Sunday, 27 November 2016 00:00

“መንግስት ከሁሉም ጋር በግልፅ መወያየት አለበት”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

• ከሃላፊነት የተነሱ ሚኒስትሮች የተነሱበት ምክንያት አልተገለጸም
• ዲሞክራሲ መንታ ልብ ያላቸው ታጋዮች ውጤት አይደለም
• የማህበራዊ ሚዲያን አፍራሽነት ለመቀነስ ድርግም አድርጎ መዝጋት ተመራጭ አይደለም

ሰሞኑ እየተካሄዱ ባሉ የኢህአዴግ ድርጅቶች  የግምገማ መድረኮች፣ በአዲሱ የካቢኔ አወቃቀር፣ በቀጣይ ፈተናዎችና ተስፋዎች እንዲሁም በተያያዥ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ የዛሚ ሬዲዮ መስራችና ባለቤት ከሆኑት አቶ ዘሪሁን ተሾመ ጋር
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምሁራን ያዋቀሩት አዲሱ ካቢኔ ቀድሞ በነበረው “ሲስተም” ውስጥ ገብቶ የሚሰራ በመሆኑ ለውጥ የማምጣት እድሉ አነስተኛ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
በተለይ ከዘመናዊ መንግስትነት ጋር በተያያዘ ማንኛውም የመንግስትን ስልጣን የያዘ ቡድን የራሴ የሚላቸው የአቋም ንድፎችና የፖሊሲ አቅጣጫዎች አሉት፡፡ ይህንንና አተገባበሩን በማሻሻልም ነው፣ ለውጥ የሚመጣው፡፡ የምንፈልገው የለውጥ አይነት፣ … አጠቃላይ ስርአታዊ ለውጥ ነው የሚል ከሆነ አስተያየቶች ይኖራሉ፡፡ በነዚህ ሰዎች አስተያየት ከሄድን፣ ሌላ ኩታ ሰፍተን ሌላ ስርአት መፍጠር ነው ያለብን፡፡ ስለዚህ፣ ስርአታዊ ለውጥ በሚል የሚደረገው ክርክር ጉንጭ አልፋ ነው። አሁን ግን፣ ለውጥ ማምጣት ማለትም ማሻሻል ነው የተፈለገው፡፡ የማሻሻል አቅም ይኖራቸዋል ወይስ አይኖራቸውም? ይሄ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ነው። የካቢኔው አባላት የተማሩ ስለመሆናቸው፣ … ብዙ ከበሮ ተደልቆለታል፡፡ እኔ ይሄን የተረዳሁት በአንድ በኩል በባህላችን ውስጥ ለረዥም ጊዜ ዘልቆ የመጣው “የተማረ ይግደለኝ” የሚል ብሂል አለ፡፡ “የተማረ ሲገድል ውበት አለው” ማለት አይደለም። ቢያንስ የተማረ አይገድልም ለማለት ነው፡፡ ከገደለ እንኳ መነሻ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ሃኪም ከሆነ ወይ አቅም አንሶት እንጂ ሆን ብሎ አያደርገውም እንደ ማለት ነው፡፡
በአንድ በኩል፣ ይሄኛው የባህል ተፅዕኖ ይታየኛል - እዚህኛው የካቢኔ አወቃቀር ውስጥ። በእርግጥ፣ እውቀት አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን እውቀትና ምትሃት ይለያያሉ፡፡ የፒኤችዲ ባለቤት የሆኑ ሰዎች ስለተሰባሰቡ ብቻ፣ መንግስታዊ ችግርና ህዝብ የሚጠይቃቸው ነገሮች በአንድ ጀምበር ይሟላሉ ከተባለ … ይሄ ምትሃት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ምትሃታዊ በትረ ሙሴ የላቸውም፡፡ ስለዚህ ለእውቀት ክብር መስጠት ተገቢ ሆኖ እውቀትን ከምትሃት ጋር ማምታታት፣ ጥቅምን ሳይሆን ጉዳትን ያስከትላል፡፡ አንደኛ ነገር፣ የማናሟላውን ተስፋ የሚፈጥር ነው፡፡ ሁለተኛ እነዚህን ሰዎችም የሚያጎብጥ ነው፡፡
