Print this page
Sunday, 27 November 2016 00:00

የአባይ ስሜት

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(4 votes)

“--- አይሁዶች በስደት ወደ ግብጽ ምድር የመጡት የአባይን ወንዝ በረከት ፍለጋ ነው፡፡ ነብዩ ሙሴ የአባይን ውሃ
እየጠጣ ያደገ ነው፡፡ በኋላም እመቤታችን ማርያም ከነ ልጇ ወደ ግብጽ ተሰድዳ በአባይ የበቀለ ፍሬን በልታለች፡፡
ውሃውንም ጠጥታለች፡፡ የመጀመሪያው ጽሑፍ ጥበብም የተፈጠረው በአባይ ወንዝ ዳርቻ ነው፡፡----”

ገጣሚው ደበበ ሰይፉ፤ በ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› በተሰኘ ግጥሙ፤
‹‹ምንድን ነውና እንባ፤ ምንድን ነውናስ ለቅሶ፤
ከእንጉርጉሮ ባለፈ እንጉርጉሮ፤ የስሜት ዘሃው ተበጥሶ›› ይላል፡፡
ገጣሚው ደበበ፤ በኪነተ ቃላት የገለጸው ነገር፤ በጉባ ሸለቆ በኪነተ ህይወት ተገልብጦ አገኘሁት፡፡ እነዚህ የደበበ ስንኞች፤ በገዛ ህይወቴ ሁነት የተከየኑ ስንኞች ሆነው በነፍሴ ሸለቆ ሲነበቡ ሰማኋቸው። በተጠቀሱት ሁለት ስንኞች ገጣሚው ለመግለጽ የፈለገው ስሜት፤ ድምጸቱ ተቀይሮ፤ በህይወት ሰሌዳ በገቢር ጠመኔ ተጽፎ እኔ ራሴ ኖርኩት፡፡ ‹‹አናባቢ›› (ቫወል) የነበረው የደበበ ስሜት፤ አሁን ‹‹ተነባቢ›› (ኮንሶናንት) ሆነ፡፡ አንባቢ የነበርኩት እኔም ተነባቢ ሆንኩ፡፡  የስሜት ሙላት በመፍጠር በህሊናዬ ወንዝ ይፈስሱ የነበሩት እነዚህ ስንኞች፤ በጉባ ሸለቆ ሁነቶች የተገነባውን ‹‹የስሜቴን ተርባይን›› በመምታት፤ ታላቅ የፍካሬ (የትርጉም) ኃይል አመነጩ፡፡ የኪነተ-  ቃሉ ኃይል፤ ወደ ኪነተ - ህይወት ኃይል ተለወጠ። የደበበ ስንኞች ይዘት ተቀየረ፡፡ አሁን የሚሰማኝ፤  
‹‹ምንድን ነውና ይባቤ፤ ምንድን ነውና ሐሴት፤
ከደስታ ያለፈ ደስፈቅታ፤ የስሜት ዘሐውን በጥሶት›› የሚል ንባብ ነው፡፡
የደበበን ስሜት ይዘት፤ ከአዲስ አበባ 800 ኪ.ሜ ርቀት፤ ከሐገራችን ድንበር 40 ኪ.ሜ ራቅ ካለ ስፍራ ሆኜ፤ በሌላ የስሜት ጎዳና ተረዳሁት፡፡ በንባብ ከተረዳሁት በላይ ደበበን በመኖር አገኘሁት፡፡ እሣት ማቃጠሉን ሲነግረኝ ያልተረዳሁት፤ ፍቺውን በመኖር (በገቢር) አገኘሁት፡፡ ደበበ ‹‹ምንድን ነውና ሐዘን፤ ምንድን ነውና ለቅሶ›› ያለው አሁን ተገለጠልኝ። ‹‹ከእንጉርጉሮ ባለፈ እንጉርጉሮ፤ የስሜት ዘሃው ተበጥሶ›› ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ጉባ ሸለቆ ውስጥ ገብቼ ገባኝ፡፡ አዎ፤ ከስሜት ባለፈ ስሜት፤ የሐሳብ ዘሐ ተበጥሶ፤ ምንድን ነውና ሐሳብ፤ ምንድን ነውና አዕምሮ፡፡››
አሁን ስሜት ብቻ ነኝ፡፡ ‹‹ከደስታ ባለፈ ደስፈቅታ፤ የስሜት ዘሃው ተበጥሶ››፤ የአዕምሮ ግድብ ተደርምሶ፤ ሐሳብ ከወዴት ይገኛል?
