Saturday, 10 March 2012 12:06

የሙስና አደጋ! “ብልህ ከጐረቤቶቹ ይማራል”

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

ሙስና የእድገት ፀር ነው፡፡ ሙስና የሀገርንና የህዝቦችን እድገትና ኑሮ በማቀጨጭ በድህነት መማቀቅን ያስከትላል፡፡ ሙስና ለሀገርና ለስርአቷ ከፍተኛ አደጋ ነው እያሉ መስበክ የአዳማጩን ወይም የአንባቢውን ንቃተ ህሊና ዝቅ አድርጐ እንደመገመት ሊቆጠር ይችላል፡፡ ለምን ቢባል? ከላይ የተገለፁት ጉዳዮች በሙሉ ተጨማሪ ማብራሪያ ሳያስፈልጋቸው ማንም እውነትነታቸውን በቀላሉ ሊረዳቸው የሚችሉ ጉዳዮች ስለሆኑ ነው፡፡ ሙስናን በተመለከተ ትልቁ አሳሳቢው ጉዳይ የሚፈጥረው አደጋ ሳይሆን ይህን አደጋ ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ነው፡፡ የሙስናን ከፍተኛ አደጋ ለማስወገድ የሚደረግ ቁርጠኛ ትግል ሳይኖር፣ ስለ ሙስና አደጋ ኤሎሄ ማለት ተራ የቁራ ጩኸት ነው፡፡

በተደጋጋሚ እንደተገለፀው ናይጄሪያውያን በሀገራቸው ለዘመናት የተንሰራፋውን ሙስና የሚገልፁበት አንድ የቅጽል ስም አላቸው፡፡ “ሰይጣኑ” ይሉታል፡፡ ከሀገሪቱ ካዝና ይህን ያህል መቶ ሚሊዮን ዶላር ተዘረፈ ወይም ደግሞ የአንጐላ መንግስት እንደሚለው “የገባበት ጠፋ” ሲባሉ እነሱ “ገንዘቡን ሰይጣኑ በላው” ይላሉ፡፡

እከሌ የተባለው የመንግስት ባለስልጣን፣ የጦር ጀኔራል ወይም ደግሞ የቤተመንግስቱን የሚስጥር መግቢያና መውጪያ የሚያውቅ ፖለቲከኛ፤ ይህን ያህል መቶ ሚሊዮን ዶላር የህዝብ ሀብት ዘረፈ ሲባሉ ደግሞ የተጠቀሰው ግለሰብ የ”ሰይጣኑ ወዳጅ ነው” ወይም ከሰይጣኑ ጋር ተግባብተው ይሠራሉ ይላሉ፡፡

“እንዲያው ለመሆኑ ይህን የሀገራችሁን ገንዘብ፣ በዚህን ያህል መጠን እያነከተ፣ እናንተን በድህነት እንድትማቅቁ ያደረጋችሁን የዚህን ሰይጣን መጋቢያ አድራሻ ታውቁታላችሁ?” ተብለው ሲጠየቁ ደግሞ ሁሉም በአንድነት “አዎ” ይሉና እጆቻቸውን ወደ ሁለት ህንፃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ወደ ሀገሪቱ ፕሬዚዳንትና የክልል ገዥዎች ቤተመንግስትና ወደ ሀገሪቱ ፓርላማ ህንፃ፡፡ እነዚህን ህንፃዎች እያመለከቱ “ሰይጣኑ ያለው እዚህ ውስጥ ነው” ይላሉ፡፡

ናይጀሪያውያን ከዚህ በኋላ የሚቀርብላቸውን ጥያቄ ባይፈልጉትም ምን አይነት ጥያቄ እንደሆነ ግን ያውቁታል፡፡ “ሰይጣኑን ብትችሉ ገድላችሁ ካልሆነም ካጠገባችሁ ራቅ እንዲል የእለት ምሱን በመከልከል የማታባርሩት ለምንድን ነው?” የሚለውን ጥያቄ ጨርሶ አይወዱትም፡፡ ለዚህ አንደኛው ምክንያት እንደ ደካማና አቅመቢስ አድርጐ ስለማያስቆጥራቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ እርግጥ ነው፡፡ ሰይጣኑን ለመግደል አሊያም ለማባረር የሚበቃ ሀይል እስካሁን ማግኘት አልቻሉም፡፡ “ከፕሬዚዳንቱ፣ ከፓርላማውና ከጦር ሀይሉ አንስቶ እስከ ዝቅተኛ የአካባቢ ባህላዊ የህብረተሰብ መሪዎችና ተራ ህግ አስከባሪ ፖሊሶች ድረስ የተጠላለፈ መረብና ከለላ ስላለው፣ ሰይጣኑን በቀላሉ ለመግደል ወይም ከወጣበት ጠርሙስ ውስጥ እንደገና አስገብቶ ለማሸግና ወደ ጥልቁ ባህር ለመጣል እንዳንችል አድርጐናል” ይላሉ፤ በከፍተኛ ብስጭትና ተስፋ መቁረጥ፡፡

