Sunday, 27 November 2016 00:00

“ድሪዝም”

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(2 votes)

ገጠመኞች ናቸው...
የተከሰቱበት ዘመንና ስፍራ እየቅል ቢሆንም፣ የሚያመሳስሏቸው ሁለት ነጥቦች አሉ።
አንድም፣ “ድራማ ቀመስ” ናቸው። ሁለትም፣ ቱሪዝም ተኮር ናቸው።
ድራማዊ ባህሪ ለተላበሱት ለእነዚህ የቱሪዝም ገጠመኞቼ የሰጠሁት የጋራ ስያሜ ነው -
“ድሪዝም”።
እነኋችሁ!...

ታሪክ እንደገና ይጀምራል እንጂ፣ ከቆመበት አይቀጥልም!...
ከአስር አመታት በፊት...
ወደ ጎንደር አቅንቼ የፋሲል ግንብን ለመጎብኘት ታደልሁ።
አንድ አስር የምንሆን ጎብኝዎች ሰብሰብ ብለን፣ የተመደቡልንን አስጎብኚ ተከትለን ወደ ፋሲል ግንቦች አመራን። አስጎብኛችን ወፈር አጠር ያሉ አዛውንት ናቸው። ጉሮሯቸውን አጸዳዱና ስራቸውን ጀመሩ።
“እንግዶቻችን ወደ ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ እንኳን በደህና መጣችሁ!... እንግዲህ፣ ‘የአጼ ፋሲል ግቢ’ ተብሎ በሚታወቀው በዚህ ሰፊ ቅጽር ውስጥ፣ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ነገስታት ያስገነቧቸው አብያተ መንግስታት ይገኛሉ። መቀመጫቸውን በጎንደር ከተማ ላይ አንድርገው የነገሱ ነገስታት የሚከተሉት ናቸው።
1ኛ. አፄ ፋሲል (ዓለም ሰገድ) ከ1623 - 1659
2ኛ. ዮሀንስ 1ኛ (አእላፍ ሰገድ) ከ1659 - 1674
3ኛ. እያሱ ...” ብለው ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ፣ ጣልቃ ገብቼ አቋረጥኳቸው።
“እያሱ ማለት...?” ብዬ ጥያቄዬን ከመጀመሬ፣ እሳቸው በተራቸው ጣልቃ ገብተው አቋረጡኝ።
“እንደማመጥ እንጂ ጎበዝ!?... ታሪክ እኮ ነው እያስጎበኘሁ ያለሁት!...” አሉና በግልምጫ አንስተው አፈረጡኝ።
ደንገጥ አልሁ።
አስጎብኛችን እንደምንም ተረጋግተው ማስጎብኘታቸውን ቀጠሉ...
“እንግዶቻችን ወደ ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ እንኳን በደህና መጣችሁ!... እንግዲህ፣ የአጼ ፋሲል ግቢ ተብሎ በሚታወቀው በዚህ ሰፊ ቅጽር ውስጥ፣ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ነገስታት ያስገነቧቸው አብያተ መንግስታት ይገኛሉ። መቀመጫቸውን በጎንደር ከተማ ላይ አንድርገው የነገሱ ነገስታት የሚከተሉት ናቸው።
1ኛ. አፄ ፋሲል (ዓለም ሰገድ) ከ1623 - 1659
2ኛ. ዮሀንስ 1ኛ (አእላፍ ሰገድ) ከ1659 - 1674
3ኛ. እያሱ 1ኛ (አድያም ሰገድ) ከ1674 - 1698
4ኛ. ዳዊት 3ኛ (አድባር ሰገድ) ከ1708 -1713
5ኛ. አፄ ባካፋ (መሲህ ሰገድ) ከ 1713 - 1722
6ኛ. እያሱ 2ኛ (ብርሃን ሰገድ) ከ1722 - 1749
7ኛ. እቴጌ ምንትዋብ... (የንጉስ ባካፋ ባለቤት) 1730 - 1755 ከ1730 - 1755...”
አስጎብኛችን ተግተው መተረካቸውን ቀጥለዋል። ትንፋሽ የማይሰጥ ተረካቸውን እያዥጎደጎዱ፣ ፊታቸውን ወደ ግዙፉ ጥንታዊ ፎቅ አዞሩ።
“ይህ ከፊታችን የምትመለከቱት፣ በግቢው ውስጥ ከሚገኙ ህንፃዎች ትልቁ እና ከሞላ ጎደል በደህና ሁኔታ ላይ የሚገኘው፣ የአፄ ፋሲል ቤተ መንግስት ነው። 32 ሜትር ርዝመት እና 3 ፎቆች፣ እንዲሁም በርካታ የምድር ውስጥ ክፍሎች አሉት። ከመጨረሻ ፎቅ በስተ ደቡብ ምዕራብ ላይ፣ በከበሮ ቅርፅ የተሰራ ክፍልም አለ። የህንፃው አራት መአዘን አናቶች...”