አሁን ጉባ እገኛለሁ፡፡ የኢትዮጵያውያንን የልብ ትርታ መስማት የፈለገ ሰው፤ እዚህ ሥፍራ መገኘት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሥፍራ የአባይ ተፋሰስ ሐገራት ህዝቦችን ወይም በአጠቃላይ የአፍሪካ ህዝቦችን ቀልብ ጨምድዶ የያዘ ሥፍራ ነው፡፡ ከጉባ ኮረብታ ቆሜ ቁልቁል ወደ ወንዙ ስመለከት፤ በጉባ ሸለቆ የሚደረገው ነገር ሁሉ ተምሣሌታዊ ዘይቤ ያለው ግጥም ሆኖ ታየኝ፡፡ አባይ ፈሳሽ ቅኔ መሆኑ ተገለጠልኝ፡፡ የቴምስ ወንዝን፤ ‹‹ፈሳሽ ታሪክ›› ያለው ማነው? እንደ አባይ ፈሳሽ ታሪክ ያለ አይመስለኝም፡፡ አባይ ሲገደብ ማየት፤ የኢትዮጵያ የታሪክ እንቆቅልሽ ሲፈታ እንደማየት ነው። የኢትዮጵያን የታሪክ እንቆቅልሽ፤ ጉባ እና ሲርባባ ተማክረው ሲፈቱት ተመለከትኩ፡፡ ‹‹ጉባ›› እና ‹‹ሲርባባ›› ከሐገራቸው ልጆች ከኢትዮጵያውያን ጋር መክረው፤ የአባይን እንቆቅልሽ ፍቺ እየገለጡት ነው፡፡
ይህ አሁን የቆምኩበት ሥፍራ፤ አባይ በጥድፊያ ቁልቁለቱን እየተንደረደረ፤ ሲበሉ የላኩት ልጅ ይመስል እየሮጠ፤ ከደጋው ምድር ለም አፈራችንን እየቧጠጠ፤ ኢትዮጵያ እንዳትይዘኝ ብሎ ሽምጥ ሲጋልብ ቆይቶ፤ ከሜዳው ሲወርድና ከኢትዮጵያ ለመውጣት 40 ኪ.ሜ አካባቢ እንደሚቀረው ሲያውቅ፤ ከእንግዲህ ሮጣ እንደማትይዘው በመተማመን ዘና - ጎምለል እያለ መሄድ ከሚጀምርበት ሥፍራ ነው፡፡ ይህ አሁን የቆምኩበት ሥፍራ፤ አባይ በኢትዮጵያ የምዕራብ ተፋሰስ ከሚገኙ መንደሮች የተደፋች የውሃ ጠብታን፤ የተተፋች ምራቅን ሁሉ ሰብስቦ፤ የታላላቅ ወንዞችንና ጅረቶችን ውሃ አግበስብሶ መፍሰስ ከሚጀምርበት ሥፍራ ነው፡፡ አባይ ከዚህ በታች ከኢትዮጵያ ምድር ከሚመነጭ ወንዝ የሚያገኘው ተጨማሪ ውሃ የለም፡፡ ይህ ሥፍራ አባይ የመጨረሻ መልኩን ይዞ የሚፈስበት ሥፍራ ነው፡፡ አባይ የጉባና የሲርባባ ኮረብታዎችን ግራ ቀኝ ታዛቢ አድርጎ፤ ጎርምሦና ጎልምሶ የኢትዮጵያን ምድር ለመልቀቅ፤ በደረቱ የሚሳብ ጥቁር ዘንዶ መስሎ ወደ ሱዳን ሲሸመጥጥ የሚታየው ከዚህ አካባቢ ነው፡፡