ናይጀሪያውያን በሙስና ሰበብ የገጠማቸው ፈተናና ሙስናንም ለማስወገድ የሚያስችል ብልሃትና ጉልበት ማጣታቸው የፈጠረባቸው የአቅመ ቢስነት ስሜት፣ እስከ ወዲያኛው ተላቀቀኝ ቢሉት ለማይላቀቃቸው ሌላ ከፍተኛ ችግር አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፡፡

ናይጀሪያውያን አሁን አንድ ነገር የተሻለ ነው ብለው ወስነዋል፡፡ ግንባር ቀደሙን ጠላታቸውን ሙስናን ለመዋጋት የሚያስችል አቅም ለመገንባት አልቻሉም፡፡ መንግስታቸውም ሙስናን የሚዋጋው በአፉ እንጂ በተግባር የሰይጣኑ ዋነኛ ወዳጅ ሆኖባቸዋል፡፡ ስለዚህ ሰይጣኑ ለወዳጆቹ ከሚያበረክተው በረከት በመቋደስ፣ ከድህነት ለመላቀቅ፣ ከሙስና ወይም ከሰይጣኑ ጋር ወዳጅነት ለመመስረትና ተስማምተው ለመኖር ቁርጥ ሀሳብ አድርገዋል፡፡

ለናይጀሪያ ይህ አይነቱ የህዝቡ ውሳኔ ራስን በራስ እንደማጥፋት ያለ ውሳኔ ተደርጐ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ለምን ቢባል? የሚያስከትለው ጠንቅ ክብደቱና ጥልቀቱ ዲካ የሌለውና የዝንተ አለም ስለሆነ ነው፡፡

በናይጀሪያ ስለተንሰራፋው ሙስና ለማስረዳት የሚሞክር ማንም ሰው ቢሆን፣ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ሳይጠቅስ ማለፉ ጨርሶ አይቻለውም፡፡ በናይጀሪያ በመቶዎች ከሚቆጠር ሚሊዮን ዶላሮች በታች በመዝረፍ እንዲሁ የሚልከሰከስና ስሙን በዝርፊያ የሚያስነሳ ባለስልጣን ወይም ከባለስልጣን ጋር አሪፍ ንክኪ ያለው ፖለቲከኛ ፈልጐ ማግኘት ከንቱ ልፋት ነው፡፡ እዚህ ግባ የማይሉት ወይም ደግሞ ጨርሶ የማይገምቱትና የማይጠረጥሩት አንድ አሳቻ ሰው፣ ከስሙኒ ቅፈላ ድንገት በብርሃን ፍጥነት፣ የበርካታ መቶ ሚሊዮን ዶላር ባለሀብት ሆኖ ይገኛል፡፡ ማናችንም ቢሆን በቀላሉና በግልጽ እንደምንረዳው ሃብትን በተመለከተ ተፈጥሮ ለናይጀሪያ አዳልታላታለች፡፡ ከርሰ ምድሯ በውስጡ የያዘው የነዳጅ ዘይት ሀብት፣ በአፍሪካም ሆነ በአለም ደረጃ ግንባር ቀደም ከሆኑ የነዳጅ ዘይት አምራች ሀገራት ጐራ እንድትቀላቀል አድርጓታል፡፡ ከዚህ ሀብትም በቀን አንድ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እየሸጠች በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ ታገኛለች፡፡ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የናይጀሪያን የመንግስት ታሪክ ያጠና ሰው መረዳት የሚችለው አንድ እውነት አለ፡፡ በናይጀሪያ ከህዝባዊ ምርጫ ይልቅ የመንግስት ስልጣንን ለመያዝ ቀላሉ ዘዴ፣ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ ነው፡፡ ናይጀሪያን ከገዙት መሪዎች ውስጥ በህዝባዊ ምርጫ ወደ ስልጣን ከመጡት መሪዎች ይልቅ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የመጡትን መቁጠር ይቀላል፡፡ በዚህ የተነሳ አንድ የናይጀሪያ ወታደራዊ መኮንን የጀኔራልነት ሹመት ሲሰጠው፣ ተሿሚው እንኳን ደስ ያለህ የሚባለው ለጀኔራልነቱ ብቻ ሳይሆን አንድ ቀን ፕሬዚዳንት ሊሆን የሚችልበትን ሰፊ እድል በማሰብም ጭምር ነው፡፡ በርካታ ወታደራዊ ጀኔራሎች በመፈንቅለ መንግስት በናይጀሪያ የመሪነት መንበር ላይ በከፍተኛ ፍጥነት የተፈራረቁበት ምስጢርም ይሄው ነው፡፡

