Monday, 05 December 2016 08:52

የኮማንድ ፖስቱና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(22 votes)

 ”ቤት ውስጥ መሰብሰብ፣ መግለጫ መስጠት አልተከለከለም”
           አዋጁን የጣሱ የኢህአዴግ አባላትም ታስረዋል”
                
      በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቤት ውስጥ ስብሰባ እንዳያደርጉ፣መግለጫ እንዳይሰጡና የፖለቲካ ሥራ እንዳይሰሩ አለመከልከላቸውን የኮማንድ ፖስት ሴክረቴሪያት አስታውቋል፡፡ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤አዋጁ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ለማድረግም ሆነ አባላት ለማደራጀትና ሌሎች የፓርቲ  ሥራዎችን ለማከናወን እንቅፋት ሆኖብናል ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ከመግለጻቸውም በላይ ኮማንድ ፖስቱ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡
 ኮማንዱ ፖስቱ በጥያቄው መሰረት፣ ሰሞኑን ከተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ጋር በፌዴሬሽን ም/ቤት ውይይት ያደረገ ሲሆን የቤት ውስጥ ስብሰባ አለመከልከሉን፣ ከቤት ውጭም ቢሆን አስፈቅዶ ማካሄድ እንደሚቻል ተነግሯቸዋል - ተቃዋሚዎች፡፡   
መድረክ፣ሰማያዊና መኢአድን ጨምሮ በውይይቱ ላይ 30 የሚጠጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች  የተሳተፉ ሲሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለኮማንድ ፖስቱ ማቅረባቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ጥያቄዎች ብቻ ግን አይደሉም፤ ትችቶችም ሰንዝረዋል፡፡  “የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ጭምር ማድረግ አልቻልንም፣ አባላትም ማደራጀት አልቻልንም” በሚል ፓርቲዎቹ ላቀረቡት አቤቱታ ኮማንድ ፖስቱ በሰጠው ማብራሪያ፤”በፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ ምንም ገደብ አልተጣለም፣ የቤት ውስጥ ስብሰባ አልተከለከለም፤ ከቤት ውጪ የሚደረግ ስብሰባ ግን አስፈቅዳችሁ ማድረግ ትችላላችሁ” ማለቱን የመኢአድ ም/ሊቀመንበር   አቶ ሙሉጌታ አበበ ገልጸዋል፡፡
በአስቸኳይ አዋጁ የተነሳ መግለጫ መስጠት አልቻልንም በሚል ከተቃዋሚዎች ለተነሳው ጥያቄ፤ ”መግለጫ አትስጡ አልተባለም፤ አመፅና ችግር የሚፈጥር ይዘት ያለው መግለጫ ነው የተከለከለው” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ጠቁመው፤ ይሄ ግን ከበፊቱ የኮማንድ ፖስቱ ማብራሪያ የተለየ አይደለም ብለዋል - አቶ ሙሉጌታ፡፡
መድረክ፣ መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ፤“በተለይ ከአዋጁ በኋላ በርካታ አባሎቻችን ታስረውብናል” የሚል አቤቱታ አቅርበው ነበር ያሉት ም/ሊቀመንበሩ፤“አዋጁን የጣሰና በሁከት ተግባር የተሰማራ ሁሉ ይታሰራል፤ የተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን የገዢው ፓርቲ አባላትም ታስረዋል” የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል ብለዋል፡፡
“መንግስት የአመራር ጉድለት አለብኝ፤እታደሳለሁ እያለ፣ እንዴት ሌሎችን ተጠያቂ አድርጎ ያስራል” የሚል ጥያቄም ከፓርቲዎች ተሰንዝሮ ነበረ። “የጥልቅ ተሃድሶው ጉዳይ የመንግስት እንጂ የኮማንድ ፖስቱ አይደለም፡፡ ስለ ተሃድሶው በሌላ መድረክ ከመንግስት ጋር መነጋገር ትችላላችሁ” መባላቸውን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል፡፡  
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለወረዳና ለበታች አመራሮች የበቀል እርምጃ ለመውሰድ የተመቻቸ ነው የሚል ስጋት እንዳላቸው ፓርቲዎች መግለጻቸውን አቶ ሙሉጌታ አውስተዋል፡፡ አዋጁ ለምን ችግር በሌለባቸው የአገሪቱ ክፍሎችም ታወጀ በሚል ለተነሳው ጥያቄም፣ ”ረብሻና ሁከቱ እየሰፋ ሊሄድ ይችላል በሚል ግምት ነው” የሚል ምላሽ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት መንግስት ከተቃዋሚዎች ጋር ሊመክርበት ይገባ እንደነበረ አስረግጠው መናገራቸውን የጠቆሙት የመኢአድ ም/ሊቀመንበር፤ የማታ ማታ ፓርቲያቸው ከውይይቱ አርኪ ምላሽ አለማግኘቱን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ይሄን አቋም የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/ቀመንበር አቶ የሸዋስ አሰፋም ይጋሩታል፡፡ ከኮማንድ ፖስቱ ፓርቲያቸው የጠበቀውን ያህል ማብራሪያ አለማግኘቱን የገለጹት ሊ/መንበሩ፤ መጀመሪያም ማብራሪያ የጠየቀው ከጠ/ሚኒስትሩ እንጂ ከኮማንድ ፖስቱ አልነበረም ይላሉ፡፡ “ምክንያቱም ፓርቲያችን ኮማንዱ ፖስቱ ከህገ-መንግስቱ ውጭ የተቋቋመ ነው ብሎ ስለሚያምን ነው” ብለዋል። በህገ መንግስቱ የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ ሊቋቋም እንደሚችል በግልፅ ቢቀመጥም “ኮማንድ ፖስት” ይቋቋማል የሚል ግን የለም ያሉት አቶ የሸዋስ፤ጥያቄውን በውይይቱ ላይ ባነሳውም ምላሽ አላገኘሁም ብለዋል፡፡

Read 4433 times