Monday, 05 December 2016 09:20

የፊደል ካስትሮ አስገራሚ እውነታዎች!!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ኮሙኒስቱ አብዮተኛ ፊደል ካስትሮ ኩባን ለአምስት አሰርት ዓመታት የገዙ አምባገነን  መሪ ሲሆኑ ከታላቋ ብሪቴይን ንግስት ኤልዛቤትና ከታይላንዱ ንጉስ ቀጥሎ ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ የቆዩ የዓለማችን ሦስተኛው መሪ ነበሩ፡፡ በከፍተኛ ህመም አስገዳጅነት የዛሬ 10 ዓመት ሥልጣናቸውን ለወንድማቸው ያስረከቡት ካስትሮ፤ ባለፈው አርብ በ90 ዓመታቸው ማለፋቸው ይታወቃል፡፡  
ከ40 ዓመት በላይ የግድያ ሙከራዎች፣ ወረራና የኢኮኖሚ ማዕቀብ የተደረገባቸው ፊደል ካስትሮ፤ ከስልጣን መንበራቸው ንቅንቅ ሳይሉ ዘጠኝ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ተፈራርቀዋል - ከአይዘንአወር እስከ ክሊንተን፡፡
ፊደል ካስትሮ በዓለም ረዥሙን ንግግር በማድረግ ክብረወሰን ይዘዋል፡፡ እ.ኤ.አ ሴፕተምበር 26 ቀን 1960 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለ4 ሰዓት ከ29 ደቂቃ ንግግር አደርገዋል። በዚህም ረዥም ንግግራቸው የዓለም ድንቃ ድንቅ ክስተቶችን  በሚመዘግበው “ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ” ስማቸው ሰፍሯል፡፡ በእርግጥ ካስትሮ በአገራቸው ኩባ ከዚህም የላቀ ክብረወሰን አላቸው፡፡ በ1986 ዓ.ም በሃቫና ሦስተኛው የኮሙኒስት ፓርቲ ኮንግረስ ሲካሄድ ለ7 ሰዓታት ከ10 ደቂቃዎች ያህል ንግግር አድርገዋል፡፡  
ፊደል ካስትሮ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት የጀመሩት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነበር ማለት ይቻላል። የ12 ዓመቱ ታዳጊ ካስትሮ በወቅቱ ለሁለተኛ ጊዜ ለተመረጡት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት በፃፈው ደብዳቤ፤በድጋሚ በመመረጣቸው ደስታውን ገልጾ፣የ10 ዶላር ኖት እንዲልኩለት ጠይቆ ነበር - ‹‹የ10 ዶላር ኖት ከዚህ ቀደም አይቼ አላውቅም›› በማለት፡፡
ደቡብ አፍሪካ ከዘረኛው የአፓርታይድ አገዛዝ ለመላቀቅ ያደረገችውን የነፃነት ትግል በአጋርነት የደገፉት ፊደል ካስትሮ፣ከኔልሰን ማንዴላ ጋር አንድ መፅሃፍ በትብብር ጽፈዋል፡፡  ርዕሱም፡- ‹‹HOW FAR WE SLAVES HAVE COME!›› ይሰኛል፡፡
ካስትሮ ከብዙዎቹ አምባገነን መንግስታት በተለየ በኩባ በስማቸው የተሰየሙ መንገዶች፣ ህንፃዎች ወይም ሰፈሮች የሉም፡፡ ይሄን ያደረጉትም አምልኮተ-ሰብዕ ለመፍጠር ባለመፈለጋቸው ነው ይባላል። ህልፈታቸውን ተከትሎ በኩባ ለ9 ቀናት ብሄራዊ ሀዘን የታወጀላቸው ካስትሮ፤ አሁን ከሞታቸው በኋላ መንገድ ወይም አደባባይ በስማቸው ሊሰየምላቸው እንደሚችል ተነግሯል።  
ከሀብታም ቤተሰብ እንደተወለዱ የሚነገርላቸው ካስትሮ፤ በስልጣን ላይ ሳሉ እዚህ ግባ በማይባል ዝቅተኛ ደሞዝ እንደሚተዳደሩ በመግለጽ በድህነት የሚማቅቅ ህዝባቸውን ሲያሞኙ ኖረዋል፡፡ እውነታው ግን ከድህነት ጋር የማይተዋወቁ፣ የቅንጦት ህይወት ያጣጣሙ ሚሊየነር መሆናቸው ነው፡፡ ሁነኛ የመረጃ ምንጮች እንደሚጠቁሙት፤ ጠቅላላ የሃብታቸው መጠን 900 ሚ.ዶላር ነው፡፡ በዚህም ሃብታቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችን እነ ቢል ክሊንተን፣ ባራክ ኦባማና ጆርጅ ቡሽን ይበልጣሉ፡፡
የኩባ የስለላና ደህንነት ቢሮ እንደሚለው፤ ፊደል ካስትሮ በስልጣን ዘመናቸው ከ600 በላይ የግድያ ሙከራ በአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ቢደረግባቸውም ከሞት  ተርፈው ለግማሽ ክ/ዘመን ገደማ ኮሙኒስት አገራቸውን ገዝተዋል። ካስትሮ ከሞት ጋር ድብብቆሽ መጫወት የጀመሩት ገና በወጣትነት የአብዮተኝነት ዘመናቸው ሲሆን በወቅቱ ሁለት ጊዜ ሞተዋል ተብሎ በኩባ ፕሬሶች ተዘግቦ ነበር። “ከግድያ ሙከራ መትረፍ የኦሎምፒክ ውድድር ቢሆን ኖሮ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ እሆን ነበር” በሚለው ዝነኛ ንግግራቸው የሚታወቁት ካስትሮ፤የማታ ማታ በሰው እጅ ሳይሆን በተፈጥሮ እርጅና ህይወታቸው አልፏል። ሲአይኤ የኩባን ፕሬዚዳንት ለመግደል ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም ይላሉ - መረጃዎች፡፡ እንደ ነፍሳቸው የሚወዱትን ሲጋር ከመመረዝ እስከ በአልሞ ተኳሽ ማስገደል እንዲሁም በሚወዱት የቸኮሌት ሚልክሼክ ውስጥ የተመረዘ ክኒን ከመጨመር እስከ ጫማቸውን በመርዘኛ ኬሚካል መበከል ድረስ... እና ሌሎችም የግድያ ሙከራዎች ቢደረግባቸውም አንዱም ለውጤት አልበቃም፡፡ 

Read 3849 times