ጀኔራል መሪዎችን የለመደው የናይጀሪያ አንጋፋ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ፣ በህዝባዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡትን ሟቹን ፕሬዚዳንት ኦማሩ ያርአድዋን በለመደበት «አፉ ጀኔራል ያርአዱዋ» እያለ ሲቪሉን ፕሬዚዳንት እስከ ብዙ ጊዜ ድረስ ይጠራቸው የነበረውም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡

ያለፉ የናይጀሪያ መሪዎች ለህዝባቸው ፍላጐትና ምርጫ ቅንጣት ቁብ ሳይኖራቸው፣ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን መያዛቸው ሳያንስ፣ ትልቁ እዳቸው በሀገራቸው ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው ዘራፊዎች መሆናቸው ነው፡፡

ለምሳሌ ከህንድና ከስሪላንካ ካስመጡዋቸው ሴተኛ አዳሪዎች ጋር ቪያግራ ውጠው ሲዳሩ ልባቸው ቆሞ ሞቱ፣ እየተባሉ ዛሬም ድረስ ስማቸው በክፉ የሚነሳው የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት፤ በስልጣን በቆዩበት የአራት አመት ከስምንት ወር ጊዜ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የናይጀሪያን ሀብት ዘርፈዋል፡፡ ከሳቸው ቀደም ባለው ጊዜ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጀነራል ሙሃመድ ቡሀሪ፣ ዛሬም ድረስ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩት በግል ጀታቸው ነው፡፡

የህዝብ ገንዘብን በሚመለከት አለምን ሁሉ ጉድ የሚያስብል ዜና መስማት በናይጀሪያ ጨርሶ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ባለፈው አመት መጨረሻ አካባቢ፣ በቀን አንድ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የሚሸጠው የናይጀሪያ መንግስታዊ የነዳጅ ኩባንያ፤ ከፍተኛ ኪሳራ ስላጋጠመኝ፣ በካዝናዬ ውስጥ ቤሳ ቤስቲን የለኝም ብሎ፣ ለናይጀሪያ ፓርላማ በማስታወቁ የሴኔቱንና የምክር ቤቱን አባሎች ልብ በድንጋጤ ሊያስቆመው ነበር፡፡

ሰዎቹ በዚህ ዜና ክፉኛ ቢደነግጡ አይፈረድባቸውም፡፡ ለምን ቢባል? በነፍስ ወከፍ እስከ 19 ሺ ዶላር የሚገመት ወርሃዊ ደመወዝና አበል የሚያገኙት፣ የቢሮና የቤት ሠራተኞቻቸው ደመወዝ የሚከፈለው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከተራ ፖለቲከኛነት በብርሃን ፍጥነት ወደናጠጠ ሚሊዬነር ከበርቴነት የሚለወጡበት ዋነኛው የሀብት ምንጭ፣ ይሄው የነዳጅ ሀብት ሽያጭ ገቢ በመሆኑ ነው፡፡

የጦር ሀይል ከፍተኛ መኮንን መሆንና ፖለቲከኛነት በተለያዩ ሀገራት ወደ ሀብት ለሚደረግ ጉዞ ዋነኛ አቋራጭ መንገድ ነው፡፡ በናይጀሪያ ግን የአቋራጮች ሁሉ አቋራጭ መንገድ ነው፡፡ በናይጀሪያ የጦር ሃይሉ ከፍተኛ መኮንን መሆን ወይ በመፈንቅለ መንግስት (ያለፉት ጀኔራሎች እንዳደረጉት) የመንግስቱን አመራር ለመያዝ፣ በሲቪል አስተዳደርም ሆነ ስልጣኑ ከሚሽከረከርበት ክበብ ውስጥ በመሆን የብሔራዊ ባንኩን እናት ቁልፍ “Master Key” ከሚይዙት ጥቂት የመንግስቱ ባለስልጣኖች አንዱ እንዲሆኑ እድል ስለሚሰጥ ነው፡፡