“Sorry sir...” ሲል አቋረጣቸው፣ ደረቱ ላይ ካሜራ አንጠልጥሎ ከፊቴ ተገትሮ የነበረ ከሲታ ፈረንጅ። የአስጎብኛችን ፊት በንዴት ሲቀላ አየሁት።
“ዋቲዚስ?...” አሉት ኮስተር ብለው እያዩት።
“Can i take pictures?...” ሲል በትህትና ጠየቃቸው።
“እ!?...” ግራ ተጋብተውዋል አስጎብኝው።
“ፎቶ ግራፍ ማንሳት እችላለሁ ወይ ነው የሚለው...” አልኳቸው ጣልቃ ገብቼ።
“የስ!...” አሉ በንዴት እንደጦፉ።
አስጎብኛችን በምሬትና በመሰላቸት ሲመለከቱን ቆይተው በረጅሙ ተነፈሱ። የእንጀራ ነገር ሆኖባቸው እንጂ፣ በቆምንበት ጥለውን ቢሄዱ በወደዱ። እንደገና ጀመሩ...
“እንግዶቻችን ወደ ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ እንኳን በደህና መጣችሁ!... እንግዲህ የአጼ ፋሲል ግቢ ተብሎ በሚታወቀው በዚህ ሰፊ ቅጽር ውስጥ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ነገስታት ያስገነቧቸው አብያተ መንግስታት ይገኛሉ። መቀመጫቸውን በጎንደር ከተማ ላይ አንድርገው የነገሱ ነገስታት የሚከተሉት ናቸው።
1ኛ. አፄ ፋሲል (ዓለም ሰገድ) ከ1623 - 1659
2ኛ. ዮሀንስ 1ኛ (አእላፍ ሰገድ) ከ1659 - 1674
3ኛ. እያሱ...”
እንደገና ንግግራቸው ተቋረጠ - የገዛ ንጥሻቸው አቋረጣቸው።
“ይማርዎት!...” አላቸው ከመካከላችን የነበረ ጎብኝ።
የወጉን መልስ አልሰጡትም።
“ከስራዬ ላይ ሲያናጥቡኝ አልወድም!...” አሉ እንደተኮሳተሩ።
ከጫፉ ሲጀምሩት እንጂ፣ ከመካከል አቋርጠው ሊቀጥሉት የማይችሉትን ሽምድድ ገለጻ፣ ዳግም ከመግቢያው እንዳይጀምሩ... ዘዴ ፈጠርኩ።
“3ኛ. አፄ እያሱ...” አልኩ - ያቋረጡበትን ቦታ ላስይዛቸው።
“ተናግሪያለሁ!... ከስራዬ ላይ ሲያናጥቡኝ አልወድም!...” ብለው አጉረጠረጡብኝ። በንዴት መሃረባቸውን አውጥተው አፍንጫቸውን ጠራረጉና ገለጻቸውን ቀጠሉ። ማለትም... ገለጻቸውን ጀመሩ።
“እንግዶቻችን ወደ ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ እንኳን በደህና...”
አብዱል ጀባር እስኪመጣ...
ያ...
“ሚሊኒየም” የሚሉት “ጦሰኛ በዓል” የመጣ ሰሞን...
