Sunday, 27 November 2016 00:00

ስለ እብጠት!

Written by  ሌ.ግ
Rate this item
(5 votes)

ምድር ጠፍጣፋ ናት እያሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ምዕመናኑን ያስጨንቋቸው ነበር አሉ፡፡ ምክኒያታቸው ምንድነው እያልኩ እገረም ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን እየገባኝ መጥቷል፡፡ ጠፍጣፋ ነገር ለሀጢአት አይመችም። ጠፍጣፋ ነገር አይን ውስጥ አይገባም። ጠፍጣፋ ነገር አይንከባለልም፣ ጠፍጣፋ ነገር አይወጋም፡፡ ጠፍጣፋ ከሌላው ነገር ተለይቶ አይጎላም፡፡
*   *   *
ሚልተን፤ የሰውን ልጅ ውድቀቶች በሰባት የሀጢአት አይነቶች ስር ይከፍላቸዋል፡፡ ጉራ (pride) አንዱ ነው፡፡ የሰይጣን አለቃው ሉሲፈር ከሰባተኛው ሰማይ የወደቀው … ትዕዛዝ አልቀበልም በማለቱ ነው፡፡ በመታበዩ ነው። በእኔነኛዊነቱ ነው። እኔ እበልጣለሁ በማለቱ ነው፡፡ “እኔ እበልጣለሁ” ማለት ማበጥ ነው። ከጠፍጣፋው ጎላ ብዬ እታያለሁ ማለቱ ነው። “ምድር ክብ ናት” ማለትም ከሌላው አብጣ ትታያለች ማለት ነው - ለኔ፡፡
*   *   *
ይህ ሁሉ ሀሳብ የመጣልኝ አንዲት ሴትን ስመለከት ነው፡፡ ከሌሎች ሴቶች ጎላ ብላ የታየችኝ በማበጧ ምክኒያት ነው፡፡ ያበጠው የሰውነቷ ክፍል ደግሞ አተያየቴን ፈር ያስይዘዋል፡፡ በመቀመጫዋ ፋንታ ግንባሯ ቢያብጥ ኖሮ ፍላጎት ሳይሆን ድንጋጤና “ምን ሆና ይሆን?” የሚል ርህራሄ ነበር እይታዬን የሚቃኘው፡፡ መቃኘት አንድ ነገር ነው። ከቅኝቱ በፊት ግን የእይታ ስበትን መፍጠሩ ይቀድማል። የትኛውንም የእይታ ስበት የሚጎትተው ደግሞ ጠፍጣፋ ነገር ሳይሆን እብጠት ነው፡፡
የልጅቷ መቀመጫ አብጧል፡፡ ከኋላ በኩል፤ ከፊት በኩልም ደረቷ ላይ አብጣለች፡፡ “ያየ አመነዘረ” ይላል ስብከቱ፡፡ አይን እብጠትን የሚለካ መሳሪያ ነው፡፡ ምናልባት የአይንን አፈጣጠር ቢያውቅ ኖሮ ደጉ መምህርም እብጠትን ከመመልከት ጋር ሀጢአትን ባላያያዘው ነበር፡፡
*   *   *
በሚልተን የሀጢአት መዝገበ ቃላት ላይ ከሰፈሩት ዝርዝሮች መሀል “ቅናት” አንዱ ነው፡፡ ቅናት ሀጢአት ነው፡፡ ለመቅናት፤ የሚቀናበት ነገርና የመቅናት አቅም ያለው ፍጡር በአንድ ስፍራ ላይ መገናኘት አለባቸው፡፡ የሚያስቀናው ነገር ምንም ጥርጣሬ የለኝም፣ የእብጠት አይነት ነው፡፡ ጎላ ብሎ በማይታይ ነገር ማንም አይቀናም፡፡ “እንቁላል የመሰለ መኪና” የሚለው አገላለፅ ስለ መኪናውና መኪናው እንቁላል መምሰሉን ከመግለፅ በላይ “ጉብ” ያለ ነገር መኖሩን ያመለክታል፡፡