ዛሬ ዛሬ ይህኛው መንገድ በናይጀሪያ ዋነኛው አቋራጭ መንገድ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ጮሌና ብዙ ደጀንና የግንኙነት አውታር ያለው ፖለቲከኛ በመሆን ፕሬዚዳንት አሊያም ምክትል ፕሬዚዳንት መሆን ይቻላል፡፡ ይህን መሆን ካስቸገረ ደግሞ ሴናተርና የታችኛው የፓርላማ ምክር ቤት አባል መሆን ይቻላል፡፡ ይህ የማይቻል ከሆነ የያዙትን ይዞ፣ ከእነዚህ ከሁለቱ ወደ አንዱ ቀረብ ማለት ከናይጀሪያ የሀብት መንደር በቀላሉ ያደርሳል፡፡

ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለውን ሁኔታ የሚገልፁበት አንድ አሪፍ አባባል አላቸው:- “ትንሽ ቆሎ ይዘህ ወደ አሻሮ ተጠጋ” ይላሉ፡፡ የናንተን ትንሽ ቆሎ አሳይታችሁ የተጠጋችሁትን ብዙ አሻሮ የቻላችሁትን ያህል እያፈሳችሁ ብትበሉ፣ በላችሁ የምትባሉት የዘረፋችሁትን አሻሮ ሳይሆን ይዛችሁት የተጠጋችሁትን ትንሽዬ ቆሎ ነው ለማለት ነው፤ ነገርዬው ሲብራራ፡፡

ልክ እንደዚሁ ሁሉ የያዟትን ይዘው የናይጀሪያን የፖለቲካ መዘውር ወደሚዘውሩት ጥቂት ምርጦች ጐራ ጠጋ ማለት፣ የፖለቲካ የኢኮኖሚም ሆነ የማህበራዊ ስብዕናው ምንም ይሁን ምን ካሰቡትና ከገመቱት ሁኔታና ፍጥነት ውጪ የባለ ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር ሀብት ጌታ  ሊያደርግ ይችላል፡፡

በናይጀሪያ የፖለቲካ ምህዳር ዋናው ወሳኝ ጉዳይ በእድልም ይሁን በጥረት ወይም በሆነ ተአምር፣ ከዚያ የጥቂት ምርጦች ጐራ አባል መሆን አሊያም ከጐራው ጠጋ ማለት እንጂ የግል ስብዕናና ስነምግባር ጉዳይ እዳው ገብስ ነው፡፡ እንዲህ የሚባለው ለጨዋታ ያህል ወይም በግምትና በሃሜት እንዳይመስላችሁ፡፡ በርካታ አጋጣሚዎችን ለአብነት እየጠቀሱ የጉዳዩን እውነትነት ማስረዳት ከሁሉም የቀለለ ተግባር ነው፡፡

ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት በአንድ የናይጀሪያ ፖለቲከኛ ተፈጽሞ የተገኘውን አስገራሚ ድርጊት ማንሳት ይቻላል፡፡ ናይጀሪያዊው የፖለቲካ ተዋናይ ጀምስ ኢቦሪ፤ የዚህ አስገራሚ ድርጊት ባለቤትና ዋነኛ ተዋናይ ናቸው፡፡ እኒህ ፖለቲከኛ የናይጀሪያ የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ያመለጣቸው “እንደተመኘሁዋት አገኘሁዋት” የሚለውን የድል መዝሙር ሊዘምሩ አቆብቁበው ሳለ ነበር፡፡

ጮሌ ፖለቲከኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጀምስ ኢቦሪ በግል ስብዕናቸው ምን አይነት ሰው ነበሩ መሰላችሁ? ከሀገራቸው አልፈው የእንግሊዝን ፖሊስ ሳይቀር በተደጋጋሚ ያስቸገሩ ተራ ኪስ አውላቂና ከሱቅ መንታፊ ሌባ ነበሩ፡፡ በፖለቲከኛነታቸው ግን የናይጀሪያ ነዳጅ ዘይት አምራች ክልል ገዥና ቀደም ብሎ እንደተገለፀው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ለመሆን በአንድ ወቅት ተቃርበው የነበሩ ሰው ናቸው፡፡

የጀምስ ኢቦሪ ታሪክ የናይጀሪያን ፖለቲከኞች እንቅስቃሴና “ትንሽ ቆሎ ይዘህ ወደ አሻሮ ተጠጋ” ተብሎ የተነገረውን ሀገርኛ አባባል በግልጽ የሚያሳይ ታሪክ ነው፡፡ ጉዳዩ ከዚህ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