በኦሮምያ ባህል ቢሮ በተዘጋጀ የጉብኝት መርሃ ግብር ላይ ተካፈልኩ። የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችን ስንጎበኝ ሰንብተን፣ ተራው የሶፍ ኡመር ዋሻ ሆነና ወደዚያው አቀናን። ከረጅም ጉዞ በኋላም ከስፍራው ደረስን። ነገር ግን፣ ፈጥነን ወደ ጉብኝቱ አልገባንም። ቀትር ስለነበር፣ የዛፎችን ጥላ ተከልለን አረፍ እንድንል በጉዞው አስተባባሪዎች ተነገረን።
ጉብኝቱ ለምን እንደማይጀመር ግራ ገባን።
የጉብኝቱ አስተባባሪዎች፣ እኛን ባለንበት ትተው ከወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ። በአካባቢው ከነበሩ ነዋሪዎች ጋር ይነጋገራሉ። ወደዚያ ወደዚህ ይላሉ። ለረጅም ሰዓት ጠበቅን። ጉብኝቱ ግን አልተጀመረም። በስተመጨረሻ... ጉዳዩን ለማጣራት ወደ አንዱ የጉዞ አስተባባሪ ጠጋ አልኩ።
“ለምንድን ነው የማይጀመረው?...” በማለት ጠየቅኩት።
“ይጀመራል... አብዱል ጀባር ከገበያ እስኪመጣ ነው...” አለኝና ባለሁበት ትቶኝ ሄደ።
“ማነው አብዱል ጀባር?...” አልኩ ለራሴ። መልሱን ያገኘሁት ቆይቼ ነው።
አብዱል ጀባር የሶፍ ኡመርን ዋሻ የማስጎብኘት ብቸኛ ስልጣን የተሰጠው የአካባቢው ነዋሪ ነው። አብዱል ጀባር፣ በአለማቀፍ ደረጃ የሚታወቀውን ይህን ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ በብቸኝነት የማስጎብኘቱን ስልጣን ያገኘው፣ በመወለድና በመወለድ ብቻ ነው።
የታላቁ የሃይማኖት አባት፣ የሶፍ ኡመር የልጅ ልጅ ልጅ ልጅ ልጅ... ልጅ ነው። እሳቸው፣ ይህንን የእምነት ስፍራ የሚያስተዳድረው ከእሳቸው የዘር ሃረግ የሚመዘዝ የመጀመሪያው ወንድ ልጅ እንዲሆን አዝዘዋል። በዚህም መሰረት፣ ተረኛው አስተዳዳሪ አብዱል ጀባር ሆኗል። ስለዚህም ጎብኝ ሲመጣ ተቀብሎ ማስጎብኘት፣ እንደ ሥራ ሳይሆን እንደ ስልጣን ለመቆጠር በቃ - የአብዱል ጀባር እና የአብዱል ጀባር ብቻ ስልጣን!
አብዱል ጀባር ጉዳይ ኖሮበት ከአካባቢው ራቅ ባለበት ጊዜ የመጣ ጎብኝ፣ ከቻለ የእሱን መምጣት መጠበቅ፣ ካልሆነ ደግሞ በመጣበት እግሩ መመለስ ግዴታው ነው። እኛም የዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብለን እየጠበቅን ነው - አብዱል ጀባር ከገበያ እስኪመጣ!...
የጎራዴው ጫፍ ለምን ተጣመመ?...
ከአንድ ወዳጄ ገጠመኝ የመዘዝኳት ተረክ ናት...
ይሄው ወዳጄ በአንድ ትልቅ የአገራችን ሙዚየም ውስጥ በአስጎብኝነት ተቀጥሮ ይሰራ ነበር። የሆነ ጊዜ ላይ ግን፣ ስራውን ቀየረና የስራ ባልደረባዬ ሆነ።
የሆነ ቀን ማለዳ...
ከዚሁ ወዳጄ ጋር ሻይ ቡና እያልን፣ የሞባይል ስልኩ ጠራ። የደወለለትን ሰው ስም ከሞባይሉ ላይ ሲያነብብ፣ በምሬት ስሜት በረጅሙ ተነፈሰ። ላንሳው አላንሳው በሚል ሲያመነታ ቆየና፣ አለማንሳቱን መርጦ ሞባይሉን ጠረጴዛው ላይ መልሶ አስቀመጠው።
“ሰላም አይደለም እንዴ?...” ስል ጠየቅኩት በጥርጣሬ።
ደዋይዋ በሙዚየሙ የእሱን የቀድሞ የስራ ቦታ ተክታ መስራት የጀመረች ወጣት አስጎብኚ እንደሆነች ነገረኝ። ነጋ ጠባ እየደወለች፣ በማያባራ ጥያቄ እንዳማረረችው አጫወተኝ።
“ጥያቄ?.... ማለቴ... ምን አይነት ጥያቄ?...” አልኩት ተጠራጥሬ።
እኔ እንደጠረጠርኩት አይደለም። ጥያቄዋ፣ “ጾታዊ” ሳይሆን “ሙያዊ” እንደሆነ ገባኝ።
ነገሩ እንዲህ ነው...
ወዳጄ የአስጎብኝነት ስራውን ከለቀቀ በኋላ፣ ሙዚየሙ ሌላ ሰራተኛ ለመተካት የስራ ማስታወቂያ አወጣ። በማስታወቂያው ላይ የተቀመጠውን የትምህርትና የስራ ልምድ የሚያሟሉ በርካታ አመልካቾች ተመዘገቡ። በስተመጨረሻም... ከብዙ አመልካቾች መካከል፣ ይህቺው ወጣት አንደኛ ወጣችና በአስጎብኝነት ተቀጠረች። ማስጎብኘትም ጀመረች...