መኪናው፤ በአስፋልቱ ላይ ቆሞ ክብና አንፀባራቂ ሆኖ ይታያል፡፡ ያላበጠ ነገር ክብም አንፀባራቂም አይሆንም፡፡ የተነፈሰ፣ የተሸበሸበ፣ የተጨማደደ ነው የሚሆነው፡፡ አልያም ደግሞ ጠፍጣፋ፡፡ እነዚህ ሁሉ ከመወጠር ጋር ተቃራኒ የሆኑ የሁነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ የተወጠረ ወይንም ያበጠ ነገር አይሸበሸብም፣ አይኮማተርም … አይጨማተርም። ስለዚህ “ቅናት” የሚኖረው የተወጠረ፣ ያበጠ፣ የተወጠረ ነገር ሲኖር ነው። የተወጠረ ነገርን ከተሸበሸበው ጋር አነፃፅሮ ያበጠውን የሚመርጥ፣ የመረጠውን የራሱ ለማድረግ የሚጓጓ ከሌለ … “ቅናት” የሚባለው ነገር አይኖርም፡፡ እነዚህን የሚልተንን የሀጢአት ዝርዝሮች ተራ በተራ በዚህ አመለካከቴ አንፃር ለመመርመር ቆረጥኩኝ፡፡ አይኔን ግን አሁንም የልጅቱ ያበጠ ዳሌ ላይ እንደተተከለ ነው፡፡ አይኔን ከተከልኩበት ሳልነቅል - ጥርሴን ነክሼ ማሰላሰሌን ቀጠልኩኝ፡፡
*   *   *
ሶስተኛው የሚልተን የሀጢአት አይነት አልጠግብ ባይነት ነው፡፡ በእንግሊዝኛ (Greed) ይሉታል፡፡ አልጠግብ ባይነት ያበጡ ነገሮችን የማግበስበስ የማይረካ ፍላጎት ነው፡፡ አልጠግብ ባይነቱ ወደ አፍ ወደ ሆድ በሚገባ እህል መልክም ሊገለፅ ይችላል፡፡ glutton ይባላል፡፡ ያበጠ ነገርን በአፍም ይሁን በንብረት መልክ ቅርጥፍ አድርጎ በልቶ ወይንም አግበስብሶ በአካልም ይሁን በስልጣን አብጦ የመታየትም ፍላጎት ነው፡፡ ብቻ ዋናው ነገር ከጠፍጣፋነት ጋር ተቃራኒ ነው፡፡
*   *   *
ከዚህ ቀጥሎ የመጣብኝ ኃጢአት አሁን አይኔ ከተተከለበት እብጠት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። በአማርኛ “አመንዝራነት” ተብሎ ይጠራል። “Lechery” ይባላል በፈረንጅኛው፡፡ ይሄም ቢሆን ያበጠ ነገር ፍላጎት ነው፡፡ ያበጠ ዳሌን ተከትሎ የሴቷ ጉድጓድ ውስጥ የመግባት ፍላጎት ነው። ከመሟሸሽ ጋር ተቃራኒ ስሜት ነው፡፡ ያበጠ ዳሌ፤ የወንዱን ብልትም እንዲያብጥ ያደርገዋል። የሴቷ ብልትም ቢሆን ወደ ውስጥ እብጠት ነው። ማህፀን ወደ ውስጥ ያበጠ ክፍት ስፍራ ነው፡፡ ዋናው ነገር ጠፍጣፋ ከመሆን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ የካቶሊክ ቀሳውስቱ ምድር ጠፍጣፋ ናት አሉ፡፡ ምድርን ጠፍጣፋ አድርገው የሰውንም ፍላጎቶች ለማሸማቀቅ ፈልገው ነበር። የሰው ፍላጎት ግን የማበጥ ነው፡፡ ያላበጠ ነገር አይታይም፡፡ አይጨበጥም፡፡ አያጓጓም፡፡ የወሲብ ፍላጎት የሚቀሰቀሰው በእብጠት ነው፡፡ የእኔም አይን እብጠት ላይ ተተክሏል፡፡ እብጠቱን በደንብ ለመወጠር ጥሩ የቻይና ሱሪ አድርጋለች፡፡ ከሱሪው በታች ሌላ ቅርፅ የሚያሳይ ቀበቶ መሳይ የውስጥ ሱሪ ከውስጥ እብጠቱን ወጥሮታል፡፡