በ1990ዎቹ ጀምስ ኢቦሪ ይኖሩ የነበረው በእንግሊዝ በስደት ነበር፡፡ በ1991 ዓ.ም በአመት አስራ አምስት ሺ ፓውንድ ወይም በወር ሁለት ሺ ዶላር ደመወዝ እየተከፈላቸው፣ ከለንደን ዳርቻ በምትገኘው የሂስደን ቀበሌ ውስጥ በሚገኝ የኮምፒውተር ቁሳቁስ መሸጫ መደብር ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር፡፡ በዚህ መደብር ውስጥ ይሠሩ በነበረበት ጊዜ ታዲያ በየጊዜው በሚጠፉ የመደብሩ ቁሳቁስ ስርቆት እጃቸው ይጠረጠር ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ግን ቀን ጣላቸው፡፡ እርሳቸው በሚቆጣጠሩት የመደብሩ ክፍል ባለቤታቸውን የተለያዩ ቁሳቁሶች በዘንቢል አጭቃና ምንም ክፍያ ሳትከፍል እንድትወጣ ሲያደርጉ፣ በአንድ ባልደረባቸው እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው፣ ከባለቤታቸው ጋር በአይስል ውድ የዘውድ ፍርድ ቤት ቀርበው ሌብነታቸው በመረጋገጡ የገንዘብ ቅጣት ተጣለባቸው፡፡

በቀጣዩ አመት በ1992 ደግሞ የተሠረቀ የዱቤ ካርድ በመያዝና በዚህ ካርድ አማካኝነትም አንድ ሺ ፓውንድ በመጠቀማቸው፣ በወንጀል ተከሠው ፍርድ ቤት ቀረቡና ተገቢ ቅጣታቸውን አገኙ፡፡

ከአመት ቆይታ በኋላ ግን ጀምስ ኢቦሪ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡ የእንግሊዝ የስደት ኑሮአቸውን በመተው ወደ ሀገራቸው ናይጀሪያ ተመልሰው፣ በፖለቲካው መድረክ ለመሳተፍ ጓዛቸውን ጠቅልለው ለንደንን ለቀቁ፡፡ እርሳቸው በተመለሱበት ወቅት ናይጀሪያ መልካም ጊዜ አጋጥሟታል የምትባልበት ጊዜ ነበር፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን ይዘው ናይጀሪያን ይመሩ የነበሩት ጀኔራል ኢብራሂም ባባንጊዳ፤ በ1993 ዓ.ም ስልጣናቸውን በህዝብ ለተመረጠ መሪ ለማስረከብና ናይጀሪያን ወደ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር በመወሠናቸው ነበር፡፡

ጀምስ ኢቦሪ ከለንደን እንደተመለሱ በቀጥታ ወደ ፖለቲካው መድረክ አልገቡም፡፡ ይልቁንስ ለክልል ገዥነት የሚወዳደሩትን የጓደኛቸውን የምርጫ ቅስቀሳና ዘመቻ ማገዝ ጀመሩ፡፡ይህ አጋጣሚ በምርጫው ይወዳደሩ በነበሩና በኋላም ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የተባለውንና ገዥውን የህብረት ፓርቲ የመሠረቱት ፓርቲዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነትና እውቂያ እንዲመሠርቱ ከፍ ያለ እድል ሠጣቸው፡፡ ነገር ግን ጀኔራል ባባንጊዳ ቃል የገቡትን ህዝባዊ ምርጫ ድንገት በመሠረዛቸው፣ ጓደኛቸው በነበሩት ጀኔራል ሳኒ አባቻ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው ተወገዱ፡፡ አዲሱ የናይጀሪያ ወታደራዊ መሪ ጀኔራል ሳኒ አባቻ፣ ህዝባዊ ምርጫ የማካሄድ ፍላጐትም ሆነ እቅድ እንደሌላቸው በግልጽ በማሳወቅ፣ ስልጣናቸውን ማጠናከርና የሀገር ሀብት በከፍተኛ መጠን መዝረፋቸውን ቀጠሉበት፡፡

ጀምስ ኢቦሪ የቀድሞ የፖለቲካ ወዳጆቻቸውን በመተው፣ ለጀኔራል ሳኒ አባቻ ለማደር የወሠኑትም በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ጀነራል ሳኒ አባቻም አላሳፈሯቸውም፡፡ ጀምስ ኢቦሪ የያዙዋትን ትንሽዬ ቆሎ ይዘው፣ ወደ አሻሮው እንዲጠጉ ፈቀዱላቸው፡፡ በ1998 ዓ.ም ግን ተቃዋሚዎቻቸውን ሁሉ በስቅላት በመቅጣትና በብረት ክንዳቸው አንቀጥቅጠው በመግዛት የታወቁት አምባገነኑ ጀኔራል ሳኒ አባቻ፣ ድንገት ስልጣናቸውን ከነአካበቱት በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ጋር ትተው ይህችን አለም በሞተ ተሠናበቱ፡፡