ሌላ መታየት ያለበት ነጥብ አለ፡፡ መንግስትነትና ህዝብን መምራት … በአንድ የአካዳሚክ ላብራቶሪና ላይብረሪ ውስጥ የሚካሄድ አይደለም፡፡ ላብራቶሪ ውስጥ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ትችላለህ፡፡ የአገር መንግስት ሆነህ መምራት ግን ይለያል፡፡ ህያዋን ዜጎች ቀን ተቀን በሚያደርጉት ጥያቄና እንቅስቃሴ የተቃኘ፤ በየደቂቃው የሰዎችን ህይወት ከሚነካኩ ውሳኔዎች ጋር መጋፈጥ፣ በዚህ ውስጥ ውሳኔዎችን የማሳለፍና የመተግበር ትልቅ ችሎታና ተሞክሮም የግድ ይላል። ስለዚህ የእውቀት ጠቀሜታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከእውቀታቸው ባሻገር እነዚህ ሰዎች በችሎታና በተሞክሮ የተፈተነ አከርካሪ አላቸው ወይ? የተሰጣቸውን ስልጣን የሚጠቀሙት የበላያቸውን ለማስደሰት ሳይሆን ፖሊሲ ለማስፈፀምና ከዚህ ፖሊሲ ተጠቃሚ የሆነውን ህብረተሰብ በትክክል ለማገልገል ነው ወይ? የማይሆን ውሳኔ እንኳ ሲተላለፍላቸው “አይ አይሆንም” ብለው የመወሰን አከርካሪ አላቸው ወይስ የላቸውም? ይሄ ነው ፈተናውን የሚለኩበት መስፈርታቸው፡፡ የተማሩ መሆናቸው ግን ጥሩ ነው፡፡
የግለሰቦች መለዋወጥ ወይም ሹም ሽረት ብቻ ሳይሆን የፖሊሲ ማሻሻያዎችም ማድረግ ይገባል፤ ህዝቡ የጠየቀው የፖሊሲና የስርአት ለውጥ ነው የሚሉ አስተያየቶች ጎልተው ይሰማሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
የፖሊሲ ለውጦች የሚባሉት በምን ዘርፎች ነው…?
ለምሳሌ በሚዲያ፣ በዲሞክራሲ፣ በነጻነት፣----.
አዎ! የዲሞክራሲው ምህዳር መስፋት አለበት። ምህዳሩ ሲሰፋ የሚሰፋባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ብዙሃኑ የሀገራችን ዜጎች የሚገኙት እታችና መሃል ላይ ነው፡፡ የእነሱ የእለት ተለት እንቅስቃሴ ያለው ደግሞ ቀበሌ በምንለው ደረጃ ተፅዕኖ የሚያርፍበት ነው፡፡ ስለሆነም በእያንዳንዷ ቀበሌና ወረዳ ያለው ዜጋችን፣ እስከ ዛሬ እንደተለመደው የፓርቲ አባል እየሰበሰቡና እየተጠራሩ የሚነጋገሩበትን ዘዴ መቀየር ይጠይቃል፡፡ ይሄ የፖሊሲ ለውጥ ይሁን የደንብ ለውጥ አላውቅም፡፡ ብቻ ይሄ አንዱ ነው። ለምሳሌ የወረዳና የቀበሌ ነዋሪዎች ም/ቤት (ካውንስል) ማቋቋም ይቻላል፡፡ የሚመራቸውን ሰው ማነህ ብለው እንዲሞግቱ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሁለተኛ በወረዳና በቀበሌ የሚመደቡ ሰዎች ዝም ብለው ተመድበው የሚቀመጡ ብቻ ሳይሆን “እነ እከሌን ልመድባቸው አስቤያለሁና እነዚህ ሰዎች ላይ አስተያየት ስጡ” ብሎ እንደ ፓርቲም በውስጥ መለካት፣ በህብረተሰቡም ማስመዘንም አለበት፡፡ ይሄ የነዋሪዎች ም/ቤት፣ የገዢው ፓርቲም የተቃዋሚም አባል ያልሆኑ ሰዎች የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡ የዚህ ጉባኤ ስራ ለወረዳው ነዋሪ ፍትሃዊ አገልግሎት ተሰጥቷል አልተሰጠም የሚለውን የሚከታተል ይሆናል፡፡ ሌላኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ነው፡፡ ሁለተኛው የውክልና ምርጫ ስርአታችን ነው፡፡ “ያሸነፈ ሁሉን