Sunday, 27 November 2016 00:00

ትራምፕ ስልጣናቸውን የሚያሟሹበት ቀዳሚ እቅድ ይፋ አደረጉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

• ስለሜክሲኮ ግንብ እና ስለኦባማኬር ያሉት ነገር የለም
• ሄላሪን ወህኒ አስገባታለሁ የሚለውን ዛቻ እንደማይተገብሩት ተገልጧል

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባልተለመደ መልኩ ባለፈው ሰኞ በዩቲዩብ በኩል ባሰራጩት አጭር የቪዲዮ መልዕክት ስልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ቀዳሚነት ሰጥተው የሚያከናውኗቸውን ተግባራትና ዕቅዶቻቸውን ይፋ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡በመጀመሪያዎቹ 100 የስልጣን ቀናቴ ቀዳሚ ስራዎቼ ይሆናሉ ያሏቸውን ጉዳዮች ያብራሩት ትራምፕ፣ ስልጣን በያዙ በመጀመሪያው ቀን የሚያከናውኑት የመጀመሪያው ነገር፣ ከትራንስ ፓሲፊክ የንግድ አጋርነት ስምምነቶች መውጣት እንደሆነ አስታውቀዋል ብሏል ሲኤንኤን፡፡ ትራምፕ ቀዳሚ ስራዎቼ ይሆናሉ ካሏቸው ጉዳዮች መካከልም፤ በፕሬዚዳንት ኦባማ የተቀመጡ
የአካባቢ ጥበቃ ክልከላዎችን ማስቀረትና የስራ ዕድሎችን መፍጠር የሚሉት ይገኙባቸዋል ብሏል ዘገባው፡፡
አሜሪካን ከተለያዩ ጥቃቶች መከላከል የሚያስችሉ እቅዶችን እንዲያወጡ ለሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች መመሪያ መስጠትም ከተቀዳሚ ስራዎቻቸው አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት ትራምፕ፣በሜክሲኮና በአሜሪካ ድንበር ላይ ግንብ ማስገባትንና
ኦባማ ኬር ተብሎ የሚታወቀውን የጤና መድህን ማስቆምን ጨምሮ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል የገቧቸውን አነጋጋሪ ጉዳዮች በሰኞው መግለጫቸው አለማካተታቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡ የስልጣን ሽግግር ቡድን አዲሱ መንግስታቸው በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች በማቀድና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመንደፍ ረገድ ውጤታማ ስራ እየሰራ እንደሚገኝና ዝርዝር መረጃዎችን ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርጉም ትራምፕ በቪዲዮ መልዕክታቸው አስታውቀዋል፡፡በተያያዘ ዜና ተቀናቃኛቸውን ሄላሪ ክሊንተንን በኢሜይል ቅሌታቸው ሳቢያ ወህኒ እንደሚያስገቧቸው ሲዝቱ የከረሙት ትራምፕ፣ሴትዮዋ በቅሌቱ ሰበብ ከገቡበት ቀውስ እንዲወጡ ድጋፍ ያድርጉላቸዋል እንጂ እንደዛቱት በኤሜይል
ሰርቨራቸው ላይ ምርመራ እንዲደረግ እንደማያዝዙ የትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ አስታውቀዋል፡፡አማካሪዋን ኬልያኔ ኮንዌይን ጠቅሶ አይሪሽ ታይምስ እንደዘገበው፣ ትራምፕ ወደ ስልጣን ሲመጡ በሄላሪ የኢሜይል ቅሌት ዙሪያ ምርመራ በማስደረግ ለፍርድ የማቅረብ ሃሳብ የላቸውም፡፡

Read 5183 times