ጌታቸውን በሞት ያጡት ጀምስ ኢቦሪ፤ እጃቸውን አጣጥፈው እንዲሁ መቀመጥ አልፈለጉም፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንት ለሆኑትና የሠሜን ናይጀሪያ ታዋቂ ፖለቲከኛ ለነበሩት አቲኩ አቡበከር ፈረስ ቀይረው በመግባት፣ ደከመኝ ሠለቸኝ ሳይሉ በታማኝነት ማገልገል ጀመሩ፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቲኩ አቡከርም የአሽከራቸውን የጀምስ ኢቦሪን ውለታ እንዲሁ በዝምታ አላለፉትም፡፡ በ1999 በተደረገው ምርጫ፣ በነዳጅ ዘይት ሀብቱ የታወቀው የዴልታ ክልል ገዥ ሆነው እንዲመረጡ በእጅጉ አገዟቸው፡፡

ከዚህ በሁዋላ ያለው የጀምስ ኢቦሪ ጉዳይ ታሪክ ነው፡፡ የናይጀሪያን የፖለቲካና የመንግስት አመራር መዘውር ለሚያሽከረክሩት ጥቂት ምርጦች አገልጋይ በመሆን ከዚህ የጥቂት ምርጦች ጐራ ዘንድ ጠንካራ ግንኙነት መመስረት ቻሉ፡፡ ይህ ግንኙነትም በአቋራጩ የሀብት ጐዳና እንዲጓዙ አደረጋቸው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ከተራ ስደተኛና አማተር ፖለቲከኛነት ወደ ናይጀሪያ ታዋቂ የፖለቲካ ተዋናይነት ተሸጋገሩ፡፡

በዚህ ጊዜ ለጀምስ ኢቦሪ ሁሉ በጄ ሁሉ በደጄ ሆኖላቸው ነበር፡፡ እሳቸው ግን “አሁን የያዝኩት በቃኝ” ብለው መቀመጥን አልፈለጉም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ወዳጅነታቸውንና ታዛዥነታቸውን ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ከአቲኩ አቡበከር ይልቅ የበለጠ በልቶ ያበላኛል ወዳሉት ወደ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን አባሳንጆ አዞሩ፡፡

የጀምስ ኢቦሪ የፈረስ ቅየራ ሌላ ሳይሆን የተለመደው ጭብጥ የማይሞላ ቆሎአቸውን ይዘው ወደ አሻሮው የመጠጋት ብልሃታቸው አካል ነበር፡፡ ለምን ቢባል? ያኔ ፕሬዚዳንት አባሳንጆ ለሶስተኛ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት መወዳደር እንዲችሉ፣ የሀገሪቱን ህገመንግስት ለመደለዝ ላይ ታች ደፋ ቀና ይሉ ስለነበር ነው፡፡

ይህ የአባሳንጆ ህገ መንግስት የመደለዝ ጥረት እንደከሸፈ፣ ጀምስ ኢቦሪ የደቂቃ እድሜ እንኳ ሳያጠፉ አባሳንጆ በግል ለፕሬዚዳንትነት ውድድር ለመረጧቸው ለኦማሩ ያርአድዋ ህብረትና ወዳጅነታቸውን አረጋግጠው ገቡላቸው፡፡ በ2006 ዓ.ም የህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲው ከምርጫ በፊት ባካሄደው ጉባኤ ላይ ኦማሩ ያርአድዋን ፕሬዚዳንታዊ እጩ ተወዳዳሪው አድርጐ ሲመርጣቸው፣ የቀኝ እጃቸውን ይዘው በአሸናፊነት ስሜት ከፍ በማድረግ፣ ለጉባኤተኛው ያሳዩት አዲሱ ባለሟላቸው ጀምስ ኢቦሪ ነበሩ፡፡ ሰውየው በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ የኦማሩ ያርአድዋን የምርጫ ቅስቀሳ በገንዘብ መደገፍ ጀመሩ፡፡ ጀምስ ኢቦሪ ይህን ያደረጉት እንዲሁ ሳይሆን ኦማሩ ያርአድዋ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ቦታውን እንደሚሠጧቸው ቃል ገብተውላቸው ስለነበር ነው፡፡

በመጨረሻ ግን ጀምስ ኢቦሪም ሆኑ ሌሎች ፖለቲከኞች ያልገመቱትን ነገር ኦማሩ ያርአድዋ ፈፀሙ፡፡ የምክትል ፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ቃል እንደገቡት ለጀምስ ኢቦሪ ሳይሆን ለጉድላክ ጆናታን ሠጡ፡፡