ግን፣... ማስጎብኘት፣... ለአስጎብኝነት ተወዳድሮ እንደ ማሸነፍና እንደ መቀጠር ቀላል አልሆነላትም።
በሙዚየሙ በተሰባሰቡት ብዙ አይነት ቅርሶች ላይ፣ ብዙ አይነት ጥያቄ የሚሰነዝር፣ ብዙ አይነት ቱሪስት ይጎርፋል... አንዱን ጥያቄ እንደምንም ስትመልስ፣ ሌላ ጎብኚ፣ ሌላ ጥያቄ ይወረውራል። ለሷ፣ አብዛኛው ጥያቄ፣... ‘መልሱ የማታወቅ ጥያቄ’ ነው። ግራ ይጋባታል። ሃፍረት ይሰማታል። ጥያቄ ከሰነዘረላት ጎብኝ ጋር መፋጠጥ ያሸማቅቃል። ሞባይሏን ከኪሷ ታወጣለች። ከሃፍረት እንዲገላግላት፣ የቀድሞው የሙዚየሙ አስጎብኝ ወደነበረው ወደዚሁ ወዳጄ ትደውላለች።
“እ... እኔ እምልህ?... በስተግራ በኩል ከተደረደሩት ጎራዴዎች ሶስተኛው፣ የፊታውራሪ መሸሻ ጎራዴ ነበር አይደል?...” ትለዋለች በጭንቀት ተውጣ እየተርበተበተች።
በማያባራ ጥያቄዋ የተማረረው ወዳጄ፣ ምሬቱን ትቶ ፈገግ ይላል።
የፊታውራሪ መሸሻ ጎራዴ፣ ፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ እንጂ ሙዚየሙ ውስጥ እንደሌለ ይነግራትና፣ የሶስተኛው ጎራዴ ትክክለኛ ባለቤት የነበሩትን ፊታውራሪ ስም ያስታውሳታል።
“ቴንኪው የኔ ጌታ!...” ትለውና፣ ስለ ጎራዴው ለጠየቃት ጎብኝ ትተርካለች።
“እንግዲህ የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት፣ ሶስተኛው ጎራዴ የፊታውራሪ መሸሻ ሳይሆን የፊታውራሪ...” ብላ በኩራት ስሜት ስለጎራዴው ጥንታዊ ታሪክ ማብራራት ትጀምራለች።
በመካከል ግን... መጠየቅ የማይሰለቸው ጎብኝ፣ ሌላ ያልጠበቀቺው ጥያቄ ይሰነዝርባታል።
“የጎራዴው ጫፍ ጠመም ያለው በምን ምክንያት ነው?...” ይላታል ወደ ጎራዴው እየጠቆመ።
በድንጋጤ ክው ትላለች አስጎብኝዋ። ሃፍረት ያሸማቅቃታል። እንደምንም፣ ከትዝብት ለማምለጥ ትሞክራለች።
“ጥ... ጥሩ ጥያቄ ነው!... ያ... ያው እንግዲህ የታሪክ መዛግብት እንደሚያትቱት፣ እኒሁ ጀግና ፊታውራሪ ከጠላት ወራሪ ሃይል ጋር በተደጋጋሚ ተፋልመው ድል አድርገዋል። ከጦርነቶቹ መካከል ግን...” በማለት አፏ እንዳመጣላት ‘ጭንቅ-ወለድ’ የታሪክ ሰበዝ መተርተር ትጀምራለች። ግን፣ ማጣፊያው ያጥራታል።
ጠያቂውን ጎብኝ በይቅርታ አይን እያየች፤ ፈጥና ሞባይሏን ታወጣና ወደ ፈረደበት ወዳጄ ትደውላለች።
“እ... እኔ እምልህ?... የጎራዴው ጫፍ ጠመም ያለው፣ በየትኛው ጦርነት ላይ ነበር?... ታሪኩ...” ትለዋለች ለጎብኝው በማይሰማ ድምጽ።
አሁንም በትዝብት ፈገግ ብሎ ይመልስላታል።
“ይሄ የታሪክ ጉዳይ ሳይሆን፣ የአስተዳደር ጉዳይ ነው። ባለፈው አመት የቅርሶች ቆጠራ ስናደርግ፣ ድንገት ከመዝጋቢው እጅ ወድቆ ነው የተጣመመው!...”



Read 1394 times