Monday, 05 December 2016 09:29

ያሬድ በዓለም ጂጁትሱ ሻምፒዮና 4ኛ ደረጃ አግኝቷል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከአፍሪካ አንደኛ ነው

        ኢትዮጵያዊው ያሬድ ንጉሴ ዲሳሳ በዓለም ሻምፒዮና በብራዚላዊያን ጂጁትሱ ስፖርት ለግማሽ ፍፃሜ በመድረስ በ4ኛ ደረጃ ያጠናቀቀ ሲሆን ውጤቱ ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም በታሪክ የመጀመሪያው ነው፡፡ በ2016 የዓለም ጂጁትሱ ሻምፒዮና ያሬድ ንጉሴ በመጀመሪያው ዙር ጀርመናዊ ተጋጣሚውን በማሸነፍ ሲሆን፤ በ2ኛው ዙር ደግሞ ከሩሲያው ተጋጣሚ ጋር ተገናኝቶ በስፖርቱ አዳዲስ ህጎች ጋር በተገናኘ ያስመዘገበው ውጤት ተሰርዞበት ለግማሽ ፍፃሜ መድረስ ችሏል። በጂጁትሱ የዓለም ሻምፒዮና የያሬድ አሰልጣኝ ሆነው የተሳተፉት በዓለማቀፉ የጂጁትሱ ፌዴሬሽን የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የሆኑትና ስፖርቱን በኢትዮጵያ በማስተዋወቅ ፈር ቀዳጅ የሆኑት ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ናቸው፡፡ ዶ/ር ፀጋዬ ከጀርመን ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት የያሬድ ውጤት ከስምንት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የተዋወቀውን የጂጁትሱ ስፖርት በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃና በአፍሪካ ደረጃ ግንባር ቀደም ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ነው ብለውታል፡፡
በግማሽ ፍፃሜው በ56 ኪ.ግ ኮሎምቢያዊውን ተጋጣሚ ያገኘ ሲሆን በዚሁ ፉክክር ላይ በስፖርቱ በቅርቡ በተቀየሩ አዳዲስ ህጎች ሳቢያ የነበረው ብልጫ ተወስዶበት የነሐስ ሜዳሊያው ለጥቂት አምልጦታል፡፡ ያሬድ ንጉሴ የጁቬንቱስ ክለብ ሰልጣኝ ሲሆን ከዚህ በፊት በጀርመን ዱሱልዶፍ በተካሄደ አለማቀፍ ውድድር ተሳትፎም ያውቃል። ባለፈው ሰሞን በፖላንድ በተካሄደው የዓለም የጂጁትሱ ሻምፒዮና ያሬድ ንጉሴ በ4ኛ ደረጃ ማጠናቀቁ ከፍተኛ አድናቆት ያተረፈበት ሲሆን፤ ከአፍሪካ በ1ኛ ደረጃ ከመላው ዓለም በ5ኛ ደረጃ እንዲቀመጥ አስችሎታል፡፡ በሻምፒዮናው ላይ ከነበረው ተሳትፎ በኋላ በአቡዳቢ በሚካሄድ ሴሚናር ከመጋበዙም በላይ በጂጁትሱ  ስፖርት ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው ብራዚላዊ አሰልጣኝ ጋር የሚሰራበት ዕድል ተፈጥሮለታል፡፡ በዚሁ የዓለም ሻምፒዮና ላይ 600 የጂጁትሱ ስፖርተኞችና 200 አሰልጣኞቻቸው ተካፋይ ነበሩ፡፡ በቀጣይ በፖላንድ በሚካሄደው የ2017 ወርልድ ጌምስ አፍሪካን በመወከል የሚሳተፍ ይሆናል፡፡ ወርልድ ጌምስ፣ ካራቴ፣ ሞተር ስፖርት፣ ዳርት፣ ጂዶ፣ ጂጁትሱና ሌሎች ስፖርቶችን የሚያካትት አለማቀፍ የውድድር መድረክ ነው፡፡
ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ነዋሪነታቸው በጀርመን ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የጂጁትሱ ስፖርትን በማስፋፋት ፈርቀዳጅ ሚና የተጫወቱ ናቸው። በታላቁ የጀርመን የመኪና አምራች ኩባንያ መርሴዲስ ቤንዝ በፕሮጀክት ማኔጅመንትና በዳይቨርሲቲ ማኔጅመንት ለ15 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን ከፕሮጀክት ማኔጅመንት ጋር በተያያዘ በርካታ መፅሀፍቶችን ያዘጋጁና በተለያዩ ጊዜያትም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የተለያዩ ስልጠናዎችና ወርክሾፖችን ይሰጣሉ፡፡ ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ጂጁትሱ ዩኒየን ምክትል ሊቀመንበር ዓለማቀፉ ጂጁትሱ ማህበር አባልና የምስራቅ አፍሪካ ዞን ተወካይ እንዲሁም በዓለማቀፉ የጂጁትሱ ፌዴሬሽን የስነ ምግባር ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የጂጁትሱ ስፖርትን ለማስፋፋት ከ8 ዓመታት በፊት በፍትህ ሚኒስቴር የተቋቋመ ማህበር መኖሩን ለስፖርት አድማስ የገለፁት ዶ/ር ፀጋዬ በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋ፣ በሐረርና በሀዋሳ የጁዶ ጂጁትሱ ማህበራት ተቋቁመው እንደሚንቀሳቀሱና በአጠቃላይ እስከ 500 የጂጁትሱ  ስፖርተኞችን በማቀፍ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡      
የጂጁትሱ ስፖርት የማርሻል አርት አይነት ስፖርት ሲሆን የመጣል የመወርወር የመጥለፍና የተለያዩ የምት ስንዘራ ቴክኒኮችን የሚተገብር ስፖርት ነው፡፡ ይህ ስፖርት በአሁኑ ወቅት ብራዚላዊያን ጂጁትሱ በሚል መጠሪያ በዓለማቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ሲሆን ዓለማቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በ2020 እ.ኤ.አ ከሚካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ በኋላ የኦሎምፒክ ስፖርት ለማድረግ ትኩረት እየሰጠው ነው፡፡

Read 473 times