ኦማሩ ያርአድዋ ይህን እንዲያደርጉ የገፋፋቸው ምክንያት የጀምስ ኢቦሪ በሌብነት የጐደፈ ስነ ምግባር ሳይሆን በበርካታ የዝርፊያና የሌብነት ክሶች፣ ተከሠው ለእስር የመፈለጋቸው ጉዳይ ነበር፡፡ “ሙት ይዞ ይሞታል” እያለ ያገሬ ሠው እንደሚተርተው፣ የጀምስ ኢቦሪ አሳፋሪ ተግባር ይዟቸው እንዳይሞት የሠጉት ኦማሩ ያርአድዋ፤ ምክትላቸው አድርገው ከመሾም ተቆጠቡ፡፡

ይህ የኦማር ያርአድዋ ውሳኔ ለጀምስ ኢቦሪ መሸከም ከሚችሉት በላይ ነበር፡፡ ጀምስ ኢቦሪ ያኔ አረጋግጠውትና ብዙ እቅድ ሲያወጡለት የነበረው ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ሳይሆን ፕሬዚዳንት ለመሆን ነበር፡፡ ይህን ማሠብ ብቻ ሳይሆን እርግጠኛ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ጉዳይ ደግሞ የፕሬዚዳንት ኦማሩ ያርአድዋን ዝርዝር የጤንነት ሁኔታ ምስጢር ጥንቅቅ አድርገው በማወቃቸው ነበር፡፡ ያኔ በእርግጥም ፕሬዚዳንት ያርአድዋ በጤንነታቸው በኩል ልጣቸው የተራሰ፣ መቃብራቸው የተማሰ ሠው ነበሩ፡፡ ከእርሳቸው ከሀኪሞቻቸውና እጅግ ቅርብ ከሆኑ ሠዎቻቸው ውጪ በከፍተኛ ሚስጢር ተይዞ የነበረው በሽታቸውም ለረጅም ጊዜ ካሠቃያቸው በሁዋላ፣ የመጀመሪያውን ዙር የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን እንኳ ሳያስጨርሳቸው በሞት ይዟቸው ነጐደ፡፡ የናይጀሪያ ህገመንግስት እንደሚያዘው፣ እርሳቸውን በመተካት ምክትላቸው የነበሩት ጉድላክ ጆናታን በፕሬዚዳንትነት መንበሩ ላይ ተቀመጡ፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው፣ እርግጠኛ የነበሩበት ስልጣን ከእጃቸው ላይ ማፈትለኩ ያንገበገባቸው ሳያንስ፣ ከየአቅጣጫው የተሠነዘረባቸው የዝርፊያና የሌብነት ክስ መቆሚያና መቀመጫ ነሳቸው፡፡

የአሜሪካው የፌደራል የምርመራ ቢሮ (FBI)፤ ጀምስ ኢቦሪ፣ በተለያዩ የአሜሪካ ባንኮች ከናይጀሪያ እያሸሹ ስላስቀመጡት በብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ጉዳይ ለማጣራት፣ ለጥያቄ እፈልግዎታለሁ በሚል የተማርማሪነት ቀላጤ አወጣባቸው፡፡

የእንግሊዝ የዘውድ ፍርድ ቤትም ቀድሞ በስደት ሳሉ ይኖሩበት በነበረው የለንደን ዳርቻ ሀምፕስቴድ ቀበሌ ውስጥ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ፓውንድ ቀጥታ ካሽ በመክፈል ስለገዙት የመኖሪያ ቤት፣ ለንደን በሚገኝ የህግ አማካሪያቸው በኩል ስለ ገዙት የግል ጀት አውሮፕላንና በለንደን አቤይ ጐዳና ላይ ሠፊ የከተማ ቦታና አፓርትመንቶችን በጨረታ እንዴት እንደገዙት ማጣራት ስለምፈልግ፣ እጃቸው ተይዞ ይቅረብልኝ የሚል የእስር ማዘዣ አወጣባቸው፡፡

