Monday, 05 December 2016 08:43

በአፍሪካ በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ውርጃ ይፈፀማል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)


       በአፍሪካ በየዓመቱ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ውርጃ የሚፈፀም ሲሆን አብዛኛዎቹም ህገወጥ  መሆናቸው ተገለፀ፡፡ በህገ-ወጥ ውርጃው ሰበብም ከ1.6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሴቶች ለውስብስብ የጤና ችግሮች የሚጋለጡ ሲሆን በቂ ህክምና እንደማያገኙም ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
ከህዳር 20 እስክ ህዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል በተካሄደውና በውርጃ ላይ ባተኮረው የአፍሪካ ሪጅናል ጉባዔ ላይ እንደተገለፀው በአፍሪካ በየዓመቱ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ውርጃ ይፈፀማል፡፡ ህገወጥ ውርጃ የአፍሪካ ዋነኛ የህብረተሰብ ጤና ችግር ሆኖ መቆየቱን በጉባዔው ላይ የተጠቆመ ሲሆን ይህም የውርጃን ህጋዊነት በተቀበሉት አገራት ጭምር የሚታይ መሆኑ ታውቋል፡፡ በአፍሪካ በመውለድ እድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ሴቶች መካከል 90% የሚሆኑት ውርጃን በሚከለክል ህግ ውስጥ እንደሚኖሩ በጉባዔው ላይ ተገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች በቀረቡበት በዚህ ጉባዔ እንደተነገረው ከውርጃ ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች በማደግ ላይ ባሉ አገራት የተለመደ ጉዳይ ሲሆን በአፍሪካ ውስጥ በየዓመቱ ከሚከሰተው የእናቶች ሞት 9% የሚሆነው በህገወጥ ውርጃ ሳቢያ የሚከሰት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በኮንፍረንሱ ላይ የቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎችን መሰረት ያደረጉ ህጎችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት በህገወጥ ውርጃ ሳቢያ የሚከሰት የእናቶች ሞትን ለማስቀረት ጥረት እንደሚደረግም ለማወቅ ተችሏል።

Read 1027 times