ከሴቷ ጎን የሚሄድ ወንድ አለ፡፡ ባሏ መሆኑ በሁሉ ነገሩ ያስታውቃል፡፡ ግን ባልየው የተላገ ሞራሌ ነው የሚመስለው፡፡ አግድም ሳይሆን በቁመቱ የሚራመድ ጠፍጣፋ ነው፡፡ ልክ በጠርዙ እንደቆመ ሳንቲም፡፡ … በዚህ ምክኒያት ሀይማኖተኛ ቅርፅ ለራሱ ፈጥሯል፡፡ ከኋላ በማየት ቦርጭ እንኳን እንደሌለው ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ጠፍጣፋ ነው፡፡ ግን ማንም አያየውም። ወይ ትከሻው ወይ ቦርጩ ወይ አንድ ተፈጥሮው አብጦ ካልጎላ አይን ውስጥ አይገባም። በጎኑ በዝግታ እየተራመደች ያለችው ሚስቱ ግን የሰውን አይን እንደ ማግኔት እየሰበሰበችው ነው፡፡ ግልፅ ነው የእብጠቱ ስፍራ ቢለያይም፣ ይህም አንዱ የሚልተን ሀጢአት ነው፡፡
*   *   *
ሰባቱ ሀጢአቶች በሙሉ ተራ መሆንን እንደ ፅድቅ የሚያዩ … እብጠትን የሚኮንኑ ናቸው። ሌላው ሀጢአት ተብሎ በሚልተን መዝገብ የሰፈረው “ንዴት” (warth) ነው፡፡ የተናደደ ሰው በፊቱ ገፅታ የሚያውቁ አሉ፤ ፊቱ ባይነፋፋም። በቦክስ ተነርቶ ካልሆነ በቀር ፊት በንዴት አያብጥም፡፡ እኔ ግን የማውቀው የተበሳጨውን ወይንም የተናደደውን ሰው ቅርፅ ተመልክቼ ነው። የተናደደ ሰው፣ ከተቆጣ ድመት ወይንም ዶሮ ምንም የተለየ አይደለም፡፡
ድመት ሲቆጣና ለጥል ዝግጁ ሲሆን አካሉን በተቻለው መጠን አሳብጦ፣ ፀጉሩን አቁሞ፣ ትልቅ መስሎ ለመታየት ይሞክራል፡፡ የዶሮም ተመሳሳይ ነው፡፡ አንገቱ ላይ ያለው ፀጉሩ ሁሉ ይቆማል፡፡ “ፀጉሩ ተቆጣ … ተነፋፋ” ማለት አንድ ይሆናሉ፡፡ ጎላ ብሎ ያታያል - የተቆጣ ሰው፡፡ አይሸማቀቅም። አይጨበጥም፡፡ ልክ እርሾ እንደገባበት ዱቄት “ኩፍ” ይላል፡፡ ስለዚህ ቁጣም ሀጢአት ነው። ጠፍጣፋ አይደለም - የተናደደ፡፡ የተሸነፈ ግን “ፀጥ ለጥ” ይላል። ፀጥና ለጥ ማለት ከጠፍጣፋነት ጋር አንድ ነው፡፡ ምድር ክብ ናት ያሉ ሳይንቲስቶች፣ በሀይማኖታዊ እይታ ሀጢአተኞች ናቸው። በዚህ ሀሊዮት አንፃር እስካልተመለከትኩት ለሀጢአታቸው ምክኒያቱ ግልፅ ሊሆንልኝ አይችልም ነበር፡፡
*   *   *