አሁን ከኮረብታው ወርጄ፤ የኮርቻ ግድቡን ወይም ‹‹ሳድል ዳሙን›› አይቼ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀከት አካል ሆኖ አሁን በመሰራት ላይ የሚገኘውን ድልድይ ለማየት፤ በአርበኛው ኢንጅነር ስመኘው መሪነት ወደ ግድቡ ግርጌ እየተጓዝኩ ነው፡፡ ከድልድዩ  በታች የሚያልፈውን አባይ ስመለከተው፤ ቁልቁለቱን በሩጫ በመውረድ ጉልበቱ ዝሎ መራመድ የተሳነው መስሎ ታየኝ። ከኢትዮጵያ ምድር ጠብ የሚለውን ውሃ ወይም ከበራችን ወጥተን የምንተፋውን ምራቅ ሳይቀር አጠራቅሞ የሚፈሰው አባይ ብዙ ውሃ ያልያዘ መስሎ ይፈሳል፡፡ ሆኖም እዚህ ሥፍራ የምታገኙት አባይ፤ ከኢትዮጵያ ሰሜናዊ ጫፍ እስከ ደቡባዊ ጫፍ ድረስ ያሉ የምዕራብ ተፋሰስ የሚገኙ እያንዳንዱን የመንደር ጅረት ውሃ አጠራቅሞ፤ እንደ ዳቡስ፣ በለስ፣ ደዴሳ፣ ግልገል አባይ፣ተከዜ፣ ሙገር ወዘተ የመሳሰሉ የታላላቅ ገባር ወንዞችን ውሃ አንጠፍጥፎ ቀድቶ፤ ሙሉ ኃይሉን ይዞ የሚፈስውን አባይ ነው፡፡
ከድልድዩ ትንሽ ዝቅ ብዬ ከቆምኩበት ሥፍራ ሆኜ አባይን ሳስተውለው፤ ዛሬ በዓለም ለሚታየው የሰው ልጅ ሥልጣኔ መሠረት የሆነ ወንዝ መሆኑን አሰብኩ። የዓለም የስልጣኔ ችግኝ የአባይን ወንዝ ጠጥቶ ያደገ መሆኑን አስታወስኩ። በዓለም ቀዳሚው ሥልጣኔ የግብጽ ሥልጣኔ ነው። ከሜሶፖታሚያ፣ ከባቢሎን፣ ከፋርስና ከግሪክ ቀድሞ  የዓለም ሥልጣኔ ችግኝ የበቀለው፤ በአባይ ወንዝ ዳርቻ ነው፡፡
የአባይ ወንዝ የኢትዮጵያን ምድር እየቧጠጠ ለም አፈር ወስዶ፤ በረሃውን አቋርጦ ተጉዞ፤ ከሜድትራኒያን ባህር ከመግባቱ በፊት የግብጽን አሸዋማ ምድር በውሃ ያለብሰዋል፡፡ ከወንዙ ግራና ቀኝ ሰፊ ሐይቅ መስሎ ተንጣሎ ይቆይና፤ በበጋው ወራት መልሶ ወደ መፋሰሻ ጨረቻው ሲሰበሰብ፤ በሚሊየን በሚቆጠሩ ብርቱ ገበሬዎች ተደጋግሞ እንደታረሰ ያለ ምርጥ እርሻ ይሰራል፡፡ የግጦሽና የእርሻ መሬቱ በየዓመቱ እየታደሰ፤ ብዙ ሴንቲ ሜትር የሆነ ጥልቀት ያለው እጅግ ለም አፈር ይተዋል፡፡
አባይ የአፍሪካ፣ የአረብና የእስያ ሰዎችን ከረሃብ ያወጣ ወንዝ ነው፡፡ አስገራሚ የመስኖ ልማት ጥበብ የተፈጠረው በአባይ ሸለቆ ነው፡፡ የአባይ ወንዝ በግል መስራትን የሚፈቅድ አልነበረም፡፡ ጥንታውያን ግብጾች ከጎረቤት ጋር በመተባበር መስራትንና አብሮ መኖርን የተማሩት በአባይ ነው፡፡ የተደራጀ የአስተዳደር ስርዓት ወይም መንግስት መፍጠር የቻሉት በዚህ የተነሳ ነው። የአባይ ቸርነት፤ ከመሐል አፍሪካ፣ ከምዕራብ እስያና ከበረሃማው የአረብ ምድር ብዙ ሰዎችን ስቧል፡፡