ይወስዳል” የሚባለው ስርአት የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡፡ የበርካታ ሀገሮች ነው፡፡ ይሁንና እኛ ሀገር በግለሰቦች በጎ ፍቃድ የማይጠፋ፣ ተቋማዊ መሆን የሚችል ዲሞክራሲ መፍጠር አለብን የምንል ከሆነ፣ የብዙሃኑ ድምፅ ብቻ ሳይሆን ወሳኝነት ያላቸው አናሳዎች ድምፅ መወከል ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ፈረንጆቹ የተመጣጠነ የሚሉት የምርጫ ስርአት መታየት ያለበት ነው፡፡ እንደኔ የቀድሞውን ትተነው ወደ ሌላ እንሂድ የሚለው አይሰራም፡፡ ሁለቱንም ያዳቀለ፣ የኛን እውነታ የሚወክል የምርጫ ስርአት ሊኖረን ይገባል፡፡ በዚህ ዙሪያ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና በፖለቲካው ተሰሚነት ያላቸው ምሁራን ጥናቶችን አጥንተው በምክንያት የዳበረ ሃሳብ ቢያቀርቡ መልካም ነው፡፡ የተቃዋሚው ጎራ ይህ እንዲሆን ራሱን መስራት አለበት፡፡ ራሱን ማረቅ መቻል አለበት፡፡ አንደኛው መንገድ፣ እርስ በእርሱ በመታረቅ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ዲሞክራሲ መንታ ልብ ያላቸው ታጋዮች ውጤት አይደለም፡፡ ከእነስህተቱ ከእነጥፋቱ እታገላለሁ የሚሉ የቆራጦች ምርጫ ነው፡፡ ስለዚህ የአጠቃቀስኩ አካሄድን ሊያጤኑት የሚገባ ነው፡፡
ወደ ሚዲያዎች ስንመጣ፣ እንደ አንድ የሚዲያ ባለቤትም ሆኜ ሳየው፣ አሁን ያለው የቁጥጥር ስርአት የሚያሰራ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን አንዳንድ አመራሮች እንደ ባላባት፣ “ዛሬ ያንተ ሬዲዮ ላይ እንዲህ የሚል ነገር ስለቀረበ ይሄ አመፅ ያነሳሳል” በማለት የሚደረግ ከህግና ስርአት ውጪ የሆነ ነገር መቅረት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ አንድ መሻሻል ይመጣል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ሌላው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ክፍት አድርገህ ብትታገለው ይሻላል እንጂ ዘግተህ የምትታገለው የሚዲያ ዘመን አይደለም። ስለሆነም በማህበራዊ ሚዲያ አካባቢ ያለው አካሄድም መታየትና መጤን ያለበት ነው፡፡ እርግጥ ነው ማህበራዊ ሚዲያ የአጎልባችነቱን ያህል አፍራሽም ነው፡፡ አፍራሽነቱን ለመቀነስ ግን ድርግም አድርጎ መዝጋት ደግሞ ተመራጭ አይደለም፡፡
በሀገራችን የፖለቲካ ባህል መሪው ስልጣኑን በጥንካሬ ካላረጋገጠ ደካማ ነው የሚል አመለካከት ይፈጠራል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሄድ ይሄን ለማረጋገጥ ያለመ ነው ብለው የሚሞግቱ  ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
በአንድ ዲሞክራሲያዊ ለመሆን እየጣርኩ ነው በሚል መንግስት፣ ጠ/ሚኒስትሩ የሚለው ቃል ከጠቅላይነት ጋር መያያዙ በጣም ነው የሚጎረብጠኝ። ጠ/ሚኒስትር፤እንደ ስሙ ጠቅላይነትን አያመለክትም። እርግጥ ነው ትልቅ ስልጣን፣ ትልቅ ኃይል ያለበት ቦታ ነው። እዚያ ቦታ ላይ የሚቀመጡ ሰዎች እንደ አቅማቸውና ልካቸው በተለያየ መንገድ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡
በምንም ተአምር አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አንድ አይነት የስልጣን አጠቃቀም፣ ችሎታም አቅምም ፍላጎትም ሊኖራቸው አይችልም፡፡ የአሁኑን ጠ/ሚኒስትር በዚያ ጫማ ለክቶ ማየት የተሳሳተም የማይጠቅምም ነው፡፡ ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ስልጣኑ ተቋማዊ ነው፡፡ ምክንያቱም ከገደብ በላይ ጠቅልሎ የመያዝ አካሄድ ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው ያመዝናል፡፡ ሌላው ያለንበት የፌደራል ስርአት ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር የተባሉትን ያህል ጠቅላይ ግዛትን የሚጠቀልሉ ሊሆኑ አይችሉም፤ እንዲሆኑም አይመረጥም፡፡
የአሁኑ ጠ/ሚኒስትርና ፓርቲያቸው “የአቶ መለስን ራዕይ እናስቀጥላለን” ብለው ከመነሳታቸው አንፃርስ ---?
 ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ለዚህች ሀገር ያስቀመጠው የራሱ ራዕይ አለው፡፡ አንደኛው የኢትዮጵያን ህዳሴ በማፋጠን፣ ይህቺን ሀገር በተወሰነ አመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ተቋዳሽ  ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛ ዳቦውን ትልቅ አድርጎ መጋገር ብቻ ሳይሆን ዳቦው በፍትሃዊ መንገድ መከፋፈሉን ማረጋገጥ፤ ሁሉም እኩል ባለቤት የሆነባትን ሀገር እውን ማድረግ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ማንም እንደሚያውቀው ጠ/ሚ መለስ ጥሩ አንባቢ፣ ጥሩ ፀሐፊ ነበሩ፡፡ ሶስት ነገሮች በዓለም ላይ ተገጣጥሞላቸው የሚኖሩ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የመፃፍ የማንበብ፣ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ተንትኖ የማስቀመጥ ትልቅ ችሎታ ነበራቸው፡፡ ይሄ ዛሬ የኢህአዴግ ንብረት ሆኖ አለመቀጠሉ ላይ ክፍተት አለ … ያሳዝናል፡፡
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሳቸው ጋር ምክትል ሆነው የሰሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ በሳቸው ራዕይ እንቁላል ውስጥ ነበሩ ሲባል፣ ሌላ እንቁላል በወቅቱ ለመፈልፈል የሚያስፈልግበት ነበር ማለት ነው፡፡ አቶ ኃይለማርያምም ሆኑ ሌላ የሚተካቸው ሰው መለስን መድገም የለበትም። መለስን ደግሞ ደጋግሞ ማነብነብ የለበትም። ጠ/ሚ መለስ እንደ ኢህአዴግና እንደዚህች ሀገር መሪ የነደፏቸው አዋጪ ፖሊሲዎች፣ እሳቸው ስለሌሉ ዝም ብሎ የሚጣል ሳይሆን እየተመረጠ ከሁኔታው ጋር እያስተካከሉ የሚሄዱበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ለምሳሌ ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር የሚለው ፖሊሲ የተዛባ ነገር ይታይበታል፡፡ ይሄን