ሁሉም ሀጢአቶችን የሚያያይዘው እብጠት መሆኑ ብቻ ሳይሆን በአንዱ ሀጢአት መንስኤ የመጣው እብጠት ከሌላው ጋር ነገር እንዳለም በዛው ቅፅበት ግልፅ ሆነልኝ፡፡ ይሄ ግልፅ የሆነልኝ በሴቲቱ ላይ የተከልኩት አይኔ ቆርቁሮት፣ ጠፍጣፋው ባል በድንገት ዞሮ ሲገላምጠኝ ነው። … አዲስ ሀሳብ ይሄኔ ብልጭ አለልኝ፡፡ ለምሳሌ፤ “ንዴት” አንዱ የእብጠት አይነት ነው፡፡ የተናደደ ሰው ያብጣል፡፡ ለምን ተናደደ? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡
ምናልባት በዚህች ቅፅበት ባልየው ዞሮ የእኔ አይን ሚስቱ እብጠት ላይ መተከሉን ካስተዋለ፣ ሁለት ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡ አመሉ ጠፍጣፋ ከሆነ ዝም ብሎ እንዳላየ ያልፋል፡፡ ከተናደደ ግን ይገላምጠኛል፡፡ ለመገላመጤ መንስኤው የሚስቱ እብጠት ነው፡፡ ወይንም እብጠት ላይ ተተክሎ ማበጥ የጀመረው “የፍትወት ስሜቴ”፡፡ ባልየው ድንገት ዞሮ ሲያተኩርብኝ እኔም መልሼ ከገላመጥኩት ሁለት ንዴቶች ይጋጫሉ፡፡ ግጭቱ ብልጭታ ፈጥሮ ቡጢ ካማዘዘን … እንጣላለን፡፡
ባልየው በ“ንዴት” ምክኒያት ወይንም በ“ኩራቱ” ምክኒያት … “እንዴት እኔ እያለሁኝ ሚስቴ ትደፈራለች” በሚል ሁለቱን የሚልተን ሀጢአቶች ያጣምራል፡፡ በሞት ምክኒያት የሚከሰት እብጠት “አሉታዊ እብጠት” ሊባል ይችላል። ከሀጢአት በኋላ የሚታጨድ ፍሬ እንደማለት። ያው በእብጠት መንስኤ የሚመጣ ውጤት እብጠት ነው፡፡ በሚስትየዋ ዳሌ እብጠት ምክኒያት የእኔ ግንባር ተቦቅሶ አበጠ እንደማለት ይቆጠር። ደግነቱ ባልየው እንደ አካሉ አመሉም ጠፍጣፋ ነው፡፡ በንዴት ሳያብጥ ቀረ። እኔም በሚስቱ መቀመጫ አማካኝነት የተለያዩ አይነት እብጠቶችን እየመዘንኩ እያነፃፀርኩኝ ዋልኩኝ።  … አሁን አሁን “The world is flat” የሚል አዝማሚያን በግሎባላይዜሽን ስም ለማፋፋም የመጡ የዘመቻ ፅንሰ ሀሳቦች በዓለም ላይ ተንሰራፍተዋል፡፡ ግን እንደ ካቶሊኩ ቤተ ክርስቲያን የቀድሞ መንፈሳዊ ሐሊዮት አይደሉም።
የዘንድሮዎቹ ፈፅሞ እንዲህ አይነት አይደለም አላማቸው፡፡ የዘንድሮዎቹ አላማ የንግድ ነው፡፡ ንግዳቸውን በአለም ላይ ያለምንም ከልካይ  ከአፅናፍ አፅናፍ ለማፋፋም ሲሉ የዘየዱት ርዕዮተ-ዓለም ነው፡፡ በተራራ እብጠት ምክኒያት የንግድ ቅኝ ግዛት ዘመቻቸው እንዳይገታ ሲሉ ነው “አለም ጠፍጣፋ ናት” ያሉት፡፡ ግን ይሄንን ያሉት ጠፍጣፋ መሆኗን ፈፅመው ሳያምኑበት ነው፡፡ ሌላውን አለም ጠፍጣፋ አድርገው እነሱ ያለምንም ተገዳዳሪ ማበጥ ይችሉ ዘንድ፣---- አለምን እንደ አንድ መንደር “ዝርግ ሰሀን አድርገናታል” ብለው ህዝበ አዳሜን አሞኙት፡፡
*   *   *
የካቶሊኮቹ ፍላጎት አንድ ፊቱን የተሻለ ነበር ጃል!