በመሆኑም፤ በታሪክ የሚታወቁት የመጀመሪያቹ ከተሞች በአባይ ወንዝ ዳርቻ የተፈጠሩ ናቸው። በቸነፈር ይጠበስ የነበረው የቅደመ ታሪክ ዘመን ሰው፤ ሆዱ የጠገበው በአባይ ነው፡፡ ከአባይ ሸለቆ ውጭ የሚኖረው ሰው፤ ከቀን 24 ሰዓታት 16ቱን ምግብ በመፈለግ የሚያጠፋ ነበር፡፡ በተቃራኒው፤ በግብጽ ከተሞችና በገጠር አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ የሚበላውንና የሚጠጣውን ነገር በቀላሉ የሚያገኝ ነበር፡፡ ስለዚህ በአባይ ሸለቆ የሚኖረው ህዝብ፤ ከሆድ ጥያቄ የተረፈ ብዙ ሰዓት ያለው ሆነ፡፡ የግብጽ ስልጣኔ ምንጭም ይኸው ነበር፡፡ ግብጻዊው ሰው፤ በትርፍ ሰዓቱ፤ ‹‹የአባይን ወንዝ ማን ፈጠረው?›› ‹‹ከዋክብት ከየት መጡ?››፣ ‹‹ይህ አስደንጋጭ መብረቅ ምንድነው?›› እያለ በመጠያየቅ የሥልጣኔን ሻማ ለኮሰ፡፡
አንዳንድ ሰዎች ከላይ የተጠቀሱትን ጥያቄዎች አጥብቀው በመያዝ መመራመር ያዙ፡፡ ግብጻውያን እነዚህን ሰዎች ‹‹ቄሶች›› አሏቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወይም ቄሶች የህዝቡ የሐሳብ መሪዎች ወይም እረኞች ሆኑ፡፡ የሥልጣኔ ፋና ወጊዎች ለመሆን ቻሉ። በህዝቡ ዘንድ የሚከበሩ ጠቢባን ሆኑ፡፡ ቄሶች ስለ ምድራዊ ህይወት ብቻ ሳይሆን፤ ስለ ሰማያዊው ህይወት ይጠበቡ ነበር። በሞት ከዚህ ዓለም የሚለዩ ሰዎች፤ በወዲያኛው ዓለም መኖር ይቀጥላሉ የሚል እምነት መነሻ ሆኖ፤ ግብጾች፤ የሬሳ ማድረቂያ ጥበብ ፈለጉ፡፡ ፋርሶች ‹‹መሚ›› የሚሉትን አመጡ፡፡ ለነገስታቱ አስከሬን ማስቀመጫ ፒራሚዶችንም ገነቡ፡፡ አይሁዶች በስደት ወደ ግብጽ ምድር የመጡት የአባይን ወንዝ በረከት ፍለጋ ነው። ነብዩ ሙሴ የአባይን ውሃ እየጠጣ ያደገ ነው። በኋላም እመቤታችን ማርያም ከነ ልጇ ወደ ግብጽ ተሰድዳ በአባይ የበቀለ ፍሬን በልታለች፡፡ ውሃውንም ጠጥታለች፡፡ የመጀመሪያው ጽሑፍ ጥበብም የተፈጠረው በአባይ ወንዝ ዳርቻ ነው፡፡
ታዲያ ጉባ ከድልድዩ በታች ቆሜ፤ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የሚሰጠውን ማብራሪያ ሰምቼ ስጨርስ፤ ደንገዝገዝ ባለው የአመሻሽ ብርሃን፤ ተከብቤ ይህን የስልጣኔ ታሪክ አስብ ነበር፡፡ እኔ ከቆምኩበት ቦታ ወደ ላይ ወይም ወደ ታች የሚፈስስ መሆኑ የማያስታውቀውን የአባይ ወንዝ ቁልቁል እየተመለከትኩ፤ አሁን ከተናገርኩት የበዛ ብዙ የነገር ስንክሳር ሳውጠነጥን ነበር፡፡