የምለው የአቶ መለስ ስለነበረ አይደለም፡፡ አሁን ለምሳሌ ጥናቶች እርሻ በቀጣዩ ዘመን ትልቁ የሀብትና የስራ ምንጭ እንደሚሆን ያስቀምጣሉ፡። ስለዚህ ሀገራት ዝም ብለው ጥለውት ወደ ኢንዱስትሪ የሚሄዱበት እየሆነ አይደለም፡፡ ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ጋር የተያያዙ መሆን አለባቸው፡፡ የዜጎቻችን ባለቤትነት ያለባቸው፣ የማምረቱን የእውቀት ሽግግር የሚያመጡበትና የዳቦ ክፍልፋዩ ከትንሽ ወደ ትልቅ የሚያድግበት መሆን አለበት። ሰፊ የኢንዱስትሪ አቅም ካላቸው እንደነ ቻይና ካሉት ጋር መኪና በማምረት መወዳደር ወይንስ ባለን የግብርና አቅም መወዳደር? ከዚህ ጋር ያሉ ችግሮችን ማየት ያሻል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የራሳቸው ሰብዕና እና አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው፡፡ እንደ አንድ የኢህአዴግ መሪ ደግሞ ደስ ሲላቸውም ሳይላቸውም በኢህአዴግ ክፈፍ ውስጥ ነው መንቀሳቀስ ያለባቸው፡፡ ደስ ያላቸውን ማስቀየር የሚችሉት ኢህአዴግን በመቀየር ነው እንጂ እሳቸው ስለተቀየሩ ኢህአዴግ አይቀየርም፡፡
የኢህአዴግ ድርጅቶች የተሃድሶ ግምገማ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ኢህአዴግ በ1993 ባደረገው ተሃድሶ ላይ የባለስልጣናት ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ለውጦችም ታይተው ነበር … አሁንስ ይሄ ነገር አለ ብለው ያምናሉ?
የ1993ቱ ግምገማ የኢህአዴግ አዲስ ውልደት አይቀሬ ሂደት ነው፡፡ በአንድ አላማ ተሳስረው ሞትን መጋፈጥ ጓዳዊ ቅርበት ፈጥሮላቸው፣ በድንገት የአንዲት 100 ሚ. ህዝብ ያላት ሀገር መሪ ሆኑ፡፡ ስለሆነም በበረሃ ትግል ውስጥ የቀመሯቸውን መፅሀፎች መከለስና ለዚህ ዘመንና ለዚህ ህዝብ የሚመጥን ነገር ማቀድ ነበረባቸው። በወቅቱ ፍልስፍናዊ ምርጫዎች ነበሩ የተገመገሙት። አንጃ ተብሎ የወጣው ክፍል በወቅቱ ዋነኛ ልዩነት ብሎ ያቀረበው ተንበርካኪነትን ነው፡፡ አቶ መለስና በሳቸው ዙሪያ የተሰባሰበው የኢህአዴግ ክፍል ለሻዕቢያ ተንበርካኪ ነበር፤ የሚል ነው ክርክሩ፡፡ ያኔ ደርግ እነ ኢህአፓን፣ ኢህዴንን፣ ህውሓትን “የእናት ጡት ነካሽ፤ የፔትሮ ዶላር ቅጥረኛ” ይላቸው ነበር፡፡
በየትኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ልዩነትን ውስጣዊ የማያደርግ ፍልስፍናዊ ቅኝት አደገኛ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ መቆረጥና መበጠስ ነው ያለበት፡፡ ከዚህ ተነስቼ ሳየው የአስተሳሰብ ግምገማ ተካሄደብን ሳይሆን እንደ ፍልስፍና ተይዞ የነበረውን አማራጭ የውጪ አድርጎ፣ ውጫዊ በሆነ መልኩ ሲያስቀምጥ አደገኛ ነው፡፡ ጀነራል አበበ አዲስ አድማስ ላይ የፃፉትን አንብቤያለሁ፤ እሳቸው የአሁኑን ነው “ደርጋዊ” የሚሉት፡፡ እኔ ደግሞ እነሱን ነው “ደርጋዊ” የምላቸው፡፡ ምናልባት ለቀባሪው አረዱት ሊሉኝ ይችላሉ ግን ማብራሪያ እስካልሰጡኝ ድረስ በዚህ ነው የምረዳው። በስብሰናል ሲባል ወደ ውስጥ መመልከት ማለት ነው። ይህ ሲባል ደግሞ የውጪ ጠላት የሚሉት ዝባዝንኬ ውስጥ አይገባም፡፡ የዚያን ጊዜው እንደዚህ ነው፡፡ የአሁኑ ላይ አስተሳሰባዊ ግምገማ አልተካሄደም፡፡
