Sunday, 27 November 2016 00:00

ኦባማ ለ21 አሜሪካውያን የነጻነት ሜዳይ ሽልማትን አበረከቱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው የመጨረሻቸው የሆነውን ታላቁን የፕሬዚዳንቱ የነጻነት ሜዳይ ሽልማት ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በዋይት ሃውስ በተካሄደ ስነስርዓት ለ21 ታዋቂ አሜሪካውያን አበርክተዋል፡፡
ኦባማ የእኔ ጀግና ያሏቸውና ታላቁን የነጻነት ሜዳይ ያጠለቁላቸው 21 አሜሪካውያን በተለያዩ መስኮች ለአገራቸውና ለህዝባቸው የጎላ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆኑ  የፊልምና የመዝናኛ ዘርፍ ዝነኞች፣ ሳይንቲስቶች፣ ስፖርተኞች፣ በጎ አድራጊዎችና በሌሎች መስኮች የተሰማሩ መሸለማቸው ታውቋል፡፡  
“ሁሉም የዕለቱ ተሸላሚዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በግሌ ተጽዕኖ የፈጠሩብኝ ናቸው” ሲሉ ተሸላሚዎችን አድንቀዋል፤ ኦባማ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፡፡
ኦባማ የአሜሪካን ትልቁ የሲቪል ሽልማት  በክብር ካበረከቱላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ታዋቂ አሜሪካውያን መካከል፣ ከመዝናኛው ኢንዱስትሪ የፊልም ከዋክብቱ ቶም ሃንክስና ሮበርት ዲ ኔሮ፣ ከበጎ ምግባር ስራዎች ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ፣ ከስፖርት ካሬም አብዱል ጀባርና ማይክል ጆርዳን ይገኙበታል፡፡ ከዘንድሮ ተሸላሚዎች በእድሜ ትንሹ የ53 አመቱ የቀድሞው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርዳን ሲሆን፣ በዕድሜ ትልቁ  ተሸላሚ ደግሞ የ91 አመት የእድሜ ባለጸጋዋ ተዋናይት ሲስሊ ታይሰን ናቸው፡፡

Read 802 times