ዛሬ ይህን ወንዝ ለመገደብ በተለያየ የርዕዮተ ዓለም፣ የፖለቲካ አቋም፣ የሐይማኖት፣ እምነት፤ የባህል፣ የብሔርና ብሔረሰብ ተፋሰስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ እንደ አባይ ገባሮች ሐሳባቸውን አስተባብረው፤ የስልጣኔ ፈለግ የሆነውን አባይ በቤታቸው ለማላመድ እየሰሩ መሆናቸውን እያደነቅኩ፤ በኢንጅነሩ መሪነት ወደ አርበኞቹ መንደር የመልስ ጉዞዬን ጀመርኩ፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሐብትና የጉልበት ጠብታ ሰብስቦ፤ የሐገሪቱን ልማት የሚያቀላጥፍ ኃይል ለመሆን እየተዘጋጀ መሆኑን በማሰብ በመኪና ጉዞ ይዣለሁ፡፡
‹‹አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መስራት አይችልም›› የሚባለው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ የሥራ ወረዳ፤ በአንድ ስሜት ሲሰራ የሚታይበት ጉባ በብርሃን ደምቆ ከሩቅ ይታየኛል፡፡ የጉባና የሲርባባ ኮረብታዎች በወገግታ ብርሃን ፈገግ ብለው ከሩቅ ይታዩኛል። ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች በአንድ የሥራ ወረዳ ተሰባስበው፤ ከአንድ ክፉ ጠላት ጋር ግብግብ ገጥመዋል፡፡ ጉባ የፀረ ድህነት ጦርነት ተከፍቷል፡፡ የትግሉ አውደ ግንባር ተጋግሏል፡፡ ጉባ የጥቁር ህዝቦች የጸረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል የድል ታሪክ የተጻፈበት ታሪካዊ ሥፍራ ከሆነው አድዋ ጋር የሚመሳሰል አውደ ግንባር መሰለኝ፡፡ በጉባ ሸለቆ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተፋፋመ የጸረ-ድህነት ጦርነት ውስጥ ናቸው፡፡ ጉባ ልዩ መንፈስ ያረበበባት ምድር ናት፡፡ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ፤ የኢትዮጵያ የሱዳን የግብጽ፤ እንዲሁም የሌሎች የተፋሰሱ ሐገራት ህዝቦች ቀልብ ያረፈበት ስፍራ በመሆኑ፤ የአካባቢው ድባብ የተለየ መንፈስ ማሳደሩ አያስገርምም፡፡ አሁን የአባይ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ዕለት ወይም የግድቡ ግንባታ የብስራት አዋጅ ከታወጀበት ዕለት ላቅ ያለ የደስፈቅታ ስሜት ውስጥ እገኛለሁ፡፡