የእንግሊዝ የዘውድ ፍርድ ቤት፣ በጀምስ ኢቦሪ ላይ ይህን የማዘዣ ጦማር እንዲያወጣባቸው የገፋፉት ሁለት ነገሮች ነበሩ፡፡ አንደኛው ከዚህ በፊት በገንዘብ ሌብነት ሁለት ጊዜ የመከሠሳቸው ሪከርድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትን ንብረቶች ለመግዛት የሠጡት ሀሠተኛ መረጃ ነው፡፡ ጀምስ ኢቦሪ ከዚህ ቀደም በወንጀል ተከሠው መቀጣታቸውን ለመሸፈን በማሠብ ከሠጡት የሀሠት መረጃ ውስጥ፣ የትውልድ ቀናቸውን የሚመለከተው በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በእሳቸውና በተከታይ እህታቸው መካከል ያለው ብቻ ነበር፡፡

በዚህ ሁሉ መሀል ደግሞ የአሜሪካው የፌደራል የምርመራ ቢሮ፣ ጀምስ ኢቦሪ ከ1999 እስከ 2001 ባሉት የሶስት አመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ፣ በሌሎች ባንኮች ካስቀመጡት በርካታ መቶ ሚሊዮን ዶላሮች በተጨማሪ ሁለት መቶ ሀምሳ ሚሊዮን ዶላር ከናይጀሪያ አሽሽተው፣ በአንድ የአሜሪካ ባንክ ብቻ ማስመቀጣቸውን ይፋ አደረገ፡፡ እነዚህ አመታት ደግሞ ጀምስ ኢቦሪ፣ የናይጀሪያ የዴልታ ክልል ገዥ ሆነው ያገለግሉ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡

የጀምስ ኢቦሪን ፋይል ከፍቶ ጉዳዩን ሲያጣራና ሲከታተል የነበረው የእንግሊዝ መንግስትም፣ በእንግሊዝ ባንኮች ውስጥ ያስቀመጡትን ሠላሳ አምስት ሚሊዮን ዶላርና ሌሎች በሚሊዮን ፓውንድ የሚገመቱ የተለያዩ ንብረቶቻቸውን እንዳይንቀሳቀስ ማገዱን በ2007 ዓ.ም አስታወቀ፡፡ የጀምስ ኢቦሪን ይህን ሁሉ ጉድ የሠማው የፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን መንግስትም፣ ሠውየው የዴልታ ግዛት ገዥ ሆነው በሠሩበት ጊዜ ውስጥ፣ ከክልሉ በጀት ሶስት መቶ ሀምሳ ሚሊዮን ዶላር የሚሆነውን ገንዘብ ዘርፈዋል በማለት የእስር ማዘዣ አወጣባቸው፡፡

የወጣባቸውን የእስር ማዘዣ በመያዝ በቁጥጥር ስር ሊያውላቸው በሄደው የፖሊስ ቡድን ላይ፣ የጀምስ ኢቦሪ ደጋፊዎች ጥቃት ስለከፈቱባቸው፣ አጋጣሚውን ተጠቅመው ጀምስ ኢቦሪ ወደ ዱባይ መኮብለል ቻሉ፡፡

ጀምስ ኢቦሪ ከናይጀሪያ አምልጠው ዱባይ ቢገቡም የፈሩትን እስር ሊያመልጡት አልቻሉም፡፡ የዱባይ ፖሊስ ያለ አንዳች ግርግር በቁጥጥር ስር አውሎና እጃቸውን በካቴና ጠፍሮ፣ ለእንግሊዝ ፖሊስ አሳልፎ ሠጣቸው፡፡ እዚያ በተከሠሱበት ከፍተኛ ሀብት የማሸሽና በህገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ ማድረግ /Money laundering/ ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ቅጣታቸውን በእስር ላይ ሆነው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

እንግዲህ ከዚህ በላይ የቀረበውን የጀምስ ኢቦራን አስገራሚ የሌብነትና የዝርፊያ ታሪክ ስናስብ፣ በአዕምሯችን የሚጉላላው ጥያቄ፣ የአንድ ክልል ገዥ ሆነው ባገለገሉበት አጭር ጊዜ ውስጥ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ የናይጀሪያን ሀብት መዝረፍ ከቻሉ፣ ሊጨብጡት በእጅጉ ተቃርበው የነበረውን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ይዘውት ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ገንዘብ ሊዘርፉ ይችሉ ነበር የሚለው ነው፡፡

እኒህ ሠው እዚህ እኛ ሀገር ቢኖሩ ኖሮ፣ “ትጉህ መንግስታዊ ሙሰኛ” የሚል ሰሞነኛ ስም እናወጣላቸው ነበር፡፡

በስተመጨረሻ ግን “ብልህ ሠው ከጐረቤቶቹ ይማራል” ተብሎ በቅዱስ መጽሀፉ የተጠቀሰውን አሪፍ መልእክት ልብ እንድንለው ማሳሰብ ተገቢ ይመስኛል፡፡

 

 

Read 1854 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 12:10