እንደ እኔ ከመንግስት ኃላፊነት የተቀነሱት ሰዎች፣ የማውቃቸውም የማላውቃቸውም---- ለምን እንደተቀነሱ አልተገለፀም፡፡ ስለዚህ የተቀነሱበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ እውቀት ከተባለ ብዙዎቹ የሚፈለገው ዲግሪ ያላቸው፣ በተሻለ መንገድ የፓርቲውን አስተሳሰብ መግለፅ የሚችሉ፣ እንደውም በፓርቲው ፖሊሲ ሳይሸበቡ ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር አጣጥመው በመርህ የሚሞግቱ ሰዎች ነበሩ፡፡ እርግጥ ነው ስልጣን ርስተ ጉልት አይደለም፡፡ ሌሎችም እውቀቶች መፈተሽ አለባቸው ግን በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ በጥቅል ከማስቀመጥ ይልቅ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የተነሱት በእንዲህ በእንዲህ ምክንያት ነው አላሉንም፡፡ አቶ ሬድዋን ሁሴንና አቶ ጌታቸው ረዳ ሁሌም በራቸውን ክፍት አድርገው የሚሰሩ ኃላፊዎች ነበሩ፡፡
በኦሮሚያና በአማራ ክልል ለተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች፣ መንግስት እየሰጠ ያለው ምላሽ የሚጣጣም ነው ብለው ያስባሉ?
እንደ ተመልካቹ ነው፡፡ የመሬት ጥያቄውና የድንበር ጥያቄው የስርአት ችግራችን ውጤትም ነው፡፡ ፌደራላዊ ሪፐብሊኩ የተቋቋመው በመንደራቸው እንደታጠሩ መቅረትን በመረጡ ዜጎች አይደለም፡፡ ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድር የሚለው መርህ፣ የዲሞክራሲ ማዕከል የሆነ መርህ ነው፡፡ ይሄ መርህ ዛሬ ላይ ከምናየው፣ “የእኔን መሬት ማንም ሰው አይጠቀመው” የሚል መሬት ተከል ታጣሪነት ጋር በጭራሽ አይገናኝም፡፡ ባለፈው 25 ዓመት ከታሪካችን የመነጨውን፣ አለ ተብሎ የሚታመን መድሎና አለመመጣጠኖች ለማጣጣት ሲባል፣ የተደለቀው የብሄር ከበሮ ትንሽ ከሚገባው በላይ አጋነን ደልቀነዋል። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “የኢትዮጵያ ታሪክ” የሚባል የትምህርት ክፍል የለውም፡፡ ቀድሞ የነበረው “የኢትዮጵያ ታሪክ” የሚባል ትምህርት የተሳሳተ ነው ብሎ መቀየር አንድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን “ኢትዮጵያ ታሪክ የላትም” በሚመስል አይነት የሞኝ ድምዳሜ ይዞ፣ ኢትዮጵያን ተረክቦ ኦሮሞ ከትግሬና ከአማራ ወይም ከሌላ ብሄር የሚያስተሳስረውን የማያይበትን ሁኔታ ፈጥሮ መጓዝ፣ ለማንም ፅንፈኛ የተጋለጠ አድርጎ ማስቀመጥ ነው የሚሆነው፡፡ ታጣሪነትን ያበረታታ አካሄዳችን መታረም አለበት፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይም በዚሁ አግባብ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ የኦሮሚያም እንደዚሁ ነው፡፡ ጉድፉም መልካም ጎኑም የኛ የሁላችንም ነው፡፡
ከኢህአዴግ ተሃድሶ ህዝቡ በሚጠብቀው ልክ ውጤት እያገኘ ነው ብለው ያምናሉ?
