴናተሮች ከተስማሙበት፣ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን ይወርዳል። ግን፣ እንደምታዩት፣ ሂደቱ ብዙ ነው። በዚህም ምክንያት፣ በአሜሪካ ታሪክ፣ እንዲህ “impeached” ሆኖ፣ ከስልጣን የመባረር እጣ የገጠመው ፕሬዚዳንት የለም። የተሞከረባቸው ግን አሉ።
ለማንኛውም፣ “impeached” ማለት መታሰር ማለት አይደለም። “ከስልጣን እንዲወርድ፣ በምክር ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ውሳኔ ተላለፈበት” እንደማለት ነው። ኢቢሲ፣ ምናልባት “imprisoned” ከሚለው ቃል ጋር ተምታቶበት ይሆናል፣ “መታሰራቸው አይቀርም” ብሎ የዘገበው። አራምባና ቆቦ ልንለው እንችላለን።
በዚያው ዜና ላይ፣ ኢቢሲ ሌላ የትርጉም ስህተት ሰርቷል።
“በባራክ ኦባማ የተሾሙ ዳኛ፣ በዶናልድ ትራምፕ ይሻራሉ” ብሏል ኢቢሲ። በአሜሪካ የመንግስት ስርዓት ውስጥ፤ ማንኛውም ፕሬዚዳንት፣ ዳኞችን መሻር አይችልም። ለነገሩ፣ እንዲህ አይነት አሰራር፣ ያልተለመደ አሰራር አይደለም። ስልጡን የፖለቲካ ስርዓትን ለወጉ ያህል የተቃመሱ አገራት ውስጥ ሳይቀር፣ በኢትዮጵያ ህገ መንግስትም ጭምር ተካተተና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ አሰራር ነው።
ፕሬዚዳንት ወይም ጠ/ሚኒስትር፣ ዳኞችን ከመረጠ በኋላ፣ ሹመታቸው የሚፀድቀው በምክር ቤት ነው። ሹመታቸው ደግሞ፣ እስከ ጡረታ ድረስ ነው። በቃ፣ ጠ/ሚኒስትር ወይም ፕሬዚዳንት ሊሽራቸው አይችልም። ምናልባት ወንጀል የሰራ ዳኛ ካለ፣ ከኃላፊነት የሚባረረው በምክር ቤት ውሳኔ ብቻ ነው።
በሌላ አነጋገር፣ ዶናልድ ትራምፕ፣ በባራክ ኦባማ የተሾሙ ዳኞችን ወይም ሌሎች ዳኞችን መሻር አይችሉም። እና ኢቢሲ፣ ይህንን ጉደኛ የፈጠራ ዜና ከየት አመጣው?
ያው፣ የዳኞች ሹመት፣ በምርጫው ወቅት ከትልልቆቹ አከራካሪ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር። “የዳኞች ሹመት” ከማለት ይልቅ፣ የ“ዳኛ ሹመት” ብንል ሳይሻል አይቀርም። ለምን?
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ ለወትሮው ዘጠኝ ናቸው። አሁን ግን ስምንት ሆነዋል። ከአንጋፋዎቹ ታዋቂ ዳኞች መካከል አንዱ፣ አምና ሞተዋል። ባራክ ኦባማ ምትክ ዳኛ ቢመርጡም፣ በምክር ቤት ሹመታቸው አልፀደቀም። አሁን ምትክ ዳኛ የመምረጥ ስልጣን የሚኖራቸው ዶናልድ ትራምፕ ናቸው። እንግዲህ ይንንን ነው፣ “በኦባማ የተሾሙ ዳኛ በትራምፕ ይሻራሉ” ተብሎ በኢቢሲ የተዘገበው።
ምናልባት፣ በአሜሪካ ምርጫ ዙሪያ በኢቢሲ የተሰሩ ዜናዎች ላይ ተደጋጋሚ ስህተቶች የሚፈጠሩት፣ በጋዜጠኛው ድክመት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን፣ ብቃት ያላቸው አዘጋጆች (ኤዲተሮች) በኢቢሲ እንደሌሉ ይጠቁማል - የአራምባና ቆቦ ዜና።

Read 4604 times