የአሁኖቹ የብልጠት ነው፡፡ በመሰረቱ አለም ጠፍጣፋ ሆና አታውቅም፡፡ “አለም የፅድቅ መናኸሪያ ትሆን ዘንድ መጠፍጠፍ አለባት” ብለው የሚሰብኩት አጭበርባሪ ናቸው፡፡ አለም እንደዚህች ሴት ዳሌና ዳሌዋ ላይ ተተክሎ አልነቀል እንዳለው የአይኔ አስኳል … ክብ ናት፡፡ ክብነት ሀጢአት ከሆነ ሁላችንም በምድር ላይ ተኮንነናል፡፡ የኮነነችን ደግሞ ተፈጥሮ ናት፡፡ ምክኒያቱም፤ ተፈጥሮ ጠፍጣፋ የስነ ልቦናም ሆነ የቅርፅ ማንነት የላትም፡፡ ሁላችንም በእብጠት የተገኘን፣ ለማበጥ ወይንም ለማሳበጥ ስንል በህልውና ላይ የምንመላለስ ነን!
*   *   *
የተከልኩት አይኔ ከልጅቱ ዳሌ ተነቅሎ ሌላ አዎንታዊ እብጠት ላይ አረፈ፡፡ በሆዷ ሽል የያዘች ሴት በቅድሟ ፋንታ ፊቴ ተደቀነች፡፡ … ሁሉም እብጠት ሀጢአት ከሆነ እርግዝና ሀጢአት መሆን ነበረበት፡፡ ምክኒያቱም እርግዝና የሚመጣው ከምን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ግን ወዲያው ትዝ አለኝ - አንድ የካቶሊክ ቄስ ፅፎ ያነበብኩት መፅሐፍ፡፡
መፅሐፉ “ጋብቻ ማለት በእግዚአብሄር ባለሟል (ቄስ) ፊት የሚከናወን ሀጢአትን የማድረጊያ ፈቃድ ማለት ነው” ይላል፡፡ በቄስ ፊት የተጋቡ ሰዎች ብቻ “The carnal act” (Lust)  የመፈፀም ፈቃድ አላቸው፡፡ በተፈቀደላቸው ትኬት ተጠቅመው የሚያከናውት ወሲብ ውጤቱ “አዎንታዊ እብጠት” ይሆናል ማለቱ ነው፡፡ “አሉታዊ እብጠት”ን በግጭት ወይንም ከአባጓሮ የተገኘ ጓጓላ መሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡ በተቃራኒው “አዎንታዊ እብጠት” ደግሞ እርግዝና ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡
በመሰረቱ በሀይማኖታዊ ወይንም ፅንሰ ሀሳባዊ መነፅር ካየነው ብቻ እንጂ በተፈጥሮ አተረጓጎም አብዛኛው እብጠት መንስኤና ውጤቱ በህልውና የመቆየትን አቅም ለመደጎም ወይንም ለማበረታታት ነው፡፡ ኃጢአት የለውም፡፡ ለተፈጥሮ ሀጢአት የሆነው ለሀይማኖት ወይንም በሃሳባዊነት (አይዲያሊዝም) ፅንሰ ሀሳባዊ ዕይታ ፅድቅ መሆኑ ላይ ይሰመርበት፡፡
በሰው ፅንሰ ሀሳብ ሲመዘን እንጂ … ተፈጥሮማ እብጠትን ትደግፋለች፡፡ ያላበጠ ነገር አይጎላም፣ አይታይም፣ ህልውናውንም አይገልፅም። … እንዲህ እና እንዲያ እያልኩ በእብጠት ላይ ያደረግሁትን እለታዊ ማሰላሰል ለጊዜው ቋጨሁት፡፡   






Read 5421 times