ከዚህ በኋላ ከዚህ ጽሑፍ የሆነ መልዕክት ለማግኘት የሚሞክር ሰው ማንበቡን እንዲተወው እመክረዋለሁ፡፡ አሁን ንግግር ማድረግ አልሻም፡፡ በእውነት የምፈልገው መዝፈን ነው፡፡ ይህን ስሜት እንደ ከተማ መኮንን መሰንቆ ወይም ክራር ይዤ ከአራዳው ጊዮርጊስ በታች፤ ውቤ በረሃ ጎዳና መሐል ቆሜ ብዘፍነው እወድድ ነበር፡፡ ከደስታ ባለፈ ደስታ፤ የስሜት ዘሃ ሲበጠስ፤ ‹‹ምንድነውና ይባቤ፤ ምንድነውና ሐሴት›› ከሚያሰኝ ስሜት ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ አሁን ስሜት ብቻ ነኝ፡፡ እንደ ኦቴሎ፤
‹‹በሰቀቀን ለቅሶ ብጎርፍ፤ ብጮህ ብጥለቀለቅ በእንባ፤
ጠብታው ሁሉ መርዝ ነው፤ ጭካኔ ነው የማነባ›› (ጸ.ገ.መ) እንዳለ፤ አሁን እያንዳንዱ የደሜ ጠብታ ስሜት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በዚህ ጽሑፍ መልዕክት ለማስተላለፍ መሞከር ነገር ማበላሸት ነው፡፡ ሁለመናዬ በስሜት ጥሩምባ ተሰብስቦ፤ የስሜት እሣተ ገሞራ ፈጥሮ፤ ህሊናዬ ከስሜት አደባባይ ቆሞ፤ ከጉባና ከሲርባ ወረዳዎች የስሜት ጀማ ነቅሎ ወጥቶ ታድሞ፤ ‹‹የሰራ ስሜቴ›› በጉባ አርበኞች የሥራ መንፈስ ተጋግሎ፤ ስሜት እንጂ ሐሳብ አይወጣኝም።
አፍንጫዬ የጉባን አፈር አሽትቶ፤ በጉባ ምድር ትኩሳት እንደ ጋለ ብረት ተተኩሶ፤ በወላፈኑ ተለብልቦ፤ በይባቤ ፍፁም ሰክሮ፤ እንዲህ በስሜት ንዳድ ተቀጣጥሎ፤ የምድረ- አዕምሮዬ አቧራ ጨሶ፤ በስሜት ላቦት ታፍኖ፤ አይሆኑ ሆኖ በስሜት ዋዕይ ተቃጥሎ፤ የነፍስ- የህሊናዬ መድረክ በምንጃር፣ በወላይታ፣ በኦሮሞ፣ በትግሬ፣ በሐረሪና በጉራጌ ወዘተ ጭፈራ ተርገድግዶ፤ የሐሳብ ዘሃ ተበጥሶ፤ የመልዕክት ገሶ ዶልዱሞ፤ ምንድን ነውና ሐሳብ፤ ምንድን ነውና የነገር ድሪቶ፤
በአርበኞቹ ተግባር፤ የጉባ ምድር ነባር መልክ ተቀይሯል፡፡ አመጸኛው አባይ፤ የአባይ ሸለቆን ዋዕይ እንደ ሸማ ተጎናጽፎ፤ በጸጥታ  - በዝምታ መፍሰስ ይዞ፤ ለኢትዮጵያውያን ገብሮ፤ እንዲህ ከጉባ ኮረብታ ከወገብ - ከተረተሩ ቆሜ፤ የሐሳብ ጥይት ሁሉ ከሽፎ - ደንብሾ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚታየኝ ትዕይንት ሁሉ ቅኔ - አብሾ ሆኖ አስቸግሮ፤ እኔ ምን ሐሳብ ለመናገር እችላለሁ፡፡ እንደ ጋሽ አበራ ሞላ በክራር ድርሰት መጻፍን እመርጣለሁ፡፡



Read 3238 times