መንገዱ ላይ ነው፡፡ ይሄ መንገድ ፍፁማዊ ነው ወይ ከተባለ ሌላ ነገር ነው፡፡ ጥንቆላ እዚህ ጋ አይሰራም፡፡ ግን መንግስት እነዚህን ጥያቄዎች ሊመልስ በሚችል አካሄድ ውስጥ ከመግባት ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ለይቶ የያዛቸው ጥያቄዎች እንዳሉ ሆኖ፣ በስፋትም በይዘትም ይመጥናሉ ወይ? የትኩረት ነጥባችን ልክ ነው ወይ? ለምሳሌ ሚኒስትር መቀየር ነው ወይ መፍትሄው? ወይስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ ያለው አሰራር የተቀላጠፈ ነው ወይንስ የተሳሰረ ነው? የሚለው ነው መፈተሽ ያለበት የሚለው መነሳት አለበት፡፡ እንግዲህ ጉዳዩ ሂደት ነው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ የሚመጥን መልስ የመስጠትን ግንዛቤ የሚያሳይ ተናባቢነት እያሳየ ነው ወይ? ከተባለ፣ በኔ እምነት አይመስለኝም፤ ተናባቢነቱ ይጎድለዋል፡፡ ተናባቢነቱን የማምጣት እድል አለው ወይ? ከተባለ፣ አዎ አለው፡፡ በነገራችን ላይ ሰዎች ብዙ እንዲጠብቁ አድርጎ ካልተሰራ አደጋ አለው፡፡ ሌላው ህብረተሰቡን ያበሳጩ ዘራፊ ሌቦችን በሰበካ አይደለም ማስወገድ የሚቻለው። አሰራሮችን በመድፈር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ትኩረቱ መስፋት አለበት፡፡ እስካሁን ባለው አካሄድ የመናበብ ችግር ይታያል ግን ትዕግስት አድርጎ ማየት ያስፈልጋል፡፡
መንግስት ለውይይት በሩን ክፍት ማድረግ እንዳለበት ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ በእርስዎ እምነት መንግስት ከማን ጋር መወያየት ያለበት?
መንግስት ከሁሉም ጋር በግልፅ መወያየት አለበት። ለምሳሌ እንደነ ኢዴፓ ያሉ ፓርቲዎች፣--- (ሰማያዊ ፓርቲም የአንድ ወቅት ስካሩን ትቶ ወደ መሬት መውረድ እየጀመረ ይመስላል) እነ ዶ/ር መረራም አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ከመወያየት ይልቅ ዋሽንግተን ከቀረባቸው ምርጫቸው ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ንግግር ግን ከነሱ ጋር ብቻ አይደለም፡፡ ከዜጎች ጋር ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ከዜጎች ጋር ሲነጋገር ደግሞ በፓርቲ መስመሮች ተሸብቦ ያለውን ወይም ካድሬውን ሳይሆን ነፃውን ሰው ያነጋግር። ተበድያለሁ የሚሉ ዜጎች አሉ፤ እነሱን ያነጋግር፡፡ ከዚያ ነው ወደ ፓርቲዎች መሄድ ያለበት፡፡
ተቃዋሚዎች ለምን ወደ የጋራ ም/ቤት አልገቡም? ይሄም መጠየቅ አለበት፡፡ አሁን ጨዋታው የፖለቲካ ነጥብ የሚቆጠርበት አይደለም፡፡ መለወጥ ያለባቸው እነሱም ጭምር ናቸው፡፡ ዶ/ር መረራና ፕ/ር በየነ ስንት ዓመት ነው ፓርቲ የመሩት? ለምን በወጣቶች ተቀይረው አዲስ ፊት አናይም? በዚህ ረገድ ኢህአዴግ ብቻ ለምን ይጠየቃል? ለውጡን ከኢህአዴግ የምንጠብቀውን ያህል ከነሱም እንጠብቃለን፡፡









Read 6856 times