Monday, 05 December 2016 09:25

ትራምፕ ከቢዝነስ ስራቸው ሙሉ ለሙሉ እንደሚወጡ አስታወቁ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 - ከ500 በላይ በሚሆኑ ኩባንያዎች የባለቤትነት ድርሻ አላቸው
       - ኦባማ ባለቤታቸው ለፕሬዚዳንትነት እንደማትወዳደር አስታወቁ

      ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሙሉ ትኩረታቸውን አገር በመምራት ስራቸው ላይ ለማድረግና የጥቅም ግጭት ስጋትን ለማስወገድ በማሰብ፣ ወደ ዋይት ሃውስ ሲገቡ የንግድ ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ እንደሚያቆሙ ባለፈው ረቡዕ ማስታወቃቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
“ሙሉ ትኩረቴን አገሪቱን ለመምራትና አሜሪካን እንደገና ታላቅ አገር ለማድረግ ስል ግዙፉን የቢዝነስ ስራዬን ሙሉ ለሙሉ አቋርጣለሁ፡፡ እርግጥ ነው ፕሬዚዳንት ሆኜ ቢዝነስ እንዳልሰራ የሚከለክለኝ ህግ የለም፤ነገር ግን  በንግድ ስራዬና በስልጣኔ መካከል የጥቅም ግጭት እንዳይኖር ማድረግ እንዳለብኝ ይሰማኛል” ብለዋል፤ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፡፡
አገር የመምራቱ ተልዕኮ የበለጠ ዋጋ አለው ያሉት ትራምፕ፣ ከተሰማሩባቸው በርካታ የቢዝነስ መስኮች ሙሉ ለሙሉ መውጣት የሚያስችሏቸው ህጋዊ ሰነዶች እየተዘጋጁ እንደሚገኙና ጉዳዩን በተመለከተ በቅርቡ ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡ ትራምፕ ከዚህ ቀደምም የቢዝነስ ስራቸውን የመምራት ሃላፊነቱን ለሶስቱ ልጆቻቸው ዶናልድ ጄአር፣ ኤሪክ እና ኢቫንካ እንደሚያስረክቡ ተናግረው እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ከሚታወቁበት ትርፋማ የሪልእስቴት ኢንቨስትመንታቸው በተጨማሪ፣ በአሜሪካና በተለያዩ የአለማችን አገራት በአያሌ የንግድ ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ ሲሆን ከ500 በላይ በሚሆኑ ታላላቅ ኩባንያዎችም የባለቤትነት ድርሻ እንዳላቸውም ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በዲሞክራቷ ዕጩ ሄላሪ ክሊንተን ሽንፈት የተናደዱ አሜሪካውያን ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከአራት አመታት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ በፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ዘመቻ መጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን ባለቤታቸው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ግን ሚሼል ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት እንደማይወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡ ኦባማ ከሮሊንግ ስቶን መጽሄት አዘጋጅ ጃን ዌነር ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ፣ ባለቤታቸው ሚሼል ፖለቲከኛ የመሆን ፍላጎት እንደሌላቸው በመጥቀስ፣ በፍጹም ለፕሬዚዳንትነት አትወዳደርም ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ መጽሄቱን ጠቅሶ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡

Read 1258 times